Translate

Friday, July 20, 2012

አቶ መለስ ሃኪም ይረፉ አላቸው፤ ህዝቡ ግን “ይረፉ” ካለ ቆይቷል!

ትላንት አቶ በረከት ስሞን መግለጫ ሰጥተው ነበር። በመግለጫቸውም የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ህመመም በይፋ አምነዋል።
በነገራችን ላይ ጋዜጣዊ መግለጫው እየተሰጠ ድንገት ወደ አዳራሹ የመግባት እድል ቢያገኙ አቶ በረከት ስሞን መሀል ላይ ቁጭ ብለው በግራ እና በቀኝ ጋዜጠኞች ከበዋቸው፤ ከጀርባቸው የአቶ መለስ እና የአቶ ግርማ ፎቶ ተሰቅሎ ሲመለከቱ ሃዘን ቤት የመጡ ነው የሚመስልዎ! ከሁለቱም ፎቶ ስር የሆነች ብልጭልጭ ነገር ቢሰቀልማ ፎቶግራፋቸውን እያዩ እንባዎ እርግፍ እርግፍ ሊል ይችላል። የምር ግን ይሄ ፎቶ ሰቀላ ለማሟረት እንጂ የወዳጅነት አይመስልም! እኔ የምለው አቶ ግርማስ በቃ ረሳናቸው ማለት ነው!?

አሁንም በነገራችን ላይ አቶ ሽመልስ ከማል ባለፈው ጊዜ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ይሄ የኢሳት ወሬ ነው!” ብለው ነበር። ያን ግዜ ብዙ ሰው አልገባውም ነበር። ይሄ የኢሳት ወሬ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ የአቶ ሽመለስ አለቆች አቦይ ስብሐት እና አቶ በረከት ስሞንን መጠየቅ በቂ ነው። እነርሱ እንዳረጋገጡት ታድያ “የኢሳት ወሬ” ማለት ታማኝ ምንጭ ማለት ሆኖ እናገኘዋለን።
እኔ የምለው አቶ ሽመልስን ግን መንግስታችን እንዲህ መጫወቻ ያደረጋቸው በምን ጥፋታቸው ይሆን!? የሆነ ጊዜ “የአሜሪካን ድምፅን እኛ አለፈንም ኢህአዴግ እንዲህ አይነት አፈና ማድረግ ባህሪው አይደለም።” ብለው መግለጫ በሰጡ በስንተኛው ቀን ነብሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ “እሱን ዝም በሉት የአሜሪካን ድምፅን አፍነናል!” ሲሉ ተናገሩ። አሁን በቅርቡም “ስካይፕ ይከለከላል የተባለው ውሸት ነው።” አሉ አቶ በረከት ደግሞ ተነስተው “እሱ ምን ያውቃል ስካይፕንም ሆነ ሌሎች የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎችን እንቆጣጠራለን!” ሲሉ መግለጫቸውን ውድቅ አደረጉባቸው። ደግመው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልታመሙም!” አሉን ነገሩ ግን ወዲህ ሆነ… በጥቅሉ እርሳቸው የሚሰጡት መግለጫ ማላገጫ እንዲሆን ስለምን እንደተፈረደባቸው ግራ ያጋባል!
የሆነ ሆኖ መለስ አሁን ተይዘዋል። ከወዳጅነታችን የተነሳ “ተይዘዋል” አልን እንጂ እንደ አንዳንድ ወገኖች ብንሆን ኖሮ በቁጥጥር ስር ውለዋል” እንል ነበር። የህመማቸው መንስኤ ረጅም ጊዜ ያለ እረፍት መስራት መሆኑን ሀኪም ነገሯቸዋል። “ይረፉ” ሲልም አሳስቧቸዋል።
አሁንም ሌላ በነገራችን ላይ ህዝቡ መለስን “ይረፉ” ካላቸው ቆይቷል። በተለይ ደግሞ በምርጫ 97 “ብዙ ደከሙ ብዙ ለፉ! እስቲ ደግሞ ይረፉ” ብሎ ሊያሳርፋቸው ሞክሮ ነበር እርሳቸው ግን ምን ሲደረግ ብለው ይረፉ ያላቸውን ህዝብ ረፈረፉ።
ከዛ በኋላም አለም አቀፍ ተሸላሚው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ “ሌላ ምንም ምክንያት ሳያስፈልግ አቶ መለስ ያለ ምንም እረፍት ይሄንን ያህል ጊዜ መስራታቸው ብቻ ለኢህአዴግም ሆነ ለእርሳቸውም ሆነ ለህዝቡ በጎ ባለመሆኑ በቃዎ ሊባሉ ይገባል!” ብሎ ተናግሮ ነበር። ነገር ግን ይህንን ባለ በነጋታው የፖሊስ ኮሚሽነሩ ጠርተው “ምን ሲደረግ እንዲህ ትላለህ… በዚህ የምትቀጥል ከሆነ ወዮልህ…! እኛ አንተን ማሰር ሰልችቶናል እስከዛሬ የደሃ ልጅ ነበር የምንደፋው አሁን ግን የመጀመሪያው አንተ ነህ!” አሉት። ልብ አድርጉ መለስ “ይረፉ” ባለ ነው ይሄ ሁሉ ዛቻ!
እዚህ ላይ የአሽሟጣጮች ስጋት ትመጣለች
እነዚህ ሰዎች የቤልጄም ሃኪሞችን በሙሉ “እንዴት ይረፉ ይሏቸዋል!?” ብለው እንዳይዘምቱባቸው ያሰጋል። ብለው የሚጠረጥሩ ሽሙጠኞች አይጠፉም።
የምር ግን ወዳጄ ህዝቡ በዘጠና ሰባት በቀልድ አድርጎ የተናገራትን እኮ ነው ዛሬ የቤልጄም ሃኪሞች እየነገሯቸው ያሉት። ባለፈው ጊዜ እነ ውብሸት ታዬ በተከሰሱበት መዝገብ ራሱ ዋና የክስ ማስረጃ የነበረው “መለስ በቃ” ብላችኋል የሚል ነበር። ዛሬ እነ ውብሸት “መለስ በቃ ይረፉ” ማለታቸው ስለተረጋገጠ ሽብርተኛ ናቸው ተብለው ታስረዋል።
ይኸው ዛሬም ሐኪሞቹ እያሉ ያሉት ይህንኑ ነው። “መለስ ሆይ ደክሞታልና በቃዎ!” ብለዋቸዋል ልዩነቱ በእንግሊዘኛ መሆኑ ብቻ ነው። እንጂ የቤልጄም ሃኪሞች “21 ዓመት ያለማቋረጥ መምራትዎ ነው ለዚህ የዳረገዎት እና ይረፉ” ማለታቸውን ራሳቸው ጓደናቸው አቶ በረከት ነግረውናል።
ይሄን ጊዜ አቃቤ ህግ ሀኪሞቹን በሽብርተኝነት ለመክሰስ እየተሰናዳ ይሆናል! ብለን እናላግጥ ይሆን!?
በመጨረሻም
እመክራለሁ!
ያለ እረፍት መስራት አዎ ያሳምማል። መለስ ባለማረፋቸው በቃኝ ባለማለታቸው ይኸው አጓጉል ሆነዋል። በቀጣይም ራሱ ኢህአዴግ እረፍት እንዲያደርግ እመክራለሁ። አለበለዛ በእረፍት እጦት ሳቢያ የአልጋ ቁራኛ ቢሆን የማን ያለ ይባላል!? ጎበዝ የግድ ሐኪም እስኪነግረንማ አንጠብቅ እንጂ!
By Abe Tokchaw

No comments:

Post a Comment