Translate

Thursday, July 13, 2017

አዲሱ የህወሓት ጋሻጃግሬ – ለማ መገርሳ (በያ ደሳለኝ)

በያ ደሳለኝ
President of Oromia Regional State, Mr. Lemma Megersa.
ለማ መገርሳ
ድፍን ኢትዮጵያ በአመፅ ስትናጥ ቆይታ ፣ መንግስት የአዲስ አበባን የማስተር ፕላን ትግበራ እንዳቆመው ከገለፀ ከጥቂት ጊዜያቶች በኋላ የጥምቀት በአልን በአዲስ አበባ ከድሮው መለስ ባለ ድባብ አከበርን፡፡ ታዲያ በጥምቀት ማግስት ፤ የሚካኤል ንግስ እለት አስራ አንድ ያክል ሰዎች ፣ በአንድ አባዱላ ሚኒባስ መኪና ሆነን ፣ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ወደሚበዙበት ለገጣፎ ጉዟችንን ጀመርን፡፡  የካራ አደባባይን ጥቂት አለፍ እንዳልን ፤ ታቦት አጅበው ባቅራቢያው ወደሚገኘው የሚካኤል ቤተክርስቲያን የሚመልሱ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች፤ በባህል ልብስ ነጭ ሆነው ከርቀት ታዩን፡፡ ቀረብ ስንል ግን ከነሱ ቁጥር የማይተናነስ ብዛት ያለው፣ የፖሊስ ግሪሳ ምእመናኑን ከቦ በተጠንቀቅ አብሮ እየተጓዘ እንዲሁ አየን፡፡

በዚህ ወቅት ከእኛ መካከል የነበሩ ሁለት ቀንደኛ የመንግስት ፖሊሲን በሶሻል ሚዲያ የሚያቀነቅኑ የኦንላይን ታጋይ (ሁለት ትግሬዎች ) ነበሩ፡፡
ከነዚህ ሁለት ደጋፊዎች ነገሩ ያላስደሰተው አንደኛው ሰው፤ የሚጠበቅ ግርግር ባይኖር ይሄ ሁሉ ፖሊስ እንደማይኖር በመረዳቱ በንዴት ስሜት ውስጥ ሆኖ፤ “አሁን ደግሞ ምን ቀረ ብለው ነው ግርግር የሚፈጥሩት፣ ማስተር ፕላኑን እንደሆነ መንግስት ትቼዋለሁ ብሏል” አለ፡፡  ከወደምስራቅ ቢወለድም በአመለካከቱ እልም ያለ የህወሓት አላማ አቀንቃኝ የሆነው ሌላኛው ተናዳጅ የመንግስት አፍም በፌዝ “ማስተርፕላኑን ለምን አሰባችሁት ብለው ይሆናላ!” ብሎ መልስ ሲሰጥ፣ ሁላችንንም በገባን መጠን ገለፈጥን፡፡
እኔ የሳቅኩበት ምክንያት፣ በንግግሩ ብስለት ወይ ከበድ ያለ ጆክነት ሳይሆን፣ ከንግግሩ ጀርባ በህወሓታውያን አእምሮ ውስጥ፣ የኦሮሚያ ተቃውሞ የፈጠረው የአቅመቢስነት መንፈስን በተለያዩ መልኩ በማስተዋሌ ነበር።
“አሁን ደግሞ ምን ቀረ ብለው ነው፣ ግርግር የሚፈጥሩት፣ ማስተርፕላኑን እንደሆነ መንግስት ትቼዋለሁ ብሏል” …. “ማስተርፕላኑን ለምን አሰባችሁት ብለው ይሆናላ!” ሳቅቅ….. ለእኔ የኦሮሚያ ስር ነቀል ተቃውሞ ፣ የህውሃት ጓዳ ውስጥ የፈጠረውን ሃይለኛ መረበሽ ምን ያክል ደረጃ ድረስ የዘለቀ እንደነበር ፍንትው አድርጎ አሳይቶኝ ስለነበር ነው በወቅቱ አብሬ ፣ ንግግሩ እንዳሳቀው ሰው እየተንከተከትኩ የሳቅኩት፡፡
እንደውም የገዛ ሳቄ በቅርቡ የሰማሁትን የሶማሌ ክልሉ ወፈፌ መሪ (አብዲ ኢሌ) በተረት መልክ ከተናገሩት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል። አብዲ ኢሌ እንዳሉት “አንዲት የሶማሌ ልጃገረድ በድብቅ ፍቅር ከያዛት ሰው ጋር ጋብቻ አስራ በድንገት የድብቅ ፍቅረኛዋን ሞት ቢነጥቃት፣ መሪር ሃዘኗን በቤተሰብ ምንተፍረት ፣ በልቅሶ ሳትወጣ ቆይታ ፣ በአንዲት የቤተሰብ ፍየል ሞት ለትዝብት እስኪጥላት ድረስ ተንሰቅስቃ ስታለቅስ፣ አባትየው ፣ “ይሄ ልቅሶ ለፍየሉ ብቻ አይመስለኝም!” እንዳሉት እኔም ግምት ውስጥ ሳልወድቅም የቀረሁ ሁሉ አልመሰለኝም፡፡
ዛሬ ታዲያ ጥቂት ወራት ብቻ በኛ እና በጥምቀት መካከል አልፎ፣ ከዚህ ከላይ ከገለፅኩት የሁለቱ ባለአንድ አይነት ፍርሃት ባለቤቶች አእምሮ ውስጥ፣ በዚህ የኦሮሚያ ተቃውሞ የሚይዙ የሚጨብጡት ጠፍቷቸው የነበሩት የመንግስት ፖሊሲን በሶሻል ሚዲያ የሚያቀነቅኑ የኦንላይን ሰላይ/ታጋዮች፣ እጅግ በሚያስገርም የተቃርኖ ትእይንት ፣ አንድ ግለሰብን በስም ጠርተው ጠቅሰው አያባርሩም!፡፡ “ለማ መገርሳ” እንደ አያያዛቸው ከሆነ ከዚህ በኋላም ለሚቀጥሉት ብዙ አመታት ሊቀጥሉበት ያሰቡ ይመስላል ፡፡ እስቲ በነዚህ ሰዎች ላይ ገፍተን ሳንቀጥል ፣ ያለፈውን አመት ተቀወውሞ መለስ ብለን ሁኔታውን ዳግም እንቃኘው፡፡
ያለፈው አመት በዚህም በዚያም፣ በአብዛኛው ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ፣ በመንግስት ላይ ያልተጠበቀ የተቃውሞ ናዳ ሲያወርድ ፣ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ከጠፉበት ወጥተው፣ በየስብሰባው እየተገኙ ፣ ሽር ጉድ እያሉ ሲዳክሩ ከነበሩት የህወሓት የልብ ምት ከሆኑ ሰዎች መሃከል አቶ በረከት ስምኦን ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት በአንድ አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ስለወቅቱ የተቃውሞ ሁኔታ የተናገሩት አቶ በረከት እንዲህ አሉ፣
“ኢህአዴግ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙት፣ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፣ እንኳን አሁን ጠንካራ የሆነ “ከሪቲካል ማስ” – ወሳኝ ስብስብ እያለው ይቅርና ከዚህ በከፋ ድርጅታዊ አቅም ላይ ሆኖ እንኳን፣ አደጋዎችን ለራሱ እንዲበጁ አድርጎ ቀልብሷቸዋል” አሉና ተናገሩ፡፡
በሶስት ዋነኛ ክስተታዊ ምክንያቶች ንግግራቸው በከፊል እውነት ሲሆን ግን ደግሞ ልክ እንደ ህወሓት ባህሪ መሰሪ ሴራውን ሳያጋልጥ የተነገረ ሽፍንፍን የአፍ ወለምታም ጭምር ነበር፡፡ እንደውም ንግግራቸው ውስጥ ያለውም ከፊል እውነታ ራሱ ፣ ለህወሓት “የእባብ አይነት ህልውና እንጂ” ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠብ ያለ ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡ እንደውም ኢትዮጵያ እንደ አገር ከእነዚህ ክስተቶች ማግስት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጭላንጭል ተስፋዎች ድርግም እያሉ የጠፉባቸው ወቅቶች ናቸው፡፡
“ከድርጅታዊ ህልውና!” ጋር በሚያያዙ ምክንያቶች ይህ የአቶ በረከት ንግግር ፣ ቀደም ብሎ ለሻእቢያ በኋላ ደግሞ ለህወሓት እዚህ ደረጃ መድረስ ፣ እነዚህ ሶስት ታሪካዊ ክስተቶች በተፈጠሩበት አጋጣሚ ሁሉ ፓርቲውን ሳይሞት እንዲቀጥል፣ከነዚህ ክስተቶች አጥቢያም ሌላ አዲስ ጡንቻ እያከለ በኢትዮጵያ ላይ እንዲሰለጥን፣ እነዚህ አጋጣሚዎች (Turning Points) ወሳኝ መሻገሪያዎች ሆነውታል፡፡ እነዚህ “ሶስት አጋጣሚዎች!” ፣ኢትዮጵያዊያንም እንደ አንድ ታላቅ ህዝብ ፣ ኢትዮጵያም እንደ አንድ ታላቅ ሃገር ልትነሳ ፣ የእውነተኛ ለውጥ ውጋገን ማየት ስትጀምር፣ መልሳ መላልሳ፣ ተሸቀንጥራ እየተወረወረች በግንባሯ የተደፋችባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ህወሓት/ኢሃዲግ፣ ከነዚህ ከባባድ ክስተቶች ማግስት እያንሰራራ፣ እስከዛሬ ድረስ አገሪቷን እየመራ ቀጥሏል፡፡
እነዚህ ሶስት ፣ በአስራ ሰባት አመታት (ከ1981 እስከ  1997 አ.ም.) ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከተፈጠሩ ፣ በህወሓት ህልውና ላይ ፈታኝ አደጋዎችን ይዘው ከመጡት ዱብእዳዎች በኋላ፡ ህወሓት እራሱን አጥንቶ እና በዙሪያው ያሉ ሁኔታዎች  እንዲለወጡ በሚወስደው ፣ “በየትኛውም!” ዋጋ የሚገዛ እርምጃ መልሶ ስልጣኑን ሲያረጋግጥ ታይቷል፡፡ በሁሉም ውስጥ ግን የህወሓት ድርጅታዊ አላማ እና በኢሃዴግ ውስጥ እንዲከወን የሚያደርጋቸው አጀንዳዎቹ (በዘር ላይ የተመረኮዘውና ኢትዮጵያ እንደ ህዝብ አንድ ሆና ለወደፊት የማትቀጥልበት ስትራቴጂ) በቅንጣት እንኳ ሳይለወጡ መቀጠላቸው ለደርድር የማይቀርብ ቅድመ ሁኔታው ነው፡፡
  • የሚመጡትም ውጤቶች ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ፣ በህወሓት ስልታዊ ገመድ ጎታችነት የሚቀመሩ ባለሶስት ገፅታ ለውጦች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ስለዚህ በነዚህ ክስተቶች ማግስት፣
  1. ህወሓት ይበልጥ የጠነከረ ድርጅት ሆኖ ለአመታት የማይንገዳገድበትን ጉልበት ፣ ከተቃጣበት አደጋ ውስጥ ሰብስቦ ሲቀጥል ይታያል፡፡
  2. ህወሓትን ከመሰረቱ ሊቆርሰው ከመጣው አደጋ ውስጥ ፣ የውግዘቱ መጠን ይለያይ እንጂ፣ “ውጉዝ ከም አርዮስ!” ተብሎ ስም የሚለጠፍለት ፣ (ሓቁ ምንም ይሁን ምን) ተወንጅሎ የመስዋእት በግ የሚሆን ቡድን ሁሌም አለ፣
  3. ባንጻሩ ደግሞ ፣ በሚያስገርም “ሸፍጣዊ ጥበብ”- የፓርቲውን አጀንዳ አንጠልጥሎ ማሳየት ሳያስፈልገው ፣ አዲስ የህዝብ ጀግና ሆኖ የሚወጣ ሌላ “ሮቢን ሁድን!” ደግሞ ፣ ህወሓት ፈጥሮ ይቀርባል፡፡
ሬድዮ ፋና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀውና ፣ “የያኔውን ጀግና ያሁኑን መናኛ” ፣ አቶ ልደቱ አያሌውን በክብር የጥናት ፅሁፍ አቅራቢነት፣ ከስልጣን ገሸሽ ያሉ መስለው ቆይተው ብቅ ካሉት ፣ አጋር አቅራቢው አቶ በረከት እና ሌሎችንም በአንድ ጠረቤዛ ላይ አስቀምጦ፣ ሁሉም ያሻውን ዲስኩር እንዲሰኩር በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተነገረው (የዚህ ፅሁፍ መነሻ) ፣ የአቶ በረከት ስምኦን (“የcritical mass” ) ንግግር ከፊሉ ብቻ እውነት ነው ያልኩት ፣ ከላይ በተጠቀሱት ጥቅል ነጥቦች ምክንያት ነው፡፡
አቶ በረከት ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እራሱን ከህወሓት የአመራር መዘውር ፣ መለየት የሚያስችለውን የመጀመሪያ እንቅስቃሴ በማድረጉ ምክንያት፣ ባልተረጋጋ የአመራር መንፈስ ውስጥ ሆነው እንኳን!፣ የህወሓትን ውጥን በምንም መልኩ መናገር ሳያሻቸው፣ -ይልቁንስ ፣ “አይናችሁን እያንቋለጫችሁ ላላችሁትም ብትሆኑ!” ፣ እውነቱን ልንገራችሁ “ምንም አይመጣብንም!” በሚል የሾርኔ መልእክት የደረበ ድምፀት ነበር የተናገሩት፡፡  እስቲ እኛም ከእውነታዎቹ ጋር ለማነፃፀር እንዲረዳ አድርገን ፣ የአቶ በረከት ስምኦን (“የcritical mass” ) ንግግር በሶስት ታሪካዊ ክስተቶች ውስጥ አስገብተን እንየው፡፡
አደጋ ቁጥር አንድ
በ1981 አ.ም. በሻእቢያ እና በስብሃት ነጋ ፊታውራሪነት ህወሓት ከተጠነሰሰበት ትግራይን ነፃ የማውጣት ተልእኮው በተጨማሪ መላው ኢትዮጵያን ከደርግ ቁጥጥር ውጪ የማድረግ መንታ መንገድ ላይ በሁለት ምርጫዎች መካከል እራሱን ሲያገኝ፣ በድርጅቱ ላይ ተጋርጦ የነበረበትን ከፍተኛ አደጋ፣ የገዛ የድርጅቱን መስራቾች ሳይቀር፣ የጭዳ ዶሮ በማድረግ እና፣ በቅፅል ስሙ “ውድም” (የትግርኛ ትርጓሜው-“ድርጅቱ”) በመባል ሙሉ ህወሓትን በስም ጭምር የሚወክለው ፊታውራሪው ፣ አቶ ስብሃት ነጋ ፤እንዲሁም፣ ኤርትራን የመገንጠል አጀንዳውን ዳር የማድረስ ሽርክና ከህወሓት ጋር ገብቶ ለየነበረው ፣ በማይወላዳው የሻእቢያ አቋም ምክንያት ፤ ህወሓት አቶ መለስን እና አቶ ስዬ አብርሃን ወደ ስልጣን በማምጣት ፤ ህልውናውን ወደፊት አስቀጥሏል፡፡
