Translate

Friday, November 16, 2012

መነገር ያለበት ቁጥር ሦስት፣ ለእውነት ወይስ ለውሸት የቀረበ


መነገር ያለበት ቁጥር ሦስት፣ ለእውነት ወይስ ለውሸት የቀረበ

ከበልጅግ ዓሊ
እስከ መቼ ነው ዝምታ? እስከ መቼ ነው አርምሞ ?
የልብን ሐቅ አስታሞ፣ የብእር አንደበት ለጉሞ፣
እስከመቼ ነው ዝሙ ? እስከ መቼ ነው አርምሞ??
“መቼን” የማታውቅ ልቤ ፣ አርምሞህን እነቀው፣
በል እባክህ እንዳቅምህ ፣ ባለችህ መንገድ አፍስሰው፣
እስከመቼ ነው አርምሞህ? ዝሙስ እስከመቼ ነው ??
ነሐሴ 1970
ፍቃደ አዘዘ
ሱዛን ራይስ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ ተወካይ ለጠቅላዩ ቀብር አዲስ አበባ በነበረችበት ወቅት ባደረገችው ንግግር መለስ ለሞኞችና ለደደቦች ትዕግስት አልነበረውም (Of course he had little patience for fools, or idiots, as he liked to call them.) ብላ ተናግራ ነበር። መለስ (fools, or idiots) ብሎ የሚጠራው ወዳጆቹን ሳይሆን ተቃዋሚውን ክፍል መሆኑ ይታወቃል።

መለስ በግል ጥቅም ምክንያት ባሰባሳባቸው ኮልኮሌዎች ወይም እንደ ሱዛን ዓይነት የሃገራቸውን ጥቅም ባስጠበቀላቸው የውጭ ዜጎች አካባቢ እንደ <<ምርጥ መሪ>> ይቆጠር እንደሆን እንጂ፣ በምንም መለኪያ አምባሳደሯ እንደካበችው ዓይነት እንዳልነበረ ቢያንስ የ97 ምርጫና ውጤቱን ለተከታተለ ግልጽ ነው።
ዛሬ  የመለስ ራዕይ ተብሎ ሽብ እረብ የሚባልለት፣ ምርጫ ከማጭበርበር፣ ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን በሽብርተኖች ስም ከማሰር፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ አካላትን ከማሳደድ፣  በሃይማኖት ውስጥ እየገባ ከማራበሽ ሊያልፍ አልቻለም። ለዚህ ነው የሱዛን ንግግር ለውሽት የቀረበ ተራ የካድሬ ፕሮፖጋንዳ እንጂ አደባባይ ላይ በግልጽ የሚታይ ክስተት ያልሆነው።
ምንም እንኳን የሱዛን ማጋነን ተራ ጭፍን ድጋፍ ቢሆንም ለእውነት የቀረበበት ጉዳይ የለበትም ማለት አይደለም።  ተቃዋሚዎች በተለይ መሪዎቻቸው መለስ እንደ ጅልና ደደብ አድርጎ እንደቆጠራቸው አይደሉም ብሎ ለመከራከር እኔ በበኩሌ ድፍረት አይኖረኝም። ተቃዋሚዎች ብዙ ቢያስወግዷቸው ለድል የሚቀርቧቸውን፣ በሕዝብ ታማኝነት ሊያስገኙላቸው የሚችሉ ጠንካራ ጎኖቻቸውን በመተው፣ ለግል ታዋቂነት፣ ለሥልጠን ጉጉት፣ ለአንዳንድ ትናንንሽ ጥቅማ ጥቅሞች ሲሉ የሚያሰድባቸውን ደካማ ተግባራትን አይፈጽሙም ማለት ለውሸት የቀረበ ይሆናል።
የቅንጅት መሪዎች በተለይ ከ97 ምርጫ በኋላ ያገኙትን የሕዝብ ድጋፍ ወደ ጎን በመተው፣ በእንቶ ፈንቶ ጭቅጭቅ ተከፋፍለው፣ ሃገር ጥለው ወጥተው በሰሜን አሜሪካ ጡንቻቸውን ሲፈታተኑና ሕዝብን ተስፋ ሲያስቆርጡ ለተከታተለ ተመልካች እነዚህ ሰዎች እውነትም ጅሎች ናቸው እንዴ? ብሎ ቢጠይቅ ወይም ቢሳደብ ትክክል አይደለም ለማለት እንደፍር ይሆን? ከዛ በኋላስ ስንት ድርጅቶች ተራ ቅራኔዎችን ሰማይ አሳክለው ተከፋፍለዋል? ይህንን እያወቅን ብንደብቀውም የአደባባይ ምሥጢር ነውና ያጋልጠናል።
በዚህ ምክንያት የሱዛን ዘለፋን እንደ ስድብ ሳንወስደው<<በገንቢ ሂስነቱ>> ከተመለከትነው ለእውነት የቀረበ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም መለስ ይህንን ዘለፋ የተጠቀመው የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እንጂ የተቃዋሚዎችን ድክመት ለማረም እንዳልሆነ በሕዝብ ላይ የሚፈጽማቸው ግፎች ደግሞ አጉልተው ያሳዩናል። ሱዛንም ይህንን በመደገፍ ለዴሞክራሲ ሳይሆን ለሃገሯ ጥቅም እንደቆመች ያጋልጣል።
በእውነት ለተመለከተው በተቃዋሚው ጎራ የሚሠሩ፣ ወይም የሚቀነቀኑ ብዙ ሊያሰድቡ የሚችሉ ተግዳሮቶች
በየወቅቱ እንመለከታለን። ተቃዋሚዎች በአንዳንድ ወቅት ከሕዝብ ድጋፍ የሚያገኙበትን ትተው በሕዝብ የተወገዘውን አንስተው መርህ መፈክራቸው አድርገው ሲነጉዱ ይታያሉ። ታዲያ ይህንን ልብ ብሎ ለተመለከተ እነዚህ ተቃዋሚዎች ሞኝ ናቸው? ብሎ ቢጠይቅ ምን ይደንቃል?
የሕዝብን ድጋፍ በመመልከት እነመለስ ሰንደቅ ዓላማችንን <<ጨርቅ>> ነው ማለት እንዳላዋጣቸው ሲያውቁ በዚያ አልቀጠሉም። እንዲያውም አልፈው ተርፈው የሕዝብ ድጋፍን ለማግኘት የማያምኑበትን ሰንደቅ ዓላማ አፍቃሪ ሆነው በእሱ ተጠቅልላው እስከመቀበር ደረሱ እንጂ። ወያኔ ይህንን የፖለቲካ ቁማር ሲጫወት አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ ሰንደቅ ዓላማውን በመሸሽ ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ የዘር ፖለቲካን በማጉላት የተለያዩ የጎጥ ሰንደቅ ዓላማዎች ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ  እስከመውጣት፣ ብሎም ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚያወራውን እስከ ማውገዝ  የተደረሰበት ሁኔታ እያየነው ነው።
ይህ የተለያየ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ <<እኛ ከወያኔ የበለጠ ዘረኞች ነን>> የሚለው መፈክር አንግቦ መጓዝ ከግል የሥልጣን ፍላጎት አንጻር የተተለመ እንጂ የሕዝብ ፍላጎት ያላካተተ መሆኑን በ21 ዓመት የተቃዋሚዎች ንቅናቄ አለመረዳት ቢያሰድብ ሊገርመን አይገባም። የሕዝብ ፍላጎትን ባለማጤን፣ የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያገናዝቡ የሚታለም ትግል የት ሊያደረስ እንደሚችል የታወቀ ነው። ግልጽ ለማድረግ የግልን ኪስ ያዳብር እንደሆን እንጂ ወያኔን በተጨባጭ መቃወም የሚችል አማራጭ አይሆንም። በሕዝብ ዘንድም ተቀባይነት አያገኝም። የዘር ፖለቲካን ከወያኔ በላይ እናስፈጽማለን ብለው የሚባዝቱ የተቃዋሚነት ትግሉን ትተው ወያኔን መደባለቅ እንደ ብልህ ያስቆጥራቸዋል።
ወያኔ የዓባይ ግድብ እያለ የኢትዮጵያዊነት ራዕይ አለኝ በሚልበት ወቅትና  በዛ ስም ለመነገድ ጥረት ሲያደርግ  አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ፣ የእከሌ ነጻ አውጭ ፣ የዚህ ዘር ነጻ አውጭ በሚል  በሚጓዙበት ወቅት ላይ ደርሰናል።ከወያኔ በኋላ የሚመጣው መንግሥት በዘር ላይ የተመሰረተ ይሆናል ብለው የሚያምኑ ካሉ ሱዛን ከመለስ ነው ብላ የወሰደችው ስድብ ትክክል ነው ማለት ነው።
በጀርመን ቋንቋ 1982 የዓመቱ ምርጥ ቃል ተብሎ የተመረጠ ቃል አለ።ይኸውም (Ellbogengesellschaft) የሚል ነው። ቃሉ የመሠረተው ከሁለት ቃላት ነው። Ellbogen – ክርን፣ ጡጫ ማለት ሲሆን gesellschaft- ማህበረሰብ ማለት ነው። በአጠቃለይ ቃሉ  በሕብረተሰብ ውስጥ  በግል ለመታወቅ ወይንም የግል ታዋቂነትን በመሻት(Egoismus) በመፈለግ የሚደረግን የእርስ በእርስ ትግል ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ነው። በእንግሊዘኛ (everyone-for-himself- dog-eat-dog society) የሚለው ይሆናል። ይህ አገላለጽ በአሁኑ ወቅት በተቃዋሚው ጎራ እየሰፋ የመጣውን የመከፋፈል ፖለቲካን በደንብ ይገልጸዋል።
ወያኔ የትግራይ ነጻ አውጭን የሚለው ስሙ ስላልጠቀመው በኢሕአዴግ ስም አንድ ሆኖ ለመታየት ሲጥር ተቃዋሚዎች ደግሞ አዲስ በተፈጠረው “የዴ“ ፖለቲካ ራሳቸውን እየከፋፈሉ የሕዝብ ፍላጎትን ሲጋፉ ለተመለከተ “ኢዲየትስ” ቢላቸው ሊጨንቀን አይገባም።
<<የዴ ፖለቲካ>> ከመከፋፈል አንጻር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የቆየ  ቢሆንም በዚህ ዓይነት መልኩ ግን አዲስ የተፈጠረ ነው።  ይህ አዲስ የክፍፍል ፖለቲካ በተለያየ ምክንያት ይምጣ እንጂ ትግሉን በጣም የጎዳ ነው። ድርጅት ሲከፋፈል  ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ከቅንጅትና ከኢሕአፓ መማር ይቻላል። የእህል ናዳ ሲቃጠል ሞኝ ይስቃል ፣ ብልጥ ያለቅሳል እንዲሉ በክፍፍል ወደ ሥልጣን የቀረቡ እየመሰላቸው ጮቤ የሚረግጡ እንደሞኝ ቢቆጠሩ ሊገርመን አይገባም። ከሁሉ የሚያሰድበው ደግሞ የድርጅት ምስጢር የአደባባይ ወሬ ሲሆን ነው። በተለይም ደግሞ ይህ ክፍፍል(እንደ ዓይጋ ፎረም ) ዓይነት የጠላት መድረክ ላይ ሲሆን ምንኛ ያስጠላል? አብረው የተገበሩትን ጉዳይ ሲጣሉ እርስ በእርስ መገላለጥ ያላሰደበ ምን ያሰድብ? የወያኔ ደጋፊዎች ይህንን እየተመለከቱ እነዚህ “ኢዲየትስ” ቢሉ ሊገርመን አይገባም።
በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ይህ የመከፋፈል አዝማሚያ ሲጀምር አብሮ የሚጀምረው የክፍፍሉ መሪዎች ብዙሃኑ እኔን ነው የሚደግፈው የሚለው ይሆናል። ይህ ሞኝነት ነው። ታሪክ ግን ያስተማረን ሌላ ነው። ብዙሃኑ በክፍፍሉ ተስፋ ቆርጦ ትግሉን ነው የሚያቆርጠው ወይም ዝምታን የሚመርጠው ነው። መሪዎች የሚከራከሩበት ብዙሃን ሊሆን የሚችለው ከደሃጣኑ ላይ ነው። ይህንን በቅንጅት አይተነዋል። ግንቦት ሰባትም ይሆን መኢአድ ቢደመሩ የቅንጅትን ዓይነት ኃይል አይኖራቸውም ። ኢሕአፓና ኢሕአፓዴም ከመከፋፈላቸው በፊት የነበረውን ኃይል አለን ብለው መዋሸት አይችሉም ። ግንቦት ሰባትና ዴውም እንደዚሁ። ሕዝብ ወይም አባላት የሚፈልጉት አንድነታቸውን ሲሆን መከፋፈላቸውን የሚቀነቅኑትን ጅሎች ቢባሉ ሊከፋን ነው ማለት ነው?
