Translate

Saturday, August 4, 2012

አንድ አስተያየት፤ አቶ ጁነዲን ቻል ያድርጉት… ሁሉም የሚታሰረው ያለ ማስረጃ ነው!

Abe Tokchaw

አቶ ጁነዲን ሳዶ ዛሬ ለታተመው ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ የነገሩትን አውራምባ ታይምስ ዌብ ሳት አቀብላን ተመልክተነዋል።
ሚኒስቴር ጁነዲን ሳዶ ባለቤታቸው ከታሰሩባቸው ዛሬ አስራ ስድስተኛ ቀናቸው ነው። በዚህም የተነሳ ቤታቸው መቀዝቀዙን ልጆቻቸው መጎሳቆላቸውን እና የመሳሰሉትን ጠቅሰው እስሩ አግባብ አይደለም ብለው ተናግረዋል።
የሚኒስቴሩ ባለቤት የታሰሩት ከአክራሪነት ጋር በተያያዘ መሆኑን ነገር ግን ምንም ማስረጃ እንዳልተገኘባቸው እና የዚህ አይነቱ እስር ነውር መሆኑን አስረድተውናል።
ጥሩ ነው ለሚስትዎ እርስዎ ካልተከራከሩላቸው ሌላ ማን አላቸው…!? ነገር ግን ኦቦ ጁነዲን፤ ካለ ማስረጃ መታሰር እኛ ሀገር ብርቅ ነው እንዴ!?
አንድ ወዳጄ በዚህ ጉዳይ ላይ ስናወራ ምን አለኝ መሰልዎ፤ በቅርቡ የዋልድባ ገዳም መነኩሴዎችን እና የአንዋር መስጊድ “ኡስታዞችን” እስር አነሳልኝ እና “ተዋርዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ ተዘነጋሽ እንዴ ኢትዮጵያ መሆኑ!” ሲል አንጎራጉሮልኛል።
እናልዎ አቶ ጁነዲን ቃሊቲ አንዳፍታ ሄድ ብለው ማን በምን ታሰረ…? የሚለውን መርመር ቢያደርጉ እውነት እውነት እልዎታለሁ “እስር ቤቱ ባዶ ከሚሆን” ተብለው የታሰሩ በርካታ ሰዎችን ያገኛሉ።
በቅርቡ እንኳ ፍፁም ሰላማዊ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሙስሊም ወዳጆቻችን “አፈሳ” በሚመስል መልኩ ወደ እስር ቤት ተግዘዋል። እነዚህ ወገኖች ለምን እንደታሰሩ ለማወቅ ከፈለጉ ዝም ብለው አንድ አርብ ወደ አንዋር መስጊድ ይሂዱ፤ በዛውም ለባለቤትዎ “ዱዓ” አድርገው ይመለሳሉ። እናልዎ በአንዋር የሚደንቅ አይነት ሰላማዊ የተቃውሞ ትዕይንት ሲደረግ ይመለከታሉ። እንግዲህ ይህንን ሰላማዊ ተቃውሞ ያስተባበሩ ወገኖች በሙሉ ተለቅመው ከታሰሩ ዛሬ ረመዳን አስራ ስድስተኛ ቀናቸው ነው።
እና አቶ ጁነዲን ከተናገሩ አይቀር ባለ ስልጣን ኖትና በርስዎ ያምራል፤ ሁሉም ያለ ምንም ማስረጃ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ይጠይቁ… አለበለዛ ግን የእርስዎ ባለቤት ያለ ማስረጃ መታሰር ብርቅ አይደለምና ቻል ያድርጉት!
አረ ሳልነግርዎ አንድ ወዳጄ ባለቤትዎ መታሰራቸውን ገና ሲሰማ ምን እንዳለ ሰምተዋል…? ከሰሙም ይድገሙት ካልሰሙም እንሆ፤ “ባለቤቱን ካልናቁ ሚስቱን አይነቀንቁ!”
http://www.abetokichaw.com/2012/08/04

No comments:

Post a Comment