የዛ የህወሓት እና የሻእቢያ ጥምረት፣ ለህወሓት እንደ ድርጅት ኢትዮጵያን የምታክል አገርን እንዲቆጣጠር የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰደበት ሲሆን ፣ በዚህም የስብሃት ነጋ እና በክንፉ ስር የታቀፉት አመራሮች፣ በኢትዮጵያዊ ህይወት ላይ የሚኖራቸውን የወደፊተ ተፅእኖ ያረጋገጠ፣ ከዚህ በተቃራኒ ለተሰለፉት ደግሞ ፣ ወጣትነታቸውን መስዋእት ያደረጉለትን ሁሉ እንዲተዉ፣ የኪሳራ ማቅ ተከናንበው ፣ አላስፈላጊ ቅርንጫፍ ሆነው ተገርዘው ቀርተዋል፡፡ ከነርሱ የሚልቀው ግን የዚያ ጥምረት ጣጣ የተረፈው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ያ ጥምረት ኢትዮጵያን፣ ከዘጠና አራት ሚሊዮን ህዝብ በላይ እያላት፣ ወደብ አልባ አገር አድርጎ አስቀርቷታል፡፡
አደጋ ቁጥር ሁለት
በ1993  አ.ም. አቶ መለስ ዜናዊ ፣ ለኤርትራ በሚወግነው አመራራቸው ላይ በገጠማቸው ከባድ ችግር፣ ህወሓት እንደ ድርጀት የመፍረስ ፣ እሳቸውም ከዚያ የከፋ አደጋ ላይ ሆነው የወሰዱት እርምጃ፣ ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ አንዱ “ውጉዝ፣ ሌላው ቅዱስ” ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እነ ስዩም መስፍን ጄነራል ሳሞራ የኑስ ፣ አቶ ስብሃት ነጋ ፣ ሟቹ የደህንነት አዛዥ ክንፈ እንዲሁም ከሁለተኛው ወገን ተመላሹ አቶ አባይ ፀሃዬ በጥምረት ፣ ህወሓትን ከገዛ ከራሱ የትግል አጋሮች አደጋ ለመጠበቅ  የነስዬ አብርሃ እና ገብሩ አስራት ቡድንን ዋጋ በማሳጣት ከህወሓት እንዲወጡ፣  በዚያ ክስተት ማግስትም ህወሓት ዳግም መልሶ ስልጣኑን እንዲያረጋግጥ ሆኗል፡፡
ከዚያ በኋላ ህወሓት ጥያቄ ይዘው የተነሱበትን ፣ የገዛ የትግራይ ተወላጅ እንዲሁም ነባር ታጋዮችን እንዴት ከትግራይ ህዝብ ልብ ውስጥ አንዳወጣቸው መለስ ብሎ በማየት ፣ በሁለተኛው አደጋም  ህወሓት ስልጣኑን ለመጠበቅ እና ሁሉን እንደተቆጣጠረ ለመቆየት የሄደበትን መንገድ በማየት ፣ የአቶ በረከትን ንግግር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ህወሓት ጎራ ለይተው የተነሱበትን ሁሉ ደብዛ ከማጥፋት በዘለለ፣ እንደ መከላከያ ያሉ ፣ ህገመንግስታዊ መሰረት ብቻ ሊኖራቸው የሚገቡ ተቋማትን፣ ህወሓት ለስልጣኑ ወሳኝ እንዲሆኑ  እና ለፓርቲው የግል መጠቀሚያ ለማድረግ ስራውን ሰርቶ ከተፍ አለ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በንደዚህ አይነት ተቋም ውስጥ ያሉትን አመራሮች ፣ ከርእዮተ አለም ብቻ ሳይሆን ከዘርና መንፈስም ጭምር ባንድ ስም የተጠመቁ እንዲሆኑ አድርጎ ፣ ተቋሙን በማያዳግም ሁኔታ ቀየረው፡፡
በዚህ ወሳኝ የህወሓት ስራ ምክንያት፣ በ1997 አ.ም. በተፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት፣ በቅርቡ ነብሳቸው ያለፈው አቶ መለስ ዜናዊ ፣ የቅንጅትን የምርጫ ውጤት ተከትሎ በተነሳው የህዝብ ቁጣ ምክንያት ፣ የህወሓት የስልጣን ጊዜ የማብቂያው ደወል በድጋሚ እንደተደወለባቸው የተረዱት ሟች፣ በሰባት ሰአት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዜና ላይ አይናቸውን እንዳፈጠጡ፣  ያለምንም መቆራረጥ እና ስቅታ፣ ለተቃውሞ የሚወጣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተተኩሶ እንዲገደል ሲናገሩ ፣ ትእዛዛቸውን ተቀብሎ የብዙ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ህይወት ፣ በጥይቱ የሚቀጥፍ ሎሌ ሰራዊት የፈጠሩትም፣ በ1993  አ.ም. በህወሓት ላይ ተጋርጦ በነበረው አደጋ ባሰናዱት መጠባበቂያ ጡንቻቸው አማካኝነት ነበር፡፡
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ህዘብ ፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንደ ህዝብ አንድ ሊያደርጉት የሚችሉትን እና ኢትዮጵያዊ ወገንተኝነት ከትግራይ ወጥተው ፣ በትግልም ከህወሓት ጋር አብረው አሳልፈው ሲያበቁ፣ ተቃውሞ ቢኖራቸው፣ ተቃውሟቸውን በግልፅ በመናገር፣ ገሃድ የማውጣት ድፍረት የነበራቸው በአመራር ደረጃ የነበሩ፣ የትግራይ ልጆች ውጉዝ ሲሆኑ፣ እነ መለስ ቅዱስ ተብለው ፣ ሌላው ኢትዮጵያዊ ቢበደል እሚጣጋቸው እንኳ ምርጫ እንዳይኖረው ተደርጎ በመኮላሸቱ ፣ ሁሉም አትዮጵዊ እንደዜጋ ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ በደልን አስተናግዷል፡፡
አደጋ ቁጥር ሶስት
በ1997 አ.ም. ህወሓት በውስጡ ከተፈጠረበት የመፈራረስ አደጋ ከተረፈ በኋላ አገርን የመምራት ስራውን በሙሉ ትኩረት እየሰራ ነበር ለማለት በሚያስቸግር መልኩ በብዙ ቅድሚያ በሰጣቸው ነገሮች እንደተወጠረ፣ የ1997ቱ የህወሓት መንግስት አድርጎት በማያውቀው መጠን ፓርቲዎች ከገዢው መንግስት ጋር በህዝቡ ፊት በግልፅ እንዲወያዩ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመፍቀዱ፣ የህዝብ ማእበል ፣ ከመንግስት ተፃራሪ ሆኖ ከቅንጅት ጋር ተሰለፈ፡፡
የዛኔ፣ ኢሃዴግ እንደ ፓርቲ በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፣ ተቀባይነት ከተባለ በህዝቡ ዘንድ የበግ ለምድ ለብሶ ተቀላቅሎ የነበረው፣ አሁን ለትግራይ ታላቅነት ጫንቃው እያለፋ የሚገኘው አርከበ እቅባይ ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ማሳያ ህወሓት የሚመራው መንግስት በአዲስ አበባ ያጋጠመው፣ የዝረራ ሽንፈት፣ አበቃለት ያስባለ ነበር፡፡
ህወሓት በ1993  አ.ም. በመደነቃቀፉ ፣ ከአራት አመታት በኋላ በ1997 ፣ ህዝብ በመላ አገሪቷ ከቁጥጥሩ ውጪ እንዲሆን ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡
ህወሓት ግን ከመቼም ጊዜ በበለጠ በተጠናከረው በቀለኛነቱ ፣  በስልጣኑ ላይ የተነሱበትን እያንዳንዱን በሌላ ጎራ የተሰለፈ በሙሉ (ለምን የእናት ልጅ አይሆንም) ሳይራራ ሁሉንም ተመልሰው ከፊት ለፊቱ እንዳይቆሙ አድርጎ፣ ከፖለቲካ ስነምህዳር እስከናካቴው አጠፋቸው፡፡* በዚያ ደረጃ የኢትዮጵን ሀዝብ አቀጣጥሎ አነሳስተቶ የነበረ የህዝብ ሱናሚ፣ እንዲረሳ ማድረግ ብቻ አይደለም፣ መለስ ዜናዊ በራሱ ምላስ ጎረቤቶቻቸው እንዲገደሉ፣ ትእዛዝ ያስተላለፈባቸው ሰዎች እና ያዘዘውን የሞት ፍርድ ብይን የሃይማኖት ተፅእኖ ትከሻውን የተጫነው ይሄ ምስኪን ህዝብ ረስቶለት፣ ፣ በስድስተኛ አመቱ እሱ ሲሞት፣ ፀጉሩን እየነጨ፣ እንባውን እየረጨ ፣ አደባባይ ሞልቶ ቀበረው፡፡ ይህንን ያደረገው ሌላ አስማት ሳይሆን፣ ህወሓት ሊቃወመው የተነሳውን ህዝብ ስሜት በኪስ አውላቂነት ልማዱ ነጥቆ፣ እራሱን ስለሚያቀርብ ነው፡፡
በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የህዝብ ተቃውሞ በማስተዋል ለተመለከተ ሰው ፣ ገፅታውን ለመረዳት ብዙ የሚያስቸግር አይደለም፡፡ ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ከተማ የማስተር ፕላን መስፋፋት ፣ እና ከቅማንት ህዝብ እና ወልቃይት ጋር ተያይዞ ይነሳ እንጂ ዋነኛው ችግር ተጠራቅሞ የነበረው እና መንግስት በህዝብ ላይ ያለው ከቁጥር ያለፈ ኢፍትሃዊነት፣ የመሬት ነጠቃ፣ የዘር ፖለቲካ (መንስኤ የሆነባቸው አያሌ ችግሮች) ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ እና ሌሎችም ተዘርዝረው የማያባሩ በደሎች ናቸው፣ የኦሮሚያ እና የአማራው ህዝብ ፊት ለፊት ወጥቶ በጥይት እስከ መደብደብ ድረስ ያበቃው፡፡
ይህ መንግስትን ከመሰረቱ የነቀነቀ፣ ህዝብን ከዚህም ኪያም እንደሚጋባ እሳት ሲዳረስ የነበረ ለአንድ አመት የዘለቀ የተቃውሞ ሁኔታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በመሳሪያ ከታፈነ፣ ኢትዮጵያም ትልቅ እስር ቤት ከሆነች፣ስምንት ወራት ያክል ተቆጥረዋል፡፡ ልብ ብሎ ከላይ የዚህ ፅሁፍ መግቢያ ሆኖ የቀረበውን የአቶ በረከት ስምኦንን ንግገር እና ማሳያዎቹን ላስተዋለ ሰው፣ አንድ ወለል ብሎ የሚታየው ስእል ይኖራል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ካልታየም ግን ግድየለም መግቢያዬ ላይ ከጠቃቀስኩት በጥቂቱ ጠለቅ ብዬ ልናገር፡፡ የኦሮሞ ህዝብ መንግስትን የተቃወመው ፣ በደል ስለደረሰበት እንጂ ተቃወም ተብሎ ፣ ከውጪ ባሉ አክቲቪስቶች ታዞ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይህንን ተቃውሞ በተለያዩ መንገዶች፣ የማህበራዊ ሚድያን፣ የቴሌቭዥንና የሬድዮ ቅስቀሳዎች የነበራቸውን ሚና ግን መካድ አይቻልም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኦሆዲድ መቋቋም ከሚችለው በላይ በህዝብ ማእበል ኦሮሚያ ሲታመስ፣ ህወሓት አትችልም በሚል ስንቱን እየበወዘ ተቃውሞውን ጋብ ለመድረግ እንደሞከረና እንዳልቻለም የኢትዮጵ ህዝብ ያየው ነው፡፡
ከዚህ የኦህዲድ አቅመ ሰንካላነት በኋላ የነበረው ተቃውሞውን የመቆጣጠሪያ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለነበረ፣ ከጠመንጃ በቀር ምስጋና ለእኔ ይገባኛል የሚል አንድም ባለድርሻ አናውቅም፡፡ እንዳልኩት በተለያዩ የሚዲያ መንገዶች ህዝቡን ያበረታቱት ሰዎች እንደውም ከሌላው በተለየ፣ ይሄንን አስተዋፅኦ አድርገናል የማለት ሞራላዊ ብቃት ሊኖራቸው ይችል ይሆናል እንጂ፣ ሌሎቹ ከስርፋው አልነበሩም፡፡
ሰሞኑን ግን፣ ትእይንቱን ሁሉ የተቆጣጠረው አንድ ግለሰብ አለ፡፡ እጅግ ደግሞ ነገሩን ሳቢ የሚያደርገው፣ በኦሮሚያ አመፅ ወቅት በንዴት በግነው፣(አሁን ደግሞ ምን ቀረ ብለው ነው፣ ግርግር የሚፈጥሩት፣ ማስተርፕላኑን እንደሆነ መንግስት ትቼዋለሁ ብሏል”፣ “ ማስተርፕላኑን ለምን አሰባችሁት ብለው ይሆናላ!” ) እየተባባሉ የኦሮሞን ህዝብ ስም መስማት እንኳን አቅለሽልሷቸው የነበሩት እነዚያው፣ ህወሓትን ሲጠብቁ ውለው፣ ሌላውን በለው እንግዲህ ሲሉ የሚውሉ አቀንቃኞች፣ ከታላቆቹ የመንግስት ባለስልጣኖች ጭምር፣ አንድን ስም አውርተው አይጠግቡም፡፡ ለማ መገርሳ!”
  • ለምን ከተባለ ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ህወሓት በክፉ ነገሮች እና አጋጣሚዎች ሁሉ ስልጣኑን የሚያቆይበትን መንገድ መልሶ ማስተዋል ነው፡፡
ለማ መገርሳ ፣ ተበደልኩ ብሎ ሲጮህ ከታፈነበት ሳለ፣ ማንም ያለሰማው ህዝብ ፣ በብዙ መስዋእትነት ያቀረበውን የስር ነቀል ለውጥ ጥያቄ እንደ 1981 – 1993 – እና 1997 ክስተቶች ወቅት ህወሓት እራሱን ከሞት ለመታደግ፣ አንድ ጭዳ የሚሆን ቡድን ላይ ሃጢያት ሁሉ ከለጠፈ በኋላ፣ ይዞት ብቅ የሚለው የቅዱስ ለምድ የተደረበለት፣ አዲሱ የህወሓት ጀግና ፣ ይህ ሰው ነው!!!
ከመንግስት ባለስልጣኖች ሁሉ በተለየ መልኩ፣ ለማ መገርሳ በንግግሩ ውስጥ ስለታሪክ ያለውን አመለካከት የሰሙ ለዘመናት በየውጪ ሃገራቱ የከተሙ ተቃዋሚ ተብየዎች ሳይቀሩ በአንድነት፣  የሚፅፉትን ነገር ቆም አድርገው፣ “እኚህን ሰው ግን ያዝልቅላቸው!” እስከ ማለት ድረስ – “ቁጭ ይበሉ!!!” መስራት የቻለ ለምድ፣  ህወሓት ያለበሳቸው፣ አዲሱ የህዝብን ድምፅ፣ እምጥ ይግባ ስምጥ፣ ሰርቀው እንዲያስረክቡ የመጡ ናቸው፡፡  ልክ እንደ ቀደመው ጊዜ፣ ተኮላሽቶ በህወሓት አገዛዝ ስር ተኮራምቶ እንዳለው የኢትዮጵያ ክፍል፣ ከኦሮሚያ ህዝብ ሙሉ ሞራሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ድባቅ የሚመታባቸው ወሳኝ መሳሪያ ናቸው፣ – አቶ ለማ መገርሳ ፡፡ ለዚያም ነው ፣ ከመንግስት ባለስልጣን እስከ ህወሓት መራሽ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ድረስ ፣ የአቶ ለማ መገርሳን ስም ጠርተው የማይጠግቧቸው፡፡
የኦሮሚያ ህዝብ ህወሓትን ገፍቶ ካንሸራተተው ገደል፣ ውስጥ ለማ መገርሳ ጎትተው እያወጡት ነው ዛሬ!!!፣
አቶ ለማ መገርሳ ፣ በዚህ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሪፑብሊክ የአስተዳደር ስርአተ ውስጥ እንደ ዋነኛ ስራ በሚቆጠረው፣ የቀደመ “ታሪክን ፣ ከዘር”- ለመዋቀሻ ብቻ ካልሆነ ፣ “ለመቀራረቢያ እና ለአንድነት” መስበኪያ የመጠቀም ልምዱ እጅግ አነስተኛ ከሆነ መንግስት መሃከል እንዳልወጡ፣ “በታሪካዊ ማንነት መወቃቀስ ይብቃን!” ብለው ሲናገሩ፣ እስቲ ነፃነት ስለጠየቁ፣ መብታችን ተነፍጓል በማለታቸው፣ ጭንቅላታቸው በጥይት የተበሱትን ሰዎች ደም እያስቆጫቸው ያወሩ እስኪመስል ድረስ፣ የህወሓት ሰዎች አዲሱ ጀግናቸውን፣
  • “እስከዛሬ የት ነበሩ ይሏቸዋል!!!” በቂ ማሞገሻ ቃላት ጭምር አጥተወላቸው፡፡
ስለዚህ ከህወሓት በተቃራኒ እንደቆሙ አድርገው እራሳቸውን ለኦሮምያ ህዝብ ያቀረቡትን እኚህን ሰው ህወሓት ዝም ብሎ አያያቸውም፣ የሚችለውን እያደረገ ፣ ኦሮሚያን መልሰው እግሩ ስር እንዲያስገቡለት ይረዳቸዋል እንጂ፡፡ ለዚህም ሲባል ነው፣  ከሃያ አመት በላይ ሲመላለስ በኖረ ጉዳይ ላይ በልዩ ጥቅም ስም አዲስ አበባ የሽንገላ ወሬ ፣ የመጀመሪያ ለአቶ ለማ መገርሳ የጀግንነት ጎዞ ጅማሬ በህወሓት የተተኮሰ ፣ የመጀመሪያ መድፍ ነው!
ስለዚህ መንግስትን ሲሳደቡ ቢውሉ፣ በመንግሰት ቁጥጥር ስር እንዳይደሉ ያለምንም ፍራቻ ሊያሳዩ ቢሞክሩ፣ ይሞግታቸዋል ብሎ የሚጠብቅ ካለ አሁንም ህወሓትን አልተረዳነውም ማለት ነው፡፡ ህወሓት የሚያደርገውማ፣ ከአቶ ለማ መገርሳ  ፊት ፊት እየቀደመ፣ ህወሓት እንዴት ፈቀደላቸው የሚያስብል ብዙ የይስሙላ ሽልማቶች ይደርብላቸዋል፡፡ ሁሉን ነገር በቁጥጥሩ ስር መልሶ ያስገባ ቀን፣ መልሶ “ውጉዝ ከም አርዮስ!” ይላቸዋል፣ ወይ ቅዱስ ብሎ የሰይጣናዊ ስራ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደርጋቸዋል፡፡ አቶ በረከት ፣ “ክሪቲካል ማስ አለን” ሲሉ፣ ያልተናገሩት ያ ክሪቲካል የተባለው ማስ፣ የሚመነተፍ የህዝብ፣ እውነተኛ ጥያቄን እንዴት እንደምንቀማ እናውቅበታል ማለታቸው ነበር፡፡ ይህ ነው ዋናው ሃቅም!!!
ህወሓት ከውጪም ሆነ ከውስጥ ብቻ እውነተኛውን የህዝብን የተቃውሞ ጉልበት ጨረፍታዋን ባለፈው አመት ተቃውሞ አጣጥሞ ነበር፤ ታዲያ በዚች ቅንጣት የምታክል የኦሮሚያና ከፊል የአማራ ክልል ተቃውሞ፤ የህወሓት ህልውና ከነአጀንዳው መርዝ እንደቆረጠመች አይጥ ጢምቢራው ዞሮ፣ የኢትዮጵያ ምድር ገደል ሆናበት የሚረግጠው ሁሉ ርቆበት ነበር፡፡ ለዚህ ቀውስ የሚከሰሰውን ከሶ፣ የሚገደለውን ገድሎ፣ የሚፈሰሰውን ደም አፍስሶ፣ የሚጠፈረውን አገሪቷን በመሳሪያ ጠፍንጎ ትንፋሹን ከሰበሰበ በኋላ፣ በተካነበት የበቀል እርምጃው ያንገዳገዱ እና ምድሪቷን ገደል ያደረጉበትን ከእግሩ ስር ለማስገባት፣ በአገሩ ፈረስ እንደሚባለው፤ አንድ ጋሻጃግሬ ይዞ ከተፍ ብሏል፡፡ እኚህ ጋሻጃግሬ በብዙ የፖሊሲና የፖለቲካ ዲስኩር ሙገሳ የታጀቡ፣ የንጹሓንን ድምፅ ቀምተው ሲያበቁ መልሰው ስልጣንን በኦሮሞ ህዝብ ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልሰው የሚያስረክቡ አዲሱ ትከሻ ናቸው!
  • ለማ መገርሳ ለኦሮሞ ህዝብ የመጡ ሳይሆኑ፣ ህወሓትን ከገደል ውስጥ እያወጡ ያሉ ምልምል አዲሱ ጋሻጃግሬ ናቸው!!!
ኢትዮጵያ ለዘልአለም ትኑር!
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!

No comments:

Post a Comment