Translate

Friday, August 10, 2012

ፌደራል ፖሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ “የጁነዲን ሳዶን ባለቤት ያሰርኩት በሽብርተኝነት ጥርጥሬ ነው” አለ

















ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሐመድ ከሁለት ሣምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ከሽብር ተግባር ጋር

በተያያዘ ተጠርጥረው መሆኑን ፖሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አደረገ ሲል ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ዘገበ። የፌዴራል ፖሊስ የውጪና ሕዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር አበበ ዘሚካኤል ስለጉዳዩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ቃለ ምልልስ ወ/ሮ ሃቢባ የተያዙት ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር
በተያያዘ ጥብቅ ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቶ ከፍ/ቤት በወጣ የመያዣ ትዕዛዝ መሠረት ነው። ፖሊስ ያለማስረጃና ያለበቂ ጥርጣሬ ከመሬት ተነስቶ
አንድን ግለሰብ ሊይዝ የሚችልበት ሕጋዊ መሠረትም እንደሌለ አስረድተዋል። ተጠርጣሪዋ ከተያዙ በኋላ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ
ችሎት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ቀነ ቀጠሮ ተፈቅዶ በምርመራ ላይ መሆናቸውን ኮማንደር አበበ አስታውሰዋል።
ሚኒስትር ጁነዲን የምርመራ ሂደቱ ሳያልቅ ባለቤታቸው ንፁህ መሆናቸውን መናገራቸው ተገቢ አለመሆኑን ኮማንደሩ ገልፀዋል። ‘‘የአንድ ሰው ነፃ መሆን የሚረጋገጠው በፍርድ ቤት በሚሰጥ ውሳኔ ነው። ፖሊስና የዐቃቤ ሕግ ክስና ማስረጃ ባልተሰማበት ሁኔታ ባለቤቴ ንፁህ ናት ብሎ መናገር ተገቢ አይደለም’’ ብለዋል።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ይኸው ጋዜጣ በዛሬው እትሙ በሕዝበ-ሙስሊሙ እና በመጅሊሱ መካከል ላለፉት ሰባት ወራት የተፈጠረውን አለመግባባት በሽምግልና ለመፍታት እየተሞከረ ነው፤ ሽምግልና ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ያሉት በራስ ተነሳሽነት የተሰባሰቡ ስምንት አባላት ያሉት ገለልተኛ ግለሰቦች ናቸው ሲል ዘገበ።
አለመግባባቱን በሽምግልና ለመፍታት ጥረቱን የጀመሩት የእምነቱ ተከታይ የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችና የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው። ይህንኑ ሙከራቸውን በተመለከተ በመንግስት በኩል ያለው ምላሽ እስካሁን አለመታወቁን ሽምግልናውን ጀምረናል ካሉት መካከል አንዱ ለዝግጅት ክፍሉ እንደገለጹለት ዘግቧል።
የሽምግልናው መጀመር በተመለከተ በሕዝበ-ሙስሊሙ ዘንድ የተደበላለቀ ስሜት መፍጠሩን ምንጮቻችን አመልክተዋል ያለው ሰንደቅ ሽምግልናውን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ ቀላል የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች ጅምሩን በጥርጣሬ አይን እያዩት ነው። ሽምግልናውን ከጀመሩት የኮሚቴ አባላት አንዱ የሽምግልናው መጀመር መደገፍም ሆነ መቃወም መብት መሆኑን
የጠቀሱ ሲሆን ‘‘እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን’’ ማለት ግን አክራሪነት ነው ብለዋል።
‘‘አንደኛውም ሆነ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሰላም ስምምነት ነው የተፈታው’’ ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሽምግልናው ኮሚቴ አባል ችግሩ በእርቅና በሽምግልና ይፈታ ማለት የሃይማኖታችንና የሀገራችን ባህል ነው ብለዋል።
የሽምግልና እንቅስቃሴው ከተጀመረ በኋላ አንዳንድ ታዋቂ ሰዎችም በጉዳዩ ውስጥ ለመግባት ፍላጐት እያሳዩ መሆኑም ታውቋል። ሽምግልናው የታሰሩትን አባላት ከማስፈታት ባለፈ ችግሩን ከስሩ መርምሮ የመፍታት ዓላማ እንዳለው ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት መንግስትን ከመደገፍና ከመቃወም በዘለለ እንደ ሀገር መኖር ስላለብን መንግስት የሽምግልናውን
ሂደት በሆደ ሰፊነት ይመለከተዋል የሚል ተስፋ አለን ብለዋል። ሕዝቡ ሙስሊሙ በተመለከተ የቁርአንን ሕግና የነብዩን ትምህርት ላይ የቀረቡ ደንብና ስርዓቶችን እያገናዘበ እንዲጓዝ
እንፈልጋለን ያሉት የሽምግልናው አስተባባሪዎች፤ ሕዝበ-ሙስሊሙ የቁርአንን ሕግ፣ የእስልምና ታሪክ በወጉ በማወቅና በሰከነ መንፈስ እንዲጓዝ ጠይቀዋል። ‘‘ጉዳዩ የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም’’ የሚሉት አስተባባሪዎቹ የሃይማኖት ጉዳይ በወጉ መያዝ እንዳለበት አሳስበዋል። የሽምግልናው ሂደት ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ሲል ማንነታቸውን በግልፅ
እንደሚያሳውቁም አመልክተዋል። ይሁን እንጂ በመንግስት በኩል ስለ ሽምግልናው ያለው ምላሽ ለጊዜው አልታወቀም።
አንደ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመንግስት ባለስልጣን መንግስት ከወንጀለኞች ጋር አይደራደርም ማለታቸው የሽምግልናውን ሂደት አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋትን ከወዲሁ ፈጥሯል። ባለፉት ሰባት ወራት በእስልምና ም/ቤት መጅሊስ አመራር ምርጫ፣ ምርጫው የትና በማን ይከናወን፣ በአወሊያ ት/ቤት አስተዳደር፣ በአሕባሽ አስተምህሮ ጉዳይ በሕዝበ-ሙስሊሙ እና በመጅሊሱ እንዲሁም በመንግስት መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ይታወሳል። አለመግባባቱንም ተከትሎ በታላቁ በአንዋር መስጊድና በአወሊያ ግጭት ተፈጥሮ ሰዎች መጎዳታቸውና መታሰራቸው ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment