Translate

Friday, March 4, 2016

ህወሃት ራሱን “ሳያጸዳ” በሌላው ዘምቷል

የዳባ ደበሌና የሰለሞን ኩቹ መጨረሻ አልታወቀም!

daba
“የኢህአዴግን መርህ እስከተከተለ ድረስ መሃይምም ቢሆን ሚኒስትር እናደርጋለን” ያሉት መለስ ዙሪያቸውን “የበታች” በሆኑ ሹሞች አስከብበው የቆዩት ያለምክንያት አልነበረም፡፡ “አዋቂ፣ ጠቢብ፣ ባለራዕይ፣ ምንተስኖት፣ …” የሚሉ “ማዕረጎችን” አስገኝተውላቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የፈለጉትን ሥልጣን ላይ ያስቀምጣሉ፤ ከዚያ በሙስና ያበሰብሳሉ፤ ከዚያም ወደ “ቆሻሻ ቅርጫት” ይጥላሉ፡፡ በሕይወት ለቆዩት “ቅርጫቱ” ትልቅ መድህን ሲሆን ለዚያ ያልታደሉት ግን ትርጉሙ ሌላ ነው፡፡ ይህ የመለስ አሠራር የህወሃት መመሪያ ሆኖ ቆይቷል፤ አሁንም እየተሰራበት ነው፡፡

በኦሮሞ ከተሞች በተነሳው ሕዝባዊ ንቅናቄ የተደናገጠው ህወሃት ከረፈደ “ጽዳት” ጀምሯል፡፡ የችግሩ መንስዔ ራሱ ሆኖ “ልክ መግባት” ሲገባው ለህዝብ “ሥራ ላይ ነን” ለማለት “የኦህዴድን አመራሮች” ማንሳቱ አስታውቋል፡፡
የጎልጉል እማኝ ዘጋቢዎች በላኩልን መረጃዎች መሠረት ዳባ ደበሌና ሰለሞን ኩቹ ከሥልጣናቸው ከተነሱ በኋላ “በደኅንነት ቁጥጥር ሥር” መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ምናልባት በካህኑ ህወሃት ፊት ቀርበው “ንሰሃ” ከገቡ የ“መዝገብ ቤት” ሥራ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ካልሆነ ግን “ለታምራት ላይኔም አንራራም” እያለ “ንጽህናውን” የሚሰብከው ህወሃት “ወደሚነጹበት ቦታ” ይልካቸው ይሆናል የሚል አስተያየት ይነገራል፡፡
እማኝ ዘጋቢዎቻችን በላኩልን መረጃ መሠረት ሁለቱም በመሬት ችብቸባ ላይ ዋንኛ ተዋናዮች የነበሩ ሲሆን ይህንንም ሽያጭ እንዲያስፈጽሙ በህወሃት ሰዎች ቀጥተኛ ትዕዛዝ ይሰጣቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ “የቡራዩን መሬት በማስቸብቸብ ቀዳሚው ሌባ መሆኑ አገር ያወቀው … (ባዶ በርሜል) የነበረና የስርአቱ መጠቀሚያ ሆኖ ያገለገለ … አሁን አገልግሎቱን ጨርሶ እንደ አሮጌ ቁና ተጣለ፡፡ የሌሎቹም አቃጣሪዎች ጊዜያቸው ሲያበቃ መጣላቸው አይቀርም” በማለት እማኝ ዘጋቢው ንዴት የተቀላቀለበትን ቁጭታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ የኦሮሞ ከተሞች የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ እያሸበረው የመጣው ህወሃት ራሱን ከማንጻት ይልቅ ሰይፉን በሌሎች ራሱ በወንጀልና በሙስና ባበሰበሳቸው ላይ መሰንዘሩ ከወትሮ ያልተለየ እና መለስ ትተውለት የሄዱትን “ውርስ/ሌጋሲ” እያስጠበቀ መሆኑ ለብዙዎች ግልጽ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment