Translate

Friday, April 12, 2013

የጊዜው የኢትዩጵያ ጬኸት፤ የተመስገን ደሳለኝ እይታና የከበደ ሚካኤል “ጽጌረዳና ደመና”


ዳንኤል፣ ከኖርዌይ

ዛሬ ማታ በኢትዩጵያ ውስጥ በዚህ ሰሞን እየተደረገ ያለውን የኢትዩጵያዊያን ከገዛ አገራቸው በዘራቸው (የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ) ወይም አማራ በመሆናቸው ብቻ “እዚህ ቦታ አትፈለጉም፣Temesgen Desalegn Feteh newspaper editor ወደ ሀገራችሁ ሂዱ” የተባሉትን ወገኖች ሰቆቃ እያሰላሰልኩ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተገኘ ምን ይከሰታል በሚል መጭውን የሀገሬን እጣ ፈንታ አሰብኩና ፍርሃት አደረብኝ። የሩዋንዳው የእርስ በእርስ እልቂት ታወሰኝና እግዚአብሄር ምድራችንን እንዲታደግ ጠየቅሁ።
የእለቱን የኢሳት ራዲዮ ዜና ሳደምጥ ደግሞ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከመሳይ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ትኩረቴን ሳበው፥የእኔን ስጋት በተመስገን ውስጥ አገኘሁት፥እርግጠኛ ነኝ ስጋቱ የብዙ ኢትዮጵያውያን ነው።
ተመስገን እንዲህ ነበር ያለው፥ “ከፊታችን ሁለት ምርጫዎች ተደቅነዋል፥ አንደኛው አቶ መለስን ለተካው አስተዳደር ኢትዩጵያን ሰጥተን አይናችን እያየ ሀገራችን ሰትጠፋ መመልከት ወይም ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንን ማዳን።”

ተመስገን ሀገራችን በሞትና በህይወት መካከል ሆና የጣር ጩኸት እያሰማች እንደሆነ ገብቶታል እኔም በዚሁ እስማማለሁ፥ ሁለተኛም እርስ በእርስ ከተደጋገፍን አገራችንን ማትረፍ እንደምንችል እርግጠኛ ነው።በምንም መልኩ ይሁን የትኛውንም ምክንያት እንስጥ ማድረግ የሚገባንን ሳናደርግ ቀርተን ሀገራችን ወደ ባሰ ቀውስ ብትገባ ፀፀቱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለትውልድም የሚተርፍ ነውና አስተውለን ለሀገር ማዳን ጥሪው አፋጣኝ ምላሽ ልንሰጥ ይገባል።
ለዚህ ጽሁፍ የጊዜው የኢትዩጵያ ጬኸት፤ የተመስገን ደሳለኝ እይታና የከበደ ሚካኤል”ጽጌረዳና ደመና” የሚል ርዕስ የሰጠሁት የእኔ ስጋት፣ የተመስገን ደሳለኝ ቃለ ምልልስና የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “ጽጌረዳና ደመና” የሚለው ግጥም ስለተመሳሰለብኝ ነው፥ለዚህም ነው ይህችን ጥቂት ቋጠሮ ለእናንተ ላካፍል የተነሳሁት።
ግጥሙ እንዲህ ይጀምራል፥
የፀሃዩ ንዳድ ያጠቃት በብዙ
ጠውልጎ የሚታይ የቅጠሏ ወዙ
አንዲት ጽጌረዳ ቃሏን አስተዛዝና
እንዲህ ተናገረች ለሰማይ ደመና
ድርቀት በጣም ጎድቶኝ እየኝ ስንገላታ
እባክህ ጣልልኝ የዝናብ ጠብታ
ቶሎ ካላራስከኝ ጉልበቴ እንዲጥናና
ምንም ተስፋ የለኝ መሞቴ ነውና።
ጽጌረዳ እጅግ ውብ አበባ ናት ውበቷ ደግሞ በብዙ ቀለማት የሚገለጥ ነው። ጽጌረዳዋ የፍቅር ተምሳሌት ናት፥ ነገር ግን ከፀሃዪ ንዳድ የተነሳ ጠውልጋለች፥ ውበቷ ደብዝዟል፥ ወደ ሞት እያዘገመች ነው። ይህችን ውብ አበባ ከሞት ሊያድን የሚችል አንድ አካል አለ፥ የሰማይ ደመና። ስለዚህ ውቧ ጽጌረዳ አበባ ለሰማይ ደመና የድረስልኝ ጩኸት አሰማች ነው የሚሉት ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል።
ውቧ ጽጌረዳ የእኛይቱ አገር ኢትዩጵያ ናት፥ የነጻነት፥የፍቅር ተምሳሌት፥ የብዙ ቋንቋዎች፥ባህሎችና ሃይማኖቶች ባለቤት። የአለም እንግዳ ተቀባዮች ውብ አበባ፥የአረንጓዴ ብጫ ቀይ አርማ ጽጌረዳ፣ የጥቁሮች የነፃነት ቀንዲል።
የ3 ሺህ አመት የመንግስት ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዩጵያ ዛሬ በዘረኝነት፥ በፍትህ እጦት፥በርሃብና በእርዛት ሃሩር ጠውልጋለች፣ የቅሏ ወዝ እየጠፋ ወደ ሞት እያዘገመች ነው። በክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል እንደተጠቀሰችው ጽጌረዳ ኢትዮጵያችን የድረስልኝ ጥሪ እያቀረበች ነው ለሰማይ ደመና።
የሰማይ ደመናው ማነው? ምንድን ነው? አዎ የሰማይ ደመናው የጽጌረዳዋን ህይዎት ሊታደግ የሚችል የብዙ ውሃ ጠብታዎች ስብስብ ነው።
ለኢትዩጵያ የሰማይ ደመናው የእኛ የኢትዩጵያውያን ህብረት ነው፥ የኢትዩጵያውያን አንድነት ነው። እያንዳንዳችን ኢትዩጵያውያን ደግሞ የእያንዳንዷ የውሃ ጠብታ ተምሳሌቶች ነን።
ዛሬ ኢትዮጵያችን የድረስልኝ ጥሪ እያቀረበች ነው ለእኛ ለኢትዩጵያውያን ጥሪው ደግሞ ጽጌረዳዋ
“ቶሎ ካላራስከኝ ጉልበቴ እንዲጥናና
ምንም ተስፋ የለኝ መሞቴ ነውና።”
እንዳለችው ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፣አጣዳፊ ነው። የሰማይ ደመና ለዚህ ጩኸት የሰጠው ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር፤
“አሁን መሄዴ ነው ለትልቅ ጉዳይ
ስመለስ መጥቸ ሳልፍ ባንች ላይ
አዘንብልሻለሁ ጠብቂኝ እያለ
ደመና ጉዞውን ወደፊት ቀጠለ።”
ጽጌረዳዋን ሊታደጋት የሚያስችል ብቃት ያለው ደመና ጥቂት የዝናብ ጠብታ አውርዶ ጽጌረዳዋን ለማዳን ጊዜ አልነበረውም። ችግሯን ተመልክቶ ስመለስ ጠብቂኝ ብሎ ቅድሚያ ወደሚሰጠው ጉዳይ ነጎደ። ዛሬ የኢትዮጵያችንን ጩኸት የሰማን፥ ችግሯን በጥልቀት የተረዳን ኢትዮጵያውያን ሳንቀር እንደ ደመናው በአጣዳፊ ጉዳይ ተይዘናል፤ የልጆች፥ የቤተሰብ፥ የትምህርት፥ የስራ፥ የክብር፥ የዝና ነገር አጣድፎናል። ለጠወለገችው ኢትዮጵያችን፣ ወደ ሞት ለምታዘግመው ኢትዮጵያችን በኋላ እደርስልሻለሁ እያልናት አይመስላችሁም?
ደመናው ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ ጨርሶ ሲመጣ የሆነው እንዲህ ነው፥
“ጉዳዩን ጨርሶ ፈጽሞ ሲመጣ
ያቺ ጽጌረዳ ስሯ ውሃ ያጣ
እንደዚያ አስተዛዝና ጭንቋን ያዋየችው
የፀሃዩ ንዳድ አድርጓት ቆየችው።
እስኪጎርፍ ድረስ የወንዝ ውሃ ሙላት
ወዲያው እንደመጣ ዝናቡን ጣለላት
ግን ደርቃለችና አልቻለም ሊያድናት።
ሳልደርስላት ቀረሁ አየጉድ እያለ
ደመናም ጉዞውን ወደፊት ቀጠለ።
ሰውም እንደዚሁ ጭንቁን እያዋየ
በችግሩ ብዛት እየተሰቃየ
ብዙ ጊዜ ኖሮ ቆይቶ ሲጉላላ
የሚረዳው አጥቶ ከሞተ በኋላ
ዘመድ ወዳጆቹ እንባ እያፈሰሱ
ተዝካር ቢያወጡለት አርባ ቢደግሱ
ይህ ሁሉ ከንቱ ነው አይጠቅመውም ለእሱ።
እውነት ከወደደው ሲቸገር ሲጎዳ
በህይወቱ እያለ ሰው ወዳጁን ይርዳ።
ደመናው ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ ጨርሶ ሲመጣ ለጽጌረዳዋ ያዥጎደጎደው የውሃ ጎርፍ ጽጌረዳዋን ከሞት ሊያድናት አልቻለም። ይልቅስ ያኔ በጠየቀችው ጊዜ ቢሰጣት ኖሮ ጥቂት የውሃ ጠብታ ህይወቷን ባዳነ ነበር። ለደመናው የተረፈው ነገር ሳልደርስላት ቀረሁ የሚል ቁጭትና ፀፀት ብቻ ነው።
ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል መልዕክታቸውን ያጠቃለሉት ወዳጃችን በህይወት እያለ በችግሩ ጊዜ የአቅማችንን እንርዳው እንጂ ከሞተ በኋላ የምናደርገው የትኛውም ነገር ርባና የለውም ነው በማለት ነው፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም ይህንኑ ነው ያሳሰበው። እኔም ከዚሁ ሃሳብ ጋር እስማማለሁ። እናንተስ?
ወዳጃችን ኢትዮጵያ ጠውልጋ የዝናብ ጠብታዎችን ተጠምታለች፣እያንዳንዱ የዝናብ ጠብታ የጽጌረዳዋን ዕድሜ የማርዘም ብቃት እንዳለው የኢትዮጵያችን ህይወት በእኔና በእናንተ እጅ ነው። ስለዚህ የአቅማችንን ጠብታ እናዋጣ፥ ኋላ ከመፀፀት ያድነናል።
ቸር አንሰንብት!
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ ይጠብቅም!

No comments:

Post a Comment