Translate

Thursday, August 16, 2012

ወያኔ ለግድያ ቢዘጋጅም ሕዝብ ደግም ወያኔን ለማስወገድ ተነስቷል!!!



ግፈኛው እና ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ፣ ሠራዊቱ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል።  በዚህ መሠረት የጦሩ የምድርና የአየር ኃይላት በአንደኛ ደረጃ ተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። የመከላከያ ሚኒስቴር እና በተዋረድ ያሉ የሠራዊቱ መዋቅሮች፤ የዘመቻ እና የድርጅት መምሪያዎች እንዲሁም ከፍተኛና መስመራዊ መኮንኖች በተጠንቀቅ ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ለጦር መሣሪያ እና ለጥይት ማከማቻ ዲፖዎችም የሚደረገው ጥበቃ ተጠናክሯል። ወያኔ ለታላቅ ጦርነት እየተዘጋጀ ነው።

ይህ ሁሉ ለምን አሁን ሆነ? ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?  ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው።
1ኛ.      በወያኔ አገዛዝ ላይ የሚቀርበው ሕዝባዊ ተቃውሞ  እየበረከተ  መምጣቱ፤ እና
2ኛ.      መለስ ዜናዊን ለመተካት የሚደረገው ሽኩታ ወደ ጉልበት ያመራ ይሆናል የሚለው ስጋት ማየሉ ናቸው።
እንደሚታወቀው በወያኔ አገዛዝ ላይ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከእለት እለት ሥር እየሰደደና እየዳበረ ዛሬ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህ ረገድ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሚያደረገው ተጋድሎ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።  የሙስሊሞች ጥያቄ አሁን የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጥያቄ ሆኗል። በየመስጊዶቹ እየጎመሩ ያሉት እቅስቃሴዎች ወደ አደባባይ መውጫቸው ተቃርቧል። ሚያዝያ 30 ቀን 1997ን የሚያስታውሱን ታላላቅ ሕዝባዊ ሰልፎች የምናይበት ጊዜ እየቀረበ ነው።  መንገዶች ሁሉ ወደ መስቀል አደባባይ እያመሩ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ እንደ ፈጣሪው የሚያመልከውን መለስ ዜናዊን አጥቶ ለሁኔታዎች ሁሉ ባይተዋር ሆኗል። መለስ በሃያ አንድ ዓመታት የሥልጣን ጊዜው ከሠራቸው ነገሮች አንዱ ራሱን አይነኬ እና አይተኬ ማድረግ ነበር። የመለስ ዜናዊ አይነኬነት ቀረ። አይተኬነቱ ግን አሁንም አለ።
የመለስ ዜናዊ አይተኬነት የወያኔ ሹማምንትን በሙሉ ዋጋ ቢስ አድርጎ  ተተኪ አሳጥቶ ጭንቀት ውስጥ ጨምሯቸዋል። “እንኳንስ ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ” እንዲሉ እንኳንስ በእንዲህ ዓይነት የውጥረት ወቅት ይቅርና ለትንሹም ኮሽታ የወያኔ ሹማምንት በጠመንጃ ጀርባ የመደበቅ ልማድ አላቸው። የአሁን ነጋሪ ጉሰማም የዚህ ጭንቀት ውጤት ነው።
ይሁን እንጂ ወያኔ በጠመንጃ የሚድንበት ወቅት አልፏል። ይህ ማለት ግን ለመግደል፣ ለማሰርና ለማንገላታት አይሞክርም ማለት አይደለም። የፈለገውን ቢያደርግ እንኳን ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ የፈሪ ዱላ አይደነግጥም። እንዲያውም የወያኔ ዛቻ እና ማስፈራራት በቀጠለ መጠን ተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን ትግሉን  ይቀላቀላሉ።
ዛሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል የቆረጡ ኃይሎች አሉ። የእነዚህ ኃይሎች ጉልበት በየእለቱ እየተጠናከረ ነው። እነዚህን ኃይሎች የሚቀላቀል አዲስና ትኩስ ኃይል ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ ነው።
ወያኔ ሠራዊቴ የሚለው አካልም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ሊሆን አይችልም ። ለዚህም   ምልክቶች እየታዩ  ነው።  የኢትዮጵያ የመከላከያ፣ የፖሊስና የደህንነት ኃይል አባላት ሠራዊቱ በጥቂት የወያኔ ከፍተኛ መኮንኖች አማካይነት የማፈኛና የመጨቆኛ መሳሪያ መሆን እንደሌለበት በማመን በቆራጥነት እና በኢትዮጵያዊነት ወኔ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መሰለፋቸው በቅርቡ በህቡዕ የተቋቋመው ነፃ የኢትዮጵያ ሠራዊት ንቅናቄ (ነኢሠን) አብስሯል።  ነኢሠን በመግለጫው እንደገለፀው ሁሉ የኢትዮጵያ መለዮ ለባሾች ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የቆሙ ኃይሎችን አይወጉም። የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች አባላት የዚህ ዘረኛ አስከፊ ከፋፋይና በዝባዥ መንግስት መሳሪያ አይሆኑም።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወቅታዊ የአገራችን ሁኔታዎች በመገምገም የሚከተሉትን ጥሪዎች ያደርጋል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ
የተጀመረው ትግል መፋፋም ይኖርበታል። የሙስሊሞች ጥያቄዎች የክርስቲያኖች፤ የክርስቲያኖችም የሙስሊሞች ነው። ስለዚህ  በሃይማኖትም  መከፋፈል ትተን ድምጾቻችንን በጋራ ማስማት መቀጠል ይኖርብናል። ወደ አደባባዮችና ስታዴሞች በብዛት መትመም ይኖርብናል። የትግላችን ዓላማም ወያኔን ማስወገድ መሆን ይኖርበታል።
ለመከላከያ ሠራዊት
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት መኮንኖች፣ ነፃ የኢትዮጵያ ሠራዊት ንቅናቄ (ነኢሠን)በህቡዕ በመመሥረታቸው የተሰማውን ደስታ ይገልፃል። በሠራዊቱ ውስጥ ያላችሁ ሌሎች መኮንኖች እና ወታደሮች የነኢሠን አርዓያነት እንዲከተሉ ያበረታታል። የሠራዊቱ አባላት “የመሣርያችሁ አፈሙዝ ወደ ወያኔ ይዙር!” ይላል።
ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንዳነሳው ግንቦት 7 ዛሬም ትኩረታችን ያለው ወያኔን በማስገደድ ስልጣን እንዲለቅ ማድረግ፤ ያ ካልሆነ ደግሞ  ማስወገድ ላይ መሆን ይኖርበታል ብሎ  ከልብ ያምናል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለመብት ለነፃነትና ለእኩልነት የሚደረገው ትግል ግቡን የሚመታው።
ግንቦት 7  ለዚህ ዓላማ ቆርጦ ተነስቷል።  በደል ግፍ የበዛበት፣ በእብሪተኛ ዘረኛ ሥርዓት ውስጥ መከራውን እንዲያ የተደረገው የአትዮጵያ ሕዝብም ለዚህ ዓላማ ቆርጦ እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!



No comments:

Post a Comment