Translate

Friday, November 30, 2012

የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልትን አንስቶ በሙዚየም ለማቆየት ኮሚቴ መቋቋሙ ተነገረ


ኢሳት ዜና:-የህወሀት ኢህአዴግ ልሳን የሆነው  ሬዲዮ ፋና እንደዘገበው የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት በግንባታው ስለሚነካ በጊዜያዊነት ይነሳና በጥንቃቄ በሙዚየም ይቀመጣል፣ ግንባታው ሲጠናቀቅም ወደ ስፍራው ይመለሳል።የዳግማዊ ምኒልክ ሃውልት ግን ከፕሮጀክቱ ጉድጓድ 15 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ አይነሳም ብሎአል።

ይፈርሳል በሚል የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ  ነው በማለት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ሀውልቱ ሲነሳም ሆነ መልሶ በሚተከልበት ወቅት ምንም አይነት ጉዳይ እንዳይደርስበትም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግና ምንም አይነት የቦታ ለውጥ እንደማይደረግበትም ራዲዮው ዘግቧል።
ራዲዮው ይህን መግለጫ የሰጡትን ሰዎች ማንነት ይፋ አላደረገም። ሀውልቱን የሚያነሳውና መልሶ የሚተክለው ድርጅት ማን እንደሆነም አልተጠቀሰም። በየትኛው ሙዚየም ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆይ፣ ሀውልቱ ቢፈርስ ወይም ጉዳት ቢደርስበት አፍራሽ ግብረሀይሉ የመልሶ ማሰሪያ ገንዘብ ማስያዝ እና አለማስያዙ ወይም ኢንሹራንስ መግባቱና አለመግባቱ በዜናው ላይ አልተገለጸም። ሀውልቱ ተመልሶ እንደሚተከል ምን አይነት ዋስትና እንደተሰጠም አልታወቀም።
የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት መነሳት ጉዳይ ከፍተኛ የህዝብ መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል። እስካሁን ድረስ በአገር ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ምሁራን ወይም ባለሙያዎች አስተያየቶቻቸውን በመግለጫ መልክ ወይም በማንኛውም መንገድ አልሰጡም በማለት የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዘገባውን አጠቃሎአል።

No comments:

Post a Comment