Translate

Tuesday, August 14, 2012

አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር 16 በመቶ ጨመረ


ኢሳት ዜና:-ግብርና ሚኒስቴር እና የውጭ ለጋሾች ትናንት በጋራ ያቀረቡት ሰነድ እንደሚያሳየው ከሀምሌ እስከ ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን 200 ሺ ወደ 3 ሚሊዮን 700 ሺ ከፍ ብሎአል። ለእነዚህ ተረጅዎች ከ189 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ3 ቢሊዮን 4 መቶ ሚሊዮን በላይ ብር እንደሚያስፈልግ ታውቛል።

41 በመቶ የሚሆኑት ተረጅዎች በሶማሊ፣ 27 በመቶ በኦሮሚያ፣ 10 በመቶ በትግራይ፣ 8 በመቶ በአማራና በደቡብ፣ እንዲሁም 4 በመቶ በአፋር ክልል ይገኛሉ።
በአጠቃላይ 193 ሺ 866 ሜትሪክ ቶን ምግብ እንደሚያስፈልግ በሰነዱ ተመልክቷል።
ይህ አሀዝ በአለም ባንክና በሌሎች የምእራብ አገራት ምግብ ለስራ በሚል መርሀ ግብር የታቀፉትን 8 ሚሊዮን ተረጅዎች አይጨምርም። የእነዚህ ተረጅዎች ቁጥር በተረጅዎች ቁጥር ውስጥ ሲገባ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ16 በመቶ ያላነሰው በውጭ በሚሰጥ ምጽዋት የሚኖር ነው።
የግብርና ሚኒስቴር በሚቀጥሉት ሶስት አመታት በምግብ ራሳችንን እንችላለን ብለው ከትናንት በስቲያ መናገራቸው ይታወሳል። ይሁን እንጅ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በምግብ ራሱዋን ለመቻል በርካታ አመታት ትጠብቃለች።
ኢትዮጵያን ላለፉት 21 አመታት የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ ከ15 አመታት በፊት በምግብ ራሳችንን እንደምንችል መናገራቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment