Translate

Tuesday, March 8, 2016

ከጠመንጃ ‘ነፃነት’ ወደ ስኳር ባርነት! (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ – የካቲት 2008
INVESTORS, WELCOME TO ETHIOPIAለስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎች ማስፋፊያ በሚል ሰበብ መጠነ ሰፊ መሬት ከዜጎች እየተዘረፈ መሆኑን ስንሰማ ቆይተናል። የታሪክ እና እምነት መናኸሪያ ዋልድባ ገዳም በይዞታው ስር የሚገኘውን ርስት በዚህ ምክንያት መቀማቱንም እንደ ዋዛ ሰምተን ነበር። ሰሞኑን በምናገኘው ወሬ ደግሞ የኦሞ ሸለቆ ልዩ ልዩ ብሔረሰብ ኢትዮጵያውያን ከክልላቸው ጭካኔ በተመላበት የወያኔ አስገድዶ ማፈናቀል ዘመቻ ከቄያቸው ሲጋዙ መክረማቸውን ተረድተናል። መሬታቸው ለሸንኮራ እርሻ ማምረቻ እና ስኳር ፋብሪካ ስለተመረጠ እነሱ ወዳልመረጡት አካባቢ በጠመንጃ አፈሙዝ ተገደው ተወስደዋል።
እንደ እንሰሳ በገመድ ተጠፍሮ ካሚዮን ላይ የተጫነውን ወገናችንን አተኩራችሁ ካስተዋላችሁ በስኳር ገበያ የጎመዘዘው የኦሞ ሸለቆ ክልል ህዝቦች ህይወት ስዕል ቁልጭ ብሎ ይታያችሁዋል። ስኳር የሚልሱ ጉልበተኛ ገዢዎች በዜጎች ጉሮሮ እንቆቆ እያንቆረቆሩ ስለመሆኑ በማያሻማ ሁኔታ ትገነዘበላችሁ። ለም የተባለ ያገሪቱ ምድር እንደ ጠላት ወረዳ ወረራ እየተፈፀመበት የይዞታው ባለቤት የሆኑ ነዋሪዎቹ ወደ ዘቀጠ ኑሮ እየተወረወሩ ይገኛሉ። በዚህም የወያኔ እውነተኛ ተፈጥሮ ይበልጥ ግጥጥ ብሎ ወጥቷል።

በመሰረቱ የዚህ አይነቱ ጭካኔ በወያኔ ወህኒዎች በታገቱ ንፁሀን ዜጎች ላይ ሲፈፀም የቆየ በመሆኑ ለብዙዎቻችን እንግዳ ነገር አይደለም። ምናልባት ይህን የተለየ የሚያደርገው በጠመንጃ አፈሙዝ ብሔረሰባዊ ነፃነታችሁ ተረጋግጧል የተባሉት ኢትዮጵያውያን በስኳር ኢንቨስተሮች ጡንቻ እውነተኛ ባርነት ተጭኖባቸው ማየታችን ሊሆን ይችላል –
ወያኔ በስኳር ገበያ ሊከብር ፣ ሊናጥጥ ፤ የወያኔ ጀሌ በስኳር ህይወቱን ሊያጣፍጥ ሌላው ዜጋ አያት ቅድም አያቱ ከተከሉት ከገዛ መሬቱ ላይ በወታደር ተገዶ ይጋዛል – እንደ ከብትም ታስሮ ፣ ተወግሮ እና ተዋክቦ ፤ ስብእናው ተክዶ እና ተዋርዶ የህይወት ተስፋው ጨልሞ ደብዛው እንዲጠፋ ሲደረግ ቆይቷል።
ስኳር መራራ የሆነበት ዜጋ ሆነን የመገኘታችን ምስጢር መፍትሔ ያሻዋል።
የኦሞ ሸለቆ ሰላማዊ ዜጎች ለም መሬታቸውን መቀማታቸው አልበቃ ብሎ በቁማቸው አሳር እንዲቀበሉ በመደረግ ላይ ነው። ወልቃይት ላይ የተፈፀመውን አይን ያወጣ ወረራ ስናስብ ፣ በኦሮሞ ክልል የተፈፀመው የመሬት ዘረፋ እና ማፈናቀል ፣ ጋምቤላ አፅመ ርስቱን የተቀማው ህዝብ – ይህ ሁሉ ድርጊት አፈፃፀሙ ወጥነትና እና ተመሳሳይነት እንዳለው መገንዘብ አያዳግትም። የዚህ እርምጃ ግብ አንድ ጠገብኩ የማይል ስግብግብ ጎጠኛ ሀይል መጠነ ሰፊ ሀብት አግበስብሶ አገዛዙን አለገደብ ማራዘም እንዲበቃ ማስቻል ነው።
ወያኔ የስልጣንና ሀብት ጥሙን ለማርካት ሲል ይሉኝታ የማያውቅ ፣ ስለ ዜጎች ደህንነት ቅንጣት ሀላፊነት የማይሰማው ፣  የሚሊዮኖች ህይወት ቢናጋ ፣ ሰብአዊ ክብራቸው ቢዋረድ… ብሎም ኢትዮጵያ ራሷ ከገፀ ምድር ብትጠፋ ቅም የማይለው መሆኑን በወሬ ሳይሆን በተግባር ሲያሳየን ቆይቷል። ይኼ ዛሬ ያየነው  ድርጊት ሌላ ተጨማሪ ኤግዚቢት ነው። የብሄረሰቦችን እኩልነት አውጃለሁ ብሎ ዘገር የነቀነቀው ባለ ቁምጣ የብሄረሰቦችን ለም መሬት በዘገር እየቀማ ለባርነት እየዳረጋቸው ነው።
የኦሞ ሸለቆ በሞላሰስ አተላ ሲበከል አናይም ያሉ ዜጎች ደማቸው እንደ ጅረት እየፈሰሰ ነው። በወያኔ ወታደር ተገደው ካሚዮን ላይ የተጫኑትን ወገኖቻችንን አካል አስተውሉት ፣ እርቃን ገላቸውን በህሊናችሁ ዳሱት ፣ የፊታቸውን ገፅ አንብቡት ፣ አይናቸውን እዩት – ከግንባራቸው የሚፈሰውን ላብና ደም አስተውሉት… – አንገታቸው ላይ የተሸመቀቀውን ገመድ ፣ ክንዳቸው የፊጥኝ ተሰትሮ መተንፈሻ እንኳ ተነፍገው በጨካኝ ወታደር እርግጫ የሚደርስባቸውን ሰቆቃ አሰላስሉት… እዚህ ፎቶ ላይ ያየናቸው ዜጎች በጥይት ተገድለው በየስርቻው ከተጣሉት የተረፉት መሆናቸውንም አስቡት… ።
አንድ ህዝብ በገዛ አገሩ ይህ ሁሉ ሰቆቃ በቁሙ የሚፈፀምበት ለስንት ስኳር ላሾች ምቾት ሲባል ይሆን?
በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች የተለቀቁትን ምስሎች ሳስተውል እስከ አጥንቴ ዘልቆ የሚወጋ ህመም ተሰምቶኛል። ወያኔ ወደ አስራስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመሳፍንት ዘመን ይዞን የሄደው በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በዚያው በጥንታዊው ዘግናኝ የባሪያ ንግድ ዘዴ አፍሪካውያን የደረሳባቸውን ሰቆቃ በመድገም ጭምር መሆኑን ተገነዘብኩ። ይሄ ነጮቹ barbaric (አረመኔ) የሚሉት ባህርይ ነው። በኔ እምነት ወያኔ በተፈጥሮው barbaric ብቻ ሳይሆን beast (አውሬ) መሆኑን ተገንዝቤያለሁ።
አንድ ኢትዮጵያዊ በገዛ ቄየው እንዲህ እርቃኑን እንደ ከብት ተጠፍሮ ሲንገላታ በአይንህ ብሌን ከመመስከር በላይ ወያኔን የሚገልፅ ምን ትጠብቃለህ። ወደድንም ጠላንም የሚካሄደው ትግል ይህን የባርነት ቀንበር ለመስበር የሚደረግ ተጋድሎ ነው። ይህን ለአፍታ የሚጠራጠር ካለ ሌላ ከዚህ የባሰ ተጨማሪ የዜጎች ውርደት እስኪመጣ ለመጠበቅ የመረጠ ብቻ ነው። ይህም ባርነትን ወዶ እንደ መቀበል ይቆጠራል።
አውሬ ህሊና የለውም – ወያኔ ህሊና የለውም!
ኦሮሞ መሬት ላይ ህፃን ከአዛውንት ፣ ነብሰጡር እናቶች ፣ ለጋ ወጣት ተማሪዎች እና አርሶ አደሮች… ማንም አልቀረውም – ሁሉንም በአውሬ ተፍጥሮው ፣ በመርዛም ጥርሱ ነክሷል… እየነከሰ ነው። ያየናቸው ምስሎች ሀፍረታቸው እንኳ በወጉ ሳይሸፈን በገመድ የፊጥኝ ታስረው በካሚዎን ላይ የታጨቁ ምሬት የተላበሱ ኢትዮጵያውያን በወታደር ሀይል እየተዋከቡ ወደማይውቁበት ስፍራ እየተጋዙ መሆኑን ነው። እነኝህ ዜጎች ምናልባትም በታሪካቸው ከዚህ ቀደም ደርሶ የማያውቅ ጭካኔ እየተፈፀመባቸው ነው። መላ የሰው ዘር ባርነትን በተጠየፈበት በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ነፃነቱን ለምዕተ ዓመታት አስከብሮ የኖረ ህዝብ መልሶ ወደ ባርነት ስርአት ሲገባ ከማየት በላይ ህሊናን የሚያቆስል ጉዳይ የለም።
ኢትዮጵያውያን በባርያ ፈንጋይ እጅ ወድቀናል። ትግላችንን የነፃነት ጥያቄ የሚያደርገውም ይኸው ነው።
ወገኖቻችን በባርነት ቀንበር ስር እየማቀቁ ሳሉ አንዳችንም ከባርነት ነፃ ነን ማለት አንችልም። እንዲህ  አይነቱን አሳፋሪ እና ፀያፍ አውሬአዊ ድርጊት ከምድራችን ለመፋቅ ባለን አቅም እና መንገድ ሁሉ መታገል አማራጭ የለውም።
ተንበርክኮ መኖር ያሳፍራል። የዜጎች ክብር የተዋረደባት ፣ አሳፋሪ አገር ለዛሬውም ሆነ ለነገው ትውልድ አያሻንም። በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ እያልን ዜጎቿ ከተራ ሰብአዊ ፍጡር በታች ተዋርደው መሳለቂያ ሲሆኑ ማየት ትልቅ የህሊና ቁስል ነው። ምኑ ነው የሚያኮራን ፣ የኩራታችን ምንጭ የዜጎቻችን ክብር ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

No comments:

Post a Comment