Translate

Wednesday, July 12, 2017

የተዳፈነ ገሞራ


የተዳፈነ ገሞራ
እነሆ በሐምሌ 5 ቀን , 2008 በመላ ኢትዮጲያ በተለይም በጎንደርና በኦሮሚያ ተቀጣጥሎ የነበረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከተከሰተ ድፍን አንድ አመት ሆነው። የኢትዮጲያ ሕዝብ በተደጋጋሚና በተለያየ መንገድ ለስርአቱ ያለውን ተቃውሞ ሲገልጽ ሩብ ምዕተ አመት ቢያስቆጥርም ያለፈው አመቱ ቁጣ ግን በቅርጹም በይዘቱም የተለየ ነበር። በዚህ የዘመናዊ አርበኝነት ትግል ውስጥ ከሁሉም ጎልተው የታዩትና የተሰሙት ሁለት አውራ መልዕክቶች ነበሩ። አንደኛው ሕዝብን ያላሳተፈ፣ ሕዝብ ተጠቃሚ ያልሆነበት ልማት ባፍንጫችን ይውጣ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እኛ ኢትዮጲያዊያን መቼ መቼም ቢሆን አንከፋፈልም የሚሉ ነበሩ።
የኮነሬል ደመቀ መኮንን እና የኦቦ በቀለ ገርባ ምስሎች በአንድነት በጎንደር አደባባይ ላይ ሲታዩና የኦሮሞ ደም ደማችን ነው የሚለው ታሪካዊ መፈክር ሲሰማና በአምቦ ከተማ የአማራ ደም ደማችን ነው የሚለው የአንድነት መንፈስ ሲስተጋባ በርግጥም የወያኔ/ሕወሃት ዕድሜ እያጠረ መሆኑን አመላካች ክስተቶች ነበሩ። እሳትና ጭድ እንዴት ተፋቀሩ የሚል እንቆቅልሽ በበታችችነት ስሜትና በዘረኝነት ካንሰር ለሚሰቃዩት ወያኔዎችና ጉጅሌዎቻቸው ይህ የአማራና የኦሮሞ አንድነት ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኖ ነበር። እንቆቅልሹ በአንድ ወይም በሌላ መልክ ራሱን እየቀያየረ እንቅልፍ እየነሳቸው መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ብዙ ናቸው።
ልብ ያለው ልብ ካለ!
በጎንደርና አካባቢው በጀግናው ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ መሪነት የተነሳው ጥያቄ በዋናነት የወልቃይት ጠገዴ መሬት የአማራ ሕዝብ መሬትና አንጡራ ንብረቱ ስለመሆኑ ጉዳይ ነበር። እኛ ትግሬዎች ሳንሆን አማሮች ነን። በግድ ትግሬነትን እንድንቀበል አታስገድዱን። ይህን የሚደግፍና የሚያጸድቅ ህገ መንግስት ካለም አንቀበልም ነበር ያሉት።
የኦሮሞ ልጆችም በማስተር ፕላን ስም መሬታችንን አትንጠቁን፣ ከቤት ንብረታችን አታፈናቅሉን፣ ወተቷን አይተን የማናውቅ የሰማየ ሰማያት የልማት ላም እያለባችሁልን በከንቱ ተስፋ ሕይወታችንን አታጨልሙ እያለ ነበር ሲጮህ የነበረው። ለነዚህ ፍትሃዊ ጥያቄዎች ግን ወያኔ ሕወሃት የሰጠው ምላሽ በገፍ ማሰር፣ ህጻን አሮጊት ሳይል በየመንገዱ መግደል፣ ማሳደድ፣ ማሸማቀቅ ብቻ ነበር። ጊዜአዊ አስቸኳይ አዋጁንና በአጋዚ ጦር የሚመራ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ በሁለቱ ክልሎች የሚኖሩ ሕዝቦችን አፍኖ እድሜውን ማራዘም ነበር የመረጠው። የስርዓቱንና የአዋጁን የመጨረሻ የዝቅጠት ደረጃ ያሳየው ግን የሰው ልጅ በተፈጥሮ የታደለውን የመናገር መብቱን ማፈኑ ብቻ ሳይሆን ኢሳትንና ኦ ኤም ኤንን የመሳሰሉ ሜድያዎችን እንዳያምጥ መከልከሉ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ለዚህ ከፍተኛ ለሆነ የሕዝብ መነቃቃትና ታሪካዊ የፍትህ ጥያቄ ሕወሃት የሚዘውረው ጠቅላይ ሚኒስትርና ፓርላማው የሰጡት ምላሽ ከባለ ራዕዮ መሪያቸው የተማሩትን የተለመደ የይስሙላ ምላሽ ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን ከማስተር ፕላኑና ከወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ አልፎ ሕዝቡ በቃችሁ ውረዱልን፣ እኛ የምንፈልገው የስርዓት ለውጥ ነው ቢልም ከባለቤቱ ያወቀ ምንድነው እንዲሉ የኢትዮጲያን ሕዝብ ጥያቄ ወደ መልካም አስተዳደር እጦት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመሳሰለው እንቶ ፈንቶ እሽቆልቁለው ካወረዱት ይኸው አመት ሞላቸው። ለነገሩ እኮ ይህንን የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሰቢነት ጉዳይ አንስቶ መነጋገሩም ባልከፋ። ግን ችግሩ ዋናዎቹ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ሙሰኞች፣ አድርባዮች፣ ዘረኞችና ነፍሰ ገዳዮቹ ራሳቸው የስርዓቱ አራማጆች መሆናቸው እንጂ። አባቱ ዳኛ፣ ልጁ ቀማኛ እንዲሉ።
የኢትዮጲያ ሕዝብ ጥያቄ አጭርና ግልጽ ነው። ኢትዮጲያ አትበታተንም። እቺ አንድና ብቸኛ የሆነች የጋራ ቤታችን አንድነቷ ሊጠበቅ የሚችለው የሕግ የበላይነት የሰፈነበት የዲሞክራሲ
ስርዓት ሲዘረጋ ብቻና ብቻ ነው። አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ "ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ሕዝቡ የሰላምና ደህንነት ዋስትና እንደሚሰማው አረጋግጠናል" ይላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ የተንሸዋረረና ራስን ከመሸንገል የመጣ ነው ብለን እናምናለን። አሁንም ቢሆን ይህ ፍትሃዊ የሕዝብ ጥያቄ እስካልተመሰለ ድረስ ይህ ሰላምና መረጋጋት ያለበት የሚመስል የሕዝብ ስሜት እንደተዳፈነ ገሞራ ሆኗል። መቼ ቀንና መቼ ሰአት ላይ እንደሚፈነዳ መተንበይ አስቸጋሪ ነው። ዋናው ነገር ግን መፈንዳቱ አይቀሬ መሆኑ ነው። እንዳውም የወያኔ በደል፣ ግፍ፣ ጭቆና፣ ህዝብን መደለል፣ ህዝብን መናቅ፣ መከፋፈልና ማጫረስ በጨመረ ቁጥር የገሞራው ውጥረትና ግለትም የዛኑ ያክል እየጨመረ እንደሚሄድ ለማወቅ ያዳገታቸው የሃይለማሪያም ደሳለኝና የአባይ ወልዱ አይነቶቹ መንፈሰ ድኩማን ብቻ ናቸው። በቅርቡ በትግራይ ኦን ላይ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ እንደሚለው የትግራይ ክልል አስተዳዳሪና የወቅቱ የሕወሃት ሊቀመንበር አባይ ወልዱ የሀገራችንን ችግር እንዴት እንደሚረዳው ሲያትት "ኢትዮጲያዊያን በውጭ ጠላቶች የተቀነባበሩ ሴራዎችን ጠንቅቀው ማወቅና መጠንቀቅ አለባቸው" ይላል። በርግጥ
የኢሬቻ በአል ላይ የተገደሉት ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ የኦሮሞ ወገኖቻችን ለሞታቸው ምክንያት በውጭ ሃይል የተቀነባበረ ሴራ ነውን? አምባ ጊዮሪስ ላይ የተረፈረፉት ሕጻናት በርግጥ የውጭ ሴራ ነበርን? ባህር ዳር ከተማ ላይ ከትምህርት ቤት ስትመለስ ግንባሯን በአጋዚ ጥይት የተነደለው ወጣት ሴት ታሪክ ላይ የውጭ ሃይሎች ያቀነባበሩት ሴራ ይኖር? በርግጥ ከአንድ አመት በላይ በእስር ላይ የሚገኘው ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ ያቀረበው ፍትሃዊ የወልቃይት ጠገዴ አማራነት ጉዳይ የዉጭ ሃይሎች የጠነሰሱት ሴራ ነበርን? አቦ በቀለ ገርባና ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በእስር ቤት የሚሰቃዩት በርግጥ በውጭ ሃይሎች በተጠነሰሰ ሴራ ነውን? እነኚና ሌሎች በሺዎች የሚቆጥሩ ኢትዮጲያዊያን በየእስርቤቱ የሚማቅቁት ነጻነትና ፍትህን በገዛ ሀገራቸው ለማግኘት ወይስ የነጻነት ጥማት፣ የፍትህ ጥማት የግብጽና የአሸባሪዎች ተልዕኮ ስለሆነ ነው? ሀብታሙ አያሌው በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ የደረሰበትን መራራ ስቃይ ሲገልጽ የህወሃት ገራፊዎች " እናንተ አማሮች አርፋችሁ ካልተገዛችሁ እቺን አገር ለኦሮሞ ሰጥተናት ነው የምንሄደው"እያሉ ሲያስፈራሩት እንደነበር ሲናገር ስንሰማ ታዲያ ይህ የበሽተኛ አስተሳሰብ በርግጥ ከውጭ ጠላቶች የመጣ ነውን? ለኛ ጠላታችን ከውጭ የመጣ ሳይሆን በኢትዮጲያ ጠላቶች ግፊትና ድጋፍ ስልጣን ላይ እንዲቆይ የተፈቀደለት ራሱ ሕወሃት ብቻ ነው!
ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በመባል የሚታወቀው አርበኛ ገብርዬ ከወያኔ ጦር ጋር አንገት ላንገት ተናንቆ መጨረሻ ላይ እንደ አጼ ቴዎድሮስ ሽጉጡን ጠጥቶ መሰዋቱ የውጭ ሃይሎች የጠነሰሱት ሴራ ነውን? አርበኛ አበራ ጎባውስ? አርበኛ ብርሃኑ ጀግኔስ? አርበኛ አለማየሁ፣ አርበኛ ፍርዱ፣ -----? አረ ስንቱ፣ ስንቱን ቆጥረን ልንጨርስ? ዛሬ በሰሜን በረሃ ወያኔን ሲታገሉ ተይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡ ጀግኖች በድፍረትና በሙሉ ልብነት " እኛ ትላንትም፣ ዛሬም ነገም አርበኞች ግንቦት 7 ነን" ብለው ሲናገሩ ስንሰማ ምን አይነት የውጭ ሃይል ይሆን እነዚህን አርበኞች የወያኔን የእስር ቤት ስቃይና መከራ ተቋቁመው እንዲያልፉ ወኔውን የሰጣቸው ወይስ በደም ስራቸው የሚንቆረቆር የአባትና አያቶቻቸው የጀግንነት ስሜት? የአልበገር ባይነት ስሜት? የነጻነት ስሜት? ይህንን ግን ለገዢዎቻችን ማስረዳቱ ጉንጭ ማልፋት እንዳይሆን ትተነዋል።
በኛ አመለካከት እነኚህ ሁሉ በሕወሃት ወያኔ አገዛዝ ስር የተሰው፣ የታሰሩ፣ የተሰደዱና ጥርሳቸውን እያፋጩ የነጻነት ቀናቸውን በተስፋ የሚጠብቁ ሁሉ የዘመኑ አርበኞቻች ናቸው። ባጭሩ አነጋገር ወያኔን ለመታገልና ለመጣል የሚደረግ ትግል ሁሉ አርበኝነት ነው። በሃገር ውስጥም፣ በበረሃም ሆነ በተለያዩ አለማት ያሉ ዳያስፖራዎች የሚያደርጉት ትግል ዘመኑን የዋጀ የአርበኘት ትግል ነው።
"ኢቢዴ ላፈጀ ለዴሙ" ይለዋል ኦሮሞኛው ከላይ ሳይታይ ውስጥ ውስጡን እየሰፋና ስር እየሰደ የሚሄድን እሳት። ድንገት ከተሸፈነበትና ከተደበቀበት ያፈተለከ እንደሆን ለወዳጅም ለጠላትም አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥር አያጠራጥርም።
እናም የዘንድሮን ሓምሌ 5 የምናስበው ከአመት በፊት ከፋሺስቱ ሕወሃት/ወያኔ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው የተሰውትን አርበኛ ኢትዮጲያዊያን በጥልቅ ኩራትና ክብር በማስታወስ ሊሆን ይገባል።
በመጨረሻም ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን "ጴጥሮስ ያቺን ሰአት" በሚለው ተውኔቱ ውስጥ አቡነ ጴጥሮስ ለኢትዮጲያ ሕዝብ ከፍተኛ ንቀት ለነበረውና በእብሪት ለተወጠረው የሞሶሎኒ እንደራሴ ግራዚያኒ የሰጡት መልስ የሚከተለው ነበር
"ጭቆናችሁ ንቀታችሁ እስካላቋረጠ ድረስ
የሕዝቡም ትብብሩ አይፈርስ - መቋቋሙ አይገረሰስ
በናንተ የበላይነት – በኛ ተደፍቶ ተገዢነት ዘላለም ተጎታችነት
የናንተ ሕግ አንጾን
ፍልስፍናችሁ ወስኖን ብቻ ነው የናንተ ህግጋት
የነጭነቱ ስርአት ( የሕወሃቱ ስርአት) የፋሽስትነቱ ድንፋት,,,,,,
ዘበቱ እዚህ ላይ ነው------አትታለል
ጸጉር ከምላሴ ይነቀል
ለክፉም ይሁን ለበጎ
በግድም ቢሆን ተደርጎ
ራሳችንን የማዘዙን – ራሳችንን የመምራቱን መብት
ከመንጋጋችሁ ገንጥለን ወስደን እኩልነት እስኪኖረን
ሰው የመባል ጸባያችን ከቶ አይበገርላችሁም
ከቶም እንቅልፍ አይሰጣችሁም.........”
አሁንም እኛ ለዘመኑ ሀገር በቀል ፋሺስት ወያኔዎች የምንላቸውም ይሄንኑ የአቡኑን ምላሽ ነው። በኢትዮጲያ ምድር ላይ የአንድ ብሄር የበላይነት ተወግዶ፣ ሕዝብ በዲሞክራሲ ምርጫ ብቻ የመረጠው የዘረጋው ስርዓት እስከሚመጣ ድረስ፣
የሕግና የፍትህ የበላይነት እስከሚረጋገጥ ድረስ፣ በነጻነት የመጻፍ፣ የመናገር መብት እዉን እስከሚሆን ድረስ፣ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ ወገኖቻችን እስከሚፈቱና የሰላምን አየር እስከሚተነፍሱ ድረስ፣ በመጨረሻም የፋሺስቱ አፓርታይድ የሕወሃት/ወያኔ ስርዓት እስካልተወገደ የአርበኝነት ትግላችን ከቶውንም አይቆምም።
ታሪካዊዉን ሐምሌ አምስትን ዳግመኛ እንደምናቀጣጥለው ምንም ጥርጥር የለንም።በትግሉ የተሰዉትን አርበኞቻችንን ነፍስ ይማርልን! እናከብራቸዋለን፣ ሁሌም እናስባቸዋለን
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment