Translate

Monday, April 22, 2013

“ኢህአዴግ እኛን ለማፈን ካለው ጥንካሬ ይልቅ፤ እኛ ለመታፈን ያለን ዝግጁነት እየበለጠ መጥቷል” ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ በአትላንታ


girma-siefu2

(ኢ.ኤም.ኤፍ) በኢትዮጵያ የሚገኘው አንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና ብቸኛው በፓርላማ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ አትላንታ ከተማ ተገኝተው ከህዝቡ ጋር ስብሰባ በማድረግ ላይ ናቸው።
(ቀደም ሲል ለስብሰባ ተይዞ የነበረው Jade Event አዳራሽ በትላንትናው ምሽት መጠነኛ የእሳት አደጋ ስለደረሰበት፤ ቦታው እንዲቀየር ተደርጎ 1711 Church St. Decatur GA 30033 ላይ እየተደረገ ነው)
ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ በአትላንታ ህዝባዊ ስብሰባ በሚያደርጉበት ወቅት

አቶ ግርማዬ የአትላንታ የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ አካል ተወካይ ስብሰባውን በህሊና ጸሎት አስጀምረዋል። ከዚያም አቶ ግርማ ሰይፉን ወደ መድረኩ ጋብዘዋቸዋል።
አቶ ግርማ ሰይፉ ስለ ግብዣው አመስግነው፤ በኢትዮጵያ ያለው የትግል አማራጭ የትጥቅ ወይም ሰላማዊ ትግል ማካሄድ ሲሆን፤ ለኛ ብቸኛው አማራጭ ሰላማዊ ትግል ነው። ነገር ግን ሰላማዊ ትግልን ከሰላማዊ እንቅልፍ ጋር የሚያይዙት ከሆነ አስቸጋሪ መሆኑን ተንትነዋል። በመቀጠልም ህገ መንግስታዊ መብቶች ወይም የህገ መንግስቱ አምስት አበይት መርሆዎች እየተከበሩ እንዳልሆኑ በመረጃ አስደግፈው ትንታኔ ሰጥተዋል።
የመደራጀትን፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የእስረኞች አያያዝ ሁኔታን አሁን እየደረሰ ያለውን ሁኔታ በመዘርዘር ገልጸዋል። ለምሳሌ በአምስተኛው የመንግስት ተጠያቂነት የሚለውን መርህ በምሳሌ ሲገልጹ… ለምሳሌ እዚህ አሜሪካ ውስጥ ቦስተን ከተማ ሶስት ሰው ሲሞት፤ ፕሬዘዳንቱን ጨምሮ መንግስት በፈጣን ሁኔታ ምላሽ መስጠቱን ተመልክተናል። ይህ ከመሆኑ ጥቂት ጊዜያት በፊት ግን በኢትዮጵያ አማሮችን ሲያፈናቅሉ 59 ሰዎችን ሲያጓጉዟቸው ህይወታቸው አልፏል። በኢትዮጵያ ለነዚህ ህይወታቸው ላለፉ ሰዎች መንግስት ተጠያቂነቱን አላሳየም። አሁን ባለው ሁኔታ ተጠያቂው ማን እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ አቶ መለስ ዜናዊ ላጠፉት ጥፋት ‘ተጠያቂ ይሆናሉ’ ብሎ መገመት ቀርቶ ይሞታሉ ተብሎም አልታሰብም ነበር።
ከ97ቱ ምርጫ በኋላ የሲቪክ ማህበራት በሰብ አዊ መብት ጉዳይ እንዳይገቡ አድርጎ ነው ያደራጃቸው። በአዲሱ አሰራር እና አደረጃጀት መሰረት ደግሞ ከውጭ አገር ምንም አይነት የገንዘብ እርዳታ እንዳያገኙ ተብሏል። በአገር ቤት ደግሞ ህዝቡ እርዳታ ከሰጠ በመንግስት በኩል ጫና ይደርስባቸዋል። በተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችም በኩል የምንመለከተው ይህንኑ ነው። ህዝቡ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን በገንዘብ ቢረዳ ተመሳሳይ ችግር ይደርስበታል።
ለምሳሌ እኛ ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን እያሳተምን ህዝቡ ጋር መድረሰ ጀምረን ነበር። ጋዜጣው በህዝብ ዘንድ የበለጠ መድረስ ስንጀምር ግን፤ ለማተሚያ ቤቶች ስልክ ደውለው ማስፈራራት ጀመሩ። ችግሩ ያለው “ኢህአዴግ እኛን ለማፈን ካለው ጥንካሬ ይልቅ፤ እኛ ለመታፈን ያለን ዝግጁነት እየበለጠ መጥቷል።” ማተሚያ ቤቶችም በፍርሃት ተውጠው ጋዜታችንን “አናትምም” እስከማለት ደርሰዋል።
እንደድሮው እየገደሉ ሳይሆን፤ በማስፈራራት ነው ስራቸውን እየሰሩ ያሉት።
የስብሰባ አዳራሽ ተከራይተን ስብሰባ ልናደርግ ስንዘጋጅ፤ የሆቴሉን ባለቤት በስልክ ደውለው ያስፈራሩታል። እሱም እግሩ እስኪሰበር እየሮጠ መጥቶ፤ “እባካቹህ እኔን ተዉኝ። ሌላ ቦታ የስብሰባ አዳራሽ ፈልጉ” ይለናል። ፍርሃታችን ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው።
ፍርሃታችንን ልናስወግድ የምንችልበት አቅጣጫ መቀየስ ይኖርብናል።
በኛ በኩል ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን “አናትምም” ሲሉን ዝም ብለን ቁጭ አላልንም። ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን በድረ ገጽ ላይ ማተም ቀጥለናል። ብዙዎቻቹህ አገር ቤት ስላለው ሁኔታ እና መረጃዎችን ከአዲሱ ድረ ገጻችን እንዳገኛቹህ እገምታለሁ። እዚህ አሜሪካ እንዳለው፤ ህዝቡ ሁሉንም መረጃ በኢንተርኔት ላይ አያገኝም። የህትመት ሚዲያ የግድ አስፈላጊ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ በኛ በኩል የራሳችን ማተሚያ ቤት መክፈት አማራጭ የለውም።
በአሁኑ ወቅት ተሰብሳቢው ለፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ የገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ናቸው። አሁን ከአምስት ሺህ ዶላር በላይ ተሰብስቧል። በመቀጠልም የአቶ ግርማ ሰይፉ ከረቫት በጨረታ በአንድ ሺህ ዶላር ተሽጧል። ከዚህ በኋላ የጥያቄ እና መልስ ክፍለ ጊዜ ይሆናል።
==============
ጥያቄ – ማተም አትችሉም ብትባሉ ምን ታደርጋላቹህ?
መልስ – ማተም አትችሉም ብትባሉ ምንታደርጋላቹህ ተብሏል። የሚፈራ ዝም ይላል፤ የማይፈራ ግን መናገሩን ይቀጥላል። የ2002 ምርጫ ስንወዳደር የክርክር ስትራቴጂውን ነድፈን ነበር። በወቅቱ ጉዳያችንን አንስተን ተዘጋጅተን ነው ለክርክር የገባነው። አንዷለም ሲከራከር ጥሩ አድርጎ ነድፏቸው ወጥቷል። ከዚያ በኋላ ስልክ ደውለው ለመድረክ አመራሮች ለአንደኛው “እንዲህ አይነት ሰው እየላካቹህ የምታሰድቡን ከሆነ ኢህአዴግ አይከራከርም” አሉ። ያኔ አንከራከርም አሉ እንጂ፤ መከራከር የለባቸውም አላሉንም። አሁንም አሁንም አታትሙም አላሉም።
በነገራቹህ ላይ ከዚህ በፊት እንግዲህ ማተሚያ ቤት ገብተን አናትምም ሲሉን፤ የግል ማተሚያ ቤቶች ሄድን። ሆኖም ለነሱም ደውለው አስፈራሩዋቸውና ማተሚያ ቤቱ ለማተም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። እኛ አለመፍራት እንጂ ሌሎችን እንዳይፈሩ ማድረግ አንችልም። እስካሁንም እኮ ብዙ ገፍተውናል። የት ጥግ ድረስ እንደሚሄዱ ግን እናያለን። እስክንድር እኮ ቤቱን እንወርስብሃለን ሲሉት፤ “ውረሱት። አንድ ቀን ለልጄ ትመልሱታላቹህ” ነው ያላቸው። እኛም ቢወርሱት አንድ ቀን እናስመልሰዋለን።
ጥያቄ – ህገ መንግስቱ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን ይፈቅዳል። ነገር ግን መንግስት ይከለክላል። አሁንም ይህንን ማተሚያ ቢከለክልስ?
መልስ – ብዙ ግዜ ጥያቄዎቻችንን ማድረግ ያለብን… እዚህ ቤት ያላቹህ ሰዎች የሚጠበቅብኝን አድርጌያለሁ ብላቹህ አስቡ። አሁንም የሚጠበቅባችሁን አድርጉ። ይቀሙናል ወይስ አይቀሙንም ሳይሆን በበኩላቹህ ለምታደርጉት ነገር ዋጋ ስጡ።
ኢህአዴግ ይህን አደረገ እያልን ስንወቅስ ይሰማል። ዋናው ትኩረት ማድረግ ያለብን እኔ ምን አደረኩ የሚለው መሆን አለበት።
ጥያቄ – በውጭ ካለነው ምን ትጠብቃለህ?
መልስ – ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የምታደርጉት ነገር የለም። ነገር ግን እናንተ ሰላማዊ ሰልፍ ብትወጡ የሚያስራቹህ የለም፡ ከስራ የሚያባርራቹህ የለም። ስለዚህ ሌላው አለም የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽ እንዲሰማው ብታደርጉ ትላቅ አስተዋጽኦ ነው። ለኮንግረስ እና ለሴኔተሮች እናንተ ቅርብ ናቹህ። ማድረግ ያለባችሁን ታውቃላቹህ። ማድረግ የሌለባቹህ ነገር ደግሞ አለ። እዚህ ሆናቹህ አገር ቤት ያለውን ፖለቲካ ለመምራት አትሞክሩ። ስለዚህ በምንስማማባቸው ጉዳዮች አብረን መስራት እንችላለን። የግል እና የጋራ ጉዳያችንን ትተን ዋና አላማችን ኢትዮጵያ ካደረግን እናሸንፋለን።
ጥያቄ – ስለ ሰላማዊ ትግል እና ትጥቅ ትግል ልዩነቱን ሲናገሩ፤ ሰላማዊ ትግሉን መቀጠል አለብን ተብሏል። ለምሳሌ ስም መጥቀስ ባልፈልግም እነብርቱካን ሚዴቅሳ ቃሊቲ ገብተው ሲወጡ፤ ትግሉን አቆሙ። ሰላማዊ ትግሉን አልቀጠሉም ማለት ነው። ይህንን እንዴት ያዩታል?
መልስ- መምራት የጀመሩ ሰዎች ሁልጊዜ መሪ ሆነው ይቀጥላሉ ማለት አይደለም። ሰላማዊ ትግሉን አያቋርጡም ማለት አይደለም። እነሱ ስላቋረጡት እኛ ማቆም አለብን ማለት አይደለም። ግን ዝም ብለን ስናስበው፤ እነዚህ ትግሉን የጀመሩት ሰዎች ያደረጉትን ስንቶቻችን አድርገናል? ቀላል መስዋ እትነት አይደለም የከፈሉት። ለዚያ ክብር መስጠት ያስፈልጋል። አንደኛው የጀመረውን ሌላው መቀጠል አለብን። ይህ ማለት ልጆቻችን እየታገሉ እድሜያቸው እንዲጨርሱ አልመኝም። እንደኔ እንደኔ ቢያንስ ልጆቻችንን ትግል ከሚባል ጣጣ ብንገላግላቸው ደስ ይለኛል። እርግጠኛ ነኝ፤ እሁን በአሜሪካ ያለው ትውልድ ያገኘውን መብት እና ነጻነት እነአብርሃም ሊንከን አላገኙትም ይሆን ይሆናል። ነገር ግን የተወሰኑ መሪዎች መርተው ሲያበቁ እነሱ እስር ቤት ሲገቡ ሌላው ማቆም የለበትም። እኛ ጀምረነዋል። ላንጨርሰው እንችላለን። እኛ ካልተጠናከርን አሁን ካለው ሁኔታ የባሰ ነገሮች እናይ ይሆናል።
ጥያቄ- የታሰሩት መሪዎች ቤተሰቦች ጉዳይ እንዴት ነው በናንተ በኩል ምን ታደርጋላቹህ?
መልስ – እኛ እዚያ ቅርብ ነው ያለነው። የምናደርገውን እያደርግን ነው። አንዳንዱ ሰው የፖለቲካ ፓርቲ ገንዘቡን ይበሉታል፤ ስለዚህ መርዳት ያለብን ቤተሰቡን መርዳት ነው ያለብን ከተባለ… ይህም አያጣላንም። ዋናው መርዳቱ ነው። እኛ የምንችለውን እያደረግን ነው። ቢያንስ ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ እያደረግን ነው። እናንተም ይህንን ማገዝ አለባቹህ።
ጥያቄ – 24 ሰዓት በስለላ መረብ ውስጥ ሆናቹህ ጠዋትና ማታ እየሰራቹህ በመሆኑ ልናመሰግን እንወዳለን። ሆኖም ቀደም ሲል ሲናገሩ ግን አገር ቤት ያለውን ፖለቲካ ልምራ አትበሉት ብለዋል። ነገር ግን እኛ ውጪም ብንሆን የአገራችን ጉዳይ ያገባናል። እናም ይሄ አባባል በአገራችን ጉዳይ ሃሳብ እንዳንሰጥ የሚያደርግ ይመስለኛል። ከዚህ በተጨማሪስ አሁን ያለውን ፍርሃት ምን አመጣው?
መልስ – ታርጋ ያለው መኪና እየነዳን ታርጋ ያለው መኪና እየነዳን እንወጣለን። እነሱ ታርጋ እየቀያየሩ ሊከተሉን ይችላሉ። አንድ ምሳሌ ልንገራቹህ። ላፍቶ አካባቢ ቤቶች ፈርሰው ነበር። አንድ ሰው ደውሎ የሆነውን ነገረኝ። ለኛ ጋዜጣ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ደውዬ ነገርኩት። እዚያ ሄዶ ሲያይ በርግጥም ቤት እየፈረሰ ነበር። እዚያ ቤት የሚፈርስበትን ሰው ቃለ መጠይቅ ሊያደርግለት ሲል፤ “የምታየውን አንተው ተናገር እንጂ!” ብሎ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆነም። እናም ሰው ቤቴ እየፈረሰ ነው ብሎ ለመናገር ድፍረት ካጣ እኛ ምን ማድረግ እንችላለን? ህዝቡን ከዚህ ፍርሃት ማውጣት መቻል አለብን። ስለዚህ ዋናው ትግላችን ፍርሃትን እንዲፈሩ ማድረግ ነው ያለብን።
ጥያቄ – እናንተ ማተሚያ ስትተክሉ ነገ ደግሞ ወረቀት እንዳታገኙ ቢያደርጋቹህስ? ሌላው ሲታሰሩ የምናየው ወጣቶቹ ናቸው።
መልስ – አቁሙ ስላሉን አናቆምም። ወረቀት እንዳናገኝ ቢያደርጉ ወረቀት እንፈልጋለን እንጂ እናቆምም። የፈለገውን ያህል ውድ ቢያደርጉብን ስራችንን አናቆምም። በውድ ገዝተንም ቢሆን እንቀጥላለን።
ስብሰባው ቀጥሏል። የተለያዩ ጥያቀዎችም ቀርበዋል። ክቡር አቶ ግርማ የመለሱትን እያለፍን እያለፍን እናስነብባለን።
***************
አማራ ሲነካ በአማራነት ተደራጅተን ሳይሆን፤ በኢትዮጵያዊነት ተነስተን ነው መከላከል ያለብን። እነሱ በሚፈልጉት እና በሚፈጥሩት መንገድ ሄደን የነሱን ቦንብ አክቲቬት ማድረግ የለብንም።
***************
እንሰማለን። ሃሳብ መስጠት አንድ ነገር ነው። ሃሳቡን ፕሮሰስ አድርጎ ጠቃሚውን መቀበል እና አለመቀበል የፓርቲው ፋንታ ነው የሚሆነው።
**************
ኢህአዴግ ዲያስፖራን የሚፈልገው ሃሳቡን ሳይሆን ኪሱን ነው። እናም ዲያስፖራውን የሚያዩት እንዴት አድርገን ገንዘቡን እናስወጣው እንጂ፤ ሃሳቡን እንቀበለው አይሉም። እኛም ከነሱ የበለጠ ገንዘብ እንፈልጋለን። በኢትዮጵያ ጉዳይ በጋራ ለመስራት ታምኖበት በፖሊሲ ደረጃ ተቀርጾ ተቀምጧል።
*************
እያነስንላቸው ስንሄድ እነሱ የበዙ እና የጎለበቱ ይመስለናል። አንዳንዱ ሳይሰልለን ጎረቤቱ ትግሬ ስለሆነ የሚሰልለው ይመስለዋል።
************

No comments:

Post a Comment