Translate

Friday, November 23, 2012

ኢህአዴግና ስርአቱ፤ በዘመመ ጎጆ የነገሰ የእብዶች ተስካር


Bizuayehu Tsegaye

ሰላም እንደምን ከረምን አንባቢያን? ክዚህ ቀደም ‘Bureaucracy; the pillar EPRDF rusting’በሚል አርእስተ አንድ መጣጥፍ ለአንባቢያን አካፍዬ ነበር። ምናልባትም በሃገርኛ ብታካፍለን ያለኝ አንድ አንባቢ ነበርና አማርኛ መተየቢያ ‘ንድፈ ቁስ‘ ስፈልግ ሳፈላልግ ሰነበትኩ። ተሳክቶም ይህዉ በእንዲህ ዳግም መጣሁ።
አርእስቱ ታዲያ በሀገራችን የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ሲደመጥ የኖረን ቅራኔ መነሻ ያደረገ ነበር። የብልሹ አሰራር ልምድ በአሁኑ አስተዳደር አጀማመር ፣ ያለፈበትን ደረጃ ፣ በወቅቱ ያለበትን ሁኔታ ፣ በዚህ የተነሳ ወደፊት ለመተግበር የሚገደዉን አሉታዊ እጣፈንታ እንዲሁም የመፍትሄ ሀሳብ በመጠቆም የተገነዘብኩትን ያህል ለማካፈል ሰፍሮአል።

ለመነሻ ያህልም በአሁኑ ወቅት ቁጥር የሌለዉ ብሶት በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ማሰማት እንግዳ አለመሆኑን ፤ እንዲያዉም በአግልግሎት አሰጣጡ እና በ አገልግሎት ሰጪ አካላት መሃከል ስላለዉ መስተጋብር  ትዝብት ለመዳሰስ ሞክሯል። መሳካቱ በምላሻችሁ የሚረጋገጥ ይሆናል። አንባብያንም በጉዳዩ የየግል አመለካት ኖርአችሁ ለማካፈል ትፈቅዱ ይሆናል። ለዚህ ግልጥ የሃሳብ ልዉዉጥ የምክንያትነት ‘ማእረጉ’ን ግን ከእኔ ዘንድ እንድታኖሩት ተጠቁሞ ነበር። አሁንም እንዳለ መሆኑን በማስተላለፍ…እንዲህ ቀርቦአል።
በሐገራችን እንዳብዛኛዉ የወቅቱ ኢትዪጲያዊ ወጣት ሁሉ ያኔ ወያነ/ኢህአዴግም በእስተዳደር ልምዱ ልጅእግር ፤ ይበልጥ ሊገልጠዉ በሚችል ቃል እንጭጭ አሊያም ጥሬ ሳለ ይብዛም ይነስ አገልግሎታቸዉን ለተጠቃሚዉ ማህበረሰብ ለማድረስ ፍሬ ያለዉ የመተዳደሪያ ህገ ደንቦች እንዲሁም በሚወጡት ህግጋት የሚገዙ/ለመገዛት ዝግጁ የሆኑ አካላት ነበሩ። በእድሜ ጠና ያሉም ይህ የቀድሞዉ አስተዳደር ዉርስ የፈጠረዉ ተጥኖ ሊሆን እንደሚችል ሊገምቱ ይችላሉ ማለት ስህተት ላይሆን ይችላል።
በወቅቱ ታዲያ የማይታጠፍ፣ የማይወላገድ፣ የማያዳላዉ ና ጥብቅ የሆነዉ ህግ፤ ደንብ ና መመሪያ ያስመረረዉ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሻ ሁሉ ‘ቢሮክራሲ’ የምትለዋን የባዕድ አገር ቛንቛ የኛዉ እስክትመስለን ድረስ በመጠቀም አገልግሎት ማግኘት የሚፈጀዉን የጊዜ እርዝመት ሲተች ይሰማ ነበር። እንዲያዉ ፍጡም የሆነ ነገር ባይኖርም ያኔ የነበረዉ የአሰራር ስርአት ያዳላ ነበር ብሎ ለማዉጋት አያመችም። በአብዛኛዉ ከነ አቅም ማነሱ ማህበረሰቡን ‘በበለጠ’ እኩልነት ያስተናግድ ነበር። ከዘር ልዩነት ና ከገዢዉ ስርአት ጋር ሊኖር ከሚችል ፖለቲካዊ ትስስር ተጥእኖ ዉጭ የሆነ ነበር ሊባልም ይችላል። እንዲያዉ በጥቅሉ ሙሰኝነቱ የመነመነ ነበር ማለት ይሻላል።
