Translate

Friday, August 17, 2012

የፓትርያርክ ጳውሎስ ገመና ፣ በደሎች ፣ መታሰቢያና ውርሶች


አዲሱ ተስፋዬ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን እስካሁን አምስት ኢትዮጵያውያን ፓትርያርኮች ተሹመው አልፈዋል:: ፓትርያርኮቹ የሚታወሱበት የተለያየ ባህርይና መታወሻan article about Abune paulos EGYPT ETHIOPIA AFRICAN UNION SIDELINESነበሯቸው:: ሰኔ 21, 1951 አ.ም የተሾሙት የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ እጅግ ሲበዛ ሊቅ እንደነበሩ ታሪክ ያስታውሰናል [1] :: ቤተ ክርስትያኒቱ የራስዋን ልጆች ፓትርያርክ አድርጋ እንድትሾም ፣ ከፍተኛ ተጋድሎ አካሂደው ቤተክርስትያኗ ነጻነት እንድታገኝ አድርገዋል[2] :: ህዝበ ክርስትያኑም ክርስትናውን እንዲያጸና ብዙ ታግለዋል :: ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም የሳቸው ውጥን ነው [3] ::
እሳቸው ሲያርፉ የተሾሙት ሁለተኛው ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስም የሳቸውን መስመር ተከትለው ለቤተክርስትያኒቱ ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክተዋል [4] :: በተለይም ኢኮኖሚም የዳበረ አቅም እንዲኖራት በርካታ መሰረተ ልማቶችን አስገንብተዋል :: “እግዚአብሄር የለም” የሚለውንም የግፈኛው ደርግን አውራዎች በመቃወም ሰማእትነትን ተቀብለዋል [5]:: ሶስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለእግራቸው እንክዋን ጫማ ለማጥለቅ የሚለመኑ ፣ በጾም ብዛት እንዳይሞቱ የሚሰጋላቸው ፣ አለምን ከነምኞቱ የሰቀሉ እውነተኛ መናኝና የእግዚአብሄር ሰው ነበሩ [6]:: በወቅቱ የነበረው የኢሰፓ መንግስት አዲስ አበባ የሚገኘውን አንድ ቤተ ክርስትያን “ዘግቼ ሙዚየም አደርገዋለሁ ” ብሎ ሲነሳ ” ሬሳዬን ተራምደህ ” በማለት የቤተክርስትያን የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ያስመሰከሩ ትልቅ የእምነት አባት ነበሩ:: አራተኛው ፓትርያርክ መርቆሬዎስ አገር ለቀው እስካሁን በምድረ አሜሪካን ናቸው:: እሳቸው “ከመንበሬ በግፍ ተሰድጄ ነው የ ወጣሁት” ቢሉም ፤ በርካቶች ግን “መንበራቸው ላይ እስከመጨረሻው ጸንተው የሚመጣውን በመቀበል ታሪክ ፣ ቤተ ክርስትያንና ህዝብ እንዲያስታውሳቸው ቢሆኑ ይመረጥ ነበር“ ብለው ይነቅፉቸዋል:: እጅግ አወዛጋቢ የነበሩት አምስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስም ትናንት ነሀሴ 10/ 2004 አመተ ምህረት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል[7]::
ህልፈታቸውን አስቀድመው የተረዱ የሚመስሉት ፓትርያርክ ጳውሎስ ፤ የዘንድሮውን በአለ ሲመታቸውን( የሹመት በአላቸውን) ያከበሩት በከባድ ዝግጅት ነበር :: በአለ ሲመታቸው ሐምሌ 5/2004  በመጀመርያ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በከፍተኛ ሸብ እረብ የተከበረ ሲሆን ፣ ሐምሌ 16/2004 ደግሞ በሼራተን ሆቴል ድል ባለ ድግስ ተከብሯል :: [8] ቅጥ ያጣውን ድግስ የታዘቡ ወገኖች ” የቁም ተዝካር ” ብለው ተቃውሞ ቢያሰሙም ፣ ያላአግባብ የሚባክነውን ገንዘብና ሀብት ቢቃወሙም ፣ ድግሱ ለሶስተኛ ግዜ በክራውን ሆቴል ተደግሞአል:: በነዚህም ድግሶች ላይ ፓትርያርኩ 20 አመት ሙሉ ያከናውኗቸውን ” የፓትርያርኩን ሀያ ውጤታማ አምታት ስራዎች” የሚዘርዝር ዜና መዋእል አስጽፈውም ለታዳሚዎች ተበትኗል:: ፓትርያክ ጳውሎስ ግን ፣ እውን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ባለውለታ ነበሩን? በምን በምንስ ይታሰባሉ? What was the legacy of patriarch Paulos ?
መንፈሳዊ አምባገነንነት
ፓትርያርክ ጳውሎስ ከሹመታቸው ማግስት ጀምሮ የመጀመርያ ስራቸው የነበረው የቤተክርስትያኒቱን ስልጣን በሙሉ በሳቸው ቁጥጥር ውስጥ ማድረግ ነበር:: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የጥንት ትውፊትና ልማድ መሰረት የቤተ ክርስትያኗ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳይ ሀላፊዎች የተለያዩ ነበሩ:: መንፈሳዊው ጉዳይ የሊቃነ ጳጳሳቱና የፓትርያርኩ ሲሆን አስተዳደሩ ደግሞ የሚካሄደው በተክለሃይማኖት መንበር ላይ በተሾሙት እጨጌ ነበር:: [9]( በጥንቱ ልማድ የቤተመንግስቱ ሀላፊ አጼጌ ፣ አጼ ሲባል የቤተ ክህነቱ አስተዳደራዊ ሀላፊ ደግሞ እጨጌ ይባል ነበር) :: አባ ጳውሎስ ግን ይህ አስተዳደራዊ ማእረግ የፓትርያርኩ እንዲሆን ካደረጉ በሗላ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሀይማኖት ተባሉ :: በመቀጠልም የአክሱምን ሊቀ ጵጵስና ለብቻው ለይተው “ሊቀጳጳስ ዘአክሱም”  የሚለውን ደረቡ [10]:: “በመሰረቱ ፓትርያርኩ – ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ( የሊቀ ጳጳሳቱ ሁሉ የበላይ) ሆነው ሳለ እንደገና ወደታች ወርደው የአክሱምን ሊቀ ጳጳስትነት ለምን ፈለጉት?”  የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን ግራ ቢያጋባም መሰረቱ ግን ፖለቲካዊ መሰረት የያዘ እንደነበረ ፣ተንታኞች ምክንያቱን እንዲህ ይገልጻሉ:: “ያ ትውልድ ” እየተባለ በሚነገርለት የ1950ውና 1960ው ትውልድ “ ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ያላት ሀገር እንጂ ጥንታዊ ሀገር አልነበረችም” የሚል አስተሳሰብ ይዘው በተነሱ ግራ ዘመሞች የተወጋ ነበር:: በነዚህ ግራ ዘመም ሀይሎች እይታ የአክሱም ስልጣኔ አክሱምን ብቻ እንጂ ሌላውን ኢትዮጵያ የሚመለከት አይደለም:: በነሱ ፓለቲካዊ እይታ ፣  አክሱም ላይ ተሹመው የነበሩት የመጀመርያው ያገራችን ጳጳስ አቡነ ፍሬምናጦስም የአክሱም ሊቀጳጳስ እንጂ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አልነበሩም:: ስለዚህ የአክሱም ሊቀ ጵጵስና ከሌላው የተለየ እንደሆነ ፣ በዚያን ዘመንም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዳልነበረች የማያሳምን ታሪክ ይዘው ይሞግታሉ :: የዛ ትውልድ አካል የሆኑት የኢትዮጵያው ፓትርያርክ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ የአክሱምን ሊቀ ጵጵስና ለብቻ ለይተው ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም የሚለውን ማእረግ መጠርያቸው ያደረጉት ምክያቱ ያ ከሆነም ወደፊት ታሪክ የሚያየው ይሆናል:: የአባ ጳውሎስ የስልጣን ጉዞ ግን በዚህ አልተገታም:: ሁለት ሺህ ዘመን ባስቆጠረው የቤተ ክርስትያኒቷ ትውፊትና ህግ መሰረት “የሲኖዶሱ የበላይ መንፈስ ቅዱስ ነው ” [11] የሚል ሐዋርያዊ ህግ ቢኖርም አባ ጳውሎስ “የቅዱስ ሲኖዶሱ የበላይ እኔ ፓትርያርኩ ነኝ” የሚል አዲስ ማሻሻያ ይዘው ብቅ አሉ:: በዚህ ወቅት ግን በርካቶች የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ጳጳሳት ዝም ብለው አላዩአቸውም [12]:: ይልቁንም የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ ታዋቂው ምሁር አለቃ አያሌው ታምሩና ሌሎች የቤተክርስትያኒቱ ሊቃውንት ባቀረቡት የመረረ ተቃውሞ ይህ ህግ ሳይጽድቅ ቀረ:: የሚሊኒየሙ በኣልም ሲከበር አባ ጳውሎስ ” የሚሊኒየሙ አባት” የሚለው ማእረግ እንዲደረብላቸው ተደርጓል[13]:: አሁን በቅርቡ ደግሞ “አለም አቀፍ የሰላም አምባሳደር” የሚለው ማእረግና ስያሜ ተመርቆላቸዋል[14]:: አሁን ያለውን የሳቸውን የስም ማእረግ ለመጻፍ ፣ ራሱን የቻለ ገጽ ሳያስፈልገው አልቀረም::
የተከፈለውና የተደፈረው ሲኖዶስ
አባ ጳውሎስ ሌላው የሚታወሱበት አብይት ጉዳይ በሳቸው ዘመንና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሳቸው ምክንያት የተከፈለው የቤተ ክርስትያኒቱ ሲኖዶስ ነው:: በኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሁለት ሺህ አመት ታሪክ ውስጥ የቤተ ክርስትያኒቱ ሲኖዶስ ሲከፈል ይህ የመጀመርያው ነው:: ዛሬ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ቤተ ክርስትያኒቱ ባለ ሁለት ሲኖዶስ ሆናለች:: በሀገር ውስጥ አባ ጳውሎስ የሚመሩት ሲኖዶስና ፣ በውጭ ደግሞ አባ መርቆርዮስ የሚመሩት ሲኖዶስ[15]:: በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም ሲኖዶሶች ተወጋግዘዋል[16]:: ይሄ ክፍፍልና ብጥብጥ ግን በዚህ አላቆመም:: አባ ጳውሎስ የሚመሩት ያዲስ አበባው ሲኖዶስም ያለመግባባቱ ከባድ ደረጃ ላይ ደርሶ አባ ጳውሎስን የተቃወሙ ጳጳሳት ቤታቸው ተሰብሯል[17]:: እነሱም ተደፍረዋል:: ጉዳዩ ግን በዚህ አላበቃም:: ፓትርያርክ ጳውሎስ ስራተ ቤተ ክርስትያንን በጣሰ ሁኔታ ያስገነቡትን የራሳቸውን ሀውልት እንዲያስነሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቢወስንባቸውም “እምቢኝ” በማለት ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ያላቸውን ንቅት በማሳየት አምባገንንተቻውን በግልጽ አሳይተዋል[18]:: በዚህም ለሲኖዶስ ውሳኔ ባለመገዛት የመጀመርያው ፓትርያርክ ሆነዋል::
የገዳማቱና አድባራቱ በደል
በአባ ጳውሎስ ሃያ የፕትርክና አመታት ክፉኛ ከተጎዱት የቤተክርስትያን ተቋማት አንዱ ፣ የኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው:: ትልልቅ የሚባሉት ገዳማት ፣ ተመልካችና ረዳት አጥተው ህልውናቸው አጠያያቂ የሆነው በሳቸው ዘመን ነው:: ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ይዞታ የነበረው በኢየሩሳሌም የሚገኘው የኢትዮጵያ ገዳም – ዴር ሱልጣን-  በኮፕቶች ያላሰለሰ ተንኮል የኢትዮጵያ ባላቤትነት ተሸርሽሯል:: በየሩሳሌም ያሉት መነኮሳት የተቻላቸውን ትግል ቢያደርጉም ካባ ጳውሎስ አሰተዳደር የተሰጣቸው ትኩረትና ድጋፍ ግን የወረደ በመሆኑ በተደጋጋሚ ለህዝቡ የደረሱልን ጥሪ ሲያሰሙ ነበር [19]:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ትላልቅ ገዳማትም የደረሰባቸው እጣ ተመሳሳይ ነው:: በቅርቡ እንዃን ታላቁ የዋድልድባ ገዳም ሲታረስ መነኮሳቱ ” ገዳማችን ታረሰ ” ብለው ላቀረቡት የድረሱልን ጥሪ ያቡነ ጳውሎስ አስተዳደር የሰጠው መልስ አጅግ አስገራሚ ነበር:: ምንም አንኳን የስኳር ፕሮጀክቱ የጋድሙን መሬት እስከ 16 ኪሎ ሜትር ዘልቆ ግበቶ ገዳሙን እንደሚያውከው የተለያዩ ጥናቶች ( በተለየ የማህበረ ቅዱሳን ሪፖርት [20]) በገልጽ ቢያስቀምጠውም ፣ ያባ ጳውሎስ አመራር ጉዳዩን በቸልታ በመመልከት ገዳሙን አሳልፎ በመስጠት መተባበሩን የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው:: በዚህ አመት ብቻ አራት ታላላቅ የቤተ ክርስትያኒቱ ገዳማት ላይ እሳት መነሳቱ ተዘግቧል:: አሰቦት ላይ በዚህ አመት እሳቱ የተነሳው አራት ግዜ ሲሆን ዝቋላ ሁለት ግዜ ነዷል [21]:; ጎንደር ውስጥም ብቸኛው የመጽሀፈ መነኮሳት የትርጉም ትምህርት ቤት ነዷል:: የቤተክርስትያኒቱ መሰረት የሆኑት ገዳማት መቃጠላቸው ያስቆጫቸው፤ በየገዳሙ ያሉትን የመንኮሳት ጥሪ መሰረት አድርገው ፣ በከፍተኛ መንፈሳው ቅናት እሳቱን ለማጥፋት እየተቃጠሉ ወዳሉት ገዳማት የተመሙትም ምእመናን አባ ጳውሎስ ከሚመሩት ቤተ ክህነት የተሰጣቸው መግለጫ እጅግ አሳዛኝ ነበር:: ገዳምትን ብቻ እየመረጠ የሚያቃጥል እሳት ምክንያቱ እንዲጣራ ምእመናኑ ላቀረቡት ጥያቄ ፣ ያባ ጳውሎስ አስተዳደር የሰጠው መልስ ይሄንን ነበር –” እሳት በመንደርም ይነሳል:: በገዳማት ቢነሳ ምን ያስደንቃል:: ይህንን የምታራግቡት ለራሳችሁ የፖለቲካ ፍጆታ ነው::” [22]በማለት እጅግ የሚገርም መልስ በመስጥት ለገዳማቱ ያላቸውን መቆርቆር አሳይተውናል:: በያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስትያን የሚይታየውም የቤተ ክርስትያንን መብትና ህልውና አሳልፎ የመስጠት ነገር ተነግሮ አያልቅም:: ለዚህም ጥሩ አብነት የሚሆነው የደብረዘይቱ ምስራቀ ጸሀይ ባቦጋያ መድሀኔአለም ቤተ ክርስታያን አንዱ ነው:: ለረጅም ዘመናት የቤተክርስታይኑ የጥምቀተ ባህር ቦታ የነበረው የቤተክርስትቲያኑን የጥምቀተ ባህር ማክበርያ ቦታ ፣ በኮሬፍቱ ሪዞርት ባላቤት ሲወሰድ፣ ምእመናን ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው ነበር:: አስገራሚ በሆነ  መልኩ የአባ ጳውሎስ ቤተ ክህነት ተወካይ ያደረገው ነገር ግን ፤ ባህረ ጥምቀቱ ላይ የነበረውን መስቀል በመቁረጥ ቦታውን ለሆቴሉ አሳልፎ በመስጠት ምእመናኑን አንገት ማስደፋትና እምቢ ያሉትንም በፍርድ ቤት በሀሰት ከሶ ማሳሰር ነበር [23]:: ይሄ የሆነው እዛው ካዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር የምትገኘው ደብረ ዘይት ላይ ነው:: በየዳር አገሩ በመናፍቃንና በአክራሪዎች ቤተ ክርስትያን እንደ ችቦ ስትጋይ ፣ ምእመናን ሲታረዱ ያባ ጳውሎስ ቤተ ክህነት አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታ ከማለፍ ውጭ ያደረገው ነገር እንደሌለ ጸሀይ የሞቀው እውነት ነው::
የምእመናን ጠባቂ ማጣትና ውጤቱ
ፓትርያርክ ጳውሎስ ስልጣን ሲይዙ የኢትዮጵያ ህዝብ 50% እና በላይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበር[24]:: የ1987 የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሹ የተዋህዶ እምነት ተክታይ ነበር:: የቅርቡ ህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት እንደሚያሳየው የኦርቶዶክስ እምነት ተክታይ ከ50% ወደ 43.5 % ወርዷል[25]:: ይህ በቁጥር ሲሰላ ደግሞ እጅግ በዙ ሚሊዮን ነው:: ቤተ ክርስትያኒቱ ይህን ሁሉ ህዝብ ያጣችበት ዋናው ምክንያት ያባ ጳውሎአ አስታዳደር ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ሌሎች ነገሮች ላይ በማትኮሩና ምእመናኑም እረኛ በማጣታቸው ነው:: ፓትርያርክ ጳውሎስ የሚታወቁትና የሚታወሱት ትልልቅ የስብከተወንጌል መርሀግብሮችን አዘጋጅተው በመክፈት ሳይሆን እጅግ በሚገርም ሁኔታ እንደ ቢዮንሴ ያሉ ዘፋኞችን በመቀበል ነው:: አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የቦብ ማርሊ የልደት በአል ለማክበር የተዘጋጀውንም የዘፈን ድግስ በጸሎት በመክፈት የእምነቱን ተከታዮች ክፉኛ ማሸማቀቃቸውና ማሳፈራቸውም የቅርብ ሩቅ ትዝታ ነው::
ሲጠቃለል
አምስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ጳውሎስ ከሚታወሱብት በጎ ነገር ፣ የሚወቀሱበት ክፉ ነገር የበዛና ቤተ ክርስትያኗን ለከፋ አደጋና ጉስቁልና አሳልፈው የሰጡ አባት ነበሩ:: በኢትዮጵያ ታሪክ የገማ እንቁላልና የሰበሰ ቲማቲም የተወረወረባቸው ብቸኛ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ናቸው:: እንደሳቸውም ከምእመንና ካህናት ተቃውሞ የገጠመው ፓትርያርክ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም:: የፓትርያርክ ጠባቂዎች ቤተ ክርስትያን አውደ ምህረት ላይ ባህታዊ ተኩሰው የገደሉት በአባ ጳውሎስ ዘመን ነው:: ሰላምን ፈልገው ቤተ ክርስትያን ተጠልለው የነበሩ ተማሪዎችንም አሳልፎ በመስጠት አባ ጳውሎስ ይወቀሳሉ:: ከሊቃውንቱም ጋር በነበራቸው ጸብ በሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን የተወገዙ ብቸኛው ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ ናቸው:: አለቃ አያሌው ገዝተውና አውግዘዋቸው እንዳለፉ ይታወሳል:: ቤተ ክርስትያኗም ለሶስት የተከፈለችው( ያዲስ አበባ ሲኖዶስ የውጭ ሲኖዶስ እና ገለልተኛ) በሳቸው ምክንያት ነው:: ተሐድሶ በማለት ቤተክርስትያኒቱን ሊያፈራርስ የተነሳው ሀይልም ቤተ ክርስትኒቷን እንዲህ እያወካት ያለው በሳቸውና አማካሪዎቻቸው ለፈስፋሳ አቛም ምክንያት ነው:: ለብዙ ሺህ አመት የቆየውም የጳጳሳት አለባበስ ከጥቁር ወደ ነጭ የተቀየረውም በሳቸው ዘመን ነው:: በታሪካችን ለመጀመርያ ግዜ ሀውልት ለራሳቸው ያሰሩ ፓትርያርክም እሳቸው ብቻ ናቸው[26]:: ሌላም ሌላም ሌላም
ቢሆንም ግን አባ ጳውሎስ የሚመሰገኑበትም ጉዳይ አለ:: “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅባት”  የሚል አዲስ ድርጅት ፈጥረው ቤተ ክርስትያኒቱን ለሁለት ሊሰነጥቁ የነበሩትን የቅባቶች የቅርብ ግዜ እንቅስቃሴ በመግታት ቤተክርስትያኒቱን ከመከፈል ማዳናቸው ሁሌም ሲያስመሰግናቸው ይኖራል:: ግዜው ካለፈ በኋላም ቢሆን “የተሀድሶ መነኮሳት ህብረት” በማለት የቤተክርስትያኒቷን አስተምህሮ ለመናድ በተነሱ መናፍቃን ላይም የወሰዱት የማውገዝ እርምጃ ቤተ ክርስትያኒቷን ከጥፋት አድኗልና ይታወሱበታል:: ለቤተ ክርስትያን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እንደ ማህበረ ቅዱሳን ፣ ማህበረ በአለ ወልድ፣ ጽርሀ ጽዮንና የመሳሰሉ ማህበራትን ፈቃድ ያገኙትና እንዲሰሩም የተፈቀደላቸው በሳቸው ዘመንና በጎ ፈቃድ በመሆኑ ምስጋና ይግባቸው::ያሰሩት የመንበረ ፓትርያርክ ህንጻና አሁንም አስጀምረውት የሄዱት የአክሱም ሙዚየም ለቤተክርስትያን ቅርሶች ናቸውና በዚህ በጎ ስራቸውም ይታወሳሉ::በቅርቡ ቤተክርስቲያኒቷ ያሳተመችው ሰማንያ አሀዱ ቤተክርስትያንም በሳቸው ዘመን የሆነ ነውና ይህን በማድረጋቸው የቤተ ክርስታያን ታሪክ ያስታውሳቸዋል::
ግን በአባ ጳውሎስ ምክንያት የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ላይ የደረሰው ጠባሳና ቁስል በቀላሉ የሚጠገን አይደለም:: የተሰበረውን የሚጠግኑ ፣ የቆሰለውን የሚያክሙ መንፈሳዊ አባት እግዚአብሄር ለቤተ ክርስትያናችን ይሰጠን ዘንድ የተዋህዶ ምእመናን ሁላችንም ካሁኑ እንጸልይ:: የቤተ ክርስትያን አምላክ ቸሩ እግዚአብሄር የቤተክርስትያናችንን ትንሳኤ ያሳየን::
አባ ጳውሎስም ወደ እውነተኛው ቦታ ሄደዋል:: ፍርዳቸውንም ሁሉን ከሚያይ ከእውነተኛው ፈራጅ ከቅዱስ እግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላሉ:: ነብሳቸውን ይማር!!!
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!
ዋቤ መጻሕፍት

1 ዜና ባስሌዎስ ሊቀጳጳሳት :: ሰኔ 10/ 1951:: ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተምያ ቤት
[2] ዜና ባስሌዎስ ሊቀጳጳሳት :: ሰኔ 10/ 1951:: ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተምያ ቤት
[3] የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን የመጀመርያው ፓትርያርክ :: አዲስ አበባ 1956::ብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ
ማተምያ ቤት ::
[4] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 አ.ም :: አዲስ አበባ 2000
አ.ም::
[5] http://www.dacb.org/stories/ethiopia/tewoflos2.html
[6] የሶስተኛው ፓትርያርክ በኣለ ሲመት:: ነሀሴ 23/ 1968:: ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተምያ ቤት
[7] http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-19285459
[8] http://www.dejeselam.org/2012/07/blog-post_26.html
[9] የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን የመጀመርያው ፓትርያርክ :: አዲስ አበባ 1956::ብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ
ማተምያ ቤት ::

[10] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 አ.ም :: አዲስ አበባ 2000
አ.ም::
[11] ፍትሐ ነገስት :: 1978 :: አዲስ አበባ::
[12] http://www.aleqayalewtamiru.org/
[13] http://www.aleqayalewtamiru.org/
[14] http://www.dejeselam.org/2012/07/blog-post_29.html
[15]www.eotcdc.org/documents/Wegezet.pdf
[16]www.eotcdc.org/documents/Wegezet.pdf
[17] http://www.dejeselam.org/2009/07/blog-post_16.html
[18] http://www.youtube.com/watch?v=mpzFq0gmX0Y
[20] http://eotcmk.org/site/images/stories/pdfs/MK_Walideba_Final_Report1.pdf
[21] http://www.youtube.com/watch?feature=player_embedded&v=oGieo5lQd3s
[22] http://www.dejeselam.org/2012/03/blog-post_3709.html
[23] http://andadirgen.blogspot.com/2012/06/13.html
[24] http://www.google.com/hostednews/afp/article/ALeqM5i-WtiPcdGx83wuVl-kZ8ZT8tQGRg
[25] http://www.google.com/hostednews/afp/article/ALeqM5i-WtiPcdGx83wuVl-kZ8ZT8tQGRg
[26] http://www.dejeselam.org/2010/07/500.html
http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/3881

No comments:

Post a Comment