Translate

Sunday, August 12, 2012

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት በአርማጭሆ ወታደራዊ ጥቃት መፈፀሙን አስታወቀ


ነሀሴ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢሕአግ በሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ልዩ ስሙ አዋሳ በተሰኘ አካባቢ ከመንግስት ልዩ ሃይል ታጣቂ ጋር ሐምሌ 28-2004 ዓ∙ም ባካሄደው ውጊያ 11 የመንግስት ቡድን ቅጥረኞችን በመግደልና 19 በማቁሰል አንፀባራቂ ድል ማግኘቱን ለኢሳት በላከው መግለጫ አመልክቷል።
በእለቱ የግንባሩ  ሰራዊት የተለመደውን ታሪካዊ ጀብድ ሲያከናውን የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍና አቀባበልም እንዳደረገለት ገልጧል።
ማህበረሰቡ የአርበኛ ግንባር ደጋፊ ነህ በሚል ሳቢያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰነዘረበት ያለው የግፍ በትር እያየለ መምጣቱ ፣በአካባቢው በኢንቨስትመንት ሽፋን አገሬውን በማፈናቀልና እርስት አልባ በማስቀረት በኩል አገዛዙም የበቀል እርምጃም እየተወሰደ እንደሚገኝ አትቷል።

ግንባሩ እየወሰዳቸው በሚገኝ ወታደራዊ ጥቃቶች ጎን ለጎን እንደ ወትሮው ሁሉ ህዝቡን የማንቃትና የማስታጠቅ እንዲሁም የድርጅቱ አቋም ገላጭ የሆኑ በራሪ ወረቀቶችና መፅሔትቶችን አሰራጭቷል።
በሰራዊቱ በኩል እየተወሰደ በሚገኘው አገርን ከጥፋት ሃይሎች የመታደግ ታሪካዊ እንቅስቃሴ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም ለለውጥ የሚያደርገውን ትግል ማጠንከር እንደሚገባውና ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሊፈጠሩ ይችላሉ በሚባሉ መላ-ምቶች መዘናጋት እንደማይገባው መክሯል።
መንግስት አርበኞች ግንባር አገኘሁ ስላለው ድል ማስተባያም ሆነ ማረጋጋጫ አልሰጠም።
በሌላ ዜና ደግሞ የአርበኛውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማክሰም በሚል አላማ የተደራጀው ልዩ ሃይል የበላይ የጦር መኮንኖች በጠራራ ፀሐይ ከወልቃይት ሶረቃ አንስቶ በአርማጭሆና መተማ አይን ያወጣ ዘረፋ መጀመራቸውን፣  ዘረፋው የሕዝብ መገልገያ በሆኑ አውቶቡሶችና አገር ሰላም ነው ብለው ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ግንባሩ ጠቅሷል።
የልዩ ሃይል ታጣቂ አባላት በዚህ ሳምንት ውስጥ የጀመሩት አይን ያወጣ ዘረፋ ይህ መረጃ ይፋ እስከተደረገበት ዕለት ድረስ ያልተቋረጠ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች በምሬት እንደሚገልጡ ግንባሩ የላከው መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment