Translate

Monday, April 15, 2013

የቅ/ሥላሴ መን/ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ቀሚሳቸውን አንጥፈው ሲለምኑ ዋሉ


የቅ/ሥላሴ መን/ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ቀሚሳቸውን አንጥፈው ሲለምኑ ዋሉ

ሐራ ዘተዋሕዶ
  • የኮሌጁ ካፊቴሪያ ለደቀ መዛሙርቱ ምግብ እንዳያዘጋጅ በሊቀ ጳጳሱ ታዝዟል
  • ሊቀ ጳጳሱ ሁሉም መምህራን በመደበኛው የቀን መርሐ ግብር እንዳያስተምሩ ከልክለዋል
  • ሊቀ ጳጳሱ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ሥራውን እንዳይጀምር አድርገዋል
  • በሊቀ ጳጳሱ ዙሪያ የተሰለፈው የቤተ ክህነቱ የጨለማ ቡድን ፓትርያሪኩንም እያሳሳተ ነው
  • ደቀ መዛሙርቱን ለማስወጣት የተጠራው የፖሊስ ኀይል ርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልኾነም
  • በኮሌጁ የሚዘዋወሩ ስመ ደኅንነቶች ደቀ መዛሙርቱን፣ መምህራኑንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን እያስፈራሩ ነው
Addis Ababa, Ethiopian Orthodox Church
ይህ ፻ውን የሐራ ዘተዋሕዶ ዘገባ ለንባብ ያበቃንበት ጦማር ነው፡፡ ከጦማሮቹ የሚበዙት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተቋማዊ መገለጫ ለመኾን ስለ ደረሰው ጥቅመኝነትን የመከባከብ፣ ሙስናንና የአሠራር ብልሹነትን የማንገሥ፣ ከሙሰኞችና ጥቅመኞች ጋራ የመደራደር አስተሳሰብና ተግባር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር እና የደቀ መዛሙርቱ ውዝግብ አያያዝና እየተወሳሰበ የመጣበት ኹኔታ ከዚህ የተለየ መነሻ የለውም፡፡

የኮሌጁ መምህራን እንደሚናገሩት፣ የትምህርት አስተዳደሩ እንዲሻሻልና የደቀ መዛሙርቱ አካዳሚያዊ መብቶች እንዲከበሩ የቀረቡ ጥያቄዎችን ሓላፊነት በተሞላበት መንገድ ደቀ መዛሙርቱን ከመምህራኑ ጋራ በግልጽ በማወያየት ምላሽ መስጠት ይቻላል፡፡ ይህም ካልኾነ የመማር ማስተማሩን ጤናማነት/ሰላማዊነት ለመጠበቅ ተቃውሞ የቀረበባቸውና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ መስማማት ያልቻሉ መምህራን ከሓላፊነታቸው ገለል እንዲሉ ማድረግ ነው፡፡
እየኾነ ያለው ግን ላለፉት 14 ዓመታት በኮሌጁ የበላይ ሓላፊነት ከቆዩ ሊቀ ጳጳስ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በቅ/ሲኖዶስ የተቋቋመው ኮሚቴ የማጣራት ሥራውን ጨርሶ ጥያቄያቸው ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የተቃውሟቸው ሁለቱ ሓላፊዎችና መምህራን ወደ ክፍል ገብተው እንዳያስተምሩ በመከላከላቸው እልክ የተጋቡት ሊቀ ጳጳሱ ‹‹ያቋረጣችኹትን ትምህርት በአግባቡ አልጀመራችኹም››በሚል የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ከመጋቢት 30 ቀን ጀምሮ የተዘጋ መኾኑን የኮሌጁን ክብ ማኅተም ይዞ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጠዋት በወጣ ማስታወቂያ አሳስበዋል፤ በቁጥር 181 ያህል የሚኾኑት የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርትም ንብረት አስረክበው በአስቸኳይ ከኮሌጁ እንዲወጡ አዝዘዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ በተለይ ከቀኑ መርሐ ግብር አስተባባሪና በክፉ ምክር እያሳተ የግል ጥቅሙን ከሚያካብተው ዘላለም ረድኤት ጋራ በመኾን ያወጡትን ይህን ማስታወቂያ የተቃወሙት ደቀ መዛሙርት ግን ከኮሌጁ አልወጡም፤ መምህራኑም ከማስተማር አልታቀቡም ነበር፡፡ ይህ በእጅጉ ያስቆጣቸው ሊቀ ጳጳሱ ትላንት ጠዋት መምህራኑን አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ‹‹ማስተማር እንደሌለባችኹ ለማሳወቅ›› በሚል አጀንዳ ሲወዛገቡ ውለዋል፡፡ ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ ከቀትር በኋላ ቀጥሎ የዋለው ስብሰባው በንዴት በጦፉና አንዳንዶቹም ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ‹‹አንተ አንቺ ቀረሽ›› እላፊ ቃላት በሚነጋገሩ መምህራን ቁጣ የተሞላ ነበር ተብሏል፡፡
‹‹የሁለት ሰዎች ችግር ኮሌጁን ሊያዘጋ አይችልም›› ያሉት መምህራኑ ችግሩን በመመካከር መፍታት እንደሚቻልና በዚህ የማይፈታ ከኾነ ግን መምህራኑን መለወጥ የተለመደ አሠራር መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መምህራኑ በቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር እንዳያስተምሩ መከልከላቸውንና መርሐ ግብሩን ላልተወሰነ ጊዜ የመዝጋት ርምጃ የገለጹት ‹‹ከእግዝአብሔር ማዕድ ለምን ትለዩናላችኹ!›› በሚል እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የቀኑ መርሐ ግብሩ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን የሚገልጸው የአስተዳደሩ ውሳኔ በደብዳቤ እንዲሰጣቸው የጠየቁት መምህራኑ ‹‹የምንጠይቀውን አካል እንጠይቃለን፤›› በማለት መዛታቸውም ተነግሯል፡፡
የመርሐ ግብሩን መዘጋት ተከትሎ ሊቀ ጳጳሱ ለካፊቴሪያው ሓላፊ በቃል ባስተላለፉት ትእዛዝ ካፊቴሪያው ከትላንት በስቲያ ምሽት አንሥቶ ምግብ እንዳያዘጋጅ፣ ሠራተኞችም በምግብ ቤቱ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከትላንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ ራትና ምሳ በመከልከል በረኀብ እንዲቀጡ መደረጋቸውን በትላንቱ ስብሰባ መምህራኑ በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡
ማስታወቂያው በወጣበት ዕለት ምሽት በግቢያቸው የተሰበሰቡት ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው÷ ሁለቱ መምህራን እንዳያስተምሩ ከመከልከላቸው በቀር 90 ከመቶው የመማር ማስተማሩ ሂደት በቀጠለበት ኹኔታ በሊቀ ጳጳሱ የተወሰደው ርምጃ ተቀባይነት እንደሌለው ተወያይተዋል፡፡ በጎጠኝነትና በጥቅም ሊከፋፍሏቸው በሚሞክሩት ጥቂት የኮሌጁ ሓላፊዎች ተንኮል ሳይለያዩ ፣ በረኀብ ሳይፈቱ ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪሰጠው ድረስ በተቃውሟቸው ለመቀጠልም ተስማምተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment