Translate

Thursday, November 22, 2012

ኢህአዴግ ኢህአዴግን ማፈን ጀመረ! የ“ንቦቹ” ፍጥጫ አቅጣጫውን እየቀየረ ነው


ኢህአዴግ ኢህአዴግን ማፈን ጀመረ!

የ“ንቦቹ” ፍጥጫ አቅጣጫውን እየቀየረ ነው
the beesየኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ስም ሲነሳ አቶ በረከት ስምዖን በግንባር ቀደም ይጠቀሳሉ። የአቶ በረከት ንብረት ሆኖ የመለስን አመራር በታማኝነት ሲያገለግል የኖረው ይህ ተቋም ቆርጦ በመቀጠል፣ የዜጎችን ሃሳብ በማዛባት፣ ወሬን ባለማመጣጠንና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማስተላለፍ የሚታወቅ ነው። ስለሚጠየፉት የማይመለከቱት እንዳሉ አፍ አውጥተው የሚናገሩም አሉ።
ለሙያው ቅርብ የሆኑ አስተያየት ሰጪዎች “ወገንተኛ እንኳን ቢኾን መሰረታዊ የሙያው ግዴታ ሳይጣስ ሊሆን ይገባል። አንድ መገናኛ ማመጣጠን ካልቻለ በራሱ ሙት ነው። እያደር ብቻውን ይቀራል” ሲሉ ኢቲቪን ይገልጹታል። እንደነሱ አባባል ኢቲቪ ከህዝብ ሳይሆን ከራሱ ጌቶችም ጋር ተነጥሎ የአንድ ወገን (ግለሰብ) ሎሌ የሆነ በድርጅት ቅርጽ የሚከላወስ ሱቅ በደረቴ አይነት ነው።
ኢቲቪ ሃሳባቸውን፣ ንግግራቸውን፣ አቋማቸውን፣ ጥቆማቸውንና ተቃውሟቸውን እየቀረጸ በማዛባት ከህዝብና ከሚወዱዋቸው ወገኖቻቸው ጋር እሳትና ጭድ ያደረጋቸው፣ ለተራ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ኢቲቪን “በደለን” በማለት መውቀስ የሚችሉበት አግባብ የላቸውም። ኢቲቪ “በአልቤርጎ ውለታ” የግል ሳሎናቸው ያደረጉትን ጨምሮ “ልማታዊ” የሚባሉት በግብር ጸረ ልማት የሆኑ ውስን ጋዜጠኞች ሎሌ ሆነው እንዳሻቸው የሚንፈላሰሱበት ቤት ስለሆነ ጠያቂም ከልካይም እንደሌለባቸው ስለ ተቋሙ የሚያውቁ ይመሰክራሉ።
ተቋሙ ከድርጅት ደረጃም ወርዶ የግለሰብና የተወሰኑ ቡድኖች መፈንጫ እንደሆነ በየጊዜው አስተያየት ቢሰጥም ማንም ደፍሮ ሊያስተካክለው አልቻለም። ኢህአዴግ መንግስት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ አቶ በረከት ብቻቸውን የሚጋልቡት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጡንቻው የራሱን የኢህአዴግ ከፍተኛ የሚባሉትን ባለሥልጣናት ድምጽ የማፈን አቅም ያለው መሆኑ በእጅጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ያካሄዱት ስብሰባ ለህዝብ ይቀርባል ከተባለ በኋላ መታፈኑ ባለሥልጣናቱን ሳይቀር አስቆጥቷል። ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ አወዛጋቢና አነጋጋሪ ዜናዎችን የሚዘግበው ሰንደቅ ጋዜጣ “ለህዝብ ይፋ ይሆናል” ተብሎ ማስታወቂያ የተነገረለት ስርጭት በማን ትዕዛዝ ታፈነ የሚለው ጉዳይ ባለስልጣናቱን እንዳበሳጫቸው ጠቅሶ ሰፊ ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ አንድ የሥራ ኃላፊ ከማናገሩ ውጪ ወደ ላይ ከፍ ብሎ አላነጣጠረም።
ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 376 ረቡዕ ህዳር 12 ቀን 2005 በፌስ ቡክ ባሰራጨው ዜና ስብሰባውን በመከታተል ሪፖርት ያዘጋጀው ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻን በማነጋገር “የባለሥልጣናቱ ውይይት የታፈነው ሆን ተብሎ ነው” በማለት ምላሽ መስጠቱን እንደሚከተለው አስነብቧል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ በዕለቱ ዝግጅቱን እንዲከታተል ተመድቦ ዜናው ከስድስት ደቂቃ ተኩል በላይ ሠርቶ በዕለቱ መተላለፉን፣ የዜናው ይዘትም አዎንታዊ ግብረ-መልስ ከውይይት ተሳታፊዎች እንደነበረው አስታውሷል። ይኸው የባለሥልጣናት ውይይት ሰፋ ባለ ፕሮግራም እንዲዘጋጅም ከድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች መታዘዙንና ይህንንም ተከትሎ በማግስቱ ቅዳሜ ዕለት ሰፊ ፕሮግራም አዘጋጅቶ እሁድ እንደሚተላለፍ የሚገልፀውን ማስታወቂያ (ስፖት) ሠርቶ አስረክቦ በግል ጉዳይ እረፍት መውሰዱን አስታውሷል።
ሆኖም እሁድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ይተላለፋል የተባለው ፕሮግራም እሱ ለጊዜው ባላወቀው ምክንያት ሳይተላለፍ መቅረቱን፣ ነገር ግን ስብሰባውን በአካል ተገኝቶ ያልተከታተለው አቶ ሳሙኤል ከበደ በተባለ ባልደረባው አማካይነት ቀደም ሲል አዘጋጅቶት የሄደው የተሟላ ፕሮግራም ተጥሎ፣ ሆን ተብሎ የባለሥልጣናቱ ሃሳቦች ተቆራርጦ ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲተላለፍ መደረጉን ገልጿል።
ጋዜጠኛ አዲሱ “የባለሥልጣናቱ ውይይት የመንግሥት አቋም እንጂ የግለሰብ አይደለም። እኔ ጉዳዩን የተከታተልኩት ባለሙያ እያለሁ፣ ሳይነገረኝና ሳላውቅ ያዘጋጀሁት ፕሮግራም ተጥሎ፣ ተዛብቶና ተቆራርጦ እንዲቀርብ በመደረጉ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ጋዜጠኛ ሳሙኤል ከበደ እንጂ ተቋሙ አይደለም” ማለቱን የሰንደቅ ዘገባ ያስረዳል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢቲቪ ምንጮች እንዳሉት ጋዜጠኛ አዲሱ መግለጫውን እንዲሰጥ ከበላይ ትዕዛዝ ወርዶለታል። የባለሥልጣናቱ ውይይት ሙሉ በሙሉ ለህዝብ ይተላለፋል ከተባለ በኋላ አለመተላለፉ፣ በማስቀጠልም ፕሮግራሙ ተቆራርጦ መቅረቡ ካበሳጫቸው ባለሥልጣናት መካከል አቶ አባይ ጸሃዬ ኢቲቪ ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን እንደሚያውቁ የጠቆሙት ምንጮች “ፕሮግራሙ ተዛብቶ እንዲተላለፍ ትዕዛዝ የተቀበሉት ሃላፊዎች መመሪያውን ከማን እንደሚቀበሉ ይታወቃል” ብለዋል።
አቶ በረከትን በቀጥታ ያልገለጹት የኢቲቪ ሰዎች፤ “ኢቲቪ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳዮች እርሳቸው ሳያውቁት አይተላለፉም። ጨዋታው ኢህአዴግ ኢህአዴግን ማፈን ጀመረ የሚያስብል ነው” በማለት ባለሥልጣናቱ ላይ ሲደርስ አዲስ ሆነ እንጂ በርካታ ዜጎች በተመሳሳይ ሃሳባቸው እየተዛባ ለፖለቲካ ቅስቀሳ እንዲውል ሲደረግ ማየት የተለመደ መሆኑን አስታውቀዋል። ኢቲቪ ከድርጅትም ወርዶ የግለሰብ “ሎሌ” እንደሆነ ሲነገር ለሚሰሙ ባለሥልጣናት ከዚህ በላይ ማስረጃ ሊቀርብ እንደማይችልም አመልክተዋል።
አሊ ሱሌማን
ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ ም በተካሄደው የከፍተኛ ባለሥልጣናት ውይይት ላይ ባለሥልጣናቱ ምን ቢናገሩ ነው ድምጻቸው እንዲታፈን የተደረገው የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል። በውይይቱ ወቅት ባለሥልጣናቱ ጠንካራና ባለሥልጣናትን እየለየ የሚያሳጣ አስተያየት መስጠታቸው፣ የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌማን ኮሚሽኑ መረጃ ቢኖረውም ከሶ እንዳያስፈርድ ጫና እንዳለበት ለተሰነዘረባቸው ወቀሳ ምላሽ ሰጥተዋል። ህዝብ መማረሩና ሰሚ ማጣቱ፣ አደገኛ የማህበራዊና ኑሮ ውድነት ቀውስ መከሰቱ፣ የመንግስትን “ሌቦች” ለመቆጣጠር የተቋቋሙ መዋቅሮች ቅርንጫፎቹን እንጂ ግንዱን ገንድሰው ሊጥሉ አለመቻላቸው፣ የግንዱን ግድግዳ መገርሰስ ካልተቻለ ግንዶቹ እንደሚጠነክሩ፣ ኢህአዴግ ለራሱ ሲል ግንዱን መገርሰስ እንደሚገባው … ይህን ማድረግ ካልተቻለ አደጋ እንደሚሆን ከተለያዩ ባለስልጣናት ሃሳብ ተሰጥቷል።
“የግንዶቹን በር በርግዶ መግባት አልተቻለም” በማለት አቶ አባይ ጸሃዬን በመደገፍ የhttp://www.goolgule.com/eprdf-against-itself/ወደፊት የአቶ መለስ ምትክ እንደሚሆኑ የሚነገርላቸው የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ አቶ ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል “ጊዜ መስጠት የለብንም።
ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል
በዚህ ከቀጠለ አደገኛ ነው” ሲሉ ስርዓቱን እየበላው ያለውን የሙስናና መበስበስ አደጋ አመላክተዋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ “የችግሩ ምንጭ መዋቅራችን ነው” ሲሉ፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው “ሰፊ ተጠያቂነት ይካሄዳል” ማለታቸው ተደምጧል።
ዘጠነኛው መደበኛ ጉባኤውን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ያለው ኢህአዴግ፣ እናት  ፓርቲዎቹና አጋር ፓርቲዎቹ በተናጠል ባካሄዱት ተከታታይ ግምገማ በተመሳሳይ ሰዉ ድርጅቱን አልቀበልም ስለማለቱ፣ በልማት ሰራዊት ግንባታ ስም ለቀረበው የመደራጀት ጥያቄ አዎንታዊ መልስ መከልከሉ፣ በአባላትና በካድሬዎች መካከል የመጠራጠርና የመከዳዳት ስሜት መጎልበቱ፣ ከሁሉም በላይ ሙስና ከቁጥጥር በላይ መሆኑ ስርዓቱን አደጋ ላይ እንደጣለው ከተሰብሳቢዎቹ መሰንዘሩ ተደምጧል። የየፓርቲው መሪዎችም በተመሳሳይ ችግር እንዳለ መልሰው ለካድሬውና ለበታች አመራሩ ማስተጋባታቸው ችግሩን ማን ይፍታው በሚል ጥያቄ እንዲያነሱ እንዳስገደዳቸው አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ኢህአዴግ ባለስልጣናትን ሆን ብሎ በሙስና በማበስበስ “አቋም የሌላቸው ታዛዥ” እንደሚያደርጋቸው፣ እንዲህ ያለው ተግባር አገርንና ራሱን ኢህአዴግን ወደ “ታላቁ” ጉድጓድ እንደሚነዳቸው ከወራት በፊት “መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ” በሚል ርዕስ ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱ አንድ የኢህአዴግ አመራር ማስታወቃቸው አይዘነጋም። በቃለ ምልልሱ ኢህአዴግ ስለመበስበሱ በስፋት የተወሳ ሲሆን በተለይም አቶ መለስ ካለፉ በኋላ ስርዓቱ እንዴት ሊፈረካከስ እንደሚችል ተመልክቷል። በተመሳሳይ ከወር በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ኢህአዴግ ከፍተኛ በሚባል የንቅዘትና የመውደቅ አደጋ እንደተጋረጠበት በመጠቆም ከወዲሁ መስተካከል ስላለባቸው ጉዳዮች ማሳሰቢያ መስጠቱም ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment