Translate

Tuesday, November 20, 2012

ከዚህም ከዚያም



students1


በአለባበሳችሁ አትፈታተኑ

በሜኔሶታ ጠቅላይ ግዛት የሜኔቶንካ ሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች የመቀመጫና የኋላ ክፍላቸውን የሚያሳይ አለባበስ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት ዴቪድ አድኔይ ለወላጆች በላኩት የኢሜይል (የጾዳቤ) መልዕክት ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን እንዲመክሩና የመቀመጫ ክፍላቸውን አወጣጥሮ እንዲሁም እግራቸውን በብዛት የሚያሳይ አለባበስ ሌሎችን የሚረብሽ በመሆኑ እንዳይለብሱ እንዲያደርጉ በማሳሰቢያው ጠቁመዋል፡፡

ርዕሰመምህሩ ለወሰዱት እርምጃ ከወረዳው ትምህርትቤት አስተዳደር፣ ከበርካታ ወላጆችና ከሌሎች ት/ቤቶች ድጋፍን አግኝተዋል፡፡ ውሳኔውን የተቃወሙ ተማሪዎች ሲኖሩ አንዳንድ ወላጆች ደግሞ “በየማስታወቂያው፣ በየቲቪው፣ በየመጽሔቱ፣ በሙዚቃው፣ … የሚሰራጨው የአለባበስ ዓይነት በየሱቁ ሲኬድ ከሚገኘው ጋር አንድ በመሆኑ ሰውነትን የማያሳይና ሥርዓት ያለው ልብስ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በውሳኔው እጅግ የረኩ ወላጆች ግን ውሳኔው በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ለሚገኙት ልጆቻችን አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ አወድሰውታል፡፡

ድመቱ ሰው ራሱን አጠፋ

ሴት ድመት ለመምሰል ሰውነቱን በተለይም ፊቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የአካል ለውጥ አካሂዶ የነበረው ዴኒስ አቭነር ራሱን ገድሎ መገኘቱ ሰማን፡፡ ይህንን የሰማነው ከ ነው፡፡ እንደወሬው የ54 ዓመቱ ግለሰብ ቀድሞ የአሜሪካ የባሕር ኃይል ባልደረባ የነበረ ሲሆን በሙያው የኮምፒውተር ፕሮግራመር ነበር፡፡ በትውልዱ የአሜሪካ ህንዳዊ የነበረው አቭነር በአንድ ወቅት የጎሣው መሪ የነብርን መንገድ መከተል እንዳለበት ከነገረው ወዲህ ወደ ድመትነት ለመለወጥ ጥፍሮቹን በማሳደግ፣ ከንፈሩ በመቀየር፣ … ድመት ለመምሰል በርካታ የሰውነት ለውጦችን አካሂዶ የነበረ ሲሆን በማሽን የሚሰራ ረዘም ያለ የድመት ዓይነት ጭራም ነበረው፡፡ “እጅግ ተወዳጅ ሰው” በማለት አፍቃሪዎቹ የሚናገሩለት ዴኒስ የሞተበት ምክንያት በውል ባይታወቅም በቅርብ በሚያውቁት ዘንድ ራሱን እንደገደለ ይታመናል፡፡

የቻይና ኮንትሮባንድ ታነቀ

“ፕላስቲክ” የሚል ጽሁፍ የተለጠፈበትና ሃሰተኛ ዕቃዎችን የጫነ ኮንቴይነር በአሜሪካ ኒውጀርዚ ግዛት የኒዋርክ ወደብ ላይ ተያዘ፡፡ ከ500 በላይ የታዋቂ ዲዛይነሮችን ስም በማስመሰል የተለጠፈባቸው የሴቶች ቦርሳ፣ የወንዶች ቀበቶና ቦርሳ የያዘው ኮንቴይነር የተነሳውም ሆነ ዕቃዎቹ የተፈበረኩት ቻይና ነው፡፡ መያዣው ወደብ ላይ ሲያዝ በውስጡ የሉዊስ ቩቶን፣ ጉቺ፣ ማይክል ኮርስ የንግድ ምልክት የተለጠፈባቸውና እውነተኛ ቢሆኑ ዋጋቸው 20ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን የወደብ ባለሥልጣናት ጠቁመዋል፡፡
ቻይና የሃሰተኛ ዕቃዎች ምንጭ እንደሆነች የሚናገረው የአሜሪካ የነጋዴዎች ምክርቤት ድርጊቱ በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ የ250ሚሊዮን ዶላር ኪሣራ በየዓመቱ ያስከትላል፡፡ የኒውዮርክና የኒውጀርዚ ወደቦች ተቆጣጣሪ የሆኑት ባለሥልጣን እንደገለጹት የሃሰተኛ ዕቃዎች አንደኛ ደረጃ ምንጭ ቻይና ስትሆን እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ወደብ በሃሰተኛ ዕቃነት ከሚያዙት ውስጥ 62በመቶው ከቻይና የሚመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የግብጽ “ጣዖቶች” እንዲፈርሱ ጥሪ ቀረበ

ከታሊባን ጋር ግንኙነት አለኝ የሚለው የግብጹ ጂሃድ መሪ ሙረጋን ሳሌም አልጎሃሪ በግብጽ የቱሪዝም መስህብ የሆኑት የስፊኒክስ ሃውልትና የጊዛ ፒራሚዶች እንዲደመሰሱ ጥሪ አቀረበ፡፡
በግብጽ ከሚገኝ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው በዚህ ቃለምልልስ “አላህ ለነቢዩ መሐመድ ጣዖታትን በሙሉ እንዲያጠፉ ትዕዛዝ ሰጥቶዋቸዋል፡፡ ከታሊባን ጋር በነበርኩበት ጊዜ መንግሥት ማድረግ ያቃተውን የቡድሃን ሐውልት አውድመነዋል፡፡ … ስለሆነም ሙስሊሙ በሙሉ የእስላምን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ ስላለበት በአፍጋኒስታን እንዳደረግነው በግብጽ እነዚህን ሐውልቶች ማውደም አለበት” ብሏል፡፡
እጅግ ወግአጥባቂ የሆኑት የሳላፊ ሙስሊሞች ከሙስሊም ወንድማማች ጋር በመሆን በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ አብላጫውን ድምጽ በማግኘት ፕሬዚዳንታዊውን ሥልጣንና ፓርላማውን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ቅርሳ ቅርስን በተመለከተ በግብጽ አዲስ ሕግ እንዲወጣ ግፊት በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ተፈርቷል፡፡

ኦባማን ገድሎ ዝና

ፕሬዚዳንት ኦባማን የመግደል ዕቅድ የነበረው ወጣት በቁጥጥር ሥር መዋሉ የተለያዩ የዜና አውታሮች ይፋ አድርገዋል፡፡ በኮሎራዶ ጠቅላይግዛት በነርስነት ሙያ እየሰለጠነ የነበረው የ20 ወጣት ሚቸል ኩሲክ ለሃኪም እንደገለጸው ዕቅዱ በታሪክ ኦባማን የገደለ ሰው ተብሎ ለመጠራት ነበር፡፡ ባለፈው የሃሎዊን በዓል ወቅት በርካታ ህጻናትን ለመግደል ፍላጎት እንደነበረው የተናገረው ኩሲክ ኦባማን ለመግደል ከአክስቱ ቤት መሣሪያ እንደወሰደና ጥይት የመግዛት ዕቅድ ላይ እንደነበር ታውቋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በቲያትር ቤት ውስጥ ተኩስ በመክፈት የ12 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን ጀምስ ሆልምስ ድርጊት እንደሚያደንቅ የተናገረው ይኸው ወጣት “አንዳንድ ሰዎች ዓለም ተቃጥላ ስትወድም ለማየት ይፈልጋሉ፤ ከእነርሱ መካከል እኔ አንዱ ነኝ” በማለት መናገሩም ተገልጾዋል፡፡ በሁኔታውን የተከታተለው ሐኪም ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጉ ወጣቱ በቁጥጥር ሥር እንዲውል የተደረገ ሲሆን ፍርድ ቤት እስኪቀርብ የአእምሮ በሽተኞች ሆስፒታል ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

ጥፋተኛዋ በመፈክር ራሷን “ደደብ” አለች

በአሜሪካ በኦሃዮ ጠቅላይ ግዛት በክሊቭላንድ ከተማ ተማሪዎች ከአውቶቡስ ሲወርዱ እንደ ሕጉ መቆም ሲገባት አውቶቡሱን አቋርጣ ለማለፍ በእግረኛ መንገድ ላይ መኪናዋን ያሽከረከረችው ሺና ሃርዲን ቅጣት ተበየነባት፡፡
“የተማሪዎችን አውቶቡስ ለማምለጥ በእግረኛ መንግድ ላይ መኪና የሚነዱ ደደቦች ብቻ ናቸው” የሚል ማስታወቂያ ለአንድ ሰዓት መንገድ ላይ ይዛ እንድትቆም የተበየነባት ሺና ለዚህ ያበቃትን የቪዲዮ ማስረጃ ያሳየው በእጅ ስልኩ የቀዳው የአውቶቡስ ሹፌር ነበር፡፡ ለጥፋቷ ምንም ጸጸት ባለማሳየቷ ቅጣቱ እንደተበየነባት የገለጹት የማዘጋጃ ፍርድቤቱ ዳኛ የመንጃ ፍቃዷ ለ30ቀናት እንዲታገድና 250ዶላር ለፍርድቤቱ እንድትከፍል ወስነውባታል፡፡

እንግሊዝ አሸባሪውን ለቀቀች

ላለፉት ሰባት ዓመታት በእንግሊዝ አገር በተለያዩ የአሸባሪነት ወንጀሎችና የኢሚግሬሽን ክስ ምክንያት ሲታሰር ሲፈታ የቆየውና በትውልድ ፍልስጤማዊ በዜግነት ዮርዳኖሳዊ የሆነው አቡ ቃጣዳ ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የ51ዓመቱና የ5 ልጆች አባት የሆነው በእውነተኛ ስሙ ኦማር ማሃሙድ ሞሃመድ ኦትማን የተባለው አቡ ቃጣዳ የዛሬ 20ዓመት አካባቢ በተጭበረበረ ፓስፖርት ወደ እንግሊዝ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ አይሁዳውያን እንዲጨፈጨፉ ፋትዋ በማውጣት፣ የአልቃይዳ ወኪል በመሆን (በአውሮፓ የአልቃይዳ መንፈሳዊ መሪ ተብሎም ይጠራል)፣ የኒውዮርኩን መንትያ ሕንጻዎች ፍንዳታ በመደገፍ፣ በዮርዳኖስ የአሸባሪ ጥቃት በማድረስ፣ … በርካታ ክሶች ተመስርተውበት ነበር፡፡ ከኢሚግሬሽን ጋር በተያያዘው ጉዳይ ወደ ዮርዳኖስ እንዲባረር ዓቃቤሕግ ቢጠይቅም ወደ ዮርዳኖስ ከተመለሰ የማሰቃየት እርምጃ (ቶርቸር) ሊደርስበት ይችላል በሚል በጠበቃው በኩል ያስገባው ይግባኝ በፍርድቤት ተቀባይነት በማግኘቱ በቀን ውስጥ የ16 ሰዓታት እላፊ ተወስኖበት ተለቅቋል፡፡
ላለፉት 10ዓመታት የአቡ ቃጣዳን ጉዳይ በተመለከተ ከ4.5ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጣ ሲሆን አሁን ደግሞ በየወሩ 1600ዶላር ለእርሱና ለቤተሰቡ እየተከፈለው በሰሜናዊ ሎንዶን አካባቢ ኑሮውን ይቀጥላል፡፡ የእርሱን ዕለታዊ ኑሮ ያለማቋረጥ የሚቆጣጠር እንዲሁም በአረብኛ የሚያደርጋቸውን የስልክ ጥሪዎችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ለመከታተል በዓመት እስከ 8ሚሊዮን ዶላር ድረስ የእንግሊዝን ግብር ከፋይ ወጪ እንደሚያስደርግ ተገምቷል፡፡
ወደቤቱ ሲመለስ በአካባቢው “አቡ ቃጣዳ ወዳገሩ ይባረር” የሚል መፈክር የያዙ መፈታቱን የተቃወሙ በርካታዎች ሲሆኑ ዓቃቤሕግም ድጋሚ ይግባኝ እንደሚል አስታውቋል፡፡

“አንቀጽ 39” በአሜሪካ

እንገንጠል የሚሉ ይባረሩልን
በአሜሪካ ከ30 በላይ ጠቅላይ ግዛት ነዋሪዎች ከአሜሪካ ለመገንጠል አቤቱታ ለቤተመንግሥቱ አቀረቡ፡፡ ባራክ ኦባማ ከተመረጡ በኋላ በእነዚህ ግዛቶች የሚኖሩ ቤተመንግሥቱ ባቋቋመው ድረገጽ ላይ አቤቱታቸውን በፊርማ ያቀረቡ ሲሆን በ30 ቀናት ውስጥ የፈራሚዎች ቁጥር 25ሺህ ካልደረሰ ጉዳዩ ሊታይ እንደማይችል ታውቋል፡፡ ከቴክሳስ ግዛት የፈረሙ አንድ ግለሰብ “አሜሪካ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው፤ … ሌሎቻችንም ደግሞ በማይመለከተን እየተጎዳን እንገኛለን፡፡ ከዚህም ሌላ አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል በየአየር ማረፊያው ፍተሻ እየተካሄደብን ሰብዓዊ መብታችን እየተጣሰና እየተዋረድን እንገኛለን፤ … ቴክሳስ በኢኮኖሚው ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ ከዓለምም 15ኛ ነው፤ … ስለዚህ መገንጠል አስፈላጊያችን ነው …” ብለዋል፡፡ ሆኖም ከዚህ በፊት የመገንጠልን ሃሳብ ይሰብኩ የነበሩት የቴክሳስ ጠቅላይ ገዢም ሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞች አሁን ይህንን አቋም ሲያራምዱ አይሰሙም፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ እዚያው የቤተመንግሥቱ ድረገጽ ላይ የመገንጠልን ጥያቄ በማንሳት አቤቱታ የሚፈርሙ ሁሉ የአሜሪካ ዜግነታቸው ተገፍፎ ወደ ግዞት እንዲላኩ የሚጠይቅ አቤቱታ መፈረም ተጀምሯል፡፡ ይህኛውም በ30ቀናት ውስጥ 25ሺህ ፈራሚዎችን ካላገኘ ጉዳዩ ታይቶ ከኦባማ አስተዳደር ምላሽ አያገኝም፡፡

በአሜሪካ ከ9ወር በኋላ በርካታ ህጻናት ሊወለዱ ይችላሉ

በቅርቡ በተከሰተው አውሎንፋስ የቀላቀለ ዝናብና ጎርፍ (ሃሪኬይን ሳንዲ) ምክንያት የዛሬ ዘጠኝ ወር በምስራቃዊ የአሜሪካ ክልል በርካታ ህጻናት እንደሚወለዱ ተጠቆመ፡፡
የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ አደጋ እና የህጻናት ውልደት ግንኙነት የሚያጠኑ ሁኔታው ያልተለመደ አይደለም ይላሉ፡፡ የቴሌቪዥን፣ የስልክ፣ … አገልግሎቶች በተቋረጡበትና ሰዎች ከሥራ በመገለል ለበርካታ ቀናት ቤት ያለምንም ሥራ በሚውሉበት ጊዜ “የድሃ ቲቪ” ብቸኛ መዝናኛቸው እንደሚሆንና ይህም ባልተጠበቀ መልኩ ወሊድን ሊያበራክት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
ሁኔታው ላይከሰት ይችላል በማለት የሚከራከሩ ሌሎች ምሁራን ደግሞ የተፈጥሮ አደጋዎች በደረሱባቸው ቦታዎች ወሊድ የጨመረበትም ያልጨመረበት ሁኔታ ስላለ በሳንዲ ክስተት ምክንያት ወሊድ ይጨምራል ለማለት እንደሚከብድ ያስታውቃሉ፡፡ የተፈጥሮ አደጋና የወሊድ መጨመር ከመብራት መጥፋትና ያንንም ተከትሎ ሰዎች ህይወታቸውን መኝታቤታቸው ያደርጋሉ ከሚል አስተሳሰብ ጋር ብቻ በቀላሉ የተገናኘ ሳይሆን እጅግ የተወሳሰበ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሁሉም ጊዜው ሲደርስ የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment