Translate

Wednesday, April 24, 2013

የህወሀት ደህንነቶችን ጤና የነሳው የፌስቡክ ጦማር



Ethiopian blogger Abraha Desta from Tigry, Mekeleበህወሀት/ኢህአዴግ ውስጥ መግባባት ጠፍቷል፣ የወያኔ ቁንጮዎች ወዴት እንደሚሄዱ አያውቁም። እንደው በደፈናው “የመለስ ዜናዊ ራዕይ” ይበሉ እንጂ ራዕዩን እነርሱም አያውቁትም። ካድሬውም ሹማምንቱም እርስ በርስ ተናንቋል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ሁኔታቸውን ህዝብ እንዳያውቅባቸው እያደረጉ ያሉት ጥረት እምብዛም የሰራ አይመስልም። የሙስሊሞች ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው፣ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ግፍ ህዝቡን ከዳር እስከዳር አስተባብሯል/ቀስቅሷል፣ ምርጫውን ምርጫ ለማስመሰል ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፣ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ አለማቀፉ ማህበረሰብ እና ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል። ለዚህም ይመስላል የወያኔ የደህንነት ሹሞች የሀሰት ዜናዎችን በፌስቡክ እያሰራጩ ፋታ ለማግኘት የሚጣጣሩት። ከዚህ በታች አብረሃ ደስታ ከመቀሌ በፌስቡክ የለቀቀውን ጦማር፣ የህወሃት/ኢህአዴግን ወቅታዊ አቋቋም እንደወረደ አቅርበነዋል።

በህወሓት የጉባኤ ኣጀንዳ ዙርያ ስብሰባ ሊጠራ ነው

አብረሃ ደስታ፣ ከመቀሌ
ከኢህኣዴግ ጉባኤ በኋላ መሪዎቻችን (ከበፊቱ ብሶባቸው) መግባባት ኣቅቷቸዋል። በፌደራል ደረጃ የሚደረጉ ስብሰባዎች ያለ ዉጤት ይጠናቀቃሉ። ለምን ኣይግባቡም? (‘ቀሽም ጥያቄ’)። የሚያግባባ ነጥብ የላቸውማ። ድሮ (ከ‘ባለራእዩ መሪ’ ዕረፍት በፊት) ሁሉም ነገር እሳቸው ይሰሩት ስለነበር) በመሪያቸው ነበር ‘የሚግባቡት’ (አብረው የሚጓዙ)። በሰው ‘ይግባባሉ’ (ሌላ ሊያግባባቸው የሚችል ሓሳብ ወይ መርህ አልነበራቸውም፣ የላቸውም)። አሁን ታድያ እንዴት ይግባቡ?
‘ባለራእዩ’ ሰውዬ መመርያ ይሰጣል፣ ‘ፖሊሲ ነው ተግብሩት’ ይላቸዋል፣ እነሱም እሱ የተናገረውን ‘ቃል’ እየደገሙ (ከላይ እስከ ታች) ይዘምራሉ። ስሕተት መሆኑ (ሊተገበር የማይችል መሆኑ) ሲረዱ ‘ስሕተቱ ያለው አፈፃፀም ላይ ነው’ ብለው ራሳቸው ያፅናናሉ። ህዝቡ በማይፈፀሙ ፖሊሲዎች ተስፋ እንዳይቆርጥ መሪዎቻችን ሁሌ ስለ አዲስ ፖሊሲ ወይ አሰራር ይሰብካሉ። ሁሌ ስለ ‘አዲስ ኣሰራር’ ወይ ዕቅድ ሲወራልን ለውጥ የመጣ ያህል እንዲሰማን ለማድረግ ያህል ነው።
አሁን ሰውየው ‘አርፈዋል’። ለተከታዮቻቸው የተውት መርህ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አቅጣጫ የለም። የኢህኣዴግ ካድሬዎች ታድያ አሁን የሚግባቡበት ቋንቋ የላቸውም። የኣምስት አመቱ ‘የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን አቅድ’ ይዘት ወይ መሰረታዊ ፅንሰ ሓሳብ ምን እንደሆነ የሚያውቀው የለም። በዚህ ጉዳይ ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ ያለ ዉጤት ተበትነዋል። (ዕቅዱ ግን ድሮውም ቢሆን ምንም የሚጨበጥ ሓሳብ አልነበረውም ….. የሚሰማን አጣን እንጂ)። ዕቅዱ ‘Ambitious’ ብለን በተደጋጋሚ አሳስበን ነበር (‘ሊተገበር የሚችል ዕቅድ አሳዩን’ ብለን ተማፅነን ነበር)። አሁን ግን ካድሬዎቹ ራሳቸው (በተለያዩ ስብሰባዎች) ‘የተለጠጠው (ዝተለጠጠ)’ ዕቅድ ማለት ጀምረዋል።
በኢህኣዴግ ደረጃ ያለው ችግር የስልጣን ሽኩቻ ነው (የባለስልጣናቱ ዓላማ ስልጣን ነው)። ህወሓቶች በኢህኣዴግ የነበራቸው ሚና ማጣት አይፈልጉም። ግን ይህንን ሚና ሊጫወት የሚችል ደህና ሰው የላቸውም። (ዓቅም የነበራቸው የፓርቲው ሰዎች በተለያየ ምክንያት እንዲጠፉ ተደርገዋል ) ። ራሳቸው በራሳቸው ችግር ፈጥረው (በሁለት ተከፍለው፣ ጓደኞቻቸው ኣባረው) ተዳክመዋል (አሁን ትግራይ እንኳ መቆጣጠር በሚችሉበት ሁኔታ ኣይገኙም)።
በኣሁኑ ግዜ በኢህኣዴግ ዉስጥ የተሻለ የስልጣን ተፎካካሪ ብአዴን ነው። ግን ብአዴን ከሌሎች ሦስቴ የኢህኣዴግ አባል ድርጅቶች ተቀባይነት የለውም። የህዝብ ድጋፍም በሰፊው የለውም። የሚጠበቀው ያህል (ኢህኣዴግ ለመቆጣጠር የሚያስችል) ጠንካራ አባላትም የሉትም። ግን በኢህኣዴግ ስርወ መንግስት የህወሓት አልጋ ወራሽ ብአዴን ይመስላል። በህወሓትና ብኣዴን ከፍተኛ ውዝግብ አለ።
ኦህዴድ በኢህኣዴግ ዉስጥ በጣም ያኮረፈ ቡድን ነው። የተለያዩ ምክንያቶች እየደረደረ ስልጣን ለኦህዴድ መሰጠት እንዳለበት ይወተውታል። ግን ኦህዴድ ሁለት ችግሮች ተደቅነውታል። (አንድ) በኦህዴድ ውስጥ መግባባት ብሎ ነገር የለም። (ሁለት) በሌሎቹ የኢህኣዴግ አባል ድርጅቶች እምነት ባለፈው የኦህዴድ ጉባኤ ወደ ሓላፊነት የወጡ ሰዎች ከኦነግ ጋር ግንኙነት አላቸው። በነሱ እምነት ኦነግ የኦህዴድ መዋቅር ተቆጣጥሮታል። ስለዚ ለኦህዴድ ስልጣን መስጠት እጅግ ያስፈራቸዋል።
ሌላው ደኢህዴን ነው። ደኢህዴን ጠንካራ ኣይደለም። በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ ትርምስ ላይ ነው። ከቡድኖቹ አንዱ ከህወሓት ጎን መሰለፍ ይፈልጋል። ብቻውን (ህወሓት ከዚህ በፊት እንዳደረገው) የኢህኣዴግ ስልጣን መቆጣጠር የሚችልበት ዕድል የለውም። ህወሓትም ቢሆን ደካማ ሁነዋል። ዶር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በኢህኣዴግ ጉባኤ ሲናገር “በቃ ወድቀናል” ብሎ ነበር። ይሄ ከህወሓት ጋር መጠጋት ለሚፈልግ ቡድን ራስ ምታት ነው።
ህወሓቶች ጉዳዩ ኣስጨንቋቸዋል። የነ አባይ ወልዱ ቡድን የነ አርከበ ዕቁባይ ቡድን ካባረሩ ወዲህ የባሰ ንትርክ ዉስጥ ገብተዋል። እርስበርሳቸው አይግባቡም፣ ይናናቃሉ። የኣሁኑ መሪዎች ማንም አያከብራቸውም። በህወሓት ጉባኤ የተሳተፉ አባላት በነ ኣባይ ወልዱ የተመለመሉ ቢሆኑም በጉባኤው ወቅት በነኣርከበ የተወሰደው እርምጃ ግራ አጋብታቸዋል። ጉባኤተኞቹ ‘እነ ኣርከበ ከውጡ ህወሓት ከማን ጋ ትቀራለች?’ የሚል ጥያቄ ነበራቸው።
የፓርቲው ሊቀመንበር የሚመረጠው (በፓርቲው ደንብ መሰረት) በጠቅላላ ጉባኤ ነው (በቀጥታ ግን አይደለም)። እንዲህ ነው። ጉባኤተኞቹ አርባ አምስት የፓርቲው የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ይመርጣሉ። በውጤቱ (ባገኙት ድምፅ) መሰረት በቅደም ተከተል (የተመረጡት ሰዎች) ስማቸው ይገለፃል። የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የፓርቲው ስራ ኣስፈፃሚ (ፖሊት ቢሮ) ይመርጣል። ፖሊት ቢሮ አባላት ደግሞ የፓርቲው ሊቀመንበርና ምክትል ይመርጣሉ።
በምርጫው ከፍተኛ ስልጣን ያለው (በመርህ ደረጃ) ጉባኤተኛው ስለሆነ ከፍተኛ ድምፅ ያለው (By Default) የፓርቲው ሊቀመንበር ይሆናል። የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ይሄንን አውቀው ባገኙት ድምፅ መሰረት ዘጠኙ (Top Nine) ለፖሊት ቢሮ ይመርጣሉ። ፖሊት ቢሮ አባላትም በተሰጠው ድምፅ መሰረት ከፍተኛውን ያገኘ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርገው ይመርጣሉ።
በጉባኤው የተሳተፉ አባላት ሊቀመንበር (ከተሰጣቸው አማራጭ) አድርገው የመረጡት ዶር ደብረፅዮን ነበር። ዶር ደብረትፅዮን የኣንደኛነት ድምፅ ሲያገኝ አባይ ወልዱ ሁለተኛ ነበር። (ደብረፅዮን ለኣባይ በ23 ድምፅ ይበልጠዋል)። ውጤቱ ግን ጉባኤተኞቹ እንደጠበቁት ኣልሆነም። የፖሊት ቢሮ አባላት ሁነው የተመረጡት (top nine) ዘጠኙ ኣልነበሩም። በውጤቱ መሰረት የህወሓት ሊቀመንበር መሆን የነበረት ዶር ደብረፅዮን ሲሆን ዉጤቱ ተገልብጦ አቶ ኣባይ ተመረጠ። ይሄ የሆነው የኣቶ አባይ ቡድን አብዛኛው የማእከላዊ ኮሚቴ ወንበር መያዝ በመቻሉ ነበር። (ጉባኤተኞቹ የነኣባይ ቡድን ደጋፊዎች ሲሆኑ አባይ ፓርቲው ይመረዋል ብለው ግን አያምኑም። ስለዚህ ጉባኤተኞቹ ደብረፅዮን ሊቀመንበር አድረገው መርጠው እንደሄዱ ነው የሚያውቁ)።
ይሄን ዉሳኔያቸው ታድያ በጉባኤተኞቹ ጥሩ ስሜት አልፈጠረም። የኣሁኑ መሪዎች የህዝብ አመኔታም የላቸውም። ይሄን ችግር ለመፍታት ሲሉ ከነገ እሮብ (ሚያዝያ 16, 2005 ዓም) ጀምሮ ጉባኤው በተመለከተ በመላው ትግራይ (በየደረጃው ከከፍተኛ የክልል ቢሮዎች ጀምሮ እስከ ቀበሌ አስተዳደር ድረስ) ስብሰባ እንደሚደረግ ታውቋል። ለስብሰባው ማስኬጃ ብዙ ሚልዮን ብር ተመድበዋል (ከመንግስት ካዝና መሆኑ ነው)።
ኣየ ህወሓት! በቃ ስብሰባ ነው። እኔ ደግሞ ስብሰባ ስጠላ! (እንኳን የህወሓት አባል አልሆንኩ)።

No comments:

Post a Comment