Translate

Wednesday, April 3, 2013

ሊነበብ የሚገባው .... ታላላቅ የታሪክ ክህደቶች ከ“ፍኖተ ገድል”


(ገብረመድህን አርአያ )

"ተራው ታጋይ በእንደ ወዲ ዜናዊ እና ብስራት አማረ ባሉ ፍጹም አደገኛ አወናባጆች እና ከሃዲዎች እየተነዳ ነው የአገር ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ታሪክም ፤ የአገራችን ኢትዮጵያም ክብር እና ሉኣላዊነትም አደጋ ላይ የወደቁት። "

"እንደ ወዲ ዜናዊ እና አቶ ብስራት ያሉ የታሪክ አሽክላዎች ግን ገና ለገና እነሱ ከቤተሰባቸው የኋላ የባንዳ አሳፋሪ ታሪክ ከመነጨ ከፍተኛ የበታችነት ስሜት ተነስተው ጠላት ነው የሚሉትን አማራውን ህዝብ አንገት እናስደፋለን ብለው መሬት ጠብ የማይል የታሪክ ቡትቶ አምጥተው አቧራቸውን ያቦኑብናል።"

"እኔ መቼም አውሮፓዊ ቅኝ ገዢን ያለፍርሃት በጀግንነት ተጋፍጦ በነጻነት ያቆየውን ሰው "ዘር" ቆጥሮ አማራ በመሆኑ ብቻ እንደምን ሊያኮሰምን ይፈልጋል?? እኔ በበኩሌ ይሄ አስከፊ የጥላቻ ደዌ ከመሆን ያለፈ ምንም ምክንያት ላገኝለት አልቻልኩም።"

"ነገሮችን እንደዚህ አገናዝቦ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ልበሰፊነትን ይጠይቃል። በጥላቻ የታሰሩ ፤ ሃሳበ ድውይ የህወሃት መሪዎች ግን ቅንነት በጣም የጎደላቸው ሰዎች ስለሆኑ አጼ ምኒልክ አማራ መሆናቸው ፤ አማራም የትግራይ ጠላት ነው ከሚል ቆሻሻ አመለካከት ውጭ ሌላ ነገር ማሰብ ፈጽሞ አይቻላቸውም። "


ለአንድ ሰሞን ለአመታት በአሜሪካኗ ግዛት ኦሃዮ ውስጥ በስደት ሲኖር የነበረው የወያኔ ነባር ታጋይ፣ በስለላ የሰለጠነ … እና መሪህ ባኽታ ብስራት አማረ የጻፈው መጽሃፍ በህትመት ወጥቶ ጉድ፣ ጉድ ከተባለለት በኋላ እኔም እንደ ኢትዮጵያዊነቴ እና እንደ ቀድሞ የህወሃት ቀዳሚ ታጋይነቴ መጽሃፉን አግኝቼ ለማንበብ እና የግሌን ግምገማ ለማድረግ መፈለጌ አልቀረም። ዘግይቶም ቢሆን መጽሃፉ በእጄ ገብቶ የማንበብ እድል አገኘሁ። መቼም ጉድ ነው የሚባለው!! ህወሃት እና በዙሪያው የከበቡት ጉዶች የቅጥፈት እና የክህደት ጉድ ማለቂያ የለውም። 

ይህ መጽሃፍ በተከታይ እትም ሊታረም የሚችል ግድፈት አይደለም የተሸከመው፤ እንደዚህ በአገጠጠ ውሸት፣ በህወሃታዊ የታሪክ ክህደት፣ በጥላቻ እና በተንኮል የታጨቀ መጽሃፍ አይቼም፣ አንብቤም አላውቅም። ብስራት አማረ ታሪክ ለዚያውም በጣም የቅርብ ጊዜ ታሪክ አንድ ሰው እንዳሻው ስለጻፈው የመጨረሻው እውነት ሆኖ ይቆያል ብሎ ያምናል። ይህ አስተሳሰብ ላዩን ሲያዩት በጣም ገራገር ሊመስል ይችላል። ነገር ግን በጊዜ አስፈላጊው የእርምት እና የማጋለጥ እርምጃ ካለተወሰደ የኋላ ኋላ ብዙሃን እንደ እውነተኛ ታሪክ እና ትንታኔ ዋጋ ሰጥተው ሊያዩት ይችሉ ይሆናል።

የህወሃትን ማንነት ህወሃት ገና የስልጣን መንበር ላይ ሳይወጣ አበክሬ ተናግሬም፤ አስጠንቅቄም ነበር። እምብዛም የሰማኝም ሰው አልነበረም እና ዛሬ ገና በበረሃ እያሉ የተናገርኩት ነገር እንደ ትንቢት ይኸው ባለፉት 21 አመታት ሲፈጸም አየን። ዛሬም ይህን የምናገረው አገር እና ህዝብን ወደ ኋላ ሄጄ ለመውቀስ አይደለም። ምናልባትም መወቃቀስ ካለብን ለሱ ወደፊት ጊዜ ይኖረዋል። ለአሁኑ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ቀዳሚው ጉዳይ መሆን ያለበት የቅጥረኛው እና የሁሉ ኢትዮጵያውያን ዋና ጠላት የሆነው የህወሃት ቡድን እና እንደብስራት ያሉ ጀሌዎቹ ናቸው። ለዛሬው ከዚህ መጽህፍ ውስጥ የታዘብኳቸውን ስምንት በጣም አደገኛ እና የዘቀጡ የታሪክ ቅጥፈቶችን አንጥሬ ያነቡ ዘንድ እነሆ እላለሁ።

ለአነባበብ ይረዳ ዘንድ ጽሁፌን ከመጽሃፉ እያጣቀስኩ ለመልሱ ከራሴ እና አስረጅ ይሆናሉ ካልኳቸው ዋቢ ማስረጃዎች ጋር አድርጌ የራሴን እነሆ እላለሁኝ።

የታሪክ ክህደት ቁጥር 1:

ይህ ጉዳይ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የትግሪኛ ፕሮግራም ላይ አረጋዊ በርሄ እና ስብሃት ነጋ ቀርበው የተወያዩበት/የተከራከሩበት እና እና ስለ መጽሃፉ በተለይ እኛ ከአገር ውጪ ያለን ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማንበት ጭብጥ ነው -የአክሱም ስልጣኔ ጉዳይ።

ከመጽሃፉ እጠቅሳለሁ:-

<< በርካታ ተመራማሪዎችና ጸሃፊዎች "አክሱም አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ የአማራ ነዋሪዎች ወዳሉበት ደቡባዊ ክፍል ስለመስፋፋቷ የጽሁፍ ማስረጃዎች የሉም። እንደኢትዮጵያ(አማራ) አባባል ሳይሆን የአክሱም ታሪክ ከሁሉ በላይ የደቡብ ኤርትራና የሰሜን ትግራይ ታሪክ ስለ መሆኑን(sic) ማስረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ በተጨማሪ አማራ የአክሱም አፄአዊ ግዛት አካል የነበረ ስለመሆኑ ምንም አይነት ታሪካዊ ጥቁምታ የለም: :>>[1]

የህወሃት መሪዎች የተጠናወታቸው የዘረኝነት በሽታ እንዲሁ በመድሃኒት ወይም በጸበል የሚለቅም አይነት አይደለም። መቼም ዘረኝነት አንዴ ከጀመረ እንደካንሰር ከጀመረበት ቦታ ተወስኖ አይቀርም። እየመዘመዘ ፣ ውስጡን እየበላ መጨረሻ ላይ ታማሚውን ላይመለስ እስከ ወዲያኛው አለም ይወስደዋል። ይኸው ዘረኝነት ዛሬ በአውራጃ ደረጃ ወርዶ የአክሱማዊት መንግስት በሙሉ ትግራይም ቦታ የለውም የሚል መከራከሪያ ከነባሩ የህወሃት ታጋይ በድርጅቱ ከፍተኛ መሪዎች ቡራኬ እና ይሁንታ ተሰጥቶት በመጽሃፍ ተጠርዞ ድል ባለ ድግስ ተመርቆ ለንባብ በቃ። እንደ ጎጠኞቹ መከራከሪያ የአክሱማዊ ኪንግደም የሚያጠቃልለው ሰሜን ትግራይ ፣ አክሱም፣ አድዋ ፣ ደቡብ ኤርትራ ፣ ሰራየ እና አካለጉዛይን ብቻ ነው። በአቶ ብስራት መጽሃፍም ሆነ በአቶ ስብሃት ነጋ ክርክር አዲግራት እና ተምቤን በአክሱማዊ ኪንግደም ውስጥ ቦታ የላቸውም።

ጉዳይ በመከራከሪያነት የተነሳው የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ለማንሳትም አይደለም። አቶ ብስራት የስርዓቱ ቁንጮ እና ዋና ታሪክ አበላሺ አወናባጁ መለስ ዜናዊ የርዕዮተ አለም እና ምግባር ልጅ ነው። መለስ በአንድ ወቅት “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው?” ማለቱ በምስለ ድምጽ ተመዝግቦ ያለ የታሪክ ክህደት ነው። ይኸው ዘረኝነት ዛሬ ላይ መዝምዞ ፣ መዝምዞ የአክሱም ሃውልት ለአጋሜው እና ለተምቤኑ ምኑ ነው ላይ ደርሷል። ይሄ ዘረኝነት እና ጥበት ነገ የሚሄድበትን ለመናገር ጠንቋይ ቀላቢ አያሻም።

የታሪክ ጽሁፎች በእውን ያሉ ማስረጃዎች እና ማሳያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? በብዙ የታሪክ አጥኚዎች መግባባት የተደረሰበት እና ማመሳከሪያ የጽሁፍ ማስረጃዎች እንዲሁም በቁም ያሉ እና በአርኪዎሎጂ ቁፋሮ የተገኙ ቁሶች በማሳያነት ማስቀመጥ የሚቻልባቸው የአክሱም ኪንግደም የግዛት ክልል በጣም ሰፊ ግዛት ሲሆን ይኸውም ከሰሜን አቅጣጫ ከደቡባዊ ግብጽ ጀምሮ ፤ በስተምዕራብ አቅጣጫ ሰሜናዊ ሱዳንን እንዲህም በስተ ምስራቅ በኩል መላውን የመንን እና ደቡባዊ ሳውዲ አረቢያን ያጠቃልላል።

በዚሁ አንቀጽ ላይ "ኢትዮጵያ" የሚለውን የሁሉም ብሄረሰብ የወል ማንነት በቅንፍ ውስጥ "አማራ" እያለ የለየለት አላዋቂ ትንታኔውን ሲሰጥ ይስተዋላል። የለመዱት "የአማራ የበላይነት" ክስ ምናልባት ለክርክርም ይመች ነበር። ዛሬ ፣ ዛሬ ደግሞ ወርዶ "አማራ" እና "ኢትዮጵያ" ሁለት ተተካኪ ስሞች አድርጎ ለማቅረብ ይሞክራል። አወይ ሰው መናቅ ፤ አወይ ታሪክ መናቅ ፤ አወይ አገር መናቅ አለ የአገሬ ሰው!!

የታሪክ ክህደት ቁጥር 2.

ጸሃፊው ለአጼ ሚኒልክ እና ለአማራ ህዝብ ያለው ጥላቻ ወደር የለውም። በአማራ ህዝብ እና በአጼ ሚኒልክ ላይ የሚያቀርበው የስድብ ውርጅብኝ፣ የቅጥፈት ውንጀላ እና የጥላቻ ደረጃ አስደንጋጭ ነው። ምናልባትም ጸሃፊው እራሱ ለአጼ ምኒልክ እና ለአማራ ህዝብ ያለውን ጥላቻ ገልጾ ቢያቆም በበቃ፤ ችግሩ ግን በዚህ አያበቃም። አፉን ሞልቶ በልበ ሙሉነት አጼ ምኒሊክ ለትግራይ ህዝብ የተለየ ጥላቻ ነበራቸው ብሎ ምንም የታሪክ ማስረጃ የሌለው ይልቅም ፍጹም ህወሃታዊ ከሆነ የራስ መተማመን ጉድለት ካለበት አእምሮ ከመነጨ አስተሳሰብ በመጽሃፍ ጽፎ ማውጣት ከምንም ነገር በላይ የሚያሳየው የጸሃፊውን ደካማ አስተሳሰብ ነው። ሌላው ጉዳይ ዛሬ ላይ ቆመው የሚቀርባበቸውን ክስ መከራክር የማይችሉ ስመ ገናና እና አስተዋይ ንጉስን ምንም የታሪክ መሰረት በሌለው የቅጥፈት ክስ በለመደው ልቅ እና ተሳዳቢ አፉ ሲዘልፍ ማየቱ በእውነቱ በጣም የሚያሳዝን እውነታ ነው።

እስቲ ስለ አጼ ምኒሊክ ከመጽሃፉ ልጥቀስ፤

<<ከቴውድሮስ እና ከዮሃንስ ይልቅ የምኒሊክ ወደ ስልጣን መምጣት ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የገጠሟትን ሰፊና ውስብስብ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ጎሳዊ ችግሮች ያስከተለ ክስተት ነበር። ኢትዮጵያን በሚገርም ጀግንነት እና ልበ-ሙሉነት ማስከበሩ ተረስቶ በሴራ እና በክህደት የተካው የአጼ ምኒሊክ ስራ በኢትዮጵያ ህዝቦች ቅራኔን ቀስቃሽ ሆኖ ተግኝቷል። ግዛቶችን ለውጭ ሃይሎች ፈርሞ መስጠት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ በየቦታው ተደጋግሞ የሚከሰት የጎሳ ግጭት እና የማያባራ የኢኮኖሚ ድቀት አገሪቷን ለረዢም ጊዜ ሲያጨናንቁ ታይቷል። >>[2]

<<አጼ ምኒልክ እና ተከታዮቹ ወደ ስልጣን ሲመጡ ስለ ሀገሪቷ የተጠራቀመ ባህላዊ እና ታሪካዊ ገጽታ እምብዛም አልተጨነቁም። ስልጣን እንደያዙ በሃገሪቱ ባሉ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጎሰኝነትንና አድልዎ ፈጥሮ ለማዋከብ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በጣም ብዙ ጥንታዊ ቋንቋዎችና ባህሎች ቢኖሩም የአንድን ቋንቋና ባህል የበላይነት አበርታቱ። ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በሁሉም የማስግደድ መንገድ በማጠናከር ባርነት እና የተማከለ አስተደደራዊ ስርዓት ለማስፋፋት ታገለ። >>[3]

<<የምኒሊክ የስልጣን ጥማተኛ ለትግሪኛ ተናጋሪ ህዝብ የነበረው ከባድ ጥላቻ ኢትዮጵያን ወደ ቀውስ እንደመራ ይታመናል።>>[4]

<<...ይኸውም የህዝባቸውን መለያየት ያስከተለው ምኒሊክን ተከታዮቹ ብሄራዊ ግዛቶችን ለውጭ ሀይሎች ፈርሞ በመስጠት የሰሩት ክህደት የትግራይ ህዝብ በሁለት ከመክፈሉ ባሻገር ኢትዮጵያ ከወደብ መውጫ ችግር እንድትሰቃይ አድርገዋል።>>[5]

<< ምኒሊክ እና ተከታዮቹ በአሳፋሪ ሁኔታ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ቅርስ በመስበር ኤርትራ ተብላ የምትታወቅ አዲስ ግዛት እንድትመሰረት ምክንያት ከመሆን ባሻገር 20ኛው ክፍለ ዘመን በሸዋ ገዢዎች ተረታ ተረት የሰለሞን ንግስና የዘር ውርስ ቅሌት የተወሳሰበ ሴራ ያየለበት ዘመን እንዲሆንም አድርገዋል።>>[6]

ከዚህም የበለጠ ብዛት ያለው ጆሮ ጭው የሚያደርጉ እና የለየላቸው የመንገድ ዳር መደዴ የታሪክ ክህደቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለጊዜው በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር ይህን ያህል ከጠቀስኩ ይብቃኝና እኔ በግሌ የተሰማኝን እና እውነተኛው እና በቅጡ የተመዘገበው ታሪክ የሚለውን ልዘርዝር።

ጸሐፊው የአጼ ምኒሊክን የሰለሞን ዘር ሃረግ "የዘር ውርስ ቅሌት የተወሳሰብ ሴራ" ምናምን እያለ ከሰከረ ሰው የወጣ በሚመስል ንግግር ሲተነትን ዋናው የመጽሃፉ እኩይ ግብን ዘንግቶም ጭምር ነው። አጸ ዮሃንስ 4ኛም የሰለሞን ዘር ሃረግ ውርስ ተቀባይ (በሴት ወግን) መሆናቸውንም የዘነጋ ይመስላል። የንግስና መሰረታቸውም ይህ የዘር ሃረጋቸው ነበር።

አጼ ምኒሊክን በጨካኝነት በተለይ ከአጼ ቴዎድሮስ ና አጼ ዮሃንስ ጋር እያነጻጸሩ መወንጀል በጣሙን የለየለት የታሪክ አላዋቂነት ወይንም ህወሃታዊ ከሃዲነት ከመሆነ የዘለለ አይደለም። እውነተኛውን ታሪክ ለመረዳት ሰዎች እጁን በደም ከታጠበ የወያኔ አላዋቂ ካድሬ አይደለም መስማት ያለባቸው። እድሜ ዘመን ላመጣው ቴክኖሎጂ በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ እንደ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን[7] እና ፕሮፌሰር ሬይመንድ ጆናስ[8] ያሉ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ የሆነ ጥናት ያደረጉ ፤ በጣም ተነባቢ የሆኑ ተጠቃሽ መጻህፍቶችንም የጻፉ እና ምንም አይነት አድልዎ ወይም ጥላቻ ሊኖራቸው የማይችል የባዕድ አገር ምሁራን የሰጡትን ምስክርነት ማድመጡ ብቻ በቂ ነው።ሌላም ብዙ ማጣቀሻ ማቅረብ ይቻላል። ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ወቅት በአጼ ምኒልክ ላይ የሚደርሰው አጸያፊ የወያኔ ክስ እና ውንጀላ አላስችል ብሏቸው መሰለኝ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌም የምኒልክን ብልሃት ማስተዋል የተመላበት አመራር በተመዘገቡ ታሪካዊ ኩነቶች አስደገፈው የተከላከሉበትን የሃተታ ጽሁፍ ለማንበብ ችያለሁኝ። ግሩም ጽሁፍ ነውና ቢያነቡት ይመከራል። “መለስ አርገው ጋሜ ፤ በምኒልክ ነፍስ” በሚል ርዕስ የተጻፈውን ይህንን ጽሁፍ ከኢትዮሚዲያ ድረገጽ ከታች ባለው አድራሻ ያገኙታል።[9]

እንዲያው ለነገሩ አጼ ምኒሊክ ከነስማቸው "እምዬ ምኒሊክ" አልነበር የሚባሉት??

አጼ ምኒሊክ ወራሪውን የኢጣልያ ጦር አድዋ ላይ ረትተው ሲያበቁ ወደ ኤርትራ መዝለቅ አለመቻላቸው በጣም ግልጽ የሆነ የታሪክ ትንታኔ ያለው በመሆኑ እዚህ መዘርዘሩ ብዙም ፋይዳ የለውም። ምናልባትም ብዙ ማወቅ ለፈለገ በኢሳት የዩቱይብ ድረ ገጽ ላይ የምሁራኑ ሙሉ ቃለ ምልልስ ስላለ ያንን ተመልክቶ አጼ ምኒሊክ በሰአቱ ያለውን የሃይል አሰላለፍ ተመልከትው በጊዜው ያገኙትን ድል ለማጽናት እና በጦርነት፣ በረሃብ እና በውሃ ጥም የተዳከመውን ጦራቸውን መልሶ ለማደራጀት ጦርነቱን እዚያ ላይ ከማቆም በላይ ምንም አማራጭ እንዳልነበራቸው መረዳት ይቻላል።። ምንአልባትም የተዳከመውን ጦራቸውን ይዘው ውጊያውን ከመረብ ወዲያ ቢቀጥሉ በርግጠኝነት በአድዋ ያገኙትን ድል መልሰው አሳልፈው የሚሰጡብት ኢትዮጵያውያንም የሌሎቹ አፍሪካውያን የቅኝ ተገዢነት እጣ የሚደርሳቸው እንደሚሆን በብዙ የታሪክ አዋቂዎች የታመነበት ትንተና ስለሆነ የአቶ ብስራት ቁምጣ አጠር የቅጥፈት ታሪክ ምንም ቦታ የለውም። የኢትዮጵያ ወደብ አልባነት እና የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል መለስ ዜናዊ በሙሉ አፉ ደግሞ ደጋግሞ እንዲሚያጣጥለው ሳይሆን እንደዚህ በጣም የሚከነክን ጉዳይ ከሆነ ምናልባት ጸሀፊው እራሱን ወይም አለቃውን ወዲ ዜናዊን ነው መክሰስ ያለበት እንጂ እናቶቻችንን ፣ አባቶቻችንን እና እኛን የጣሊያን አሽከር ከመሆን ሞተው ያዳኑንን አያቶቻችንን አይደለም።

እንግሊዝ ህንድን ለቃ ስትወጣ እንደ አፍሪካ ቀንድ ሁሉ አገራቱ በሰላም ይቀጥሉ ዘንድ ሁሉን አሰናድታ አይደለም የወጣችው። የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ህንዶች እና ብዙሃኑ የሂንዲ እምነት ተከታዮች የኋላ ኋላ ተፋጠው በስተመጨረሻ ፓኪስታን ራሷን ችላ ነጻነት በማወጇ ለሁለት መከፈል የተገደዱበት የታሪክ ኹነት እናያለን: የህንዶች የነጻነት አርበኛ እና የነጻነት ትግሉ ሰላማዊ መሪ የነበረው ሞሃንድራስ ጋንዲ ብዙም አማራጭ ስላልነበረው ጊዜው የሰጠውን የታሪክ እውነታ ይዞ ነጻይቱን ህንድ ወደፊት ማራመድ ቻለ። ፓኪስታንም ሌላ አገር እንደውም የህንድ የዘመናት ባላንጣ መሆን ቻለች። በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ህንዳውያንም ሆኑ ሌሎች የታሪክ አዋቂዎች ጋንዲን ሲወቅሱት አይታይም። እንደ አቶ ብስራት እና መለስ ዜናዊ አይነት የአእምሮ በሽተኛ ካልሆነ ጤነኛ ጭንቅላት ያለው ሰው ታሪክን በቅንነት እና በትክክለኛ አገባቡ ነው ማየት ያለበት።

አጼ ምኒሊክ በኢትዮጵያ የተማከለ ስርዓት ማምጣታቸው ምንም የማይካድ የታሪክ ሃቅ ነው። እንደ ጊዜውም ሲቻል በብልሃት እና ማግባባት ሳይሆን ደግሞ በጉልበት በዘመኑ የነበሩ ያለ ጦርነት በቀር ስራ የሌላቸው የሚመስሉ መሳፍንትን መትተው የኢትዮጵያን ማዕከላዊ አስተዳደር እንደመሰረቱ ማንም የማይክደው ሃቅ ነው። አጼ ምኒሊክ ይህን ሲያደርጉ በአገሪቷ ላይ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት አፍርሰው አይደለም። ኢትዮጵያ ውል እና ማለቂያ በሌለው ውጊያ የምትታመስበት የዘመነ መሳፍንት ወቅት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ሌላው አቶ ብስራት አጼ ምኒልክን በስልጣን ጥመኝነት ይከሳል። መቼም አጼ ምኒልክ ንጉስ ናቸው። ንጉስ ደግሞ በየትም አገር እንደነበረው አሁንም እንዳለው ሲነግስ ተመርጦ ወይም እንደ ዘመናዊ የፖለቲካ ስርዓት በገደብ አይደለም። ስለዚህም እሳቸውን ነጥሎ "በስልጣን ጥማት" መወንጀል ምንም ትርጉም የለውም። ዘውዳዊ ስርዓት ለኢትዮጵያ አይበጅም አንድ ክርክር ነው ነገር ግን ዘውዳዊ ስርዓትን በስልጣን ጥመኝነት መክሰስ የጅል ክስ ካልሆነ በቀር ምንም ፋይዳ የለውም። ምን አልባትም አውሮፕላንን ስለምን በአየር በረረ ብሎ የመጠየቅ አይነት ነው። እሳቸውም ቢሆኑ በ 99.6 በመቶ ድምጽ ተመረጥኩ ብለውም አልዋሹም። ጊዜው እንደሚፈቅደው አስገብረው ስልጣን ላይ ወጡ በቃ። ጥያቄው መሆን ያለበት እንደንጉስነታቸው በዘመነ ንግስናቸው ምን አደረጉ ነው እንጂ በስልጣን ላይ ለምን ቆዩ ወይም በስልጣን ላይ ስለቆዩ የስልጣን ጥም አለባቸው የሚል ሊሆን አይችልም።

እስከ ዛሬ አጼ ምኒሊክን የሚወቅሱ ሰዎችን እንሰማ የነበረው የሌሎችን ብሄሮች ማንነት ጨፍልቀው ኢትዮጵያን በማዕከል ከአዲስ አበባ ሆነው አስተዳደሩ ነበር። ዛሬ ደግም ሌላ አዲስ ከዚህ ክስ በተጻራሪ የሚቆም የክህደት ታሪክ እየሰማን ነው። በጣም የሚደንቀው ነገር ሁልቱም ፍጹም ተቃራኒ ክሶች የሚመጡት ከወያኔው ጎራ ነው። መቼም ሁለቱም ክስ በአንድ ጊዜ እውነት ሊሆን አይችልም።

አጼ ምንሊክ የዘመናዊ የተማከለ አስተዳደርን በጊዜው ባላቸው የግንዛቤ ደረጃ ሞክረውት ለቀጣይ ትውልድ አሳልፈው ሄደዋል። እውን አቶ ብስራት አስተዋይ ሰው ከሆነ ከዛ በኋላ ያለው ትውልድ ይኼኛውን ጨምሮ ምን ያህል ከዚያ ወዲህ አደረገ ብሎ ነበር መጠየቅ ያለበት። በወቅቱ የነበረውን ቅጥ የለሽ የመሳፍንት ውጊያ አደብ ያስያዙት አጼ ምኒልክ ናቸው። ሌሎቹ ነገስታት ከዚህ በፊት ሊያደርጉ ያልቻሉትን ነገር ነው ንጉሱ ሊያደርጉ የቻሉት። አሜሪካኖች አብርሃም ሊንከንን በአሜሪካን የርስ በርስ ጦርነት ጊዜ በደቡብዊ የአሜሪካ ግዛቶች በሸንኮራ አገዳ እና ጥጥ እርሻዎች ውስጥ የሚሰሩ ባሪያዎችን ጉልበት ብዝበዛ ማስቀጠል ከሚፈልጉ ግዛቶች ጋር ውጊያ አድርገው የአገሪቷን አንድነት ማስጠበቅ ችለዋል። በአብርሃም ሊንከን ጊዜ ግን ባርነት ነበር ጥቁሮችም በተጻፈ ህግ እንደ 3/4 ዜጋ ነበር የሚታዩት መምረጥም ፤ መመረጥም አይችሉም ነበር። የሆኖ ሆኖ አብርሃም ሊንክንን በባሪያ ንግድም ሆነ በሌላ የሚከስ ጥቁር አሜሪካዊ አይገኝም። ይልቁንም የአሁኑ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የአብርሃም ሊንከን ቀንደኛ አድናቂ እንደሆኑ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው። ፕሬዚደንቱ ወደ ዋሽንግተን ጠቅለው ከመግባታቸው በፊት የሚኖሩባትን ግዛት እና አብርሃም ሊንከን የተወለደባትን ኢሊኖይን ብዙ ጊዜ "የሊንከን አገር" እያሉም ነው የሚጠሯት። ነገሮችን እንደዚህ አገናዝቦ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ልበሰፊነትን ይጠይቃል። በጥላቻ የታሰሩ ፤ ሃሳበ ድውይ የህወሃት መሪዎች ግን ቅንነት በጣም የጎደላቸው ሰዎች ስለሆኑ አጼ ምኒልክ አማራ መሆናቸው ፤ አማራም የትግራይ ጠላት ነው ከሚል ቆሻሻ አመለካከት ውጭ ሌላ ነገር ማሰብ ፈጽሞ አይቻላቸውም።

አጼ ምኒሊክ እንደ አሁኑ የወያኔ ከሃዲዎች አገር በመሸጥ ታምተውም አያውቁም። አንድ ሰው ምን አይነት የአእምሮ ደሃ ቢሆን ነው አጼ ምኒሊክን በአገር መሸጥ የሚወነጅለው? ለዚያውም እንደ ወያኔ አይነት ከሃዲ እና አገር ሸቃጭ። አገሪቷን ወደብ አልባ ያደረገ፣ በሱዳን በኩል 1600ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ለም የአገሪቱን ግዛት ቆርጦ የሰጠ፣ በጋምቤላ ፣ በቤኒሻንጉል ፣ በኦሮሚያ እና በአፋር በዚህ በአሁኑ ሰኣት ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን እያፈናቀለ አገር እየሸጠ ያለ የሌቦች ቡድን ነው አጼ ምኒሊክን በአገር መሸጥ እየወነጀለ ያለው።

በእውነቱ የአጼ ምኒሊክን መልካም ስም እና በጎ ምግባር በጥላሸት የሚለውሱት የህወሃት ከሃዲዎች ዋንኛ መነሻቸው መሰረታዊው የአያቶቻቸው አሳፋሪ የባንዳ ታሪክ ነው። ሌላው ደግሞ ፍጹም በደማቸው የሚዛወረው እጅግ ከፍተኛ የሆነ የበታችነት ስሜት ነው። አጼ ምኒልክ ከኢጣልያ ጋር ለተደረገው ጦርነት "አመልህን በጉያህ፤ ስንቅህን በአህያህ" ብለው ክተት ሲያውጁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊባል በሚችል መልኩ ነው አብሯቸው የተሰለፈው። ሁሉም ኢትዮጵያዊም ዋጋ ከፍሏል። ዋጋ ከፍለው ነጻነት ያመጡትን ጀግኖች ኢትዮጵያውያንን ዘርህ ከዚህ ነው ወይም ከዚያ ብለው ዋጋ አልነሷቸውም።ዋና የሚባሉት የጦር ጀነራላቸውም የዶጋሊው ጀግና ራስ አሉላ አባነጋ ነበሩ። የትግራይ ህዝብ የአጼ ምኒሊክን የጀግንነት ታሪክ ከልብ የሚያደንቅ እና ለመላው የጥቁር ህዝቦች ኩራት በሆነው የአድዋ ድል ታሪክ እርሱም እንደማንኛውም ኢትዮጵያውያን የሚኮራበት እና የሚጠብቀውም ጭምር ነው። የመለስ ዜናዊም ሆነ የከሃዲ ካድሬዎቹ የክህደት ታሪክ በፍጹም የትግራይን ህዝብ አመለካከት ይወክላል ብዬም አላስብምም፣ አላምንምም።

አዎን አጼ ምንሊክ በዛን ወቅት እንደቅጣት ይፈጸም የነበረውን እጅ እና እግር የመቁረጥ ነገር መጀመሪያ አካባቢ ይፈጽሙ ነበር። ይህን ያደርጉ የነበረው እሳቸው ብቻም አልነበሩም። አጼ ቴዎድሮስም ይህን ያደርጉ ነበር አጼ ዮሃንስም ይህን ያደርጉ ነበር። ንጉስ አሊም የሳቸው ልጅ የሆነችም ንግስት መነንም ይህን ያደርጉ ነበር። ነገሩ የዘመኑ የፍትህ አሰጣጥ ኋላ ቀርነት እንጂ የሰዎቹን የክፋት መጠን አይገልጽም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ግን በፍጹም አጼ ዮህንስንም ሆነ አጼ ቴዎድሮስን በክፉ ሲያነሱ ሰምቼም አንብቤም አላውቅም። ይህ ሊሆን የቻለም ምናልባትም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ታሪክን በታሪክነቱ ለመረዳት ስለመረጡ ይሆናል።

ይህም ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ቅጣት በአዋጅ ያስቀሩት አጼ ምኒልክ ነበሩ። ታዲያ የታለ ለዚህ በጎ ስራቸው ክብሩ?? የህወሃት ከሃዲዎች እውነት እና ክብር የት ያውቁና?!

የባንዳ ልጆች ምን ያህል በአያቶቻቸው እንዲሁም በአባቶቻቸው ታሪክ ቂም ይዘው ይህን ህዝብ እና አገር እንደሚያሰቃዩ የግለሰቦቹን ቀዳሚ የቤተሰብ ታሪክ በማየት መገንዘብ ይቻላል። የስርዓቱ ቁንጮ እና የክህደቱ ዋና መሪ መለስ ዜናዊ የሚያስተዳድረውን ህዝብ እና አገር ባለፈ ባገደመ ቁጥር የሚዘልፈው ወዶ እንዳይደል የትግራይም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም ሊገነዘብው ይገባል።

ከታች በአቶ መለስ ዜናዊ መኖሪያ ቤት በኩራት ተሰቅሎ በልጅነት ዘመን ያየሁት እና ዛሬ በዘመን አመጣሹ ኢንተርኔት ተበትኖ ከብዙ አመታት በኋላ እንደገና ለማየት የበቃሁትን የአቶ መለስ ዜናዊ የክህደት መሰረት የሆኑት የአያቱ የባሻ አስረስን ፎቶ ለአስረጅነት ከዚህ አያይዣለሁ። ጀግኖች ዱር ቤቴ ብለው ለአገር ነጻነት ሲዋደቁ እሳቸው ከወራሪው ሰራዊት ወታደር ጋር በኩራት ካባ ደርበው ይታያሉ።

የታሪክ ክህደት ቁጥር 3

<<በ1881 ዓ.ም. ዮሃንስ ከሞቱ በኋላ የትግራይን ህዝብ ኑሮና የወደፊት ዕጣ የጎዳ ድርቅና በሽታ በድንገት ተከሰተ። እስከ ዛሬ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ የእያንዳንዱ ቤተሰብ የቁም ከብቶች እንዳለ አለቁ። ከቁም ከብቶች ባለፍ የዱር አራዊት የመሞት ምክንያት በምኒሊክ ከተተገበረ የኢጣልያ እቅድ መመንጨቱን የሚጠረጥሩ አሉ። ይህ ዕቅድ አፍሪካውያንን በበታችነት ከሚቆጥሩ የአውሮፓ ሃያላን አገራት ኢጣልያን በመቋቋም ላሳየው ቆራጥ ድፍረት የትግራይ ህዝብ ለመቅጣት የታቀደ እንደነበር የሚያምኑ በርካታ ናቸው።>>[10]

አቶ ብስራት እንዳሉት በዘመኑ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ መጥቶ እንስሳቱን ፣ አራዊቱን እና ሰዉንም ጭምር አጥቅቶ እንደነበር የተዘገበ የታሪክ ኹነት ስለሆነ እሱ ላይ ክርክር ማንሳት አልፈልግም። ነገር ግን ከልጅነት ጀምሮ አባቶቻችን እንደነገሩን ይህ ድርቅ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመልከዓምድራዊ አቀማመጥ በአብዛኛው ተመሳሳይ በሆነው በወሎ ፣ በጎጃም ፤ በዛኔው አጠራር በበጌምድር እንዲሁም በኤርትራም ጭምር ነበር የተከሰተው። ታዲያ ለዚህ የተፈጥሮ ክስተት እንዴት ሆኖ ነው አጼ ምኒሊክ ሊጠየቁ የሚገባው?? የእርዳታ ገንዘብ አሸዋ እየሞሉ እህል ነው ብለው ሸጠው ገንዘብ አልሰበሰቡ። እሳቸው የህፃናትን ነብስ ለማዳን ተብሎ ከውጪ ለጋሾች የተላከን ብር በትግራይ ህጻናት ነብስ ላይ ተረማምደው አልበሉት። የተለገሰውን እህል በየመንገዱ ከምረው ህዝብ በረሃብ እያለቀ እንዲበሰብስ አላደረጉ። ወይም የተለገሰውን እህል በመኪና እየጫኑ ወደሱዳን እና አረብ አገራት ወስደው አልቸበቸቡት[11]። እንደው በምን የንጉሱን መልካም ስም ላጉድፍ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?? በጣም የሚገርመው ደግሞ ከጣሊያን ጋር ተባብረው ይላል። ምን ብለው ነው የሚተባበሩት?? እባክይ የጣሊያን መንግስት ሆይ በቫቲካን ያሉት ፖፕ ለእግዚያብሄር ትግራይ ላይ ዝናብ እንዲያቆም ጸልዩ ብለው ነው ወይስ ሌላ ጣልያኖች የሚያውቁት ዝናብ ማቆም የሚይስችል ተዓምር ነበራቸው?? በኢትዮጵያ ከዚያም በፊትም ሆነ በኋላ የዝናብ መዛባት እና ድርቅ እንግዳ ነገር አይደለም። እናስ በቅርብ ጊዜ የታዩትን ተከታታይ የድርቅ እና የተፈጥሮ መዛባት ክስተቶች አጼ ምኒሊክ ከሞቱ ከ100 ዓመት በኋላ ማነው ያስከሰታቸው? የንጉሱ መንፈስ?? እንኚህ ናቸው እንግዲህ ሚኒስቴርም ፣ ኮሚሽነርም ሆነው አገር እያስተዳድሩ ያሉት። በትግሪኛ አንድ ተረት አለ "ልማደኛ ሓሳውስያ በቕሊ ቀርኒ አውፂኣ ኢሉ ይምስከር" ወደ አማርኛ ስመልሰው "ልማደኛ ውሸታም በቅሎ ቅንድ አወጣች ብሎ ይመሰክራል" ማለት ነው። ብስራት አማረ እና የህወሃት መሪዎች በምን አይነት አፀያፊ የውሸት ጥበብ እንደተካኑ በግልፅ የሚያሳይ ነው። የትግራይ ህዝብ ዛሬ ከውስጡ በወጡ አሪዎሶች አፉ ተለጉሞ ቢያዝም የሚሆነውን እና የሚባለውን በአይኑ እያየ በስሙ ሲነገድ እና አገር ሲሸጥ አይቶ እንዳላየ ሆኖ እንደ ሌላው ወንድሙ ቀን እስኪወጣ እየጠበቀ ቢሆን እንጂ ይህን የተጨማለቀ የህወሃትን ስራ መቼም ቢሆን ትክክል ብሎ ይቀበላል የሚል እምነት ኖሮኝ አያውቅም።

የታሪክ ክህደት ቁጥር 4

<<የሃሰት ታሪክ በመመንዘር የሃገሪቷን ታላቅ ቅርስና ትክክለኛ ገጽታም መሸርሸር ችለዋል።የማህበረሰቡ አብዛኛው ክፍል ማንበብ እና መጻፍ በማይችልበት ሁኔታ ታሪክን ጠምዝዞ በመቸርቸር ፈጠራው የተሳካና እውነተኛ እንዲመስል አድርጎት ቆይቷል። ያለመሰረታዊ ማስረጃ ብዙ መጻህፍት ተጽፈዋል።እንደ እውነተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ተደርጎ ታዳጊ ህጻናት በትምህርት ቤቶች ተረታ ተረት ተምረውበታል። እነዚህ ሁሉ ለሸዋ ገዢዎች ዙፋን መጠናከር ታሳቢ ያደርጉ ከእውነት የራቁ ተረቶች መሆናቸው ግን አልቀረም ። በአሜሪካ ላይብራሪ ኦፍ ኮንግረስ ምርምር ዋና ክፍል ኢትዮጵያ የተዘጋጁ ጥናታዎ ጽሁፎች ሃሰቱን በተመለከት ያረጋግጡታል።>>

ይልና አንድ ከኋላ ኪሱ አውጥቶ የጻፈው የሚመስል ከእንደርሱ አይነት ጭንቅላት እንጂ ከአንድ የታሪክ ተመራማሪ አእምሮ የወጣ በማይመስል አጻጻፍ የተጻፈ ጽሁፍ በትምህርተ ጥቅስ አድርጎ ያስቀምጣል። በጥቅስ የተቀመጠው ጽሁፍ ሳይቴሽን ስላለው በጉጉት የጽሁፍን ምንጭ ለማየት ወደ መጽሃፉ የመጨረሻ ገጾች ላይ ሄድኩኝ። ያገኘሁት ሳይቴሽን ግን እንዲህ ይላል:-Ethiopia: a county study, p. 91. መቼም ጉድ ነው። አንድ የታሪክ ምርምር ለዚያውም ከአለማችን ትልቁ በሆነው የኮንግረስ ቤተ መጻህፍት የተደረገ ምርምር እንዲህች ያለች ኩርማን ለመጀመሪያ አመት የኮሌጅ ተማሪ የሳምንት የቤት ስራ እንኳን የማትበቃ ርዕስ ተሰጥቶት ሊሰራ ይችላል ብሎ ሰው ያምናል ማለቱ ያው የተለመደው የህወሃት ሰው መናቅ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላ። ለነገሩስ የክህደቱ ጳጳስ መለስ ዜናዊስ አፉን ሞልቶ የአድዋ ድል የነፍጠኛው ተረት ተረት ነው ብሎስ አልነበር። ከፕሮፌሰር መስፍን አማርኛ ልዋስና ሰዎቹ የለየለት የክህደት ቁልቁለት ላይ የተቀመጡ ስለሆነ ለማያውቃቸው እንጂ ለኛማ ከበቁን ዘመናት ተቆጠረ።

ወደ ዋናው የክርክሬ ጭብጥ ልመለስና በአብዛኛው በኢትዮጵያ በጽሁፍም ሆነ በአፈ ታሪክ ያሉ የቅርብ ጊዜ ታሪኮቻችን የትርጉም ካልሆነ የኹነት ክርክር ሊያስነሳበቸው የሚችል ጉዳይ የለም። ይህም የሆነው ከበቂ በላይ በአገር ውስጥ የታሪክ ጸሃፊውችም ፤ አውሮፓውያንም ጭምር የተጻፈባቸው በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይህን "ተረታ-ተረት" ለማለት ወኔው ካለህ ለፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ ፈልገህ ንገራቸው። ማሞ ቂሎ እንደሆንክ በትህትና ነገረው ይመልሱሃል።

የኢትዮጵያን ታሪክ ሞቅ ሲል ማናናቅ የመቶ አመት ነው ማለት ፤ ሲቀዘቅዝ ደግሞ ኑ 2ሺኛውን ዘመን እናክብር ብሎ ማላዘን የወያኔ መገለጫ ባህሪ ነው። ታሪክ እንዲህ አንድ መደዴ መሃይም ካድሬ እንደፈለገ የሚሰቅለውና የሚያወርደው ጉዳይ አይደለም። ይልቁንስ የታሪክ ምርምር ለሙያው የበቁ ሰዎች ማስረጃ እያጣቀሱ ለብዙ ጊዜያት በአንድ የጋራ አተረጓጎም ላይ እስኪሰክኑ ድረስ ከግል የፖለቲካም ሆነ ጊዜያዊ የስሜት ጥቅም ታቅበው የሚሟገቱበት ውስብስብ ሳይንስ ነው። እንደ ወዲ ዜናዊ እና አቶ ብስራት ያሉ የታሪክ አሽክላዎች ግን ገና ለገና እነሱ ከቤተሰባቸው የኋላ የባንዳ አሳፋሪ ታሪክ ከመነጨ ከፍተኛ የበታችነት ስሜት ተነስተው ጠላት ነው የሚሉትን አማራውን ህዝብ አንገት እናስደፋለን ብለው መሬት ጠብ የማይል የታሪክ ቡትቶ አምጥተው አቧራቸውን ያቦኑብናል።

የታሪክ ክህደት ቁጥር 5

<<የአድዋ ጦርነት የምኒሊክን ታሪክ ትልቅ ሰው አስመስሎ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ብሔርተኛ እና ጀግና መሪ በምትፈልግበት ወቅት ያለ ቦታው የተገኘ (ሰረዝ የተጨመረ) ሰው ምኒሊክ ወደደም ጠላ የአድዋ ጦርነት የማይቀር ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር። ምኒሊክ ግዛቷ የተቀናነሰ አነስተኛ ኢትዮጵያ አጼ ብቻ ተብሎ ለመንገስ እቅድ እንዳለው ጣልያኖች አስልተው ደርሰውበት ነበር። አዲሱ ታዛዣቸው(ሰረዝ የተጨመረ) ሀገሩን በማስከበር ረገድ እንድ ዮሐንስ ሃገር ወዳድ አለመሆኑን ተገንዝበዋል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውን የጥንት እና ህዝቦችዋ ለነጻነት ያላቸውን ቀናኢነት ታሳቢ ሳያደርጉ በምኒልክ ፍርሐት እና ስግብግብ ተፈጥሮ(ሰረዝ የተጨመረ) ብቻ ሀገሪቷን በቅኝ አገዛዛቸው ስር ለማስገባት ያነሳሳቸው ስሌት ለውድቀትና ሽንፈትም ዳርጓቸዋል። የራስ አሉላና ሌሎች ጀግኖች በህይወት መኖር ሌላው የጣሊያኖች የተሳሳተ ስሌት አድዋ ላይ ራሳቸውን አዋርደዋል። የአድዋን የአንድ ቀን ጦርነት በድል ለመፈጸም መረጃዎች ወሳኝ እንደነበሩ ይታወቃል በረቀቀ የጦርነት ጥበብና ወታደራዊ ታክቲኮች ከሁሉም የኢትዮጵያ ጠላቶች ልቀው የተገኙት አሉላ የኢጣልያ ሽንፈት አድዋ ላይ ዳግም እውን እንዲሆን ጥሩ አጋጣሚ ሆነዋል።>> [12]

መቼም ህወሃት ከሁለት አስርት አመታት በላይ ጆሮ ሰጥቶ ለሰማኝና ላዳመጠኝ ሁል ምን ያህል በውሸት የሰከረ አደገኛ ቡድን እንደሆነ ለማስረዳት የቻልኩትን ያህል ሞክሬያለሁኝ። ተራው ታጋይ በእንደ ወዲ ዜናዊ እና ብስራት አማረ ባሉ ፍጹም አደገኛ አወናባጆች እና ከሃዲዎች እየተነዳ ነው የአገር ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ታሪክም ፤ የአገራችን ኢትዮጵያም ክብር እና ሉኣላዊነትም አደጋ ላይ የወደቁት።

በምኒሊክ፣ በአጼ ሃይለስላሴ ጊዜም ሆነ በደርግ ወቅት አጼ ዮሃንስን እና ራስ አሉላ አባነጋን በመደበኛው የታሪክ ስርዓተ ትምህርትም ውስጥ ሆነ በአፍአዊ የታሪክ ትምህርት ከጀግንነታቸው እና አገር ወዳድነታቸው በቀር በክፉ ስማቸውን የሚያነሳ ኖርም የሚያውቅ አይመስለኝም። ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነውና ውስጡን በርብረን እናውራ ቢባል ግን ምንም ረብ የለሽ እንከን ማውጣት ይቻላል። ያ ግን ጥቅም የለውም። ይልቁንስ ታሪክ ለትውልድ መኩርያ እና አቅጣጫ ማሳያ ነውና ለበጎ ታሪካችን ተገቢውን ቦታ ሰጥተን መንከባከብ ተገቢ ነው። ለደንቆሮው አቶ ብስራት ግን ጀግና ለመባል አንድ ሰው ከትግራይ መምጣት አለበት። ታሪኩ ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ ህወሃት የስልጣን መንበሩ ላይ እስኪወጣ ድረስ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞውን የምኒልክ የጦር መሪ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴን ፣ ኦሮሞውን ጀግና አብዲሳ አጋን ፣ የትግራዩን ጀግና ዘርኣይ ደረስን ፣ የትግራዩን ጀነራል ራስ አሉላ አባነጋን ፣ ዛሬ ዛሬ በኤርትራዊነት የሚመደቡትን ነገር ግን ያኔ በኢትዮጵያዊነት መስዋትነት የከፈሉትን አብርሃም ደሞጭ እና ሞገስ አስገዶምን ጀግንነታቸውን ሲያከብር ፣ ሲዘክር እና ሲያስብ ነው የኖረው። አጼ ዮሃንስን ጀግና ብሎ አጼ ምኒልክን ፈሪ ለማለት መከጀል ከፍጹም ዘረኝነት የዘለለ ሌላ ትንታኔ ሊሰጠው አይችልም።

ከዚህ ዘባተሎ የታሪክ ክህደት በፊት የምኒሊክን የአድዋ ድል ወሳኝ አመራር ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባ መጽሃፍም ይሁን ንግግር ሰምቼም አላውቅም። ስለ አጼ ምኒሊክ የጦር ስትራቴጂ አወጣጥ እና አመራር ብዙ የተጻፈለት እና የተነገረለት በመሆኑ ለዚህ ተራ እና የወረደ ቅጥፈት ማስተባበያ ለመስጠት ጊዜ አላጠፋም። ይልቁንስ ከላይ ስላሰመርኩባቸው ጉዳዮች ትንሽ ልበል። "ያለቦታው የተገኘ ሰው" ምን ማለት ነው??እናስ ጣልያን አገር ሲወር ሸዋ ላይ እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጥ ነበረባቸው ማለት ነው? ሻዕቢያ ባድመን ሲወር እዛ ሊዋጋ የመጣው ኢትዮጵያዊ መምጣት አልነበረበትም ማለት ነው?? እንደዚህ ነው ለአገር ነጻነት ለመሞት የመጡ ኢትዮጵያውያንን የትግራይ ህዝብ የሚያመሰግነው?? መቼስ ነው በታሪክ አጼ ምኒሊክ የጣሊያን ታዛዥ ተብለው የሚታወቁት?? በአድዋ ድል የተደመደምው ጦርነት የተጀመረውስ የኢጣልያ መንግስት የውጫሌ ውል አንቀጽ አስራ ሰባትን የአማርኛውን እና ጣሊያንኛውን ትርጉም አዛብቶ በማቅረቡ ለውሉ አልገዛም በማለታቸው አልነበረምንም?? ተስማምተው ለፈረሙት ውል አልገዛም ፤ አይን ያወጣ ማጭበርበር መኖሩን ሲያውቁ በዘመናዊ ወታደር እና መሳሪያ ለታጠቅ አውሮፓዊ ሃይል እምቢ ከማለት በላይ ምን ጀግንነት አለ። አዎን ለእውነት ፣ ለነጻነት ፣ ለሉአላዊነት ከመቆም በላይ ምን ጀግንነት አለ?? አዎን የህወሃት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት የድንበር ማካለያ ኮምሽን በባድመ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ባድመ ለኛ ተወሰነች ውጡና ጨፍሩ ብሉ ህዝቡን ከበሮ ሲያስደልቅ አልነበረም ወይ?? ኋላ ላይስ በርግጥም ባደመ የተካለለችው ወደ ኤርትራ መሆኑ ግልጽ ሲሆን ከዚህ በኋላ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ የሞተለትን ጉዳይ ለቁራጭ መሬት ብለን ጦርነት አንገባም ያለው ወዲዜናዊ አልነበረም ወይ?? ይሄኮ ከመቶ አመት በፊት የሆነ ጉዳይ አይደለም። ሁላችንም በህይወት አለን።
እኔ መቼም አውሮፓዊ ቅኝ ገዢን ያለፍርሃት በጀግንነት ተጋፍጦ በነጻነት ያቆየውን ሰው "ዘር" ቆጥሮ አማራ በመሆኑ ብቻ እንደምን ሊያኮሰምን ይፈልጋል?? እኔ በበኩሌ ይሄ አስከፊ የጥላቻ ደዌ ከመሆን ያለፈ ምንም ምክንያት ላገኝለት አልቻልኩም።

"በምኒልክ ፍርሐት እና ስግብግብ ተፈጥሮ" አጼ ምኒሊክ በየትኛው ማስረጃ በፍርሃት እና በስግብግብነት ተወንጅለው እንደሚያውቁ አንብቤም አላውቅ። ንጉሱ ገና በልጅነታቸው የሸዋው ንጉስ ልጅ በመሆናቸው ለስልጣኔ ያሰጋኛል በማለት ይመስላል አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ አስረዋቸው ነበር። ታዲያ የያኔው አቤቶ ምኒሊክ በኦሮሞዎቹ የየጁ ንጉስ አሊ እና ንግስት ወርቂቱ ትብብር ከአስቸጋሪው የአጼ ቴዎድሮስ የመቅደላ እስር ቤት አምልጠው ነው ወደሸዋ በመመለስ የሸዋ ንጉስ ተብለው የተሰየሙት። መቼም እንደ አጼ ቴዎድሮስ ተፈሪነት ከሳቸው እስር ቤት ለማምለጥ መሞከር የማይታሰብ እና ብዙዎች ሞክረው ያልሆነላቸው ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው የየጁ ኦሮሞው ራስ አሊ እና የወሎዋ ንግስት ወርቂቱ ትብብር እና ድጋፍ ታክሎበት ነው አቤቶ ምኒልክ ከመቅደላ አምልጠው ሊወጡ የቻሉት። መቼም ይሄ የፈሪ ስራ አይደለም። አጼ ቴዎድሮስ ያሰሯቸውን አውሮፓዎያንን ለማስለቀቅ እኮ የእንግሊዝዋ የወቅቱ ንግስት ቪክቶሪያ በጀነራል ናፒየር የሚመራ ብዙ ሺህ ጦር መላክ አስፈልጓት ነበር።

ይልቁንስ አጼ ምኒልክ የሚታወቁት ድርቅ ሲመጣ ግብር በመቀነስ እና በፍትሃዊነታቸው ነው። መቼም ከእንደ ብስራት አይነቱ የህሊና ደሃ እና ሃሳበ ጉድጉድ ግለሰብ ካልሆነ በቀር አጼ ምኒሊክን በስግብግብነት መወንጀል ይቅር የማይባል ቅጥፈት ነው። እንዲያው ለመሆኑ አቶ ብስራት ስግብግብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግክ "ስግብግብ" ማለት አሁን ልክ በኢትዮጵያ በወያኔ አገዛዝ እየሆነ እንዳለው ነው። ሰዎች በረሃብ እየረገፉ ባሉበት አገር የስርዓቱ ቁንጮዎች በርዳታ እና ብድር ወደ አገር ከሚገባው ገንዘብ ውስጥ ከ11.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በተለያየ መንገድ ከአገር ማሸሽ ፤ ገንዘብ ተገኘ ተብሎ ቅዱሱን የጉዲፈቻ ባህል በመቶ ሚሊዮን ዶላር ወደሚያስገኝ የመበልጸጊያ መንገድ መቀየር፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ሳውዲ አረቢያ ብቻ ሴት ኢትዮጵያውያንን በወር እስከ 45,000 ከፍተኛ ስቃይ እና እንግልት እንደሚደርስባቸው እየታወቅ ወያኔ ገንዘብ ስለሚያገኝበት ብቻ መላክ፤ ሰፋፊ የአገሪቷን የ እርሻ መሬቶች ገንዘብ ተገኘ ተብሎ ለአረብ እና ህንድ ባለሃብቶች መቸብቸብ ነው መስገብገብ ማለት።

ሰዎች ስለ አጼ ምኒሊክ ታሪክ መስማት ካለባቸው ከበቁ የታሪክ ጸሃፊዎች እንጂ ከካድሬ ለዚያውም ከህወሃት ካድሬ መሆን የለበምትም። ስለ አጼ ምኒሊክ ታላቅነት ታላቁ ኬኒያዊ ምሁር እና የታሪክ ተመራማሪ አሊ ማርዙዪ የምኒሊክን ታላቅነት ከባራክ ኦባማ መመረጥ ጋር አያይዘው በአሜሪካ በሚተላለፈ "ዲሞክራሲ ናው" ቴሌቪዢን ከአዘጋጇ ኤሚ ጉድማን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በዋቢነት ከዚህ ገጽ ግርጌ ያለውን ሊንክ ጠቅ በማድረግ ይመልከቱ።[13]

የአድዋ ድል አኩሪ ታሪክ በምኒሊክ ወሳኝ አመራር፤ በጦር መሪዎቻቸው ብቁ እና ቆራጥ ፊት አውራሪነት እንዲሁም በብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ቆራጥ ተጋድሎ እውን የሆነ ድል ነው። አጼ ምኒሊክ በጦር መሪነት ካሰለፏቸው ኢትዮጵያውያን ውስጥ ጣይቱ ብጡል፣ ራስ ወሌ ብጡል ፣ ራስ መንገሻ አትከም፣ ባሻይ ሓጎስ ፣ ራስ አሉላ አባነጋ ፣ ራስ መንገሻ ዮሃንስ ፣ ዋግሹም ጓንጉል ፣ የወሎው ራስ ሚካኤል ፣ ደጃዝማች ሰንጋል ፣ ራስ መኮንን ፣ ራስ ገበየሁ፣ ራስ ስብሃት ፣ በጅሮንድ ባህታ ገሰሰ ፣ የጎጃሙ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት ተሰማ እንዲሁም ደጃዝማች ገሰሰ ይጠቀሳሉ።

ከወያኔ በፊት የትኛውንም ድል በተለይ እንደ አድዋ ያለውን በውጭ ወራሪዎች ላይ የተገኘን ታላቅ ድል የኢትዮጵያ ነገስታት "የኢትዮጵያውያን ድል" ከማለት በዘለለ የአማራ ፣ የትግሬ ወይ የኦሮሞ ድል ብለው አሳንሰውም አያውቁም። ያ ደግሞ ትልቅነታቸውን እንጂ አቶ ብስራት እንደሚወሸክቱት የነገስታቱን ክፉ ጎን የሚያሳይ ጉዳይ አይደለም።

እርግጥ ነው አገር ተወሮ ፣ ነጻነት ተደፍሮ ፣ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት ለጠላት አድረው አገር ሲያስወጉ ፤ መረጃ ሲያቀብሉ ፤ መንገድ ሲመሩ ፤ ወገን ሲፈጁ እና ሲያስፈጁ በነበሩት ላይ የጊዜው የፍትህ ስርዓት በሚለው መሰረት እርምጃ ተወስዷል። የ እርምጃዎቹ ተመጣጣኝነት ላይ ክርክር ማንሳት ይቻል ይሆናል። ነገር ግን አገር ክህደት አሁንም ድረስ በየትኛውን አገር ከፍተኛ ወንጀል ነው ከፍተኛውንም ቅጣት ያስጥላል። ለዘመናት ሲባል እንደ ነበረው እኛም ፤ አባቶቻችንንም ምናልባትም አያቶቻችንም ለጣሊያን እንቁላል እየገበርን በገዛ አገራችን በባርነት እንቀር ነበር። ከነተረቱስ እንደዚህ አይደል የሚባለው :- "ምኒሊክ ተነስቶ ባያነሳ ጋሻ ፤ ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ።"

የታሪክ ክህደት ቁጥር 6

ጸሃፊው አጼ ምኒሊክን በቀጥታ እንዲሁም አጼ ኃይለስላሴን ደግሞ የንግስና ዘመናቸውን በመጥቀስ በባሪያ ንግድ የበለጸጉ አድርጎ ይወቅሳል። እስቲ ይህን ጉዳይ ያነሳበትን አንቀጾች እያነሳው የራሴን ምላሽ ልስጥ።

<< ስለኢትዮጵያ በርካታ ጥናቶች ያካሄዱ የታሪክ ተመራማሪዎች እና ጸሃፊዎች ምኒሊክን ለዚህ ተግባሩ <<የኢትዮጵያ የባሪያ ንግድ ድርጅት ባለቤት>> ማለታቸው አልተሳሳቱም።>>[14]

<< እነዚህ ብሔረሰቦች ፍትህ የማግኘት መብት የተነፈጉና በአብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች ተደርገው የማይታዩ ነበሩ። በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎችም በጎንደር እና ጎጃም መስመር ፣ መተማ ፣ አርማጭሆ በተባሉ ስፍራዎችና በተወሰነ መጠን ከአርማጭሆ ጋር በሚዋሰኑ የወልቃይት ምዕራባዊ ክፍሎች የባሪያ ንግድ ሲካሄድ እስክ 1960ዎቹ ታይቷል። በታሪካዊ እይታ በክርስቲያን ኢትዮጵያ ማህጸን ውስጥ መጀመሪያ በ1850ዎቹ እ.ኤ.አ በምኒሊክ አባት በሃይለመለኮት በመጨረሻም እስክ ህልፈቱ ድረስ በዓጼ ምኒሊክ የባሪያ ንግድ ስራ የሸዋ ገዢዎች ቅርስ መሆኑ ታውቋል።>>[15]

በኢትዮጵያ ታሪክ ባሪያ ፍንገላ እንደነበረ ማንም የሚክደው ሃቅ አለነበረም። በጠራ ሁኔታ አጼ ምኒልክን ዋና ባሪያ ፈንጋይ አድርጎ የሚከስ ታሪካዊ ማስረጃ የለም። እርግጥ ነው እሳቸው ወደ ስልጣን መንበር ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ ለዘመናት ይካሄድ የነበረው የባሪያ ፍንገላ በዘመናቸውም ቢሆን ይካሄድ ነበር። ለዛ ደግሞ በቀጥታ እሳቸውን ተጠያቂ አድርጎ ማቅረቡ እምብዛም የሚያስኬድ ጉዳይ አይደለም። በኢትዮጵያ በአብዛኛው ይካሄድ የነበረው የባሪያ ስርዓት በአሜሪካ እና አውሮፓውያን ሰፋፊ የሸንኮራ ፣ ጥጥ እና ሻይ ቅጠል እርሻዎች ውስጥ በነጻ ጉልበት ማሰራት አልነበረም። ይልቁንም በመሳፍንቱ እና መኳንንቱ መኖሪያ ቤት የቤተሰቡ አባላት ሊሰሩ የማይፈቅዱትን የግርድና ስራዎች ማጽዳት ፣ ማብሰል ፣ እንዲሁም ቤት መጠበቅን የመሳሰሉ ስራዎችን ነበር የሚሰሩት። ይህም ቢሆን ባርነት ነው ና በምንም አይነት ማህበረሰቡ ሊያደርገው አይገባም ነበር።

ለማጣቀሻነት የአፊካን ሆሎኮስት የሚባል በአፍሪካ የተደርጉ እልቂትን ያስከተሉ ታርካዊ ክስተቶችን የሚመዘግበው ድረ ገጽ ላይ ያለውን በኢትዮጵያ ስለነበረው የባሪያ ፍንገላ ስርዓት የተጻፈውን ለአንባቢያን ከዚህ ገጽ ግርጌ አስቀምጫለሁኝ።[16]

ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴን በሚመለከት በዚህ ጉዳይ ላይ ክስ ማቅረቡ የሞኝ ክርክር ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ገና ከመንገሳቸው በፊት እና በንግስት ዘውዲቱ የንግስና ዘመን በ1924 ልዑል አልጋ ወራሽ እያሉ ነው የባሪያ ፍንገላን በህግ በኢትዮጵያ እንዲታገድ ያደረጉት። ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ይህን ከማድረጋቸውም በፊት የባሪያ ፍንገላ በኢትዮጵያ እንዲቀር ከሳቸው በፊት የነበሩት ነገስታት አጼ ምኒልክን ጨምሮ የራሳችውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ልክ በባሪያ ንግድ እንደከበሩ አድርጎ የነገስታቱን መልካም ስም በጭቃ ለመለወስ የፈጠራ ክስ ለማቅረም መሞከር ከንቱ ልፋት ከመሆን አያልፍም።

እስቲ አጼ ኃይለስላሴ እ.ኤ.አ በ1963 በአሜሪካን አገር ታዋቂ በሆነው የሲቢኤስ ቴሌቪዢን ሚት ዘ ፕሬስ ፕሮግራም ላይ የዛሬዋ ታላቋ አሜሪካ የራሷን ዜጎች በእኩል አይን በማታይበት ወቅት ስለ የቆዳ ቀለም ልዩነት የተናገሩበትን ታሪካዊ ቃለ ምልልስ ቁራጭ ቪዲዮ ይመልከቱ[18]

ይልቅስ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ህጻናትን በማደጎ ስም በመሸጥ እየከበረ ያለው ማነው?? ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በግርድና ስም በየአረብ አገራት እየላከ ገንዘብ እየሰበሰበ እየከበረ ያለው ማነው?? አዎን ስሙን ሲያሳምሩት "ቻይልድ ትራፊኪንግ" ይሉታል ነገር ግን ዘመናዊ የባሪያ ፍንገላ እንጂ ሌላ ስም ሊሰጠው አይገባም። የወያኔ መንግስት በአንድ ህጻን እስክ 30,000 ዶላር ድረስ እየሰበሰበ እንደሚገኝ በ2007 በወጣ አንድ የኤቢሲ ቴለቪዥን ዘገባ መሰረት የመለስ መንግስት በአመት እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ከዚሁ አጸያፊ የህጻናት ንግድ እንደሚያገኝ የተዘገበ ጉዳይ ነው።[19]

አርማጭሆ እና መተማ አካባቢ ያለፈጠረ ታሪክ ይዞ መልከስከሱ ጉዳዩ ሌላ ነው። በአካባቢው ለዘመና ኗሪ የሆኑ የጎንደር ክፍለ ሃገር አማሮችን አፈናቅለው ሲያበቁ ቦታውን ወደትግራይ ከማካለል ጋር የተያያዘ ታሪክ ፍብረካ ወያኔያዊ አጉል ብልጣብልጥነት ከመሆን አያልፍም።

ልብ በሉ በንጉሳውያኑም ሆነ በጨካኙ የመንግስቱ ኃይለማሪያም ዘመን ያልነበረ እና በአሁን የወያኔ አገዛዝ እጅግ እየተስፋፋ የመጣው ለአቅመ አዳም ያለደረሱ የለጋ ህጻናት የወሲብ ብዝበዛ ንግድ እና ማዘዋወር ስለ ህጻናት ጉዳይ የሚቆረቆሩ ግብረሰናይ ድርጅቶችንም ሆነ ኢትዮጵያውያንን እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ነው። ታዲያ እነዚህ የታሪክ አተላዎች ናቸው በበጎ አሳቢነት እና በቅን ፍላጎት ነጻነት ለማስጠበቅ ፣ አገር ለማሳደግ ፣ ስልጣኔ ለማስፋፋት የለፉ ፣ የተጉ አባቶቻችንን ባልተገራ የባለጌ አፋቸው የሚሰድቡ።[21]

የታሪክ ክህደት ቁጥር 7

<<በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አስርት አመታት አብዛኛዎቹ የባሪያ ንግድ ሰለባዎች ከአናሳ ብሔረሰቦች ወይም የስራ እድል ለማግኘት ከሌሎች ክልሎች ከሚጓዙ ህዝቦች የተገኙ ነበሩ። በአገሪቷ ደቡባዊ እና ሰሜን ምዕራብ የተከሰቲት ያልታወቁ ሰብዓዊ ሰቆቃዎች ታሪካዊ ምርመራ ለሚያካሂድ ሰው በርካታ ግፎች ፈልፍሎ እንዲሚወጣ ይታመናል። ከሃምሳ አመታት በላይ ሃገሪቷን በጭካኔ የገዛው የመጨረሻው ንጉሰ ነገስት ኃይለስላሴ ይህ ድርጊቱ ቢያንስ በታሪክ ሳያስጠይቀው አልቀረም።>>[22]

በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመናዊ መንግስት የማቋቋም ሙከራ በአጼ ምኒልክ ከተደረገ በኋላ በዘመናዊ መንገድ አገራችንን ለማስተዳደር የበቃ መንግስታዊ መዋቅር እና መተክል ማድረግ የቻሉት አጼ ኃይለስላሴ ነበሩ። አጼ ኃይለስላሴ ለዘመናዊ ትምህርት የሚሰጡት ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነበር። ስለዚህም ብዙ ኢትዮጵያውያንን በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ልከው ዘመናዊ አስተዳደርን በአገር ለማስፋፋት ይህ ነው የማይባል ጥረት አድርገዋል።

አገራችን በዚህ ረገድ መልካም መሰረት ተጥሎ ወደፊት እየተራመደች በነበረችበት ወቅት ቂመኛው የፋሽስት ኢጣሊያ መንግስት ዳግም ኢትዮጵያን በቅኝ ለመያዝ እ.ኤ.አ በ1935 ወረራ ፈጸመ። በወረራው እና በቀጣይም በአምስቱ አመት የጣሊያን አገዛዝ ዘመን ብዙ የተደረጉ ግስጋሴዎች ወደኋላ ተመለሱ። በ1941 ፋሽስት ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ስትባረር አገሪቱ እንደገና ከጦርነት ድቀት አሃዱ ብላ መጀመር ግዴታዋ ነበር።

እ.ኤ.አ ከ1941 እስክ 1974 ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በግርግር ከስልጣን እስኪወርዱ ድረስ ለ33 አመታት አገሪቷን ለመገንባት እና ትምህርትን ለማስፋፋት ይህ ነው የማይባል ጥረት አድርገዋል። በዚህ አገር የመገንባቱ ጥረት ንጉሱ በየግዛቱ ያሉ መሳፍንትን ስርዓት ከማስያዝ ይልቅ በማባበል እና በማስታገስ ለመያዝ መሞከራቸው የኋላ ኋላ ለህዝብ ቁጣ ማየል እና ለስርዓቱ መናድ አስተዋጽኦ ማድረጉ አይካድም። ይሁን እንጂ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ በየ አስተዳደር ፊናቸው ለፈጸሙት በደል ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ተጠያቂ ማድረግ አላዋቂነት ከመሆን ያለፈ ትርጉም የለውም። መከሰስ እና መጠየቅ ካለባቸው እሳቸው ባደረጉት ነገር እንጂ ሌሎች በሰሩት አይደለምና።

ቀድሞ ነገር ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ራሳቸውን ከስልጣን ለማውረድ አመጽ ሲደረግባቸው እና በየቀኑ በደጃቸው ሰልፍ ሲወጣባቸው በጣም ሲከፋ አለማቀፍ ህግ በሚፈቅደው መሰረት በውሃ ፣ በአስለቃሽ ጭስ እና በቆመጥ ካልሆነ እርምጃ እንዲወሰድ አልፈቀዱም። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በጉልበት በስልጣን ጉብ ብለው አልወርድም ያሉት የነ መለስ ቡድን እና ጀሌዎቹ ግን በጠራራ ጸሃይ እንደ ነብዩ አለማየሁ የመሳሰሉ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህጻናትን በአልሞ ተኳሾች አስፈጇቸው። ይህ ብቻም አይደልም: በጋምቤላ ፣ በኦጋዴን ፣ በአዋሳ ፣ በአደባባይ ኢየሱስ ፣ የለየለት ጭፍጨፋ አካሄዱ። በቀጣይነትም በወልቃይት እንዲሁም በኦጋዴን በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊያስጠይቅ በሚያስችል ደረጃ አሁንም ጭፍጨፋው እንደቀጠለ ነው።

የዚህ መጽሃፍ ደራሲ አቶ ብስራት አማረ እራሱ በበረሃ በነበርንበት ወቅት ስንት ህንፍሽፍሽ ሰበብ እና በሌሎችም የፖለቲካ ውሳኔዎች ከላይ ከነመለስ ዘናዊ እና አባይ ጸሃዮ በተሰጡ የግድያ ትዕዛዞች የፈጃቸው የትግራይ ጨቅላ ህጻናት ደም አሁንም ድረስ ይጮሃል። የነኚህ ህጻናት ደም ደመ ከልብ ሆኖም አይቀርም

No comments:

Post a Comment