Translate

Friday, March 18, 2016

ሾተላይ የሚጫወትባት ሀገር – ትንሽ ስለበውቀቱና ነቃፊዎቹ (ይሄይስ አእምሮ)

ይሄይስ አእምሮ
Bewketu Seyoum is a novelist and poet from Ethiopia.በዚያን ሰሞን በውቀቱ ሥዩም ከ“አሜን ባሻገር” የምትል አንዲት ግሩም መጽሐፍ ጽፎ ለንባብ አብቅቷል – ሳቢን መግረፍ የለመድነው ጥቂት እኛዎች እንደአህያዋ ማር አልጥመን ብሎ በስድብና በዘለፋ ተቀበልነው እንጂ፡፡ ይህችን መጽሐፍ ተከትሎ በውጪም በሀገር ውስጥም የሂስ መዓት ሲዥጎደጎድ ይስተዋላልኝ፡፡ እኔም ሲያቀብጠኝ ከመጽሐፊቱ በፊት ትችቶቹን እያነበብኩ ቅንጭላቴን ሳዞር ከረምኩኝ፡፡ እንዲያውም በሂሶቹ ሰበብ መጽሐፊቱን የማንበብ ፍላጎቴ ሣይቀር ደብዝዞብኝ ነበር፡፡ እርሷም በማከያው ከገበያ ጠፋች፡፡ ሁሉም ወደዳትና ልኩራ አለች፡፡ እናም ተሰወረች፡፡ በኋላ ግን ደግማ መጣችና ገዝቼ – ኧረ ንሺ እቴ የምን መዋሸት ነው – አንብቦ ካጨረሳት ጓደኛየ የቅሚያ ያህል ወስጄ ማንበብ ያዝኩ፡፡ በሣቅ እየነፈርኩ – ከንባብ ጋር የተጣላችውን ባለቤቴን ሌሊት ሌሊት እየረበሽኩ በሁለት ግማሽ ውድቅቶች ጨረስኳት፡፡ መጽሐፊት መጽሐፍ አይደለችም፤ ቅመም ናት፡፡ ሂሶችን ቀድሜ ማንበብ አልነበረብኝም፡፡ አጠፋሁ፡፡

መጽሐፏን እንዳነባት በጣም የገፋፋኝ ግን የአንድ ሰው መረን የለቀቀ ትችት ነው፡፡ ያን ትችት መጽሐፊቱን ከማንበቤ በፊትና በኋላ ሁለት ጊዜ አነበብኩት፡፡ ብታዩት እኮ ከመርዘሙ የተነሣ እንኳንስ ሁለቴ ለአንዴውም የማይሞከር ነው፡፡ እኔ ግን አለወትሮየ እልኸኛ ሆንኩና ደገምኩት – ኧረ የሰለስኳቸው አንቀጾችም አሉ፡፡ ይህ “የትችት” ጽሑፍ በቀላሉ ትችት ተብሎ የሚታለፍ አይመስለኝም፡፡ በውቀቱን በሚመለከት የሚሰነዘሩ ቃላት አጠገባቸው ዱላ ቢኖር አንባቢንም አለርህራሄ የሚደልቁ ዓይነት ናቸው – እንዴት መተቸት እንደሚገባን ከማወቅ/ካለማወቅ አንጻር ትልቅ ርግማን አለብን፤ ፊደል መቁጠር ሰውን በነገር ዱላ ለመነረት ዋስትና እንደሚሰጥ የምናምን ሰዎች አለን፡፡ ያ እጅግ እያፈርኩና እየሰቀጠጠኝ ያነበብኩት አቃቂር ትችትን እስከመፈጠሩ የሚያስጠላ የቦካ ቂም የተጣጣፈበት የሚመስል የነገር ድሪቶ ነው – ባዶ የቃላት ኳኳታ፡፡ በጣም አዘንኩ፡፡ መቼም አንድ ኢትዮጵያዊ ሲያጠፋ ሌላውንም በጅምላ መውቀሱ ያለ ስለሆነ ይቅርታ አድርጉልኝና እኛ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሯችን ዴሞክራት እንዳይደለን፣ ልንሆንም እንደማንችል ያ ጽሑፍ በግልጽ ያሳብቃል፡፡ ዱላ በወረቀት በሉት የሰውዬውን ጽሑፍ፤ ደግሞም በአንድ ገጽ ሊገለጽ የሚችል ነገር ሃሳቦች በሞክሼ ቃላት ስለሚደረቱ ትችቱ ተምቦረቀቀና መጽሐፍ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
ግን ምን ነካን? አዎ፣ ሁልጊዜ እንደምለው ብዙዎቻችንን የምቀኝነት አባዜ ቤቱን እላያችን ላይ ስለሠራብን ይመስኛል አንድን በአንድ ነገር ይበልጠናል ብለን የምናስበውን ሰው በቻልነው ነገር ሁሉ እንደባብ ቀጥቅጠን ድራሹን ማጥፋት ይቀናናል፡፡ ኢትዮጵያ “ጀግናን መውለድ እንጅ ማሳደግና ለወግ ለማዕረግ ማብቃት አይሆንላትም” የሚባለው ትክክል ነው – እንደዚህ ዓይነት ነውጠኛና ሞገደኛ ሂስ ተብዬ ጽሑፎችን አልፎ አልፎ አያለሁ – ሂስ በመሠረቱ የሚጠሉትን ወይም በአንድ ነገር በለጠኝ ብለው የሚሰጉበትን ሰው ለማጥቂያ ሣይሆን የአንድ ሥራ ጠንካራ ጎን ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን፣ ደካማው ጎን ደግሞ የሚሻሻልበትን፣ የተደበቁ እውነቶችን በማፍታታት ተራው አንባቢ ስለጽሑፉ የበለጠ ግንዛቤ የሚያገኝበትን መንገድ የምንጠቁምበት ጥሩ መሣሪያችን ነው – መስታውታችን፡፡ ከዚህ  ከሰውዬው “ትችት” የምቀኝነታችን መጠን ምንም ዓይነት መለኪያ እንደማይገኝለት ተምሬበታለሁ፤ የጠሉትን ሰው ለማጣጣል እስከምን ድረስ መውረድና ራስን ለትዝብት መዳረግ እንደሚቻልም ተገንዝቤበታለሁ፡፡ “ስለዚህም” አልኩ ለራሴ “ስለዚህም እንትናዬና እንትናዬ ባለፈው ዓመት በኔ ላይ ያደረሱብኝ በደል ከዚህ ከሰው ልጅ የትንሽነት ባሕርይ በመነሣት መሆን አለበትና ይቅር ልላቸው ይገባኛል ማለት ነው” አልኩ፡፡ አዎ፣ በሕይወቴ የማልረሳውና በወዲያኛው ዓለም ፍርድ ቤት ሣይቀር የምገትራቸው ሁለት ሰዎች በኔ ላይ እንደዘበት የሰጡት የሀሰት ፍርድ ሲታወሰኝ በውቀቱም ያን ትችት ሲያነብ የሚሰማው ስሜት በስሜቴ ውስጥ ግዘፍ ነሣ፤ እናም ለኔ ያዘንኩትን ያህል ለርሱም አዘንኩ – ሰዎች አንዳችን ለአንዳችን ስሜት ለምን እንደማንጠነቀቅም አልገባህ አለኝ፡፡ ሰው ስንባል እንዲህ ነን እንግዲህ፡፡ የምንጠላውን ሰው ለመወንጀል ጥቁርን ነጭ፣ ነጭን ጥቁር እስከማለት የምንደርስና የኅሊናችንን የፍርድ ሚዛን ለትንሽዬ ሥጋዊ እርካታ ብለን ሰባብረን የምንጥል ብዙ ከንቱ ሰዎች አለን፡፡ እንዲያው ለምሳሌ – እስኪ አስበው – በደምብ መራመድ የሚችልን ሰው “ሽባ ነው” ብለህ ትመሰክራለህ? ራስህ በፈጠርከው መረጃስ ንጹሕን ሰው ወንጅለህና ቅስሙን ሰብረህ ከሆነ ፕሮግራም ለአብነት ከነፃ የትምህርት ዕድል ወይም ከሥልጠና ወይም ከመሰል ተግባራት ውጭ ታደርጋለህ? የመማር አንዱ ትርጉም ክፋትን ከደግነት በመለየት ከክፉ አስተሳሰብና ከመጥፎ ድርጊት ራስን ማቀብ ይመስለኛል፡፡ ይህን አለማወቅ መረገም ነው፡፡ አዎ፣ ትልቅ መረገም፡፡ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ስንት መሆን ይችላል? ሃቀኛ ወይንስ ውሸታም? ወይንስ እንዳስፈላጊነቱ ከሁለቱ አንዱን እየሆነ እንደስስት በመለዋወጥ ኅሊናውን ሸጦ ይኖራል?…