በአሁኑ ወቅት ‘ቢሮክራሲ’ የተሰኘዉ ይህ የተለምዶ አጠራር ጊዜ ና ዘመን ያለፈበት ሆኖአል። አደባባይ የወጣዉ አስተዳደራዊ አገልግሎት አሰጣጥ መድሎ ፣ ወገንተኝነትና ተቃራኒ ጎራ የለየ የዜግነት ጥቅም አደላደል ና መጋራት ሁሉ ቃሉን ላለመጠቀም ምክንያት እስኪመስሉ  በአሁኑ ግዜ ማህበረሰቡ ሲጠቀምበት አይደመጥም። የገዥዉ መደብ ተግባር ከቃሉ ትርጉም ና ይዘት ጋር የተጣረሰ ነዉ። የዚህ ቃል አጠቃቀም መደብዘዝ ማህበራሰቡ የቃሉ ጸረ-አድሎአዊነተን የተረዳዉ በሚያስመስል ምልኩ መሆኑ ህዝብ አያዉቅም እንዳማይባል ግንዛቤም ያስጨብጣል።
ጨዋታዉ ከተነሳ ዘንዳ ‘ቢሮክራሲ‘ የሚለዉ ጥሬ ቃል ለፈጣሪዉ አለም በዋንኛነት ስራዎችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከፈፍሎ በየበኩላችዉ የስራ ክፍል ለአፈጻጸም መመደብ ነዉ። ተመራጭ ባልሆነ ቅጥረኛ/ደሞዝተኛ(ፖለቲካዊ ወገንተኛነትን ያገለለ ማለትም እንችል ይሆናል) ሃላፊ የሚመራ አስተዳደራዊ መዋቅርም ጭምርም ነዉ። እንዲሁም ተቋማቱ ያላቸዉን ጠጣር ና ያለመለሳለስ ተፈጣሚ የሚሆኑ ህግጋት ና መመሪያዎችን ለማመልከት ይጠቀሙበታል።
ዐድሎ ፤ ጥብቅ አስተዳደራዊ ህገ-ደንብ፣ መመሪያ አለመኖር በነገሰበት አስተዳደር አንድ ምርት አሊያም አገልግሎት ለተጠቃሚዉ በተዘበራረቀ ስርአት ይሰጣል። የተቋሙ አገልጋዩች የድርጅታቸዉ ራዕይ፣ አላማ፣ ግብ፣ ባህል፣ የዘወትር ተግባሮት እንዲሁም ስራዉ የሚጠይቀዉን ስነ-ምግባር በተመለከተ እኩል እዉቀት አይኖራችዉም። ይብስም በተከታዩች ዘንድ የፈላጭ ቐራጭነት ስልጣን ስለሚኖር ለ ህጋዊዉ/ደንባዊዉ የአስተዳደር የስልጣን ተዋረድ ተገዥነት አይኖርም። እነዲያዉ በጥቅሉ መዋቅሩ ’የእብዶች ተስካር’ ነዉ የሚሆነዉ።
ጠንካራ አስተዳደራዊ ስርአት/’ቢሮክራሲ’ መኖር በራሱ ብቻዉን የህጎች ና ደንቦች ተከባሪነትን ላያስተማምን ይችላል። ነገር ግን ለጠንካራ ገምጋሚና ተቆጣጣሪ አካል መኖር መሰረታዊ ምክንያት ነዉ። የተሰራን ስራ ሊሰራ ታልሞ ከነበረ ዉጥን በማመሳጠር ጉድለት ካለ እርማት እንዲወሰድ በማድረግ መሻሻልን ያበረታታል። ጠንካራ ፣ በአፈጣጠሙ ያልተለሳለሰ አሊያም መድሎን ያገለለ ህግ ፣ ደንብ እንዲሁም መመሪያ የሌለዉ ተቛም ፣ ማህበር  ብሎም ማንኛዉንም አይነት የተደራጀ አካል እጣፋንታዉ ተበትኖ መቅረት እንደሚሆን ጥርጥር የለዉም።
በዝግመት የደበዘዘዉ ጥብቅ የአገልግሎት/የእድሎች አሰጣጥ ስልት ፣ ህግ ፣ ደንብ ና መመሪያ/’ቢሮክራሲ’ መነሻዉን ያደረገዉ ካለዉ የጎጥ አመራር ስርአት አላማ ነዉ። በሙሉ የስልጣን ቁጥጥር ሀብትን በብቸኝነት መቀራመት። ይህ ሲሆን የተለያዩ ደረጃዎችን አልፏል።
የመንግስት ስልጣን ተፎካካሪዎችን ፤ የቀድሞ የአስተዳደሩ አጋር ‘አማፂ’ ተዋጊዎች፣ ቀስ በቀስም ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቀጥሎም ተጥእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ማስወገድ የመጀመሪያዉ ምራፍ ነበር ማለት ይቻላል። የእነዚህ ተቋማት ና ግለሰቦች መኖር ለጠንካራ አገልግሎት አሰጣጥ ስርአት መፈጠር ብቻ ሳይሆን ቀድሞዉኑም የነበሩትን ለማሻሻል ፣ አቅማቸዉን ለመገንባት ቀላል የማይባል አስተዋጥኦ ማድረግ በቻሉ። ምክንያቱ ደግሞ በሀገራችን የጋራ ዉሳኔዎችን ለማሳለፍ የነዚህ ተቋማት መኖር ልዩ ሃሳቦችና ፉክክሮችን ለማስተናገድ የጋራ የሆነ ፣ አንዱ የአንዱ ተገዢነትን አስወግዶ የሁሉም ገዢ ስርአት እንዲፈጠር ምክንያት ስለሆኑ ነዉ። የሆነዉ ሆኖ ይህ የኢህአዴግ ተግባር በተለምዶ ‘ቢሮክራሲ‘ እያልን የምንጠራዉን መድሎን ያገለለ ህገ-ስርአት በቅጥበት አላሽመደመደም።
የመንግስት ስልጣን በአንድ አካል ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር በወደቀበት ና ስልጣንም ያለ-አግባብ ለመዋል በተጋለጠበት እንዲህ አይነቱ ሁኔታ የ‘ሲቪክ‘ ና የ ባለሙያዎች ማህበራት በስልጣን መማገጥን ፣ የህግ ጥሰትን ና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን በማጋለጥ የተቅጣጣሪ አካልን ባህሪይ ተላብሶ በማገልገል መልካም አስተዳደር እንዲበረታታ ፣ እንዲጎለብት የማይተመን ሚና ይጫወት በቻለ። በተቃርኖዉ እነኝህ ተቋማት የወያኔ/ኢህአዴግ ዋንኛ ኢላማ ሆኑ ፤ ለእንግልት ፣ ለማስፈራራት ብሎም ለመበተን ተገደዱ። አሊያም እንዲበተኑ ተደረገ።
ወያኔ/ኢህአዴግም ለብልሹ ተግባሩ እንቅፋት የሚሆኑበትን የማጥዳት ተግባር ሲያገባድድ የታማኞቹን ጠብታ ለልዩ ሀሳብ መመንጨት መከላከያ ይሆን ዘንድ በሀገሪቷ ተቋማት አካላት ሁሉ አሰራጨ። የራሱን ’ማላይ’ ማህበረሰብ በፓርቲ አባልነት መልክ ማደራጀትና መገንባት ተግባሩ ሆነ። በሂደትም ማንነቱን በማሳነስ ፣ የአስተዳደር አድማሱን በአባለቱ ና በደጋፊዎቹ ልክ ዝቅ አደረገ። የተቀረዉን የማህበረሰብ አካል አስተዳደራዊ ዋስትና ነፍጎ በግዞት መልክ በመቆጣደር ከመሀሉ መልምሎ በማጥመቅ በፈቃዱ ከፈጠረዉ የጥቂቶች ማህበረሰብ/’ማለይ ማህበረሰብ’ ወደ ግዙፍነት ለማደግ አለመ። ይህም ህልም የሀገሪቱን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አድማስ/ራዕይ እንዲጠብ፣  ዉሳኔ የማሳለፍ አቅም ፤ የማቀድ አቅማቸዉን፣ ግባቸዉን ለማሳካት ሊያዳብሩአቸዉ ይችሉ የነበሩ አማራጮችን፣ ቁሳዊ ፍጆታን ጭምር በመገደብ ዉጤታመነትን/ምርታማነታቸዉን በማጥፋት የሐገር ሃብት አባካኝ አደረጋቸዉ።
እነኚህም እንደ ወረርሽን መከላከያ በየአገልግሎት ሰጪ አካላት የተሰራጩት የገዥዉ ‘ታማኞች‘ የሃገሪቱን ተቋማት እንደ ብረት ምሰሶ ደግፈዉ ያቆሙትን ጥብቅ የአገልግሎት አሰጣጥ ህገ-ስርአትን አቅም እንዲገነባ ከማድረግ ይልቅ የማስፈጸሚያ ሃብታቸዉን በመቀራመት ዝጎ እንዲመነምን መንስኤ ሆነዋል። ፈሬዉም በወቅቱ የሚታየዉ በግልጥ ሊጨበጥ የማይችል፣ በጠሃፊዉ እንኳ ሊከበር የቻለ የህግ ና ደንብ ማእቀፍ አሊያም እንደወትሮዉ ’ቢሮክራሲ’ አለመኖር ሆነ። ደካማ የማስፈጠም አቅም ያላቸዉ ተቋማት…የትምህርት፣ የጤና፣ የህግ፣ የንግድ ና የመሳሰሉት መፈጠር። ደካማነታቸዉም በአገልግሎት አሰጣጥ ወገንተኝነት፣ አድሎ እንዲሁም በማህበረሰቡ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚንጸባረቀዉ አሉታዊ እይታ ነዉ። የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተወካይ የገዥዉ ፓርቲ አባላት ግላዊ ፍላጎታቸዉን እስከመጨረሻዋ ጠብታ የሚያረኩበት ፤ በጥቃቅን ጉዳዮች ግጭት ዉስጥ የሚገቡበት…ምሁሩን የሀገሪቱን የሰዉ ሃይል የአስተሳሰብ ና የፍላጎት አድማስ የሚያጠቡበት   መድረክ እየሆነም መጥቷል። እንዲያዉ በጥቅሉ የህዝብ አገልግሎቶችና የእድል ተጠቃሚነት በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ስልጣን ማራዘሚያ ማድረግ ሊያንጸባርቅ የሚችለዉ ሀገርን በሁሉ ነገር ወደሚያሳድግ ሃይል ሰጪ መዘዉርነት ለመቀየር የሚችል ብቁ አስተዳደር እንደሌለ ነዉ። ሁናቴዉ በዝህ ከገፋ መጨረሻችን የያልተደራጀ፣ ተበታትነዉ ያሉ ግለሰቦች ስብስብ ያለዉ ማህበረሰብ…ከለላ አሊያም ንብረት ማፈራት፣ ፍለጎቱን የሚያሳካበት እድል፣ እራሱን መግለጥ የሚስችለዉ መብት የተነፈገዉ፤ የተበደለ፣ የተገለለ፣ የተገፋ፣ ክብሩ የተነካ…በቀላሉ ለመግለጥ ያህል የተቃወሰ ሁኔታ ና ማህበረሰብ ማፍራት ይሆናል።
በቅርብ ባሳለፋናቸዉ ወራት በአንዱ በእድሜ የገፉት አቶ ስብሃት ነጋ “ማህበረሰቡ ለዲሞክራሲ ብቁ አይደለም።“ ማለታቸዉ በዝህ ‘የተቃወሰ ሁኔታ‘ ዉስጥ ነን ብለዉ ማመናቸዉን አሊያም ሊያሳዉቁን አስበዉ ነዉ ከማለት ዉጪ ሌላ ለማለት እድል አይሰጥም። በዚህ አባባላቸዉ የመንግስት ስልጣን ምንጩ ከህዝብ መሆኑ ቀርቶ በስልጣን እርከን ከሰፈሩት ጥቂት ግለሰቦች ነዉ ከማለት ባለፈ ሃሳብ የሚያስመነጭ ሆኖ አላገኘዉም። በእርግጥም የመልእክታቸዉ ይዘት እንዲህ ሆኖ ከሆነ ቀላል የማይባል የአስተሳሰብ መዛባት በመሰል አእምሮዋች አለ ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም የአቶ ስብሃትን አይነት ቃላት የሰዉ ልጅ የመደራጀት ፈላጎት አነሳስና አላማን ልብ ያላሉ ስለሆኑ ነዉ። ይህን ስል የሰዉ ፍጡር በግለሰብ አቅም መፍታት የሚያስቸግሩ  የደህንነት ስጋትን ሊቀርፍ የሚችል ከለላ በሻበት ወቅት መደራጀት መጀመሩ ፤ አሁን ለደረስንበት የአለማችን የአስተዳደር ስርአትም መሰረት መሆኑ መዘንጋት የሌለበት ቁም ነገር እንደሆነ ነጥብ ለማስያዝ ነዉ። ታዲያ የማህበረሰቡ ባለዉ አስተዳደር መከፋት ጣራ ሲደርስ ከመሰረቱ “ሀ“ ብሎ በማንኛዉም አይነት መንገድ እራሱን ዳግም ማደራጀት፣ አቅሙን መገንባት ብሎም ክብሩን ለማስመለስ ገፍቶ መሄዱ አይቀሬ ነዉ። ይህን አስመልክቶ በአሁኑ ግዜ በትጥቅ ትግል ዘርፍ ና በሌላ መልክ የተደራጁ እንቅስቃሴዎችን ለዚህ ትንተናዊ ሃሳብ ድጋፍ ይሆኑ ዘንድ መጥቀስ ይቻላል።
አቶ ስብሃት ‘ድንቁርና’ን ለመቀነስ ሊናቅ የማይችል የህይወት ተሞክሮ እንዲሁም ብቃት እንዳላቸዉ ለቃላቸዉ ግዜ በመስጠት መልእክታቸዉን በማስተላለፍ ማስመስከር በቻሉ። ሳይሆን በመቅረቱ እስካሁን ለኢህአዴግ አስተዳደር ጥሩ አመለካከት ያለዉ አለ ለማለት ቢቸግርም ጥርጣሬዉን ወስዶ ለራሳቸዉ እንዲሁም ለድርጅቱ ጥላቻ መቆስቆስን አተረፉ እንበል። በአጥንኦት ለተመለከተዉ ሁናቴዉ የግለሰቡን ብቃት ጥያቄ ዉስጥ ከማስገባት ይበልጥ  የማይሸራረፍ ፣ በጥኑ ተከባሪ የሆነ አስተዳደራዊ መርህ አለመኖር አሉታዊ ተጥእኖ በተቀሩት ተቋማት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በኢህአዴግ ዉስጥም መንገሱን ጠቋሚ ነዉ።
ኢህአዴግ በከፍተኛ አባላቱ አማካኝነት በተደጋጋሚ በህዝብ አይን የገቡ እርስ-በረስ መጣረሶች አሳይቷል። በአባለቱ በተለይም በከፍተኛ የስልጣን እርከን ዙሪያ ባሉት ስለሚተገብሩት ድርጊት እንዲሁም ስለኖሩበት ማህበረሰብ እኩል አመለካከትና መረዳት ሊኖር በተገባ። አልሆነም። ለምሳሌ ያህልም ያለፉት ጠቅላይ ሚንስትር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ህዝብ የስልጣን ምንጭ መሆኑን ወደዉም ይሁን በሁኔታዎች ተገደዉ መጠቆማቸዉ አይዘነጋም። ይህም የሆነዉ በባለቤታቸዉ ህልፈት ሰሞን ነበር። ብዙም ሳይዘገይ ነበር በተቃርኖ አቶ ስብሃት ህዝብ የስልጣን ምንጭ አይደለም ለሚለዉ ቃል እኩሌታ “ህዝቡ ለዲሞክራሲ ብቁ አይደለም“ በማለት የገለጡት። ይህ የሚያመላክተዉ በጋራ እነደ የአንድድርጅት አባልነታቸዉ የድርጅታቸዉ አገልግሎት ትኩረት ስላደረገበት ማህበረሰብ (የኢትዮጵያ ህዝብ) አንድ አቋም እንደሌላቸዉ ነዉ። አሊያም በአንድ ድርጅት ስር ሆነዉ የየግል ጥቅማቸዉን ከድርጅቱ አብልጠዉ እንደሚያራምዱ ምንኛ ጠቋሚ መሆኑን ነዉ። ክስተቱ ከላይ በመግቢያችን ላይ ለመግለጥ እንደተሞከረዉ ፤ ጥብቅ የአሰራር ህግ፣ ደንብ እንዲሁም መመሪያ የሌለዉ ተቋም ከሚያንጠባርቁት ባህሪ አንዱ የአመለካከት ና የጥቅም ልዩነት( የግለሰብ ጥቅምን በማስቀደም) በኢህአዴግ ዉስጥም እየተስተናገደ መሆኑን ያሳያል። ባጭሩም የድርጅቱ ራዕይ፣ አላማ ና ግብ በአባለቱ ዘንድ እኩል ግንዛቤ እንደሌለ ይጠቁማል። በጥምረት የጋራ ሃላፊነት ቢኖራቸዉ ከመፈጠም እንደሚሰናከሉ ላያጠራጥር ይችላል። ኢህአዴግም በዚህ ሁናቴ ረጅም ርቀት እንደማይጓዝ እርግጥ ነዉ።
መሰል ተቃርኖ በኢህአዴግ ዉስጥ ሲንጠባረቅ ይህ ብቻ አይደለም። ‘የጉድ ግዜ ጨዋታ ተነግሮ አያልቅ’ እንዲሉ አንድ ላክል። በተመሳሳይ ወቅት አቶ በረከት የቀድሞዉን ጠቅላይ ሚኒስቴር ከዚህ አለም አለማለፍ ታማኞቻቸዉን ለቃላቸዉ ታማኝነት እማኝ ጠርተዉ ማሰተላለፋቸዉ የሁላችንን ቀልብ የሳበ እንደነበር አይዘነጋም። ለዚህ ከእዉነት የተቃረነ መግለጫ ግዜ እዉነቱን ከማሳወቁ ቀደም በማለት አቶ ስብሃት አንደበት መግለጫዉ የታማኝነት መሰረት እንደሌለዉ የሚያሳዉቁ ቃላት ሰንዝረዋል። የአቶ በረከት አንደበትም ‘ታማኝ‘ ናቸዉ የሚሏቸዉን የማህበረሰባችንን አካላት ክብር ዝቅ አድርጎ ከማሳየት ባለፈ ከአቶ ስብሃት ጋር ሊኖር ስለሚችል የጥቅም፣ የአላማ መረዳት ክፍተት ጠቋሚ ነዉ። ይበልጡንም እየዛገ ያለዉ አስተዳደራዊ መዋቅር አሊያም ጥብቅ ገዥ ህገ-ደንብ ከመዛግ ብሶበት እንደ ‘ቅቤ እየቀለጠ ይሆን?’ በሚል ትኩረት የሚስብ ነዉ። በርግጥም ወያኔ/ኢህአዴግ ግራ ማጋባትን ለስልጣን ማራዘሚ የሚጠቀምበት ስልት መሆኑ ከግምት ቢኖርም እንዲህ መሰሉ የድርጅቱ አባላት መጣረስ ለከፈተኛ ዉስጣዊ ቀዉስ የሚዳርግ ነዉ።
ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስቴር ማለፍ ጀምሮ እንኳ በቁጥር የበረከቱ መስመር የሳቱ ዉል የለሽ ዉሳኔዎች ተላልፈዋል። ‘ስዉር ስርአተ-ህግጋት’ በግልጥ ስራ ላይ ዉለዋል። ሁሉም ክስተት በኢህአዴግ የላይኛዉ እርከን ተቀባይነት ያለዉ በጽኑ ተፈጻሚ የሆነ አስተዳደራዊ ህገ-ደንብ ና የመመሪያ ስርአት(ቢሮክራሲ) ላለመኖሩ እማኝ ነዉ። አንዳንዴ በበላይ ድርጅቱ አባላት የሚወረወሩ ቃላት የአፍ ወለምታ፣ እንዳመጣጣቸዉ የሚሰነዘሩ አሊያም በደመነ-ነብስ የሚናገሯቸዉ መስለዉ ከቁም ነገር እንዳንቆጥራቸዉ ይከጅላሉ። ለጋራ መገማገሚያነት መነሻ የሆነ ጽኑ ‘የህገ-ደንባዊ ስርአት’ መስፈርት እከሌለ ድረስ የግንኙነት መጣረሶች ለልዩነቶች መስፋት ዋንኛ አመላካቾች ናቸዉ።
ይህ ከሆነ እስካሁን ለኢህአዴግ አባላት ዉሳኔዎችን ለማስተላለፍ የጋራ መሰረት ሆኖ ሲያገለግል የኖረዉ ምን ነበር? የሚል ጥያቄ ማንሳት የማይቀር ይሆናል። ከመሃላቸዉ ጠንካራ ፣ በጉልበት ፈርጥሞ የታዉ አካል የሚያሳድረዉ/ የሚያሰፍነዉ የፍርሃት መንፈስ የጋራ ዉሳኔ ለማስተላለፍ መሰረት ሆኖ ሲያገለግል መኖሩ የሚያከራክር ነጥብ ነዉ ብዬ አላምንም። ይህ የፍርሃት መንፈስ እያደገ በመጣ ቁጥር እየዛገ የመጣዉን ’ቢሮክራሲ’ በመደገፍ ፤ የወያኔ/ኢህአዴግን የጎጆ ጣራ በመሸከም አገልግሎአል። የአስተዳደሩ የቀድሞ ራስ ካለፉ ወዲህ ግን ይህ የፍርሃተ መንፈስ የዉሃ ሽታ እየሆነ መጥቷል። የኢህአዴግም እጣ ፈንታ ጠንካራ በጥኑ ተፈጣሚ የሚሆን ህገ-ደንብና መመሪያ እንደሌለዉ አደረጃጀት ከመሆን አያልፍም። ከመበታተን፣ ጣራራዉ በላዩ ከመደርመስ ዉጭ አይሆንም።
የተጠቀሱትን እዉነታዎች መሰረት በማድረግ ኢህአዴግ ራሱን ከዉስጥ በመነጨና ካገለለዉ የማህበረሰቡ አካል እያደገ የመጣበትን ፈተና ተቋቁሞ እድሜዉን የሚያራዝምበት ሁለት አማራጭ መንገዶች ማስቀመጥ ይቻላል። ማደናገሪያዎችን በየጊዜዉ እየፈጠሩ በመንዛት ጊዜ ከመግዛት ዉጭ ማለት ነዉ።
አንድም ይበልጡን ፍርሃትን ማንገስ ፤ እየደበዘዘ ያለዉን ትክክለኛ የአስተዳደር ስርአት መሳሪያ አጥፋቶ ፤ ማህበረሰቡ ለአስተዳደሩ ያለዉን አሉታዊ ምለሽ ማቀጣጠል ና አማራጭ የጥቅሙ አስከባሪ አካል ፈለጋ እንዲገፋበት ማድረግ። መጨረሻዉ መልካም ባይሆንም የስልጣን ጊዜን ለተወሰነ ማስረዘም። አሊያ ሁሉን ጠቀሚና ሁሌ ኖዋሪ መሆን። ምንም እንኩዋ ያለዉን ሙሉ የስልጣን ቁጥጥር አሳልፎ ማካፈልን ቢጠይቅም እስካሁን የተጓዘበትን መንገድ መቀልበስ ፤ መድሎንና ወገንተኝነትን ያገለለ አስተዳደር እዲኖር መትጋት ፤ ሁሉንም የማህበረሰብ አካል ማስጠልል የሚችሉ ተቋማትን በአስተማማኝ ና ብቃት ባለዉ መንገድ ሊያቆም የሚችል  ምሰሶ (አስተዳደራዊ ስርአት) እንዲገነባ ማገዝ የግድ ይሆናሉ።
Bizuayehu Tsegaye

No comments:

Post a Comment