Translate

Monday, March 7, 2016

ከድጡ ወደ ማጡ አሰብ በአረቦች እጅ ገባች‬

 ዶ‬/ርያዕቆብ ኃ/ማሪያም


የአገራችን አንድነትና ብሎም ሕልውና በቋፍ ባለበት በዚህ ቀውጢ ወቅት ውይይቱ ሁሉ ማተኮር ያለበት ለሥጋቶቹ ምንጭና ምክንያት ስለሆኑት ስለ ዴሞክራሲ ደብዛ መጥፋት፣ ስለፍትህ መቅጨጭ. በብሔረሰቦች መካከል ስለሚታዩት ጥላቻና ግጭቶች እነዚህን የወለደው ሥርዓት ስለመለወጥ ብቻ መሆን አለበት ሌላው ሁሉ ገብስ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በአሁን ወቅት ከእነዚህ ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ስርዓቱን ለውጦ ዴሞክራሲና ፍትሕ ለማስፈን የሚደረገው ትግል መዘናጋት ይሆናል የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የአሰብ ወደብ ወደ ሳውዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ መተላለፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሳወቅና በውጭ አገር በቪዥን ኢትዮጵያና በኢትዮ-ኤርትራ ሶሊዳሪቲ ኮሚቲ የሚደረጉ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የማግባባትና የማቀራረብ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ ታስቦ የተጻፈ ነው፡፡ በተጨማሪም ዘላቂ የአገር ጥቅሞችን መዘንጋት የኋላ ኋላ ሕልውናን መፈታተን ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ አገር ከሌለ ዴሞክራሲ ምን ሊፈይድ፣ ፍትሕስ ምን ሊረባ፡፡
ምናልባት የአገር ሕልውናን እስከመፈታተን ሊደርሱ ከሚችሉ ከዋነኛ የአገር እሴቶች አንዱ የባህር በር አለመኖር ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ፡፡ በማይጨው ጦርነት ለሽንፈታችን ምክንያት ከሆኑ ከዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ የገዛችው የጦር መሳሪያ በጅቡቲ በኩል ወደ አገር እንዳይገባ ፈረንሳይ መከልከልዋ እንደነበር መዘንጋት የለብንም፡፡ 


ኢትዮጵያ ምትገኝበት አደገኛ አካባቢ ሲሆን ጂኦፖለቲካውና ሃይማኖት ከስሌት ሲገባ የባህር በር በተለይም የኢትዮጵያ የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ ከሸቀጥ ማስተላለፍ በዘለለ የሕልውና ጥያቄ ሆኖአል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ወሳኝነት እንዳለው እያወቁ “አሰብ አሰብ የምትሉት ምንድን ነው” እያሉ ይህንን ትልቅ ሕዝብን ያስጨነቀና እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ሲያጥላሉ ተደምጠዋል፡፡ በዚህ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም በተቃዋሚዎች መሃከል ሌላ አዲስ የጭቅጭቅ ርእስ ላለመክፈት ሲባል ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትዝብት እንተወዋለን፡፡ ጥቅሙን ከሕዝብ በላይ የሚያውቅ የለምና፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም የዓለም የሃይል አሰላለፍ ባልተገነዘቡ፤ የአካባቢው ጂኑፓለቲካና ሃይማኖታዊ ሁኔታዎችን ማገናዘብ ባልቻሉ ከዘር ወይንም ከጎሳ ውጭ ሌላ ነገር በማይታያቸው የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ሁለዘርፍ ቁርኝትና መስተጋብር ከመጤፍ ባልቆጠሩ መሪ ተብዮች አመራር ስር ወደቁ፡፡ ከዚያም ወንድም እህት የሆነው ሕዝብ በጦርነት ተላለቀ:: ኢትዮጵያ በታሪኳ በፍፁም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከቀይ ባህር አካባቢ ተገልላ በዓለም ትልቁ ወደብ አልባ ዝግ አገር ሆነች፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካም ታሪክ ወደ ተከታታይ ትውልድ ሲንቆረቆር ኢሕአደግ በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ የሚታወሱበት ዋነኛ ቅርስ (ሌጋሲ) ኤርትራን አስገንጥለው ኢትዮጵያን በእግር መንገድ እርቀት ወደብ አልባ ማድረጋቸው ይሆናል፡፡

እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል የተደረገው አሳዛኝና ዓላማ ቢስ ጦርነት እንደ ተደመደመ ሁለቱም አገራት ለድርድር ወደ አልጄሪያ ከማቅናታቸው ቀደም ብሎ በአገርም በውጭም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ወደብ አልባ ከመሆን ጋር በተጓዳኝነት የኤኮኖሚ የስኩሪቲና የፖለቲካ ክስረቶች ለኢሕአደግ ለማስገንዘብ ኒው ዮርክ በተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ደጃፍ ከተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ጀምሮ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልማሱት ሳር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባትም የአስብ ኢትዮጵያዊነትና የቀይ ባህር አፈሮች አንድነት ያህል የተተነተነ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ አሰብን ወደ ኢትዮጵያ የሚያጥፍ የወሰን ሽግሽግ እንዲደረግ ይኸ ባይሆን ለሰላም ሲባል አሰብ በሁለቱም አገሮች የጋራ ባቤትነት (Joint sovereignty) ስር ሆኖ ራስ ገዝ እንዲሆን ኢትዮጵያውያን ከአቀረቡአቸው አሳቦች ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥረቶች በአቶ መለስ አማካኝነት ኢሕአደግ የሰጠው መልስ ወይንም አስተያየት የዚህ ሐሳብ አቀንቃኞችን ኋላ ቀር ነፍጠኞች፤ ከጊዜው ጋር የማይራመዱ ጊዜ የማይለውጣቸው መሃይማን የሚል ስድብ ነበር፡፡
 አስብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የጭንቀት ምክንያት የሆነችው አገሪቷ ለወደብ አገልግሎት ለቀረጥና ለደሜራዥ ለመሳሰሉት ኢሕአደግ ሕዝቡን ሳያማክር በነፃ ለጅቡቲ የሰጠው ውሃ ዋጋ እንኳን ቅናሽ ሳያደረግ በዓመት ወደ ስድስት ቢልዮን ደላር የሚጠጋ ገንዘብ ለጅቡቲ በመክፈላችን ብቻም አይደለም፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ እጅግ ስተራተጂክ ከሆነው ከቀይ ባህር ባትገለል ሊኖራት ይችል የነበረው ጀኦ ፓለቲካ አቅም ዜሮ በማግባቱም ብቻም አይደለም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ጉዳታቸው የላቀ ቢሆንም የኢትዮጵያውያን ዋናው ጭንቀት የሚመነጨው አስብ በኤርትራ እጅ ከገባች አቶ ኢሳያስ ምናልባትም ለኢትዮጵያ በጎ ለማይመኙና ለማያስቡ ሀይላት ወይንም አገራት አሳልፈው ሰጥተዋት የኢትዮጵያ ደህንነትዋና ሉአላዊነትዋ ለአደጋ ይጋጥል ከሚል ፍራቻ ነው፡፡ ይኸው እንግዲህ የተፈራው ደርሶ የኤርትራ ሕዝብ ሳያውቅና ሳይመክርበት አቶ ኢሳያስ አሳብን በኪራይ ስም ለሳውዲ አረቢያና ለዩናይትድ አረብ ኤምሬት አስረከቡት፡፡ ቀደም ሲል አቶ መለስ ዜናዊ አሰብ ኢትዮጵያ ካተጠቀመችበት የግመል ውሀ ማጠጫ ይሆናል የሚል ራዕይ ታይቶት ይህንኑ ለሕዝብ አሳምቶ ነበር፡፡ ከአቶ መለስ አባባል ቀደም ብሎ "ሌሎች ኢትዮጵያውያ በአሁኑ ጊዜ ለኤርትራ ምንም ጥቅም የማይሰጥው አሳብ እራስዋ ኤርትራ ባትጠቀምበትም ለለየላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች አሳልፋ መስጠትዋ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ብለው ነበር"፡፡ አሰብ የማን ናት! የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ 2003 ገጽ 190)
አቶ መለስ ዜናዊ 70% የዓለም ነዳጅ በሚተላለፍበት ስትራተጂክ አካባቢ የሚገኝ ወደብ ኢትዮጵያ ካተጠቀመችበት የግመል ውሀ ማጠጫ ይሆናል ማለቱ ካንጀቱ ሳይሆን በጉዳዩ እጅግ ይቆጩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ለማዘናጋት ነበር፡፡

አቶ ኢሳያስ አሰብን ለአረቦች ያስረከቡት ለአረቦች ከማከራየት ውጭ ለሌላ ጥቅም ሊውል አይችልም ከሚል አይደለም፡፡ አቶ ኢሳያስ አሰብን ለአረቦች አስረክበው አገራቸውን ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጡት የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን በኢትዮጵያውያን በኩል ምን ያህል ቁጭት እንደስከተለ ስለሚያውቁ ኢትዮጵያ አንድ ቀን ወደቡን በኃይል ለመያዝ ትሞክራለች ከሚል ፍራቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በኢሕአደግ የአገዛዝ ዘመን ይህ የማይታሰብ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር በዚህ ላይ የነበረው አቋም ከላይ የተጠቀሰውን ሲሆን የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ደግሞ የአቶ መለስን አቋም በማስተጋባት የካቲት 24 ቀን በ2002 ዓ.ም ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢሕአደግ ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለውና እንደማያምንበትም አረጋግጠው ነበር (አሰብ የማን ናት? ዝኒ ከማሁ ገፅ 60)
የእነዚህ የሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስተሮች አቋም አንድ ገጣሚ በውስጥ ወይራ አገላለጽ አስቀምጦታል ፡፡

ከጫካ ሰው ጋራ ቁማር ተጫውቼ
ወና ወጥቻለሁ አገር ተበልቼ
እኔም ስጠባበቅ ምርት እህሌን ላፍሰው
ከጫካ የወጣ ዝንጀሮ ጨረሰው
ይህ የአሰብ በአረቦች እጅ መግባት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሎም ሕልውና ሊፈታተን ቢችልም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከቶም ጉዳዩ ሆኖ የማያውቀው ኢሕአደግ ድርጊቱን ይቃወማል ብለን አንጠብቅም " ውሀ ሲጎድል ተሻገር፣ ዳኛ ሲኖር ተናገር" እንደሚባለው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚቆረቆር ዳኛ (አስተዳዳሪ) ሲመጣ አቤት እንላለን፡፡

የአሰብ በአረቦች ቁጥጥር ስር መሆን ብዙ ለውጦችን አስከትሎአል፡፡ የአፍሪቃ ቀንድን የሚያዋስነው ቀይ ባህር ለመጀመሪያ ጊዜ በምስራቅም በምዕራብም ዳርቻ ከመቆጣጠራቸውም በላይ ለዘመናት ሲያልሙትና ሲመኙት የነበረው የቀይ ባህር የአረብ ሀይቅነት እውን ሆኖላቸዋል፡፡ "የጎረቤት ሌባ ባያዩት ይሰርቃል ቢያዩት ይስቃል" እንደሚባለው እኛም ለኢትዮጵያን ኩታ ገጠም ጎረቤቶች መሆኑን በቀረብን፡፡ ምክንያቱም ከጉርብትናቸው ጋር ተያይዞ የሚመጡ ብዙ መዘዞችም አሉ፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ ለሚፈልቁ አሸባሪዎች ቀላልና በቅርብ እርቀት የምንገኝ ኢላማ ሆነናል፡፡ ባህር ማቋረጥ የሌለባቸው አክራሪ ወሀቢዎች በኢትዮጵያ በወንድምነትና በመፈቃቀር የኖሩ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች ግንኙነት በአክራሪ ዋሃቢዎች ሊደፈርስ ይችላል፡፡

በኤርትራውያን ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከኢትዮጵያውም በብዙ እጅ የበለጠና የከፋ ነው፡፡ በሳውዲ ንዳድ ይቃጠሉ የነበሩ ሼኮች ቱጃሮችና ልፁላን በነፋሻው አስመራ እየተሽሞነሞኑ ሕዝቡን ወደ ሁለተኛ ዜግነት ዝቅ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ በሂደት የጥንቱ የአክሱም ስልጣኔ አካል የነበረችው ኤርትራ ደብዛዋ ጠፍቶ አረባዊ ማንነት ሊጫናባት ይችላል፡፡ ከአርባና ከአምሳ ዓመታት በኋላ ሳውዲ አረቢያ የሚኖረው ሙቀት የሰው ልጅ ሊቋቋመው አይችልም ስለሚባል የውሉ ጊዜ ሲጠናቀቅ ተደላድለው ለዘመናት የኖሩ አረቦች ጓዛቸውን ጠቅላለው ለመውጣት ፈቃደኛ ይሆናሉ ወይ? ከመነሻው መለያየት የማይገባቸው የነበሩ ወንድማማች ሕዝቦች ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን በስልጣን ጥመኞችና አርቆ ማሰብ በተሳናቸው መሪዎች ውሳኔ ቢለያዩም ተመልሶ የመተሳሰር ዕድል ይህ የሦስተኛ አካል ጣልቃ ገብነት አጥብቦታል፡፡

አቶ ኢሳያስ ከሳውዲና ከአረብ ኤምሬትስ ጋር የተፈራረሙት ውል የኤርትራን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ሕዝብ ወይንም የሕዝቡ ተወካዮች ያልመከረበት የአቶ ኢሳያስ የግል ውሳኔ በመሆኑ ጊዜው ሲያመች ኤርትራውያን ውሉን መሰረዝ እንደሚችሉ የኤርትራ ምሁራን አያጡትም፡፡ ኤርትራውያን ይህንን ውል የሚቃወሙ ቢሆን የኢትዮጵያውያን እገዛ እንደማይለያቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በማይበጠስ የዘር፣ የቋንቋ የባህል፣ የሀይማኖት ወዘተ ሀረግ ተሳስረዋል፡፡ ጊዜያዊ ጥላቻውና መራራቁ የሁለቱ አገራት መሪዎች የፈጠሩት እንጂ ሕዝቡ ዘንድ ዘልቆ የገባ ስሜት አይደለም፡፡ ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኤርትራ ሕዝብ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ በተባበሩ ጊዜ ሕዝቡ ሲችል እየደበቃቸው ሳይችል ስንቅ እየሰጠ በእምባ እንደሸኛቸው ሰው ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ስለዚህ የአካባቢውን ጂኦ-ፓለቲካ በጥልቀት የገባቸው፤ ህብረት ኃይል መሆኑን የተረዱ፤ በዘረኝነትና በጎሰኝነት ደዌ ያልተለከፉ መሪዎች በሁለቱም አገር በሕዝብ ተመርጠው ስልጣን ሲጨብጡ በጠላት የማትደፈር፣ በልማት የዳበረች፣ በዓለምና በአፍሪቃ ጫና ልትፈጥር የምትችል አንድ የተዋሃደች ወይንም በፌዴሬሽን የተሳሰረች አገር ሊፈጥሩ መቻላቸው ሲታሰብ በራሱ ያማልላል፡፡ የኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ፣ ሰፊና ለም መሬት በአፍሪቃ በሁለተኛነት የሚመደብ የውሀ ሀብት ሁለቱም አገራት የታቀፉአቸው ብዙ ዓይነት ማድናት፣ በዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ተስማሚ አየር፣ እጅግ ስትራተጂክ የሆኑ ሁለት ወደቦች ያለው አገር በጥቂት ጊዜ የበለጸገና የታፈረ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ በሁለቱም ሕዝቦች በኩል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጉጉትም አለ፡፡ ጥያቄው እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ራዕይ የሰነቁ እሩቅ አሳቢ ራሳቸውን እረስተው ለአገር ያደሩ መሪዎች ይኖራሉ ወይ? ነው እንዲህ ዓይነት መሪዎች በሁለቱም አገራት ብቅ ካሉ ይህ በምድረ ገነት የተመሰለችው አገር ዕውን ማድረግ ይቻላል፡፡

ለዚህ ለዘለቄታ ግብ የሁለቱም አገራት ሕዝቦች በተለይም ወጣቱ መነጋገር መተዋወቅ መግባባት ስለሚኖርበት ይህንን ዓላማ አንግበው የተነሱት እንደነቪዥን ኢትዮጵያና ኢትዮ ኤርትራ ሶሊደሪቲ ግሩፕና ሌሎችም ተመሳሳይ አላፊነት አንግበው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚያደርጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ያበርታችሁ እንላለን፡፡

No comments:

Post a Comment