ዋዜማ ራዲዮ- ከኦሮሚያ የጨለንቆ ነጋዴዎች ተነስቶ ጊንጪ፣ አምቦና ወሊሶን ያዳረሰው የግብር በዛብን ስሞታ መልኩን እየቀየረ ባለፉት ሦስት ቀናት ወደ አዲስ አበባ ኮልፌ፣ ታይዋንና አጠና ተራ ተዛምቶ ቆይቷል፡፡ ኾኖም የግብር እምቢታ አመጹ በዚህ ፍጥነት ታላቁን የገበያ ስፍራ መርካቶን ያዳርሳል ብሎ የገመተ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ለብዙ ነጋዴዎች ያልጠበቁት ክስተቱ ኾኖ መገረምን የፈጠረው ይህ አመጽ ለመንግሥት ሹማምንትም ዱብ እዳ ሆኖባቸዋል፡፡
ከትናንት ጀምሮ ግምገማ የተቀመጡ የአስሩ ክፍለ ከተማ የድርጅት ኃላፊዎች አመጹን ማን አስተባበረው በሚለው ጥያቄ ላይ ከረር ያለ ግምገማ ያካሄዱ ሲሆን አዝማሚያዎችን ዐይቶ ማስቆም ሲቻል ይህ አለመደረጉ ትልቅ የመንግሥት ድክመት ሆኖ ተነስቷል፡፡
ትናንት ከቀትር ጀምሮ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮና የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በአንድነት በማዘጋጃ ቤት የካቢኔ አዳራሽ፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የድርጅት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች ራስ ኃይሉ ሜዳ በሚገኘው ቢሯቸው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በስብሰባ ተሰንገው ማምሸታቸውን የዋዜማ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
የማዘጋጃ ቤቱን ስብሰባ ከተካፈሉ ምንጮች ዋዜማ እንደሰማቸው አመጹ ገፍቶ ከቀጠለ ቁርጥ ግብሩን የመክፈያ ጊዜ በተራዘመ ዓመታት እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እስከማንሳት የሚሄድ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ከኃላፊዎች ፍንጭ መሰጠቱን ነው፡፡ ኾኖም እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ መንግሥት ሁኔታዎችን መቆጣጠር እየተሳነውና እየተዳከመ የመጣ ስለሚያስመስል የመጨረሻ አማራጭ እንደሚሆንና አሁን ዋናው ሥራ የእምቢታ አመጹን አስተባባሪዎች የመለየት ሥራ እንደሚሆን አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ የዚህ ሥራ መጀመርያ የሚሆነው ደግሞ ነጋዴዎች ስሜታቸውን የሚተነፍሱባቸው መድረኮች በየወረዳው እንዲመቻቹላቸው ማድረግ፣ ቅሬታ አቅራቢዎችን በፍጥነት ማስተናገድ፣ በእምቢተኝነት የሚጸኑትን መለየት እንደሚሆንና ይህንንም የየክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች በአስተባባሪነት እንዲያስፈጽሙ ተወስኗል፡፡