Translate

Monday, March 14, 2016

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ፈተናዎች

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ፈተናዎች
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሥድስት ዓመታት የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ዐይን እና ጆሮ ሆኖ መሰንበቱ የመገናኛ ብዙኃኑ ተከታታይ እና ደጋፊዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ፤ ዕውነትን እንደ ሰደድ-ኢሳት የሚፈሩት ጠላቶቹም ጭምር እንቅልፍ አጥተው ሲከታተሉት እና ሲፈታተኑት በመቆየታቸው ሳይወዱት በግድ (በተግባራቸው) መስክረውለታል።


እስከ 20 ሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያኖች በረሀብና ቸነፈር በሚማቅቁበት በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አፋኙ መንግስት ፤ የህዝብን ዕሮሮ ከማዳመጥ ይልቅ ፤ የህዝብ ድምፅ የሆነውን (ኢሳትን) ለማፈን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን እያፈሰሰ ይገኛል። ህወሓት ኢሳትን ከተለያዩ ሳተላይቶች ለማውረድ ወጪ ከሚያደርገው የህዝብ ገንዘብ በተጨማሪ ፤ የኢሳት ጋዜጠኛ ላፕቶፖች ላይ የሚገኙ መረጃዎችን ለመስረቅ (ሀክ ለማድረግ) በጣልያን የሚገኙ ሀከሮችን (Hacking Team) በአንድ ላፕቶፕ ብቻ እስከ አንድ ሚልዮን ዶላሮች ወጪ ማድረጉን ዊኪ ሊክስን ጠቅሰው እነ BBC , The Guardian , Washington Post'ን ጨምሮ ሌሎችም አለም አቀፍ የሚድያ አውታሮች የህወሓትን ድብቅ ሴራ በአለም አደባባይ ይፋ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ኢሳት የጉጅሌዎቹን ጥቃቶች በመቋቋምና ነጻነቱን ተነፍጎ ለሚኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ መረጃ ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት የቀጠለ ቢሆንም እንዳበደ ውሻ እየተንጨረጨረ ካልተናከስኩ ሞቼ እገኛለው የሚለው ህወሓት በኢሳት ላይ አዲስ የክስ መዝገብ በዋሽንግተን ዲሲ ከፍቷል። (ከታች ተያይዞ የምታዩትን) የክስ መዝገብ የከፈተው ግለሰብ መስፍን ብዙ የተባለ በኢትዮጵያ ዋሽንግተን ዲሲ ኢንባሲ ተቀጥሮ የሚሠራ (የሚያሴር) ኮካ ሲሆን ግለሰቡ የኢሳት ጋዜጠኞችን በተደጋጋሚ በመክሰስ ጋዜጠኞቹን intimidate ለማድረግና በዝባዝንኬ ክስ ሥራ ለማስፈታት እንዲሁ ጠቃት እና ማታ እንደ ጥቅምት ውሻ በከንቱ እየተክለፈለፈ ይገኛል።
የመስፍን አለቆች አንድ ያልተገነዘቡት ሀቅ ቢኖር (ሀቅን እንደ መታነቅ ስለሚቆጥሩት ይሆናል) ህወሓቶች ኢሳትን ለማፈን የተለያዩ ጥቃቶችን በሰነዘሩ ቁጥር ኢሳት በአንፃሩ ተደማጭነቱ እያደገ ፣ አድማሱን እያሰፋ ፣ የመረጃ ምንጭነቱ እየገነነ መምጣቱ ነው። ይህ ግለሰብ በጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማና በአቶ ነአመን ዘለቀ ላይ አዲስ በሬ ወለድ ክስ የከፈተ ሲሆን ፤ (ምንም እንኳን ክሱ ውሃ ባይቋጥርም) "የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሽምጠጣ" እንዲሉ በአገር ቤት ለሙያቸውና ለህሊናቸው ያደሩ ጋዜጠኞችን እያሳደደ በማዋከብ እና በማሰር በአለም የተጨበጨበለት ቡድን ፤ በውጭ ሀገርም የሚኖሩ ጋዜጠኞችን በሙያቸው ለማሸማቀቅ ፣ ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ለማንገላታት ፣ አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስወጣት ፣ የጋዜጠኞቹን ቤተሰቦች በድንጋጤን ለማሸበር እና ለማስፈራራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከወር በፊት የአላሙዲ ቀኝ እጅ የሆነው አቶ አብነት ወደም የተባለው ግለሰብ በጋዜጠኛ ተቦርነ በየነ ላይ ተመሳሳይ የሀሰት ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
ኢሳት ይህን ሁሉ ፈተናዎች እየተጋፈጠ ነው ለኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ መረጃን ለማድረስ ደከምኝ ሰለቸኝን በማያውቁ ቆራጥ ሠራተኞቹና በኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ዛሬ ላይ የደረሰው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከፊቱ የተጋረጡትን የአፈና እና የስነልቦና ፈተናዎች ተቋቁሞ እና በአሸናፊነት መንፈስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተገቢውን ድጋፍ መስጠት የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሀላፊነት ነው።
ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዐይን እና ጆሮ ሆኖ ይቀጥላል !

No comments:

Post a Comment