Translate

Monday, April 8, 2013

ምርጫ እስኪያልፍ ሙዚቃ ቤቶች የቴዲ አፍሮና የፀጋዬ እሸቱን ዘፈኖች መክፈት ተከለከሉ


tedy afroበአዲስ አበባ የተለያዩ ስፍራዎች በሚገኙ መዝናኛዎችና ሙዚቃ ቤቶች በሚያዝያ መጀመሪያ የሚደረገው የአካባቢ ምርጫ ሳያልፍ ሀገር ፍቅር ስሜት የሚቀሰቅሱ ዘፈኖችን እንዳይከፍቱ ክልከላ ተደረገ፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚደረገው የከተማ መስተዳድርና የአካባቢ ምርጫ ብቻውን የሚወዳደረው ኢህአዴግ በካድሬዎቹ አስገራሚ ትዕዛዞችን እየሰጠ እንደሚገኝ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ጠቆሙ፡፡

በአዲሱ ትዕዛዝ መሰረት ምርጫው እስኪያልቅ ድረስ ሙዚቃ ከፍ አድርገው የሚያጫውቱ ሙዚቃ ቤቶችና የመዝናኛ ስፍራዎች የሀገር ፍቅር ስሜት የሚቀሰቅሱና ስለባንዲራ የተዜሙ ዘፈኖችን መክፈት ተከልክለዋል፡፡በትዕዛዙ በተለይ የተከለከሉት የቴዲ አፍሮና የፀጋዬ እሸቱ አዲሱ አልበም ላይ የተካተቱት ዜማዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ነጋዴዎቹ “ክልከላው ከምርጫው ጋር ምን እንዳያያዘው አልገባንም፣ሆኖም ከመንግስት የመጣ ትዕዛዝ ስለሆነ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ዘፈኖቹን ማጫወት አቁመናል” ብለዋል፡፡
ነጋዴዎቹ ጨምረው ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት በተለያየ ጊዜ ለቁጥጥር የሚመጡት የወረዳ ካድሬዎች የተከለከሉትን ዘፈኖች ተከፍቶ ከሰሙ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚያደርሱባቸው ፡፡ “የቴዲን ዘፈን በተለያዩ ወቅቶች አትክፈቱ ተብለን እናውቃለን” የሚሉት ነጋዴዎቹ የፀጋዬ እሸቱ አዲሱ አልበም ውስጥ ያሉት ሀገርንና ባንዲራን የሚመለከቱ ዘፈኖች በሬዲዮ እየተለቀቁ እነሱ እንዳይከፍቱ መደረጋቸው እንዳስገረማቸው ገለፀዋል፡፡
ምንጮቻችን ተዘዋውረው ያነጋገሯቸው ነጋዴዎች እንደገለፁት ይህ ክልከላ ጎልቶ የታየው በመርካቶና በፒያሳ አካባቢ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment