Translate

Tuesday, March 22, 2016

በደቡብ ኦሞ ዞን በኢንቨስትመንትና በስኳር ልማት ፕሮጄክት ስም የሚፈጸመው ሙስናና የሃብት ዘረፋ መረን የለቀቀ ነው

በልሁ ማንከልክሎት (ክፍል ሁለት)
  1. በኢንቨስትመንት ስም በሚደረገው የመሬት ቅርምት የወ/ሮ አዜብ መስፍን እጅ እንዳለበት ተገለጸ፤
  2. በመሬት ቅርምቱ አንድ መሬት/ቦታ ለተለያዩ ‹የሃሰት ኢንቨስተሮች › ተደጋግሞ እየተሰጠ ነው፤
  3. ህወኃቶች የዞኑን መሬት በመቀራመት ብቻ የሚዘርፉት የአገር ሃብት ከ930 ሚሊዮን ብር በላይ ይደርሳል፤
  4. በስኳር ልማቱ ፕሮጄክት በተለያዩ የሥልጣን ቦታዎች የህወኃት አባላት ተሰግስገዋል፤
  5. በስኳር ልማቱ ፕሮጄክት የሃሰት ሪፖርት እንዲያቀርቡ የተገደዱ ሠራተኞች እየለቀቁና እየተባረሩ ነው፤
  6. ደቡብ ኦሞ ዞን እኩይ ተልዕኮ ባለው ሰፈራ ስም የግጭት ቀጠና ሥጋት ተጋርጦባታል፡፡
This is 2016 Ethiopia where the government chains and forcefully removes indigenous peoplesባለፈው ሣምንት በደቡብ ኦሞ ዞን የህወኃት አባላትና ደጋፊዎች በኢንቨስትመንት ሥም የሚፈጸመውን የመሬት ቅርምት በሚመለከት በዞኑ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች  ባለሙያዎች በተደረገው ጥናት ላይ የተመለከተውን መረጃ ትክክለኛነት ያረጋገጡ ወገኖች ከ2006  በኋላ የተፈጸመውና የተገኘው መረጃ ደግሞ በእጅጉ የሚያስገርም ዓይን ያወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ተጨማሪ መረጃ መሰረት 5 490 ሄክታር መሬት ‹ባለቤት› የኦሞ ሸለቆ አግሮ ኢንዱስትሪ የበላይ ጠባቂ ወ/ሮ አዜብ መሥፍን መሆናቸው፣ እንዲሁም ሳትኮን 16 500 ሄክታር መሬት ከተረከበና በመሬቱ ሥም ብድር ከወሰደ በኋላ መሬቱ ላይ አንዳችም ሥራ ሳይሰራ በመተው መሬቱ ለሌሎች ሰዎች መከፋፈሉን ፣…. የተገኙት ተጨማሪ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የወ/ሮ አዜብ መስፍን እጅ እስከ ደቡብ ኦሞ መድረሱና የ፣ሳትኮን› ድርጊት በእጅጉ እንዳስገረማቸውና ህወኃት በአባላቱና ደጋፊዎቹ በአገሪቱ ሃብት ላይ የሚፈጽመውን ዘረፋ በግልጽ የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ  በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል የዞኑ ተወላጅ አልሚዎች /ኢንቨስተሮች ላይ የሚፈጸመው ደግሞ የዚህ ተቃራኒ መሆኑ እንዳሳዘናቸው አልሸሸጉም፡፡ ይህም በዞኑ ነዋሪዎች የሚደረገው በመሬት ላይ የሚታይ ተግባራዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሴክተር መ/ቤቶች የአዋጭነት፣ የአካባቢያዊ  እና የማኅበራዊ ተጽዕኖ ተስማሚነት በባለሙያ ጥናት ተረጋግጦ የተሰጠ የባለሙያ ምስክርነትና ድጋፍ ዋጋ ተነፍጎት  የባንክ ብድር ያልተፈቀደላቸው ሲሆን በተቃራኒው አየር በአየር አንዳች ነገር ላልሰሩት የህወኃት አባላት እንደሚሰጣቸው ፣እነዚህ የጊዜው ሰዎች  የጂንካ ባንኮች ሲያነገራግሩ በቀጥታ ወላይታ ወደሚገኙ ባንኮች እንደሚሄዱና በቀላሉ ብድሩን እንደሚቀበሉ በተጨባጭ ማስረጃዎች የተረጋገጠ መሆኑን  ባለሙያዎች ያስረዳሉ ፡፡ ለዚህ ማስረጃነትም የዞኑ አግባብ ያላቸው መ/ቤቶች ባለሙያዎች ባካተተ ቡድን ጥናት ላይ ተመርኩዞ 156 ሄክታር ያለሙትና ቡና ያመረቱት  አቶ ተፈሪ ከበደ እና 300 ሄክታር ላይ ጥጥ አምርተው ለገበያ ያቀረበው ናሳ/አቶ ገበየሁ ምናሉ/ እርሻ ብድር ተከልክለው ሳትኮንን ጨምሮ እነ ‹እንቶኔ› ያለችግር አዲስ አበባ ተቀምጠው ብድር ማግኘታቸውን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዞኑ የግብርናና የኢንቨስትመንት ቢሮ ሠራተኞች በዞኑ አንድን ቦታ  ለተለያዩ ‹የሃሰት ኢንቨስተሮች› በመሰጠቱ የተሰጠው የኢንቨስትመንት መሬት ድምር በዞኑ ውስጥ ለዚህ ዓላማ ሊውል ከሚችለው ቦታ እንደሚበልጥ፣ ለዚህም ባለፈው ዓመት ለሎጅና ደን ቁጥጥር በሚል ለአንድ ‹የትግራይ ኢንቨስተር ›በበና ጸማ ወረዳ  የተሰጠውን በምድር ላይ የማይታይ  50 000 ሄክታር መሬት (ይህን በማሳየትም ለቦታ ዝግጅት/ምንጣሮ በሚል ብቻ ከባንክ  ብር 297 ሚሊዮን 500 ሺህ ሊጠየቅ እንደሚችል፣ይህም ህወኃቶች ከዞኑ የሚዘርፉትን ወደ ብር ከ930 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያደርሰው )፣ እንዲሁም ምንም ሳይሰራበት ብድር ከተወሰደበት በኋላ  ለሌሎች የተከፋፈለውን የ‹ሳትኮን› 16 500 ሄክታር  በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚያስረዱት  ከዞኑ ተወላጆች ውጪ ያሉት  የህወኃት ‹ኢንቨስተሮች› የኢንቨስትመንትና የንግድ  ፈቃድ ለማውጣትና መሬትና ብድር ለማግኘት የአካባቢው ማኅበረሰብ ቀርቶ የዞኑ ሴክተር መ/ቤት ባለሙያዎች እንዲያውቁት እንደማይደረግ…….  እና ከዞኑ አስተዳደር ከላይ በሚወርድ መመሪያ  የድጋፍና ትብብር ደብዳቤ እንደሚጻፍላቸው ፣ በባለፈው የባለሙያዎች ጥናት የለማ የተባለው ቦታም ለሠራተኞች ቀለብ በሚል በቆሎ ከመመረቱ ውጪ አንዳቸውም በፕሮጀክቱ ላይ የተገለጸውን የምርት ዓይነት (ጥጥ፣ ቡና፣ፓልም….) አንድም ሄክታር አልለማም፣ አንድ  ኩንታል አልተመረተም፡፡ ነገር ግን መሬቱን  ለምርት ለማዘጋጀት በሚል በቦታው ላይ ያለውን የግራር ዛፍ በመጨፍጨፍ ከሰል እንደሚያመርቱና ወደ አዲስ አበባ እንደሚጭኑ በዚህም የአካባቢው ደን እየተጨፈጨፈ መሆኑን ባለሙያዎች በመስክ ስራ ከህዝቡ ከሚቀርበው አቤቱታና በአይናቸው ከተመለከቱት እንደተረዱ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ባለሙያዎቹ የህወኃት የሃሰት ኢንቨስተሮች ዓላማ ማልማትና ከልማቱ ጥቅም ማግኘት ሳይሆን የአካባቢውን ሃብት በማሳየት  አየር ባየር ብድር ከመሰብሰብ ያለፈ እንዳልሆነ በቁጭት ይገልጻሉ፤ ከዚህም አልፎ በነዚህ የህወሃት አባላት በሚቀርቡ ከላይ ጸድቀው በሚመጡ የኢንቨስትመንት ፕሮፖዛሎች መሰረታዊ የአዋጭ4ነትና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ መስፈርቶችና  የጥናት ግብኣቶች አለመካተታቸው ላይ ጥያቄ በሚያቀርቡ ባለሙያዎች ላይ ከ ‹ታዛዦቹ የዞን ሰክተር መ/ቤቶችና አስተዳደሩ› ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው አክለው ገልጸዋል፡፡
በሌላ ወገን ያሉት የዞኑ ተወላጆች ግን ያለበቂ ድጋፍና ትብብር ያላቸውን አቅም በሟሟጠጥ  የተንቀሳቀሱ መሆኑን  በዚህም ከላይ በተጠቀሱት የለማውን 456 ሄክታር ጨምሮ  በዞኑ ከ950 ሄክታር በላይ አልምተው ( አቶ ሁሴን 150 ሄክታር ፣ አቶ አሸናፊ ግርማ 50 ሄክታር፣ አቶ ሙስጠፋ 100 ሄክታር፣ አቶ አህመድ 36 ሄክታር፣ ሱዳሜል 162 ) ቡና፣ ጥጥ፣ ሰሊጥና ሌሎች ሰብሎችን አምርተው ለገበያ ማቅረባቸውን ይህም በግልጽ   ከሴክተር መ/ቤቶችና አስተዳደሩ አልፎ በአካባቢው ነዋሪዎች የሚታወቅ መሆኑንና ከዚህ ልማትም በፕሮጄክቱ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በቀጥታና ተዘዋዋሪ ጥቅም እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
እነዚህ‹‹ ስለዞናችንና አገራችን ከእንግዲህ ዝም አንልም›› የሚሉ በየሴክተር መ/ቤቶች ያሉ ባለሙያዎች በብሄራዊ ደረጃ በተጀመረው የስኳር ማምረት ስም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በስኳር ፕሮጄክቱ እርሻ ዙሪያ የሚገኙትን የሱርማ፣ የሙርሲ እና ቦዲ ብሄረሰቦች ህይወት ለችግር መጋለጡን፣ በቀጣይም  የ- ኛንጋቶም፣ዳሰነች፣ ካራ ፣ሃመር ብሄረሰቦች ህይወትም ለአደጋ እንደሚጋለጥ ግልጽ መሆኑን በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የአካባቢው ነዋሪዎችና  ከመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ጋር ለተደጋጋሚ ግጭት መዳረጋቸውንና የውጪ ዜጎችን ጨምሮ ለሳላ ማጎ ወረዳ  የመንግስት ሰራተኞችና ነዋሪዎች እንዲሁም ለፕሮጄክቱ ሠራተኞችና ወደዚያ ለስራ የሚሄዱ ዜጎች ህይወት መቀጠፍና አካል መጉደል ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የሚደረገውን ሙስናን የሚደግፍ  ህገወጥ አሰራር፣ የህወኃት አባላት መሰግሰግና የሚቀርበውን የሃሰት ሪፖርት በሚመለከት እንዲሁም እኩይ ተልዕኮ አንግቦ በሚከናወነው ሰፈራ በዞኑ ያንዣበበውን የግጭት ሥጋት በሚመለከት በቀጣይ ክፍሎች በተከታታይ እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተው፤አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንና ሚዲያዎች ሁሉ እነዚህን የጥናት ሪፖርቶች ለኢትዮጵያዊያን እንዲያሰራጩ፣ በመተርጎም ለዓለም አቀፍ የአካባቢ ውድመትና የሰብዐዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት እንዲያደርሱ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

No comments:

Post a Comment