Translate

Monday, March 7, 2016

የህወሃት መከላከያ ሠራዊት ወደ ኤርትራ መጠጋት እውን ከኤርትራ ጋር ጦርነት ለመግጠም ወይስ በኤርትራ የሚገኙ አማጽያን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ለማድረግ?

አንተነህ ገብርየ
አጭር መግቢያ፦ከ1998 እስክ 2000 የዘለቀው ጦርነት ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ የሰው ሕይወትና የሀገር ሀብት ማውደሙ ይታወቃል።ያኔ ህወሃት ጨርቅ ነው ሲለው የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ በማውለብለብ መላ ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲሰለፉ ጥሪ ማቅረቡ፤እንደ አሮጌ ቁና የጣለውንና የበተነውን የቀድሞ ሠራዊት መማጸኑም ይታወቃል ማንም አላቅማማም ሁሉም ጥሪውን ተቀብሎ ዘመተ ዘመቻው ቀጥሎ ወደ አሥመራ ብቅ ሲል የኢትዮጵያው ጦር እንዲያፈገፍግ ተደረገ የኢትዮጵያን መሬት ለኤርትራ በማስረከብ የተጠናቀቀው ጦርነት የኢትዮጵያ ድል ተብሎ በቅጥፈት ታወጀ።  ነገር አሁንም እልባት አላገኘም ገዥው የህወሃት ቡድን የንጹሐንን ደም በማጉረፍ ተኪ አይገኝለትምና ይህንም እንዲህ አድርጎት ፀጥ አለ።
ያኔ የቀድሞው ጦርም ሆነ ሕዝቡ ህወሃትን የተቀላቀለው የህወሃትን ውስጣዊ አጀንዳ ማንነትና ግብ ባለመረዳት ሲሆን ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ህወሃት ምን ያህል አረመኔያዊ ተቋም እንደ ሆነ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ራሱን በተግባር አስተዋወቀ ይህ ጦሱም ብዙ የተቃዋሚ ኃይሎች እንዲያብቡ፤ በርከት ያሉ ጋዜጠኞች ጦማሪያን የሥርዓቱን ጭራቅነትና ዝርክርክነት በስፋት እንዲያጋልጡት አደረገ።
በነዚህ ጥረቶች ህወሃት እንደ እባብ ገላ ከሕዝብ ሾልኮ እርቃኑን ቀረ።ሕዝብና ህወሃት ዳግም ላይገናኙ ሕዝብ ሥርዓቱን በማስወገድ ጎዳና ብቻ መብቱን ማስከበር እንዳለበት አመነ።አሁን ከላይ እንደገለጽኩት ኤርትራና የህወሃት መከላከያ ኃይል ወደ ጦርነት ቢገቡ ምን ሊከሰት ይችላል የሚል ነጥብ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ያነጋገረ ጉዳይ መሆኑና እያነጋገረ እንዳለ ግልጽ ነው ። እንደ እኔ የግል አስተያየት ህወሃት ከጉራና ማስፈራራቱ አልፎ ጠብ ቢጭር የህወሃት ፋሽስታዊ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ትካሻ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከትምለታል እንጅ የሚያገኘው ትርፍ አይኖርም(አዲዮስ ህወሃት)። የምንልበት ጊዜ እየቀረበ መምጣቱን አመላካች ነው።
በመግቢያ ያስቀመጥኳቸውን መሠረታዊ ሀሳቦች በዝርዝር ለመመልከት እንደሚከተለው አቅርቤያቸዋለሁ።
ህወሃት ጦሩን አስጠጋ የሚባለው በኦማሐጀርና ተሰነይ ነው ይህ እንግዲህ በሱዳን በኩል በገዳሪፍና በከሰላ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ሱዳን ደፍራ ይህን ተግባር ከፈጸመችው በሱዳንና በኤርትራ ሊያስነሳ የሚችለው አደጋ ቀላል አይሆንም ። ኤርትራ እንደ ህወሃት ከሱዳን ጋር በጥቅም የተሳሰረች አይደለችም። ስለዚህ ኤርትራ በሱዳን ላይ የምትወስደው ርምጃ ሱዳንን የሚጎዳ ይሆናል።ህወሃት እውን ኤርትራን ለመግጠም የሚያስችል መሠረታዊ ምክንያት አላት ወይ? ያላት ሠራዊትስ ብቃት አለው ወይ?ምንም አይነት ምክንያትና ማስረጃ ሳይኖር ጦርነት እገጥማለሁ ማለትና ጦር ማስጠጋት በራሱ እንደ ጦር አጫሪነት አያስቆጥርም ወይ? የሚሉ ጉዳዮችን ማንሳታችን የማይቀር ነው።እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በኔ እይታና አመለካከት የሚከተለውን አይነት አንድምታ አስቀምጣለሁ።
1ኛ/ የህወሃትን አነሳስና አሁን ላይ ያደረሰውን ጉዞ ስንመለከት፦
ህወሃት መጀመርያ አንድ ሁለት እያለ ራሱን ወደ ድርጅትነት አሳድጎ ሲነሳ መሠረታዊ ጥያቄው የክፍለ ሐገሩን ምርታማ አለመሆንና በኢኮኖሚ በኩል ትግራይ ውስጥ ያለውን ድኸነት ለመቅረፍ ሲባል ለም የሆኑ የአጎራባች ክፍለ ሐገሮችን በኃይል በመንጠቅ ትግራይን ገንጥሎ ሌላ አገር ለመፍጥር መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ መጀመርያ ሁለት ነገሮችን አስቀድሞ ማጽዳት የግድ ይል ነበር።ይኸውም አማራን ከምድረ ኢትዮጵያ ማጽዳትና ዘሩን ማጥፋት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ እምነትን ህወሃት የሚቆጣጠረው ውስጡ የተዳከመ ተቋም ማድረግ ነበረበት።ለምን?ብለን ጥያቄ ልናነሳ እንችል ይሆናል? መልሱ የሚሆነው አማራው ለዚህ አመለካከት ፈቃደኛ ሊሆን ስለማይችል የመረረ ርምጃ መውሰድ ነበረበት እነሆ በወሰዱት ርምጃ ከ5ሚሊዮን በላይ የሚሆን የአማራ ነገድ ሕዝብ ደብዛው ጠፍቶ ዛሬ በሞረሽ ወገኔ ከፍተኛ ጥረት ጥናት ተካሂዶ የጥናቱ ከፊል በአንዳንድ ድረ-ገጾች በይፋ ለአንባብያን ቀርቦ ኢትዮጵያውያን እየተነጋገሩበትና በጣም አስደንጋጭ አሳዛኝና እልህ የሚያስይዝ ሆኖ ተገንቷል።የዚህ አካል የሆነው አንዱ ገጽታ በጠለምት፤ጠገዴና ወልቃይት ነዋሪ ሕዝብ በኃይል ተገደህ ትግሬ ትሆናለህ የሚለው የመሬት ነጠቃ አባዜ ነገር አጭሮ ነብስ ዘርቶ የህወሃትን የመብት ረገጣና አፈና ሰብሮ ጢም ብሎ በሞላ አዳራሽ ውስጥ እነማን መቼ የት እንደተገደሉ በሕይወት ተርፈው የተገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች የምስክርነት ቃላቸውን እየሰጡበት ይገኛል።
በኅይማኖታችን ጣልቃ በመግባት መንግሥታዊ (ህወሃታዊ ኃይማኖት)እምነት እንዲኖረን ህወሃት ካድሬዎቹን በቤተክርስቲናችን ውስጥ አስርጎ በማስገባት ለዘመናት ተከብሮ የኖረው ሲኖዶስ ተጥሶ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ እንደፖለቲካው ሁሉ መሾምና የህይማኖቱ ሹመትም ከአንድ አናሳ ጐሣ የተወለዱት እንዲቆጣጠሩት ተደርጎ ሕዝበ ክርስቲያኑ በውጭና በውስጥ በሚባል ሲኖዶስ ተከፍሎ በመሀሉ የመከፋፈልና አለመተማመን ብርድ ገብቶ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉኡላዊነት ለዳር ድንበሯ መከበር ትልቁ ጋሻና ጦር ሆኖ ሲያገለግል የኖረው ቤተክርስቲያናችን በዘመነ ህወሃት ተደፍሮ እኛም ማዶ ለማዶ ቆመን እንድንተያይ አድርጓል።ይህ አሁን ህወሃት እተገብረዋለሁ ለሚለው ከኤርትራ ጋር ጦር የመማዘዝ ጉዳይ ህወሃትን በከፋ ሁኔታ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው።ይህን ህወሃቶች ጠንቅቀው ያውቁታል እንዲያው በአዋጅና በጉራ በከንቱ ድንፋታ ስነ-ልቦናዊ ጫና ለመፍጠር እንጅ የህወሃት አቅም ዳገት እንደማያወጣ መገመት ወይም እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።ይህ አሁን ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ እየተቀጣጠለ የመጣው የኢትዮጵያውያን አልገዛም ባይነትም የህወሃትን አቅም ወይም ሕዝብ ለመምራትና ለማስተዳደር የሞራል ይሁን የአካላዊ ብቃት እንደሌላቸው ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምልከታ ነው።እስኪ ማን ይሙት የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት ከህወሃት ካድሬ ልቆ ነው እንዴ በኦሮሞ ክልል ሠራዊቱ ወደ አስተዳዳሪነት የገባው?የህወሃት ሥርአት አንዱን ጨበጥ አድርጎ በመያዝ በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ የሚመረምር ሳይሆን የሞክረን እንየው አይነት በመሆኑ ወደ ውድቀት መግባት እንዲችል አድርጎታል።
2ኛ/ እራሱን የመከላከያ ሠራዊቱን ቁመናና ተክለ ሠውነት እንመልከት፦
የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት ከላይ እስከ ታች ያለው መዋቅር የሚመራው በአንድ አናሳ ጎሳ የትግራይ ተወላጆች ብቻ ሲሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያ በክልል ወይም በአዲሱ መሳፍንታዊ አገዛዝ እጅ እንደገባች አስታውሳለሁ የመከላከያ ኃይሉ በክልሎች የህዝብ ብዛት ስብጥር እንዲኖረው ሲደረግ ከህወሃት የሚቀነሰው ኃይል ብዙ በመሆኑ አማርኛ መናገር የሚችለው የህወሃት ሠራዊት የአማራውን የሠራዊት ኮታ እንዲሸፍን የተደረገ ሲሆን ከሌላው ብሔርና ብሔረሰብ ከመጣው የመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ያለው ግንኙነት የሻከረ ሊበጠስ ትንሽ ምክንያት ብቻ የሚፈልግ በመሆኑ እና ይህ ከታች እስከ ላይ ያለው በመከላከያ ኃይሉ ውስጥ በመሪነት የሚገኘው አካል የተደራጀ በዝርፊያ ሀብት ያፈራ ባለ ሰፊ እርሻ ባለትልቅ ፎቅና ቱጃር ነጋዴ ስለሆነ ጦሩ ከሰገባው ሲወጣ ሞትን መርጦ ደፍሮ ይገባል ብሎ ማሰብ ከንቱነት ነው። የጥይት ማብረጃና የጦርነት ገፈት ቀማሹን ከድሃ ቤተሰብ የመጣውን  የሠራዊቱ አባላት ማን መርቶ ወደ ጦርነቱ ይከተዋል ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው።አማራውን ከአማራ ኦሮሞውን ከኦሮምው፤ኦሮሞውን ከአማራ ወንድሞቹ ጋር እያባሉ የመጡ አይደሉ በቀላሉ ሹመት መስጠት እርስ በርሱ እንዲተላለቅ ማድረግ የተካኑበት ሴራ ስለሆነ ይህን ማድረግ ይችላሉ ወደፊት መግፋት እንዲችል ደግሞ ከኋላው ሆኖ ጀርባውን የሚመታ ከግንባሩ የተጻራሪው ወገን የጥይት አረር እንዲበላው ማድረግ የተለመደ ነው።
ይህ ጉዳይ ከጉራነት አልፎ ወደ ተግባር ከተቀየረ ሊሆን ይችላል ያልኩትን ከፍ ብየ ሳስቀምጥ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ሲፈጠር የመከላከያ ሠራዊቱ ከህወሃት እሥር ሊወጣ የሚችልባቸው ብዙ እድሎች ሊፈጠሩለት ይችላሉ። ትጥቁን ይዞ ወይም ትጥቁን ደብቆ ከፊት ለሚገጥመው ወይም ወደ ሌላ አቅጣጫ ከድቶ መጥፋት ይችላል።እንደ እምሰማውና እንዳለኝ መረጃ ኤርትራ ውስጥ ቢያንስ ከ12 የማያንሱ ህወሃትን በነፍጥ እናስወግዳለን ብለው የተደራጁ የተቃዋሚ ኃይሎች ስለሚኖሩ ወደ እነሱ የመሄድ ወይም እነዚህ ኃይሎችን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ከተመቻቸ ህወሃት ወሽመጡ የሚቆረጥበት ሌላኛው መንገድ ነው።እንዲህ አይነቱን መንገድ መከተልና መጠቀም በአንድ አውደ ውጊያ ከሚገኘው የጦርነት ድል የበለጠ ይሆናል።
3ኛ/ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙትን የህወሃት ተቃዋሚ ኃይሎች እንዳይወጡ እንዳይገቡ ለመዝጋት ታስቦ ከሆነ ለሚለው፦
