Translate

Thursday, August 9, 2012

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሐምሌ 28 ቀን 2ዐዐ4 ዓም ባካሄደው የገንዘብ ማሰባሰቢያ የራት ፕሮግራም ላይ በፓርቲው ሊቀመንበር በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የተደረገ የመክፈቻ ንግግር


የተከበራችሁ እንግዶች!
የተከበራችሁ የአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት!
የተከበራችሁ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች!
የተከበራችሁ በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር ሆናችሁ ትኬት በመግዛት ለተሳተፋችሁ!
ከሁሉ አስቀድሜ በራሴና በፓርቲው ስም በዚህ የእራት ምሽት ላይ በመገኘታችሁ በታላቅ አክብሮትና ምስጋ እንኳን ደህና መጣችሁ እላለሁእንዲሁም በትላንትናው እለት  በለንደን ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ወክላ የ1ዐ ሚትር ሩጫ  ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳሊያ ለአገራችን በማስገኘቷ ለአትሌቷና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያለን እላለሁ፡፡
ክቡራንና ክቡራት!

በቀጥታ ወደ እለቱ ፕሮግራም ዝግጅት ዓላማና ምንነት ከመግባቴ በፊት ምንም በስፋት የምታውቁት ጉዳይ ቢሆንም ስለ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ትንሽ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ዛሬ በአገራችን የሕግ የበላይነት፣ ነፃ የፍትሕ ሥርዓት ከመቼውም በላይ እየጠፉ ናቸው፡፡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች በማንአለብኝነትና በግፍ እየተደፈጠጡ ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በየወቅቱ አዳዲስ የልማት መፈክሮችን እየፈጠረና 11.2% እድገት አሳይቻለሁ ቢልም ለብዙሃኑ ሠፊ ሕዝብ ያስገኘው የኑሮ መሻሻል የለም ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ ገብቷል፡፡  ከ4ዐ% የበለጠው የዋጋ ግሽበቱና ድህነቱ የሕዝበን ምሬት ጫፍ አድርሶታል፡፡  ለግሽበቱ ምክንያት ደግሞ የመንግሥት የላላ የገንዘብ ፖሊሲ ነው፡፡ መንግሥት መጠነ ሠፊ ገንዘብ ማሳተሙና በባንኮች ውስጥ ማከማቸቱና መበደር ከሚፈቀድለት በላይ መበደሩ ነው፡፡ በቀን አንድ ጊዜ መብላት የማይቻልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ መልካም አስተዳደር በመጥፋቱ ሙስና ተንሰራፍቶ ሕዝብን እያስለቀሰ ነው፡፡ አዲሱ የሊዝ አዋጅም የሕዝብን የንብረት ባለቤትነትን የገፈፈና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ አምባገነናዊ እርምጃ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የኢኮኖሚ እድገት በወረቀት ላይ እንጂ በምድረ ላይ የለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2ዐ11 ዓ.ም ምደባ እንደሚያሳየው ከሆነ ኢትዮጵያ ከ185 አገሮች መካከል በ174 ደረጃ ላይ ነው የትገኘው፡፡ 38.9% የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት የሚማቅቅ ነው፡፡

