Translate

Tuesday, July 25, 2017

ግብር አልገብርም ማለት መንግስት የለም ማለት ነው (መስቀሉ አየለ)

መስቀሉ አየለ
Taxation in Ethiopia
ለአበሻ ግብር መገበር ማለት ታክስ መክፈል ማለት አይደለም። ነገሩ ከዛ በላይ አልፎ የሚሄድ ውስብስብ መልዕክት አለው። ግብር በገንዘብ ብቻ የሚለካው ለፈረንጅ ነው። “አይ አም ኤ ታክስ ፔየር” ይላል። ለነሱ ሙሉ ለሙሉ የገንዘብ ጉዳይ መሆኑ ነው። ታክሱ በዝቶብኛል ብሎ ሲያስብ ለላንድ ሬቬኑ አንዲት ቁራጭ አፕሊኬሽን ፎርም ሞልቶ በመላክ ያስቀንሳል።
ሲፈልግ “ታክስ አልከልም፤ ጡረታዬን አሁኑኑ መብላት እፈልጋለሁ” ካለም አመቱ መጨረሻ ላይ የተቆረጠበት ገንዘብ ታስቦ ይመለስለታል። ወይንም “ለመንግስት የምከፍለውን ታክስ እከሌ ለተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ይሰጥልኝ” ካለም መብቱ ነው።
ነገር ግን ግብር መገበር ባበሻ አገር እንዲህ አይደለም። የአበሻ ንጉስ በእከሌ በኩል ዘምቶ አስገበረ ከተባለ ከአመታዊ የገንዘብ መዋጮም በላይ በዚያ አካባቢ የመንግስትነት ይዞታውን አጸና፣ እንደ ንጉስነቱ እውቅና አገኘ ማለት ነው። እነ አጼ ቴዎድሮስም ሚኒሊክም ያደረጉት ይኽንኑ ነው። ያኔ እነርሱ ሲሆን በደብዳቤ ሳይሆን ደግሞ በባዶ እግራቸው መጋዣ እየሳቡ ያስገበሩትን ወሰንና ህዝብ ዛሬ መረጃ በብርሃን ፍጥነት ህዋውን በሚያክልልበት በዚህ ሰዓት ወያኔ ግን ሮኬት ጭምር ታጥቆ እንኳን መልእክቱን ማድረስ አልተቻለውም። እንደ አራዳ ልጆች አገላለጥ ገበሬው “መስሚያየ ጥጥ ነው” ብሏል።
አሁን ወያኔ ውልቅልቁ በወጣው አመራሩ በኩል አንድ ግዜ “ግብሩን አንስቻለሁ” ሌላ ግዜ “ውሸቴን እያለ ነው። በደም ብዛት ህግ የሚሰራ የሽፍታ ቡድን፤ ግራ የሚሰራውን ቀኙ የማያውቅበት መንግስት፣ በደናቁርት ዋር ሎርድስ የተተበተበ መንግስት፣ ይበልጥ ጫና በበዛበትና ይበልጥ በተገፋ ቁጥር ገና ብዙ መደናበር እናይበታለን። ያም ሆነ ይኽ የኛ ህዝብ ግብር አልገብርም አለ ማለት ከእግዲህ አራት ኪሎና መቀሌ ለመሸገው አውሬ እንደ መንግስት እውቅና አልሰጥም ማለቱ ነው። “አራት ነጥብ”። በተቃዋሚው ጎራ ያለ ማንም አካል ልብ ሊል የሚገባው ሃቅ ይኽ ህዝብ ከመቸውም ግዜ በላይ ለለውጥ ብቻ ሳይሆን ከለውጥም በላይ አልፎ ለሄደ ስር ነቀለ አብዮት (ራዲካል ሪቮሊዩሽን )ዝግጁ መሆኑን ያሳየ መሆኑን ነው።ላለፉት ሶስት ሽህ እና ከዚያ በላይ አመታት ያለ መንግስትና ያለ ስርዓት ኖሮ የማያውቅ ህዝብ አንድ ግዜ መንግስት የለም ብሎ ደመነፍሱ ከነገረው የራሱን መንግስት ማቆም እንዳለበት ቢወስን አይገርምም። ለዚህ ደግሞ ተሰብስቦ ቀን መቁረጥ አይጠበቅበትም። ክፉ ቀን መምጣቱን እንደሆን አየሩ ሲቀላ፣ ነፋሱ ክፉኛ ሲነፍስ፣ ያልተለመደ የበረዶ ግግር ሲውጠው እንደ ፈረንጅ ግሎባል ወርሚንግ ብሎ እራሱን አያታልልም። ህዝባችን ለተፈጥሮ ቅርብ ነውና ገና ቀድሞ በደመነፍሱ ይተዋወቃል።”ካንተ ሜትሮሎጅ ያህያ ጆሮ ተሻለ” እንዶሉ ጃንሆይ።ዋናው ነገር ይኽ ቀን ለነማን የሳት እረመጥ ሆኖ መጣባቸው ለነማን ደግሞ የብሃን ፍኖት ሆኖ መጣላቸው የሚለው ነው።ከዚህ ስር ነቀል አብዮት ማግስት የሚነጋለት አለ፤ የሚነጋበት አለና። ያኔ መሰንቆዋቸውን በተከዜ ወንዝ ላይ እየሰቀሉ ይሻገራሉ፣ አይሁዳውያን ዮርዳኖስን ተሻግረው በባቢሎን ምርኮ ስር እንደ ወደቁት። መሰንቆ ለምናችን እንዳሉት። ከእንግዲህ በባቢሎን ለቅሶ እንጅ ዘፈን የለም ማለታቸው ነበር።

No comments:

Post a Comment