ህወሃት የማይፈነቅለው ድንጋይ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለምና አጥር አጥሮ በር ዘግቶ የግዛት ዘመኑን ለማራዘም ያስባል ይሁን እንጅ ይህ ከቅጀት የዘለለ ሊሆን አይችልም።ምክንያቱም እነሱም በአንጻራዊነት የህወሃት ሠራዊት የታጠቀውን ነፍጥ የታጠቁ ስለሆነ እንኳን ያን ያህል ሰፊ የመሬት ቆዳ ስፋት ሊሸፍን የሚችል ኃይል የሌለውን ቢኖረውም የተቃዋሚ ኃይሎች ቁልፍ በሆነና ገዥ በሆነ ቦታ ከኤርትራ ለመግባትም ሆነ ለመውጣት ካሰቡ ደፈጣ በመጣል ሰብሮ መውጣት ወይም መግባት ይችላሉ።ከዚህ ባሻገር ሊሆን የሚችለው ከየአቅጣጫው ጦርነት በመክፈትና ኃይሉን በመከፋፈል አቅሙን ደካማ ማድረግና የፖለቲካ ሥራ በመስራት የህወሃትን ሠራዊት ወደ እነርሱ እየሄደ እጁን እንዲሰጥ የሚያደርግ አጋጣሚ ነው የሚኖረው።
4ኛ/ የኤርትራ ሠራዊትና ሕዝቡ ወይም ሠራዊቱ ለመንግሥት ያለው ታማኝነት፦
በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ እውቀት ባይኖረኝም የምገምተውን ማስቀመጥ እችላለሁ።አገዛዙ ወይም የኢሳይያስ አፈወርቂ መንግሥት አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ሕዝቡን ያስመረረ እየተባለ እንደሚተች፤ጋዜጠኞችን የሚቃወሙትን ፖለቲከኞች እንደሚያስር እንደሚገርፍ ከራሳቸው ከኤርትራውያን እሰማለሁ።መሠራዊቱ በኩል ግን አቅሙን ባላውቅም እንደ ህወሃት ሠራዊት ውስጡ እንዳለቀ ጨርቅ የተበጣጠሰ አለመሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል።ከሁለቱ ማንኛው በከፋ ጫፍ ላይ ይገኛል ሲባል ግን ህወሃት ግማሽ አካሉ መቃብር ውስጥ ያለ ያም በመከላከያ ሠራዊቱና በደህንነቱ በፖሊስ መዳፍ እጅ ያለ ስለሆነ የተቃዋሚ ኃይሎች እርስ በርስ ከመሰረጃጀት አልፈው ወሬያቸውን ከምንሰማ እንዲህ አይነቱን ለህወሃት የጀርባ አጥንት ሆኖ በሚገኘው ኃይል ላይ የማፍረስ ጨርሶም የመናድ ተግባር ላይ ቢያጠምዱ በለሱ እንደሚቀናቸው አምናለሁ።
በመጨረሻ ጹሑፌን ከማጠናቀቄ በፊት መግለጽ የምፈልገው ነገር ቢኖር ጦማሪያን፤ጋዜጠኞች፤ምሁራን፤ጸሐፊና ደራሲያን የፖለቲካ ድርጅት አባላትና አመራሮች ትኩረታችሁን ሕብረት እንዲፈጠር ከዚያም አልፎ አንድነት እንዲመጣ በማድረግ ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን እየተማጸንኩ አሁን ላይ ከየአቅጣጫው የሚሰሙት የሕዝብ አልገዛም ባይነት በአግባቡ በድርጅት ደረጃ ካልተመራ የየካቲት 1966ቱ ሕዝባዊ ማዕበል ተቀልብሶ ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት ማጥ የወደቀችበት አይነት ሁኔታ ላይከስት ምንም ዋስትና የለንም። እንዲያውም የ1966 የየካቲት የሕዝብ አመጽ ቢያንስ መፈክሮቹ አገራዊ ነበሩ ያሁኑ ግን ለየት ያለና ሕዝቡም አንዱ ከሌላኛው ጋር በጋራና በእኩልነት ሊያኖረው የሚችል ሁኔታ መኖሩን የጨለመበት የህወሃት ሥርአት አደገኛ ጠባሳ ያሳረፈበት ስለሆነ ብርቱ ትግል የሚጠይቅ በመሆኑ ለሕዝብ ተአማኒነትና የሕዝብን ይሁንታ አጣምረን ልንጓዝ ይገባናል።ትክክለኛና ዲሞክራሲያዊ ሥርአት እንመሠርታልን ብለን ከተነሳን የመንግሥት ሥልጣን ሊይዝ የሚችለው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ ስለሚሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አመዛዛኝ አርቆ አሳቢ ትክክለኛ ፍርድ ፈራጅ ስለሆነ ማን ከሕዝብ ጋር እንደቆመ ማን ለሕዝብ ነፃነት እንደታገለ ፍርዱን በካርዱ ስለሚፈርድ ይህን በፀጋ ተቀብለን አገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት መጠነ ሰፊ አደጋና ከነዚህ የባንዳ ዘር የሆኑ አራዊቶች መንጋጋ ለማላቀቅ እንትጋ እላለሁ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አንድነታችን ጥንካሬያችን ነው!!

No comments:

Post a Comment