ዛሬ በኢንቨስትመንት ስም ሠፋፊ መሬቶች ለውጭ ኩባንያዎች እየተሰጡ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ለቻይና ኩባንያ 25ዐዐዐ ሄክታር ለሳውዲ ኩባንያ 1ዐ,ዐዐዐ ሄክታር ለስድስት የሕንድ ኩባንያዎች 2,465.ዐ12 ሄክታር ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ስፋት 5 እጥፍ የሚያክል ነው፡፡ የመሬቱ ኪራይ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ገበሬውን የመሬት ባለቤትነት መብት አሳጥቷል፡፡ የተፎከረለት የሥራ እድልም ላም አለኝ በሰማይ ነው፡፡
የአገሪቱንም የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ  የተመረቱት ምርቶች በዶንያ ተጭነው ወደ ውጭ አገር የሚላኩ ናቸው፡፡ በሙስና በሚስጥራዊነቱና በአስተዳደራዊ ችግሮቹ የሚታወቀው የመሬት ሽያጭ ድሆች ገበሬዎችን ገለልተኛ የደረገ ነው፡፡ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቲግሬቲ የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም እ.ኤ.አ ከ2ዐዐ3-2ዐዐ9 ዓም ድረስ 11.7 ቢሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ ወጥቷል የሚለው አንዱ የሙስናን አስከፊነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ክቡራንና ክቡራት!
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንዱና ወሳኝነት ሚና ያለው የነፃ ሚዲያ መኖር ነው፡፡ ዴሞክራሲ በዳበረባቸው አገራት ውስጥ ነፃ ሚዲያ አራተኛው የመንገሥት አካል ተደርጎ ነው  የሚወሰደው፡፡ ልክ እንደ ሕግ አውጭው ሕግ አስፈፃሚውና እንደ ነፃ ፍርድ ቤቶች ሁሉ፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ አያለ በአሁኑ ጊዜ በነፃ  ጋዜጦችና ጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለው ሕገ -ወጥ እርምጃ አሳሳቢና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከሥራ ኃላፊነቱና ድርሻው ውጭ የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ባዘጋጀው አዲስ የውል ረቂቅ ላይ ቅድመ ምርመራ ወይም የሴንሰርሽፕን  ሕግ በጓሮ በር እያስገባ ይገኛል፡፡ በዚህም በኤ.ፍ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 የተፈቀደውን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽና የማሰራጨትን መብትን የሚያፍን ነው፡፡ በመሆኑም የውል ሰነዱን መፈረም በእራሱ ሕገ ወጥነት ነው፡፡

የውል ረቂቁ ሰነድ ጉዳይ ገና በአልተቋጨበት ሁኔታ ላይ ‹‹ ፍትሕ›› ጋዜጣ ከህትመት እንዲወጣ ዓይን ያወጣ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እርምጃ እየተወሰደበት ነው፡፡ የሐምሌ 13 ቀን 2ዐዐ44 ዓም የፍትሕ ጋዜጣ ሕትመት በፍትሕ ሚኒስቴርና በዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት አማካኝነት እንዳይሰራጭ ተደርጓል፡፡ ሐምሌ 2ዐ ቀን 2ዐዐ4 ዓም ለሕትመት የተዘጋጀውን የፍትሕ ጋዜጣ ብርሃንና ሠላም አላትምም ብሏል፡፡ የሐምሌ 27 ቀን 2ዐዐ4 ዓም ሕትመትም  እንደታገደ ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ ልሣን የሆነው ‹‹ፍኖተ ነፃነት›› ጋዜጣም ታላቅ ፈተና ላይ ነው፡፡ አንዴ ፕሌት የለም፡፡ ሌላ ጊዜ ማሽን ተበላሸ በሚል ሰበብ አስባብ ሕትመቱ እየተስተጓጎለ ነው፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ ምን ሊከተል እንደሚችል መገመቱ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ በአለፉት ጊዘያት በአዲስ ነገርና በአውራምባ ታይምስ  ጋዜጦችና ጋዜጠኞች ላይ የደረሱት ችግሮች የወደፊቱን አመለካቾች ናቸው፡፡ ወደ ጨለማው ዘመን እየተመለስን ነው፡፡ ሕዝብ የማወቅና ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብቱ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መሆኑ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ክቡራንና ክቡራት!
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የሕግ የበላይነት ያለመከበሩ ጉዳይ ነው፡፡ በአባሎቻችንና በደጋፊዎቻችን ላይ በየጊዜው የተለያዩ በደሎች ይፍፀማሉ፡፡ ድብደባ፣ ሕገ-ወጥ እስራት፣ የእርሻ መሬት መቀማት፣ አፍኖ መሰወር፣ ከቀበሌ ቤቶች ማስወጣት፣ የንግድ ፍቃድ እድሳትን መከልከል፣ ማዋከብ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ጥቃቶቹም የሚፈፀሙት በመንግሥት የፀጥታ ኃላፊዎች፣ በቀበሌ መሪዎችና ካድሬዎች ነው፡፡ ትግሉ እየመረረ እየከረረና መጥፎ መልክ እየያዘ መጥቷል፡፡ የዚህ አንዱና  መገለጫው መስከረም 3 ቀን 2ዐዐ3 ዓም  የፓርቲውን ም/ሊቀመንበረና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ አንዱዓለም አራጌንና የብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆኑትን አቶ ናትናኤል መካንን በሽብርተኝነት ከሶ በእስር ቤት በአሣሪዎቻቸውና በደረቅ ወንጀለኞች እንዲደበደቡና የከፋ ሰቆቃ እንዲደርስባቸው መደረጉ ነው፡፡

በአቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ  የእድሜ ልክ እስራትና በአቶ ናትናኤል መኮነን ላይ ደግሞ የ18 ዓመት እስራት  ተፈርዶባቸዋል፡፡ እስራቱና ወከባው በዚህ የሚቆም ሳይሆን በባሰ መልኩ  የሚቀጥል ለመሆኑ ፍንጮች አሉ፡፡ ለዚህ ፈተና በቂና ዝግጁ ሆኖ መገኘት ወሳኝነት አለው፡፡ አንድነትና መድረክ የምር የሕዝብ ፓርቲ ሆኖ ለመገኘት ወደ ሕዝብ የሚደርሱበትን ሕዝብን ሊያንቀሳቅስ የሚችሉበትን ስልቶችን አዘጋጅተው  ተግባራዊ ማድረግ የጠበቅባቸዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ  በሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ አፈና በድፍረት ማጋለጥ ይጠበቅብናል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን የፍርሀት ቆፈን በመቅረፍ ‹‹ለውጥ ይቻላል›› ‹‹ረሀብ በቃ›› ‹‹ ፍርሀት በቃ›› በአገራችን የሚገባንን ክብር ማግኘት አለብን ብሎ  ሕዝብ እንዲነሳና በሠላማዊ ትግል ነፃነቱን እንዲቀናጅ ማድረግ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ መልካም ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከነአንዱዓለም እስር በኋላ በርካታ ወጣቶች ከምንጊዜውም በላይ ፓርቲያችንን በመቀላቀል ላይ ሲሆኑ የነባር አባላት ተነሳሽነት በከፈተኛ ደረጃ  እየጨመረ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋችንን የሚያለመልመው በእስር ላይ የሚገኙ የትግል አጋሮቻችን በፍረዱ ሂደትና በመጨረሻው የውሳኔ እለት ያሳዩት የመንፈስ ጥንካሬ፣ ቁርጠኘነትና ድፍረት ነው፡፡

ክቡራንና ክቡራት!
በአሁኑ ጊዜ አገራችን ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነች፡፡ የወደፊቱ የአገራችን የፖለቲካ አቅጣጫ ግልጽ አይደለም፡፡ ግልጽ የሆነ ነገር ቢኖር አደጋ ከፊታችን የተደቀነ መሆኑ ነው፡፡  ይህም ወደ ጨለማ ዘመን መልሶን የተቃውሞ መገለጫ ብቸኛው መንገድ በኃይል መጠቀም  ነው ወደ ሚል ድምዳሜ እንዳያደርስ ከፉኛ ያሰጋናል፣ ያስፈራናልም፡፡ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ አሁን ያለው ሁኔታ እየከፋ ሄዶ አመጽ ቢቀሰቀስ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ትልቅ ጉዳት መሆኑን ነው፡፡ ለአገሪቱ ህልውናም አሳሳቢ አደጋ አለው፡፡ የአመጽ ፍጥጫ መወገድ አለበት ማስወገድም ይቻላል፡፡ የጥላቻና የመጠፋፋት ፖለቲካ መወገድ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅን መንፈስ in-good-faith በኢህአዴግ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል በሚሉ ባለድረሻ አካላት መካከል ድርድር፣ ውይይት በአስቸኳይ መጀመር አለበት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ  ጤንነትን በሚመለከትም ግልጽና  ደረጃውን የጠበቀ የሐኪም ሪፖርት በየወቅቱ መቅረብ መስጠት አለበት፡፡ ሕዝቡ ተገቢ መረጃ የሚሰጠው አጥቶ ለተለያዩ ውዥንብሮች መጋለጥ የለበትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ስለሆኑ ሌሎች መጠየቅ የለባቸውም የሚለው ቀልድም መቆም አለበት፡፡ ጉዳዩ በሚገባው የኃላፊነት ደረጃና መንፈስ መያዘ ተገቢ ነው እንላለን፡፡

ኢህአዴግ ችግሮች ሲፈጠሩና ቀውሶች ሲያጋጥሙ ወደ እራሱ ማየቱን ትቶ እንደሁልጊው ለችግሮቹ ተጠያቂዎችንና ተከሳሾችን መፈለግ መሄድ ወቅቱ ያለፈበት ዘዴ ከመሆኑም ባሻገር ለማንም ጠቃሚም አዋጭም አይደለም፡፡ መንግሥት ከሁሉ አስቀድሞ በግፍ የአሠራቸውን የሕሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታቸው እንጠይቃለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕዝብ ‹‹ሕምቢ ለነፃነቴ፣ እምቤ ለመብቴ፣ እምቢ ለሰብአዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶቼ›› ብሎ በአገዛዙ ላይ ቢነሳ አንድነት ፓርቲ የሕዝብን ተፈጥሮአዊ መብቶች ከማክበር ሌላ አማራጭ  የሌለው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ፡፡

ክቡራንና ክቡራት!
ሕዝብ ለነፃነቱ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ በገንዘቡ በእውቀቱና በጉልበቱ የሚችለውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁና ፍቃደኛ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ይገልፃል፡፡ ሆኖም አምባገነኑ የኢህአዴግ ሥርዓት በሕዝቡ መካከል በፈጠረው የፍርሀት ቆፈንና እየተከታተለ  ተቃዋሚዎችን የሚደግፉ ባለሀብቶችን፣ ነገዴዎችን፣ ሠራተኞች የሚያጠቃቸውና ድምጥማጣቸውን የሚያጠፉቸው በመሆኑ በሥጋት ተሸብበው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም፡፡ ‹‹ፍርሀት በቃ›› እንላለን ‹‹ ነፃነት በነፃ አይገኝም›› እንላለን፡፡ የመጀመሪያው ተግባር እራስን ከፍርሀት ማላቀቅ ነው፡፡ ለመብት ለነፃነት ለአገር ባለቤትነት መከፈል ያለበት መስዋእትነት ሁሉ መከፈል አለበት፡፡ ለበርካታ አስርተ ዓመታት በአምባገነኖች መዳፍ ስር ሲማቅቅ የኖረው የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጨቋኝ ሥርዓት ማስወገዳቸውንና በማስወገድ ላይ መሆናቸውን በምሳሌነት መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ቆርጦ ከተነሳ የእድሉና የሥልጣኑ ባለበት ከመሆን፣ ምንም የሚያግደው የሚያቆመው ነገር አይኖርም፡፡

ክቡራንና ክቡራት!
እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ በምናይበት ወቅት   ፀረ-አምባገነናዊ ትግሉን ለማጋጋልና አንድ እምርታ ለማሳየት የሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር አብሮ መስራትና መዋሀድ አንዱ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም አንድነት ፓርቲ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መስከረም 3ዐ ቀን 2ዐዐ2 ዓም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክን መስርቶ አብሮ ሲሰራ  መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ የ5ዐ ዓመታት የዘመናዊ የፖለቲካ ትግል ያስተማረን ተሞክሮ ቢኖር የፖለቲካ ድል መቀናጀት የሚቻለው በተናጠል በሚደረግ ትግል ሳይሆን በተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና በሕዝብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲጨመርበት ብቻ ነው፡፡ ለዚህ የትብብር ጥያቄ ከዚህ ቀደም በርካታ የህብረት ጥረቶች ቢደረጉም የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም፡፡ በ1997 ዓም ምርጫ ወቅት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው ቅንጅት ውስጥ የደረሰው መከፋፈልና በሕዝብ ስሜት ላይ ያደረሰው የቅስም መስበርና የተስፋ መቁረጥ መንፈስ በአሳዛኝ ምሳሌነቱ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ሆኖም በአለፉት አሳዛኝ ክስተቶች ተስፋ ያልቆረጡ የስድስት ፓርቲዎች   ቅንጅት የነበረው መድረክ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንቦቻቸውን እንደ ገና መርምረውና የሚሻሻሉትን አሻሽለው ድርጅታዊ ብቃታቸውን በማጎልበት ከ‹‹ቅንጅት›› ወደ ‹‹ግንባር›› ሐምሌ 2ዐዐ4 ዓም በተደረገው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ተሸጋግሯል፡፡ መድረክ በተመሠረተ አጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘና የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ከኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ ያለው ድርጅት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩልም አንድነት ፓርቲ በስትራቴጂክ ፕላኑና በአምስት ዓመት እቅዱ ላይ ፓርቲዎችን የማሰባሰብ ዓላማውን ለማሳካት ከፍተኛና ውጤታማ ይሆናል የተባለውን  እንቅስቃሴ በስፋት እየሄደበት ነው፡፡ ለዚህ ተግባር የተቋቋመው ኮሚቴም ከስምንት ፓርቲዎች ጋር ውይይት እያካሄደ  ነው፡፡ ይህ ጅማሮ ውጤታማ እንዲሆን የፓርቲው አባላት ደጋፊዎችና ሕዝቡም የእራሱን ድጋፍ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ እጠይቃለሁ፡፡

ክቡራንና ክቡራት!
ወደ ዛሬው ፕሮግራም ስንመጣ  ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፈጽሞ ለማጥፋት በሚያደርገው የአፈና እንቅስቃሴ በሕይወትና በሞት መካከል እንድንኖር እያደረገ ነው፡፡ በአጠቃላይ መድረክን በተለይም አንድነትን ‹‹በሽብርተኝነት›› ‹‹በፀረ-ሠላምነት›› ‹‹በሻዕቢያ ተላላኪነት›› ወዘተ እየወነጀለ እና አባላቱንና ነፃ ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት ከሶ እያስፈረዳባቸው ነው፡፡

በመሆኑም ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሕዝቡ ተደራጅተው እጅ ለእጅ ተያይዘው በሠላማዊ መንግድ ነፃነታቸውን መቀዳጀትና  የአገራቸው ባለቤት መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ፓርቲዎች በሰው ኃይል በገንዘብና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እራሳቸውን አብቅተው የሕዝቡን  የመከራ ጊዜ ማሳጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዚህ የእራት ግብዣ አንዱና ዋናው ዓላማ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ ጥንካሬ መሠረት በአጠቃላይ የአገሩ ሕዝብ ሲሆን በተለይ ደግሞ አባላትና ደጋፊዎቹ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ሥራ ደግሞ ከፍተኛ የገንዘብ  አቅም ይጠይቃል፡፡ የዚህ አቅም መሠረት በዘላቂነት ደግሞ አገር ቤትና ሕዝቡ መሆን አለበት፡፡ በመርህ ደረጃ ይህ ዱሮም የሚታመንበት ቢሆንም በተግባር ግን ብዙም ያልተሰራበት ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ፓርቲው ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ መልኩ የሚደገፈው በውጭ አገር ከሚገኙና ለአገራቸው እድገት፣ ልማናትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሌት ከቀን ተግተው ከሚሰሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያኖች ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚም ለእነዚህ ኢትዮጵያውኖች ያለኝን ከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት እንድ ገልጽ  እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ፡፡ በየጊዜው በአገር ውስጥ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለትግሉ መጎልበት በቂ ገንዘብ ካልተገኘ የሚከፈለው መስዋእትነት ከባድና አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዱሮው መንገድ ገንዘብ ከውጭ እየጠ በቁ መታገል ተገቢም የማይቻልም እየሆነ መምጣቱ ግንዛቤ ሊወስድበት ይገባል፡፡
ክቡራንና ክቡራት!
በመጨረሻም ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ግብዣ ፕሮግራምን በማዘጋጀትና ለውጤታማነቱ ከፍተኛ  አስተዋጽኦ ላደረጉ የፋይናንስ ኮሚቴ አባላት፣
-   የሥራ አስፈፃሚ አባላት
-   የብሔራዊ ም/ቤት አባላት
-   የቋሚ ኮሚቴዎች አባላት
-   የአዲስ አበባ ም/ቤትና ሥራ አስፈፃሚ አባላት
-   የአዲስ አበባ ወረዳ ኮሚቴዎች አባላት
-   በውጭ አገር የሚኖሩ የአንድነት የድጋፍ ሰጭ ኮሚቴዎች
-   ቲኬቱን በመግዛት ለተባበሩን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከፍተኛ አክብሮቴንና ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡


አመስግናለሁ
የሕዝብ ሀቀኛ ትግል ያሸንፋል!

No comments:

Post a Comment