በሌላ ደግሞ እንመልከት ለደቂቃ ታክል የአሁኑ መሪ መፈክራችን ምንድነው? ብለን እንጠይቅ። መልሱ ቀላል ነው። <<አዜብ ከቤተመንግሥት ትውጣ>>?ከቤተመንግሥት ለማውጣት ነው ወይ የምንታገለው? ብለን ብናስብ መልሱ ቀላል ነው። የተነሳንበት ዓላማ የኢትዮጵያ አንድነት እንጂ የአንዲት እንስት የቤተመንግሥት የቤት ኪራይ ጉዳይ አይደለም። አሁንም ቢሆን ከልደታም ሆነ ከቄራ ፣ ከጨርቆስም ይሆን ከቦሌ ይህንን መንግሥት እስከ መራች ድረስ ቤተመንግሥት መኖር አለመኖሯ ልዩነት አያመጣም። ግን ተቃዋሚዎች የአዜብ የቤት ኪራይ ጉዳይ እንደ ወሳኝ ጥያቄ በሚስተዳድሯቸው የመገናኛ ዘዴዎች ሲቀነቅኑ መስማት ደግሞ ለምንድነው የምንታገልው ? እውነትም “ ኢዲየትስ “  ነን እንዴ?  ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ተቃዋሚዎች የሚሰባስባቸውን አንድ መሪ መፈክር ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህ የመሪን መፈክር በወቅታዊ መፈክር መቀየር በተከታታይ የታየ የተቃዋሚዎች ድክመት ነው።
ደግሞ ቀጥለን እንመልከት በየወቅቱ እንደ አሽን እየፈሉ የሚፈጠሩና አንድ ሰሞን ፖለቲካውን ሞልተው ይተርፉና የሚጠፉ ድርጅቶችን ስንመለከት ደግሞ ምን እየተደረገ ነው? ማለታችን አይቀርም ። ጎበዝ በዚህ ተጠያቂነት በሌለበት ትግል ውስጥ የሕዝብ ንብረትን ዘርፈው የተደበቁና አመቺ ሁኔታ ሲፈጠር ብቅ የሚሉ የድርጅት መሪዎች ብዙ ናቸው። ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ አዲስ በተፈጠሩ ድርጅቶች ሁሉ ውስጥ ብቅ የሚሉ ግለሰቦች ተመሳሳይ ናቸው። አዲስ ከሚፈጠሩት ድርጅቶች ብዙ በመጠበቅ ንብረታቸውን የሚከሰብሱ የዋሆችን ስንመለከት ማዘናችን አይቀርም። ግን እነዚህን ግለሰቦች እንደ ጅል መቁጠር አንችልም። የሃገር ፍቅር አንገብግቧቸው ምንአልባት ትግሉን ብረዳ በሚል ገንዘባቸውን የሚከሰክሱትን ልንወቅስ አይገባም። በዚህ የፖለቲካ ንግድ የተሰማሩትን ግን ታሪክ እንደወቀሳቸው ይኖራል።
ይህ የተቃዋሚዎች ጎራ ሌላው ሞኝነት ደግሞ ከአሜሪካ መንግሥት የሚጠበቀው ድጋፍ ነው። ከደርግ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የአሜሪካ ድጋፍ ቢጠበቅም ጠብ ያላለ ጉዳይ ነው። ባለፈው ሳምንት ኦባማ ኢትዮጵያን ይጠቅማልና እንምረጥ ተብሎ ጠብ እርገፍ ሲባል ነበር። ጉድ እኮ ነው! ሱዛን የእሱ አስተዳደር አባል መሆኗ ተዘንግቶ ነው? ወይስ የግል ቦታ ፍለጋ? አንዳንድ ፕሮፌሰሮች ሁላችንም አሜሪካዊ የሆንን  ይመስላቸዋል ልበል?  ኦባማም ሆነ ራምኒ የአሜርካ ፕሬዘደንት የሚሆነው የሚሠራው ለሃገሩ ጥቅም ነው።  ሃገራችንን እኛ ነን ነጻ የምናወጣት ። <<ኦባማን ምረጡ ሊረዳን ይችላል>> የሚለው መፈክር ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ  አይነት ነው። ሊሆን የሚችለው ትግልን አዘናጊ መፈክር ነው። የእነርሱ መመረጥ ከአሜሪካ ጥቅም እንጂ ከእኛ ሃገር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ቢኖረውም ወያኔን ከመደገፍ አላለፈም። አስረጅ መጠየቅ አይኖርብኝም።
እንግዲህ እንዳንሰደብ ከፈለግን ድክመቶቻችን አስወግደን መጓዝ ይኖርብናል። የመጀመሪያ ጉዳይ መጀመሪያ መሆን አለበት። በእንቶ ፈንቶ የተከፋፈሉ ድርጅቶች ችግራቸውን ሲያስወግዱ ብልሆች ብለን ማድነቅ እንጀምራለን ። የሕዝብ የማይደግፈውን መፈክር አሽቀንጥረን ጥለን ሕዝባዊ የሆኑ መፈክሮች ስናንግብ ፤ ወይም ወቅትዊ የሆኑ መፈክሮችን ትተን በቋሚ መፈክሮች ዙሪያ ስንስባሰብ ብልሆች እንሆናለን።  በሕዝባችን እንጂ በውጭ ሃገር መሪዎች መተማመን ስንተው ብልሆች እንሆናለን። የምንናገረውን የምንሰራው ሲጣጣም ያኔ ብልሆች እንሆናል። ይህ ፕሮፌሰርነት የማያሻው ተራ እውቀት ነው።
ከሁሉ ተቃዋሚዎችን ከስድብ ሊያድናቸው  የሚችለው ከወያኔ የተሻለ አማራጭ ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው። ከሚፈከርበት የመለስ ራዕይ የተሻለ ራዕይ ሲኖራቸው ብቻ ነው። <<ከመለስ በላይ እኛ ዘረኞች ነን>> የሚለው መፈክር ወይም በአንደነት ሳይሆን በተበታተነ መልክ በመቅረብ የሕዝብን ድጋፍ እናገኛለን ማለት ዘበት ነው። ከመሰደብ በላይ ሊያመጣ የሚችለው ምንም የለም።
ብልህነታችን ደግሞ ለድላችን ጥርጊያ መንገድ ከፋች ነው። አሊያ <<ኢድየትስ>> ሲያሰኝን ይኖራል። ዛሬ ብዙ የተማሩ፣ ብዙ ልምድ ያላቸው፣ ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ አሉ። ውስጥ ለውስጥ ከማልጎምጎም  አልፈው ከተደበቁበት ወጥተው የተበታተነው በማሰባሰብ ለሌሎች ድርጅቶች ትምህርት ሊሠጡ ይችላሉ። ይህ አዋቂነት እንጂ ደካምነት አይደለም።  በመደበቅና ዝም በማለት ከተጠያቂነት ለመዳን አይቻልም። ለሠራነው ብቻ ሳይሆን መሥራት ሲገባን ላልሠራነውም እንጠየቃለንና።
ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የተነሳሁበት ሱዛን ራይስ የጠቅላዩ ቀብር ላይ በተናገረችው ላይ ነበር። ግን በመሃል ድህረ ገጸችን ስዳስስ አንድ የሚያሳዝን ጽሁፍ አውራምባ ታይመስ ላይ አነበብኩ። <<የተረሳው ጋዜጠኛ>> በሚል በወስንሰገድ ገብረኪዳን በወያኔ እስር ቤት ስለሚማቅቀው  ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ የተጻፈው ነው። ይህ በጣም የሚሳዝነውና ተቃዋሚ ክፍሎችን የሚያሰድበው ትልቁ ድክመት ነው። ይህ ጽሁፍ ዛሬ በተቃዋሚዎችና እነርሱ በሚያስተዳድሯቸው የሕዝብ መገናኛውዎች ከዛም አልፎ ነጻ ነን የሚሉትንም ጨምሮ ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት የሚተገበረውን አሳዛኝ ሁኔታ የሚያጋልጥ ነው። ከጽሁፉ ለመጥቀስ ያህል ፡ -
የውብሸት ግን ያለመታደል ነው ብዬ አላምንም፤ አይደለምም፡፡ ሆን ተብሎ የመረሳት፣ ሆነ ተብሎ የመተው የአድሎአዊነትና የአግላይነታችን ምስጢር መገለጥ እንጂ፡፡ ለዚህም አባባሌ ምክንያት አለኝ፡፡ ካለእኔ ታማኝ የዜና ምንጭ የለም የሚለው የESAT ፊትአውራሪና የቀድሞው የ2 ወር አለቃዬ ፋሲል የኔ አለም ከሁለት ቀን በፊት ስለውብሸት ለጠየቁት የፌስቡክ ጓደኞቹ የሰጣቸው ምላሽ “ተፈቷል” የሚል ነው፡፡ ‹‹አንድ ለእናቱና ለኢትዮጵያውያን ሐቀኛ የዜና ምንጭ›› የሆነው ኢሳት ዋና ጋዜጠኛ መረጃ ይህ ከሆነ ውብሸት ሆነ ተብሎ ነው የተረሳው፤ ወይም እንዲረሳ የተፈለገው ማለት ያስደፍራል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሁላችንም ራሳችንን፣ ፍላጎታችንን እና ተግባራችንን እንፈትሽ ዘንድ ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር ይህ የሚዲያ ተቋም ያሰራጨው አንድ ዜናም እጅግ አስደንቆኛል፡፡ ‹‹ጋዜጠኛ ርዕዮት ከታሰረች አንድ አመት ሞላት፤›› ይልና በእስር ቤት ውስጥ ቀኑን አክብራ መዋልዋን ይዘግባል፡፡ ሌላው ይቅር ቢያንስ ይህ ዜና ሲሰራ አብሯት በቁጥጥር ስር ውሎ፣ በአንድ የክስ ፋይል አመቱን ሙሉ አብሯት ፍርድ ቤት ተመላልሶ፣ አብሯት እስርቤት ውስጥ አንደኛ አመቱን እያከበረ ስላለው ጋዜጠኛ ምንም ሳይባል እንዴት ዜናው ይደመደማል? የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የተሻለ ራዕይ አለን ባዮች፣ ዓለም አቀፍ የሙያ ማህበራትም ሆኑ ለለውጥ እንታገላለን የፖለቲካ ድርጅቶች …ወዘተ ሁሉ አንዱን ከፍ፣ ሌላውን አቃልለው የሚያዩበትን መስፈርት ሊመረምሩ፣ መመዘኛቸውን በእኩልነት ሊቃኙና ሊያገናዝቡ እንደሚገባ የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ደግሜ ደጋግሜ ለማለት የምፈልገው የሚከተለውን ብቻ ነው፡- መድሎ እና ማግለል ይቁም!! አዎ ይቁም!!
ይኸው ነው፡፡ አበቃሁ!!
ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ይህንን ታላቅ ጽሁፍ በማስነበቡ እያመሰገንኩ የሰብዓዊ መብት አድሎ እንደገና እንዳነሳው ተገድጃለሁ። ይህ አድሎ የተጀመረው አሁን አይደለም። ስንብቷል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ በተከታታይ የኢሕአፓ አባል ስለነበሩት ስለነ ጸጋዬ ደብተራው ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። የወቅቱ የጉባዔው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መስፍን ጥያቄውን እንዳልሰሙ በመሆን አልፈውታል። በተደጋጋሚም በአውሮፓና በአሜሪካ ቢጠየቁም አሻፈረኝ በማለት ጥያቄው እንዳይነሳ አድርገውት ነበር። አሁንም በተደጋጋሚ ስለነዚህ ደብዛቸው ስለጠፋ ዜጎች እንዳይጠየቅ የሚፈልጉ ትንሽ አይደሉም። ነጻውም ፕረስ(ይህ በወስንሰገድ ገብረኪዳን ያካትታል) ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች በአድሎ ይህንን የሰብዓዊ መብት ጥያቄ አንስተውት የማያውቁት በደል ሆኗል።
እነ ጸጋዬ ወይም እነ ውብሸት ብቻ አይደሉም የሚታለፉት። ሌሎች በሽህ የሚቆጠሩ በቅንጅት ወቅት የታሰሩ <<የቅንጅት መሪዎች ይፈቱ>> በሚል መፈክር የተወሰነን ክፍል ብቻ መፈታት በሚጠይቅ መፈክር ተሸፍነው ተንገላተዋል። በነገራችን ይህ <<የቅንጅት መሪዎች ይፈቱ>> የሚለው መፈክር የተጭበረበረውን ምርጫም ይሁን የተሰዉትን ወጣቶች ጥያቄ ወደ ጎን አድርጎት ነበር። ይህ ራሱ ለወቅታዊ መፈክር ትኩረት መስጠትን ያመለክታል። መሪዎቹም ከተፈቱ በኋላ ከእርስ በርሱ ትግል ባሻገር ስለነዚህ ሰዎች አላነሱም። አድልዎ አንዱ በነቀዘው ፖለቲካ ውስጥ የምናየው ክስተት ከሆነ ሰንብትዋል። ይህ ጽሁፍ የዚህ በተቃዋሚዎች በኩል የሚደረግ አድልዎ ግፍ ማብቂያ መሆን ይኖርበታል።
የጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ሙሉ ጽሁፍ ከሚከተለው ድረገጽ ላይ እንድታነቡት እየጋበዝኩ ለዛሬ እዚህ ላይ ልቋጭ።

No comments:

Post a Comment