Translate

Tuesday, March 1, 2016

“ሀገራችን ላይ እየኖርን አይመስለኝም” ታክሲ አሽከርካሪ

“አብዛኛው ታክሲ በአድማው ስላልተሳተፈ በማኅበራዊው እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ችግር የለም" ጌታቸው ረዳ

add taxi

“ሁላችንም የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ነን።ሕጉ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ክሥራ ውጪ እንሆናለን።’’ በዛሬው ዕለት የታክሲ ማቆም አድማ ካደረጉት የታክሲ አሽከርካሪዎች በከፊል፡፡

በአዲስ አበባ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ደንብን ለማስከበር ከአምስት ዓመት በፊት የወጣውና በከፊል ሲተገበር የነበረው ሕግ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ በመጀመሩ የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች በሙሉ በዛሬው ዕለት ሥራ የማቆም አድማ መተው ውለዋል፡፡
ፌደራሉ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ትናንት ባወጣው መግለጫ ትግበራው ለሦስት ወር መራዘሙን አስታውቋል፡፡አሽከርካሪዎቹ ደግሞ “ለሦስት ወር ማራዘም መፍትኄ አይደለም ዘላቂ መፍትሄ እንፈልጋለን” ይላሉ፡፡
አሽከርካሪዎችን የአዲስ አበባን ፖሊስ ኮሚሽንን ያነጋገረችው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ድምጽ እዚህ ላይ ያድምጡ፡፡
ከዚህ ሌላ ኢሣት ባሰራጨው መረጃ ላይ እንደተጠቆመው አድማው ከመካሄዱ ሁለት ቀናት በፊት ከተሰሙት ብሶቶች መካከል የሚከተሉት እንደሚገኙ ጠቁሟል፤
“መብላት ብቻ ሳይሆን መኖር ነው ያቃተን። ትላንት ተከሰሰኩ … እየፈራሁ እየተንቀጠቀጥኩ ነው የምሰራው። መኖርኮ አልተቻለም።”
ሌላው ትራፊክ ፖሊስ ሊቀጣው ያለ የታክሲ ሾፌር የተናገረው ይህ ነበር፤
“የኛ ልጆች ሲራቡ፣ የአንተ ልጆች ጠግበው ይበላሉ ሠርቼ መኖር ስለማልችል የምፈልገው መታሰር ነው፡፡”
የህወሃት/ኢህአዴግ አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ ሰኞ ከሰዓት በኋላ በሸገር ኤፍ.ኤም. ሲናገሩ “አብዛኛው ታክሲ በአድማው ስላልተሳተፈ በማኅበራዊው እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ችግር የለም” ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ የታክሲ አድማ ሁለተኛ ቀኑን ቀጥሎዋል፡፡

No comments:

Post a Comment