Translate

Thursday, July 27, 2017

የስነ-ልቦና ጦርነት (የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)


ትልቁ የጦር ሜዳ የሰው ልጅ ጭንቅላት ነው። የብዙ ሰዎችን ጭንቅላት ያሳመነ አስተሳሰብ አሸናፊ መሆኑ የማይቀር ነው።ስለሆነም ጠላትን ለማሸነፍ በአስተሳሰብ በልጦ መገኘት ወሳኝ ነው። በአስተሳሰብ በልጦ ለመገኘት ደግሞ ምክንያታዊነት ብቻውን በቂ አይደለም። ከምክንያታዊነት በተጨማሪ ስሜቶችን (emotions) መቆጣጠር ይገባል።Patriotic Ginbot7 Radio
አሸናፊ ስነልቦና ያለው ተፋላፊ ስሜቶቹን የሚቆጣጠር፤ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንኳን መንፈሱ የተረጋጋ ነው። ስለሆነም ለማሸነፍ አንተ በተረጋጋ የአዕምሮ ሁኔታ ላይ መገኘት ይኖርብሃል። በአንፃሩ ተፋላሚህ ደግሞ መዋከብ፣ መርበትበትና መደንገጥ ይኖርበታል። “ጠላትህ ማዋከብ” የስነልቦና ጦርነት ግብ ነው።
አምባገነን ሥርዓትን ማሸነፍ የሚቻለው የሥርዓቱ አራማጆች ወደ እብደት የተጠጋ የስነልቦና ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ነው፤ ያኔ ውሳኔዎቻቸው ሁሉ የጭንቀት ይሆንና በስህተት ላይ ስህተት ይጨምራሉ፤ ከጭንቀት ብዛት የራሳቸውን ወዳጆች ሳይቀር ያጠፋሉ።
የስነልቦና ጦርነት በተለያዩ መንገዶች ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል።

በጦርነቶች ውስጥ ፉከራ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶ፣ ሰልፍ የሚደረገው ወዳጅን ለማጀገንና ጠላትን ለማሸማቀቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በበራሪ ወረቀቶች፣ ከሰው ወደሰው በሚተላለፊ ወሬዎችና አሉባልታዎች አማካይነት በሚላኩ መረጃዎችና ማሳሳቻዎች አማካይነት ከፍተኛ የመረጃ ጦርነት (Information warfare) ይካሄዳል።
በዚህ አጭር ጽሁፍ በቀላሉ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ሶስት የስነልቦና ጦርነት ስልቶች ላይ እናተኩራለን: “ማግለል”፣ “ማድነቅ” እና “ማብራራት”።
ማግለል – የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድና የደኢህዴግ እንዲሁ የአጋር ድርጅቶች ቀንደኛ አባላትን፤ ግፈኛ የፌደራል ፓሊስ አባላትን፣ በየመንደሩ እያነፈነፉ ያሉት ጆሮ ጠቢዎችን፣ ጭንቅላት የለሽ ፓሊሶችን፣ ፍርደ ገምድል ዳኞችን፣ ሀሰተኛ አቃቢያነ ህግ፣ ካድሬ መምህራንን፣ የመንደር ለፍላፊ ካድሬዎችን ማግለል፣ መጠየፍ፣ ማራቅ፣ መናቅ፣ ማዋረድ። ጆሮ ጠቢዎችንና ገራፊዎችን ማጋለጥ፣ ፎቶግራፎቻቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ መበተን፤ በእነሱ ላይ ማፌዝ፤ ድንቁርናቸውን፣ ሆዳምነታቸውንና ዘረኝነታቸውን የሚገልፁ የቅሌት ስሞችን ማውጣት እና ማሰራጨት ወደ እብደት ሊመራቸው ይችላል። ማግለልን ተግባራዊ ለማድረግ “ጨዋ” ለመሆን መሞከር አያስፈልግም። ማንኛውም ዜጋ “ከውሸታም፣ ሆዳምና ደንቆሮ ጋር አብሬ አልውልም” ማለት መብቱ ነው። ከትንሽ ሰው ጋር መዋል ያሳንሳል፤ በዛሬዋ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የህወሓት አገልጋይ መሆንን ያህል ትንሽነት የለም። ከዚህ አንፃር ሲታይ የህወሓት ሰዎችን ማግለል መብት ብቻ ሳይሆን ብልህነትም ነው።
ማድነቅን – ለነፃነት ሲሉ ዋጋ የከፈሉ እና እየከፈሉ ያሉ ዜጎችን ማድነቅ፤ አርዓያነታቸውን ማጉላት፤ ማበረታታት፤ ሁለተናዊ ድጋፍ መስጠት። ከታጋዮች መካከል ጀግኖችን ማውጣት። በእስር ላይ የሚገኙ የህሊና እስረኞችን መዘከር፤ ማወደስ፤ ማበረታታት፤ ቤተሰቦታቸውን መደገፍ። በትጥቅ ትግል የተሰለፉ ወገኖችን መደገፍና ማበረታት፤ የሕዝባዊ አመጽ ጀግኖችን ማስነቅ፣ ማበረታት። በትጥቅ ባልተደገፈ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሥርዓቱን እየተገዳደሩ ያሉ ወገኞችንም መደገፍ፣ ማበረታት፤ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ጀግኖችን ማውጣት።
ማብራራት – የሥርዓቱ አገልጋዮች አድርባይነት ከዚያም አልፎ ወንጀለኝነት በማስረጃዎች አስደግፎ ይፋ ማድረግ። ስለ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፤ ሰለ ሀብት ዘረፋ፣ ስለ ሙስናን፣ ስለ መሬት ቅርምት፣ የባለስልጣኖች ሀብት ማሸሽን በሀሪቱ ከተንሰራፋው እና እያደገ ከመጣው ድህነት ጋር እያነፃፀሩ ማቅረብ። አስከፊ ስለሆነው የእስረኞች አያያዝ በሀቅ ላይ የተመሰረቱ ጽሁፎችን በጋዜጦች፣ ሬድዮና ቴሌቪዥኖች መሰል መገናኛ ብዙሀን እንዲሰራጭ ማድረግ። ሥርዓት በያዘ ጨዋ ሙግትና ተጨባጭ ማስረጃዎች ሥርዓቱን እርቃኑን ማስቀረት።

No comments:

Post a Comment