የበውቀቱ መጽሐፍ በኔ ዕይታ ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ እጅግ በጣም ግሩም ነው፡፡ እያዝናና ትልቅ ሀገራዊ ቁምነገር የሚያስጨብጥ፣ የታሪክ ጸሐፍት በፍርሀት ቆፈን ተቀፍድደው በተቀመጡበት ወቅት የሥነ ልቦና ተማሪው የትናንቱ በውቀቱ ካለሙያው ገብቶ ድንቅ የታሪክ በረከት የሰጠንና በዚያም ልናመሰግነው የሚገባን ባለዕዳዎች ነን፡፡ ለአንዳንዶቻችን ማመስገኑ ይቅርብንና ቢያንስ ልንሰድበው ግን ባልተገባን፡፡ እኛ ልንሠራው ያልቻልነውን ነገር ሌሎች ሲሠሩት ከመቅናትና ስማቸውን ለማጠልሸት ከመራወጥ ይልቅ በነሱ ፈለግ ወይም በሌላ መስመር ስማችንን ለማስጠራት መሞከር ይኖርብናል፡፡ በውነቱ የበሉበትን ወጪት መስበር ነውር ነው – እንደኔ ወርቅ ላበደረ ጠጠር መመለስ የሚቻለውና እንደጥሩ ምግባርም የሚቆጠረው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ የበውቀቱ ዋጋ በቀላሉ የማይገመትና በታሪክና በትውልድ መሀል ሲዘከር የሚኖር ነው፡፡ በውቀቱ በሥራው ያገኘውን ክብርና ሞገስ በምንም ዓይነት ስድብና ዘለፋ ልንገፈው አንችልም – እንጨምርለት እንደሆነ አንጂ – የሚሠራ ይሰደባል፤ ዝም ብሎ የተቀመጠ ግን ዱሮውንም የድንጋይ ያህል ነውና የሚደርስበት ስድብም ሆነ ግልምጫና ዘለፋ አይኖርም፡፡ በውቀቱ የሚያስቀና፣ “የርሱን ፈለግ በያዝኩ” በሚል ስለሀገር ፍቅር ብዙ ትምህርት የሚቀስሙበትና “ቢስ አይይህ” ሊባል የሚገባው ድንቅ ብላቴና ነው(እዚች ላይ መቼም አዝለኸው ዙር የሚለኝ እንደማይጠፋ አምናለሁና የአንቀልባውን ነገር አደራ እንጂ አቅሜ እስከፈቀደ መሞከሬ አይቀርም)፡፡
በዚያ መጽሐፍ ውስጥ በውቀቱን ለስቅሎ ስቅሎ ግልብ ፍርድ የሚያበቃ አንድም ነገር አላገኘሁም፡፡ “አንዲት ሽምብራ የሚያህል ቄስ” ማለቱም ከሥነ ልሣናዊ የግነት ዘይቤ ባለፈ አላየውም፡፡ የቱንም ያህል በጥልቀት እናንብበው ሃይማኖትን በግልጽ የሚወርፍ ነገር የለውም – እርግጥ ነው “አንድ ሰው በአንድ ጽሑፍ ውስጥ የሚፈልገውን ያነባል፤ ራሱ የሚጨምርበትንም አብሮ ያነባል” የሚል አባባል ካለ በዚያ ላምን እችላለሁ፡፡ አንድ ሰው ግራ ዘመም ተፈጥሮ ካለው ማንኛውንም ነገር እያጣመመ መረዳት ተፈጥሯዊ ባሕርዩ ነው – የተባለውን ወይም ሊባል የተፈለገውን ከተቃራኒው ሃሳብ ጋር እያዛነቀና እያወሳሰበ የመረዳት ዝንባሌና ዕኩይ ተፈጥሮ አለው፤ ቀናነት የሚባል በጭራሽ አይጠበቅበትም፡፡ ሕይወት እንዲያ ከሆነች ደግሞ ማንም በጤና ውሎ አይገባም፡፡ “እንዴት አደርክ” ሲሉት “ባድር ባላድር ምን አገባህ? ያ የኔ ጉዳይ ነው፡፡” የሚል ሰው ካለ ይህ ሰው ወፈፌ ወይ የለየለት ዕብድ ነውና ከእንደዚህ ዓይነቱ ሰው ጋር መግባባትም ሆነ መጎዳኘት አይቻልም፡፡
እንደትችት ከተወሰደልኝ እኔ ከታዘብኳቸው ጥቃቅን የአርትዖት ችግሮች ውስጥ አንድን ሰው አንዴ አንተ ብሎ ሌላ ጊዜ አንቱ ማለትና አንዳንድ የቃላትና የሆሄያት ግድፈቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በተረፈ መጽሐፉ በይዘቱም ሆነ በቅርጹ ማንም ወለፈንዴ በስሜት ተነስቶ ሊጽፈው የማይችል ግሩም ሀገራዊ ገጸ-በረከት ነው፡፡ እንዲያም ስለሆነ ነው ጠላት የበዛበት፡፡ መልካም ሀገራዊ ነገር ለመሥራት በግድ አውሮፓዊ ወይም አሜሪካዊ መሆን የለብንም፡፡ ይህ ዓይነቱ መጽሐፍ በሌሎች ሀገራት ያሸልም ነበር፡፡ እዚህ ግን በባንዳነት ያስፈርጃል፡፡
ስለበውቀቱ የሃይማኖት ጉዳይ ብዙዎች ሥራየ ብለው ይነጋገሩበት ይዘዋል፡፡ በዚህ የግል ጉዳይ የተነሣም የበውቀቱን ሥራ የሚያጣጥሉ አሉ – ይህ ዓይነቱ ነገር ሕጻኑን ከነታጠበበት ውኃ እንደመድፋት ይቆጠራል – በፈረንጅኛው ፈሊጥ፡፡ ዱባና ቅል አጣጣሉ ለዬቅል ነውና ሁለቱን ነገሮች እንለይ፡፡…
በውቀቱ ሲፈልግ ኢአማኒ፣ ሲፈልግ በፀሐይና በጨረቃ የሚያምን አረማዊ፣ ሲሻው ቡድሃ ወይም ታኦይስት ይሁን፡፡ እኔን ምን አገባኝ? የኔን ሃይማኖት ተከትሎ የኔን መዳን እንዲያገኝ ከፈለግሁ አንድም እርሱ ወደሚገኝበት ሥፍራ ሄጄ መስበክ፣ አለዚያም ወደማምለኪያ ቦታየ እንዲመጣና እዚያ እንዲሰበክ ማድረግ ይኖርብኛል፡፡ ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል፡፡ ሀገር የጋራ ናት፡፡ ሃይማኖት ደግሞ የግል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያሏት 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ልጆቿ የተለያዬ ሃይማኖት ተከታይ ናቸው – የእነበውቀቱንም ሃይማኖት-አልባነት ሳንዘነጋ፡፡ አንዱ ችግራችን የሚመስለኝ “የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ካልሆነ ኢትዮጵያዊ አይደለም” የሚለው ቆየት ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሀገርን ከሃይማኖት ጋር በተለይም ከአንድ ብቸኛ ሃይማኖት ጋር ማዋሃድ አደጋ አለው፡፡ ያ ዓይነቱ አስተሳሰብ አክራሪነት ይመስለኛል፡፡ አክራሪነት ደግሞ የብዙ ዐረብ ሀገራትን ኅልውና እያናጋ ነው፡፡ ስለዚህ “እንዳገርህ ቀድስ እንዳገሬ እቀድሳለሁ” እንደተባለው የሚያዋጣው ተስማምቶ መኖር ነው – ተቻችሎ ያላልኩት ሆን ብዬ ነው፡፡ ለመቻቻል ጠብ ወይ አለመስማማት መኖር አለበት፡፡ ሁሉም የየራሱን ሃይማኖት አጥብቆ በመያዝ ከጠብጫሪ ስብከቶችና ጸሎቶችም በመቆጠብ ከተጓዘ ማንም በማንም ላይ ቅሬታ አይኖረውም፡፡  መለማመድ ያለብን ብዙ አዳዲስ ነገሮች አሉ፡፡ ዐይናችንን እንግለጥ፡፡ እንሰልጥን፡፡
በውቀቱ ኢአማኒነቱን ተጠቅሞ ሀገርና ሕዝብ የሚጎዳ ነገር ካደረገ ያ ሌላ ነገር ነው፡፡ በህግም ያስጠይቀዋል፤ መንግሥት ቢኖረንና ሲኖረን ደግሞ ያስቀጣዋል፡፡ ነገር ግን በፀጉር ስንጠቃና በቃላት ዐውዳዊ የፍቺ ልዩነት የተነሣ አንድን ሰው ማብጠልጠል ስህተት ነው፡፡ ኩነኔም ነው፡፡
እርግጥ ነው በውቀቱ የተወውን ሃይማኖት አላግባብ እያነሳ የሰው ሃይማኖት የሚያንቋሽሽ ከሆነ ተሳስቷልና መታረም ይኖርበታል፡፡ ገና ለገና የእምነቱ ተከታዮች ለዘብተኛ ናቸው ብሎ፣ በሜንጮ ነው በሜንጫ አንገት አይቆርጡም ብሎ የብዙኃንን ሃይማኖት ሊያጣጥል አይገባም፡፡ ያ ዐወቅሁሽ ናቅሁሽ ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለን መታወቅ አለበት፡፡ አሜሪካንና አውሮፓ ያለው ዓይነት የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ ባለመድረሳችን በሃሳብ የመግባባትና የመቻቻል ባህላችንም ያን ያህል የዳበረ አይደለም፡፡ ስለዚህ በውቀቱ ከዚህ መሠረታዊ ችግር አንጻር ሊታረምበት የሚገባው አግባብ ቢኖር እኔም ደስ ይለኛል፡፡ እንቃወም ብንልማ ስንትና ስንት ሊቃወሙት የሚገባ ሃይማኖት አለ አይደለም እንዴ – የንጹሕን ሰው አንገት ቆርጦ በሰማይ ጽድቅ አለ የሚል የአክራሪዎች “ሃይማኖት”ም እኮ አለ፡፡ ከዚህች ነጥብ አንጻር በውቄ ሕዝብን ቢያከብር ደስ ይለኛል፡፡ እኛ ስንፈልግ ድንጋይ እንሳም – ስንፈልግ ለስዕል እንስገድ፣ ስንፈልግ ፍሩዳውያን እንደሚሉን እግዚአብሔርን ራሳችን ፈጥረነው ስናበቃ እናምልከው፣ ስንፈልግ የልጅታችንን የበላይ ጠባቂ ፈላጊነት ስሜት ስናድግ ለማካካስ የአባትነትን ሚና የሚጫወት ፈጣሪ አምላክ አለን ብለን እንመን – ይህ ሁሉ የኛ ጉዳይ ነው፡፡ የበውቀቱ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው የሌሎችን እምነት ማንጓጠጥና በነሱም ድርጊት ማሾፍ ሳይሆን በመከባበር ላይ የተመሠረተ ተራክቦ እንዲኖር መጣር ነው – የሕዝብ ሰው ዋና ተግባርም በማኅበረሰብ ውስጥ ጥላቻና መናቆር ሣይሆን ፍቅርና መተሳሰብ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ እኔም ክርስቲያን ነኝ እላለሁ – ተሳስቼ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልችልም ምርጫየ ሆነና ዐረፈው፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ “ተሳሳትኩ”ና ክርስቲያን ሆንኩ – ማንንም ለመጉዳት ወይ ለመጥቀም በማሰብ ግን አይደለም፤ ለራሴው ብዬ ነው፡፡ እናም የክርስቶስ ባሪያ ነኝ፤ ታዲያም ተገድጄ ሣይሆን ወድጄ በገባሁበት ባርነት ልከሰስና ልወቀስ አይገባኝም – ለነገሩ ራሴን እዚቺው ላይ ላርምና ባሪያ ሳልሆን ልጁ ነኝ (ዝርዝር ኪስ ይቀዳል)፡፡ በውቀቱም ምንም ማድረግ ባለመቻሉ ኢአማኒነት ምርጫው ሆነና ዐረፈው፡፡ ሁለታችንን የሚያገናኘን ግን ብዙ ነገር አለ – ለምሳሌ ኢትዮጵያዊነት፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ የሰው ልጅነት፡፡ እኔ የርሱን የአለማመን እምነት ማክበር አለብኝ፤ እሱም የኔን የማመን – በምንም ነገር የማመን – መብት ማክበር አለበት፡፡ ኢአማኒ ስድና መደዴ ማለት እንዳልሆነ የብዙዎች ኢአማኒያን የግል ሕይወት ይመሰክራል፡፡ እኔ እንኳን የማውቃቸው ጥቂት ኢአማኒያን ጓደኞች አሉኝ፤ የመርህ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰው ሲበደል አይወዱም፡፡ ኢአማኒነት በትክክለኛው የአስተሳሰብ ዕድገት ላይ ከተመሠረተ ከአማኒነት ባልተናነሰ ሰብኣዊነትን የሚያላብስ ግለ-መርህ ነው፡፡ ከበደ ሚካኤል “ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” ብለው ዘመን ተሻጋሪ ግጥም የገጠሙት የርሳቸውን እግዜር ይወቀው ለሌሎች ኢአማኒያን ግን ትልቅ መመሪያ ለማስተላለፍ መፈለጋቸውን ይጠቁማል፡፡ ማንም በፈለገው ይመን፤ እኛን ወደርሱ ለመሳብ እስካላስገደደን ድረስ አንቃወመው፡፡
በነገራችን ላይ እምነቴ ተነካ ብለው ሰዎች ሲንጨረጨሩ በጣም ይገርመኛል፡፡ ይህን መንጨርጨር ስገለብጠው በምንም ነገር ያለማመን ውጤትም ይመስለኛል፡፡ እኔ የዓለም መድኅንና የዓለም ፈጣሪ ብዬ የማምነው እግዚአብሔር የኔን የደካማ ፍጡሩን ጉልበትና ዕውቀት ተማምኖ የገዛ ፍጡራኑ እንዲሰድቡትና እንዲክዱት የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡ በኔ ጉልበት የርሱን ጠላቶች ድባቅ መትቼ ገነትን የሚያወርስ ፈሪ ፈጣሪ የለኝም – እውነቴን ነው የምለው ፈጣሪ አቦካቶ ወይ ነገረ-ፈጅ አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የየፍርዱን ለሚያገኝበት የግል እምነታችንና ምግባራችን ሰውን በከንቱ አንቃወም፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ – ፈጣሪ ምንም ዓይነት ምድራዊ ጠበቃና ደምመላሽ የሚፈልግና የጥቃት ሰለባም ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ይልቁንም የራሳችንን የቤት ሥራ እንሥራ፡፡ ደግ እንሁን፡፡ ትዕዛዙን እናክብር፡፡ ከትዕዛዙ ስናፈነግጥ እሱን እናሳዝናለን፤ እኛን ከክብራችን እናወርዳለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ወቅት በውቀቱ ተናገረው በተባለው ሃይማኖት ነክ ነገር ዱላና ቡጢ አስተናግዷል አሉ፡፡ የበውቄ መናገር ስህተት አንድ ሲሆን የደብዳቢዎቹ የአዛኝ ቅቤ አንጓች ዓይነት ድርጊት ደግሞ ስህተት ሁለት ነው፡፡ ምን ጥልቅ አደረጋቸው? ለእግዚአብሔር መንግሥት ያን ያህል ወንጀል እስከመሥራት “ቀናኢ” ከሆኑ በአራት ኪሎው መንበረ ፓትርያርክ ቃለ ዐዋዲው ከሚያዘው ውጪ ፓትርያርኩን ጨምሮ ምድረ ጳጳስ የሰው ሚስት እየቀማ ሣይቀር ሲሸራሞጥና ቤተ እግዚአብሔርን ሲያረክስ፣ በጎችንም ተኩላና ቀበሮ በጠራራ ፀሐይ እየቀማ ሲቦተርፍ የት ሄደው ነበር? ዘርን እየመረጠ በዲን እሳት የሚፈጅ የዐውሬዎች መንጋ በመንግሥትነት ስም አራት ኪሎ ተቀምጦ ሕዝብን ከሕዝብ ሲያፋጅና ሀገርን ሲያፈራርስ የሚመለከቱ፣ አልፎ ተርም ቡራኬያቸውን የሚሰጡ ዘረኛ ካህናትና የሃይማት አባት ተብዬዎች ሲገጥሙን እኚያ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀናኢዎች የት ነበሩ? “ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” … አያናግሩኝ! ብዙ አለ በሆዴ፡፡
ለማንኛውም በውቀቱ ዕደግ ተመንደግ – ከሃይማኖት አንጻር ባለህ አቋም ሣይሆን ለሀገርህ በምታደርገው ተሣትፎ፡፡ ታሪክን እየከተብክ ለነገ አስቀምጥ፡፡ እምነትህ የግልህ ነው፤ ገና ወጣት ስለሆንክ ደግሞ እውነትህን ነው ሁሉንም ዕይ፡፡ የኔ አባት ክርስቶስ “ኩሎ አመክሩ ወዘሰናየ አፀንዑ” ይላል፡፡ ክርስቶስ ዴሞክራት ነው፡፡ አያስገድድም፡፡ ሁሉንም ዓይነት መንገዶች በግልጽ አሳይቶናል፡፡ ስለሆነም ዕድሜ ከሰጠህ ነገ ደግሞ ሌላ ይበልጥ የሚጠቅምህን ነገር ይዘህ እናይህ ይሆናል፡፡ አሁን ግን ሀገርህን መውደድህን ቀጥል፤ እሱም “ያጸድቃል”፡፡
ነገር ግን ሃይማኖታዊ ጉዳይ ወደሀገርህ ጉዳይ እየሠረገ ነገርህን እንዳያበላሽብህ ጠንቀቅ በል፡፡ ደግሞም ባልና ሚስት ከተፋቱ በኋላ የባል ውሽማ ደግ አይደለምና አንዴ የተውከውን ነገር ጅባት ብለህ ጣለው እንጂ ከሰዎች ጋር እልህ ተያይዘህ በነገር ለመጎንተል አትሞክር፤ ባይጎዳህም አይጠቅምህም፡፡ ሰው ሥራ ሲሠራ ጠላት እንደሚበዛበት ይታወቃልና አንተን መሳይ ድንቅና የልጅ ዐዋቂ “ደንቆሮ” ብለው ቢሰድቡህ ሣቅባቸው እንጂ አትዘን፡፡ የኔ ሃይማኖት የማዕዘን ራስ ላይ ግብዝና ደናቁርት ሰዎች የእሾህ አክሊል ደፍተው ሲያሾፉበት ለነሱው ዞሮ ያዝንላቸው ነበር፡፡ ምራቃቸውንም በፊቱ ላይ እየተፉ ተዘባብተውበታል፡፡ ያን ሁሉ የታገሰው ትዕግስትን ሊያስተምረን፣ ትህትናን ሊያሳየን፣ ኃይላችንን መቆጣጠር እንዳለብን ሊያመላክተን፣ እንዴት መኖር እንዳለብን ሊጠቁመን እንጂ ደካማ ሆኖ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ከምነግርህ “ተረት ተረት” (ለኛ ነው የጥቅሱ ምልክት) ብዙ መማር ትችላለህና ማንም እየተነሣ ቂጣ በቆረጠ አፉ ሲሰድብህ መስዋዕትነት ነውና ቻል አድርገው፡፡ በባንዳነት እንደተነሣህ አንብቤያለሁ፤ የሰው ጽሑፍና ሀሳብ እንደዘረፍክም ተጽፎ ተመልክቻለሁ፡፡ ገረመኝ፡፡ የተንኮለኞችን ስሜት የማይሰጥ የጡት ቁራጭ ሀውልት ለመቃወም ምን ማድረግ እንደነበረብህ ሳስበው ስላንተ ጨንቆኛል፡፡ እንደመልካችን ሁሉ የጠባያችንም መዥጎርጎር የቱን ያህል እንደተለጠጠ ታዘብኩ፡፡ የምንጠላውን ሰው እንዴቱን ያህል ጥላሸት እንደምንቀባው አየሁ፡፡ መጥኔ ለኢትዮጵያ፤ አንተ ግን በርታ፡፡ ቢቻልህ ደጋግሜ እንደጠቆምኩልህ በሃይማኖት ላለመግባት ሞክር፡፡ ማርክሳውያን ሃይማኖት ናርኮቲክስ ነው የሚሉት ወደው አይደለም – ክርስቶስንም እኮ ሰቅለው የገደሉት አክራሪ ሃይማኖተኞች ናቸው፡፡ በደደብ ሰው እጅ የገባ ጠበንጃ ብዙ አደጋ እንደሚያስከትል ሁሉ እምብዝም ባልተማረ ሰው ዘንድ በስሜት ብቻ ዘልቆ የሚገባ ሃይማኖትም ለከፋ አደጋ ይዳርጋልና የሀገርህን አጠቃላይ ሁናቴ ዕወቅ፡፡ እየየም ሲዳላ ነው ወንድማለም፡፡ ሀገርህ ልታጣህ አትፈልግም – ይህን ጠንቅቄ አውቃለሁ በውቀቱ፡፡ በል እንግዲህ አፄ ቴዎድሮስን አንኳሰህላቸው እንግሊዞች ለባንዳነትህ ከሸጎጡልህ  ከዚያች የገንዘብ ጉርሻ ቆንጠር አድርገህ በአድራሻየ ላክልኝ (አሃ! “ቆንጠር” አድርገህ የሚባለው ለካንስ ለጥሬ ነው – “ቀንጨብ አድርገህ” ለማለት ነው – “ስምህን አውሰኝ” ማለትህን ተከትሎ በተሰጠህ ትምህርት ላይ የታከለ ሌላ ትምህርት ነው – ስማንጂ ግን “ስምህን ንገረኝ” ማለት የሚያቅትህ ዐማርኛ ያን ያህል የሚያጥጥህ ነበርክ እንዴ? ለነገሩ ዐማርኛ ተወለደበት ከተባለ ክ/ሀገር የወጣ ሊቅ ዐማርኛ አደገበት ከተባለ ክ/ሀገር የወጣን ተማሪ ቢያስተምር ነውር የለውም – የምር ግን ያም ቁም ነገር ሆኖ መነገሩ ገርሞኛል በውቄ)፡፡ ሆ!

1 comment:

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete