Translate

Monday, July 17, 2017

አጋዚ በአምቦ ሁለት ወጣቶችን ተኩሶ ገደለ | በአድአ ከተማ ቀብር ከሚሄዱ ሰዎች መካከል ሰላሳዎቹ በአጋዚ ታፈኑ | ጊንጪ ዛሬ ሰኞ ንግድ ቤቶች ሁሉ ዝግ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል

አምቦ ከተማ ፎቶ ከዘ-ሐበሻ ፋይል
(ዘ-ሐበሻ) በገንዘብ እጦት እየታመመ እንደሆነ በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚተቸው ሕወሓት መራሹ መንግስት በሕዝቡ ላይ በጫነው አግባብ ያልሆነ ግብር ተቃውሞ እየተነሳበት እንደሆነ ዘ-ሐበሻ በተለያዩ ዜናዎች እየዘገበች ትገኛለች::
በአምቦ ከ4 ቀናት በፊት በጀመረው ሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ የተረበሸው የሕወሓት አጋዚ ሰራዊት ትናንት እሁድ ጁላይ 16, 2017 አምቦ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ሁለት ወጣቶችን ተኩሶ መግደሉን የዓይን እማኞች ገልጸዋል::

የዓይን እማኞቹ እንደሚሉት አምቦ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ከሞቱት ሁለት ወጣቶች መካከል የአንደኛው ስም ይፋ ሆኗል:: ሟቹ ወጣት ዲና ኦል ይሰኛል:: ትናንት እሁድ አምቦ ከተማ በከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ስትናጥ መዋሏም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያስረዳል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ በውጥረት ላይ ያለው የሕወሓት አገዛዝ ምዕራብ ሸዋ አድአ በርጋ በሞጎር ከተማ ወደ ቀብር በመሄድ ላይ ከሚገኙ ወገኖች መካከል ወደ ሰላሳ የሚጠጉት ተመርጠው በአጋዚ ሠራዊት ታፍነው መወሰዳቸውን የ ዓይን እማኞች ገልጸዋል:: የአድአ ከተማ በግብር መጫን የተነሳ ሕዝቡ መቆጣቱትን የተረዳው የሕወሓት መንግስት ለቀብር የሚሄዱ ሰዎችን ካለምንም ምክንያት አፍኖ ወስዷል በሚል ከተማዋ ተረብሻ መዋሏን ነው እማኞቹ የሚገልጹት::
በሌላ ዜና በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ከተማ ዛሬ (ሰኞ) ጁላይ 17 የንግድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተው እንደሚውሉ የአካባቢው አክቲቭስቶች ገልጸዋል:: በጊንጪ ከተማ ሕዝቡ አላግባብ በተጫነበት ግብር መቆጣቱንና ቁጣውንም ለመግለጽ ንግዱን ዘግቶ እንደሚውል ይጠበቃል የሚሉት ምንጮች አካባቢው በውጥረት ውስጥ እንዳለ ገልጸውልናል::

No comments:

Post a Comment