Translate

Saturday, July 21, 2012

ኢትዮጵያ፤ ከሥዩመ-እግዚአብሔር ወደ ሥዩመ-ፓርቲ

ሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)
Ethiopian Kings logoየፖለቲካ ጭንቀቱና ጥበቱ ስለውክልና ጉዳይ ነው፡፡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባላቸው አስተሳሰብና አመለካከት መሰረት በፖለቲካው ሸንጎ/መድረክ መወከል አለባቸው፡፡ ብዙኃንም ሆኑ ጥቂቶች ውክልና ሊኖራቸው የተገባ፡፡ አለበለዚያ፣ “አልተወከልኩም” የሚል የህብረተሰብ ክፍል ወደ አመጽና ነውጠኝነት ያዘነብላል፡፡ ያ ደግሞ ለማንም፣ በምንም መልኩ ፋይዳ-ቢስ ነው፡፡ በተለይም ያልሰለጠነና በድህነት አረንረቋና ውስጥ የሚኖር ህዝብ ከሆነ የሚከተለው መዘዝ ቤተ-መንግስትን ብቻ ሳይሆን ሃገርንም ያወድማል፡፡ ሶማሊያ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ አልተወከልንም የሚሉ ጎሳዎ የጫሩት እሳት መላ ሃገሪቱንና አካባቢውን መለብለብ ከጀመረ እነሆ ሃያ አራት አመት ደፈነ፡፡

የወካዮቹ ንቃተ-ሕሊና እስከሚያድግ ድረስ ጊዜ ሊሰጥ ቢችልም፣ የባዕዳን አመለካከትና የግራ አዝማሚያ ዘልቆ ፖለቲካ ጥያቄው ሽብርና ነውጥን ያስከትላል፡፡ ዛሬ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የሚደረጉት የፀደይ አብዮቶች የውክልና ማጣትና የአገዛዞች ድቀት ውጤት ነው፡፡

ስለሆነም፣ “ማን ይግዛ?” ወይም “ማን ይምራ?” የሚለው ዘመን አይሽሬ ጥያቄ እናነሳው፡፡ ቅርፁንና መልኩን ቀየሮ “ስንት ይግዛ?” ወደሚል ጥያቄ ሊለወጥም ይችላል፡፡ ተያይዞም፣ በምን “አኳኋን ይግዛ ወይም ያስተዳድር?” ወደሚል ሙግት ይከታል፡፡ ጥያቄውን ወደ ጓዳችን አዙረን፤ “ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያን “ማን ይግዛቸው?” (የለም-የለም “ማን ይምራቸው?”) የሚለውን ጥያቄ በተቻለ መጠን ለውይይት ከሚበጁ ኃሳቦች ጋር ለማንሳት ጥረት ይደረጋል፡፡ ሕሊናችን በሥነ-ሥርዓትና በቀመራዊነት ጉዳዩን ለማቅረብ እንዲችል የአንብሮ፣ የተቃርኖና የአስተፃምሮ መንገዶችን ለመከተል እንሞክራለን፡፡
አንኳሩ ጥያቄያችን “ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያን “ማን ይግዛቸው?” (“ማን ይምራቸው?”) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ለኢትዮጵያ ምን አይነት አገዛዝ ነው የሚያዋጣት? (ኢትዮጵያን ማንEthiopia from King to party ይምራት?) የትኛው ሥርዓት ያስተዳድራት?” የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ወደዚህ ጥያቄ መልስ በቀጥታ ከመግባታችን በፊት ስለአገዛዝ/አመራር አይነቶች መጠነኛ ብያኔዎችን እንስጥ፡፡

“አንድ ይግዛ!” የሚሉና ገዢውም “ስዩመ-እግዚአብሔርነትን የተጎናፀፈ” መሆን አለበት የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ከሃይማኖት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ገዢው፣ እግዜር የቀባው፤ እግዜር የመረጠው መሆን አለበት፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግስትም ሥርወ-መንግስት (monarchy) ይባላል፡፡ “አንድ አህያ የሚነዳ ወይም እረኝነት የዋለ ሰው” አምላክ “መርጦና ቀብቶ” ነጋሢ ይሆናል፡፡ በተቀባበት ግዛት ሥር ያሉትን ሊቅ-ደቂቅ፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ፣ ሳርና ቅጠል ሳይቀሩ አምላኩ በፈቀደለት መሰረት እንዳሻው ያደርጋቸዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከፍርድ ቤት በላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ከጦር ጄኔራሎችና ከፊልድ ማርሻሎችም (ራሶችም) በላይ የጦሩ ራስ ነው፡፡ ከሊቃውንቱ በላይ ሊቅ ነው፡፡ ከካህናቱም በላይ ካህን፤ ከኢማሙም በላይ ኢማም፤ ከከያንያኑም በላይ ከያኒ ነው፡፡ ሥልጣኑ ከ- እስከ የለውም፡፡ የሥልጣን ዘመኑም ገደብ የለውም፡፡ የንጉሡ ቤተሰብ አባላት የሥልጣን ወራሾች ናቸው፡፡ “ሥርወ” ነው፤ የዘር ሃረግ እየመዘዘ የሚቀጥል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በዚህ ዓይነቱ መንግስታዊ አስተዳደር ከንግሥተ ሳባ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድረስ ሁለት መቶ ሃያ አምስት የነገስታት አገዛዝ ስር አልፈዋል፡፡ ቀላል ጊዜ አይደለም፡፡ ታሪክ ብቻም አይደለም፡፡ ባህል ነው፡፡ እምነትም ነው፡፡ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የዋዛ ጉዳይ አይደለም፡፡

ስዩመ-እግዚአብሔር ይግዛ የሚለው ኃይለ-ኃሳብ ተቃራኒ አለው፡፡ እግዜር የመረጠው አንድ ይግዛ የሚለው ሃሳብ የሚቃረነው ሃሳብ “ስዩመ-ሕዝብ” (Democracy) ይግዛ/ ይምራ ይላል፡፡ ከሕዝብ የወጣ፣ በሕዝብ የተመረጠ፤ ለህዝብ የሚያገለግል መሪ መሰየም አለበት ነው – አቋሙ፡፡ “ከሕዝብ-በሕዝብ-ለሕዝብ!” የሚሰየመው መሪ፣ የስልጣን ዘመኑ የተገደበ ነው፡፡ ከተወሰነ ዙር በላይ መምራት የለበትም፡፡ እንደአሜሪካኖቹ፣ ሁለት ዙር አራት-አራት አመት፣ ወይም እንደጀርመኖቹ ሁለት ዙር አምስት-አምስት አመት ከተመረጠ (የመተማመኛ ድምፅ ካገኘ) ብቻ የሚያገለግል መሆን አለበት፡፡ ሁለተኛ፤ ሥልጣን ርስተ-ጉልት አይደለምና ለቤተሰቡ አባላት ወይም ለወደዳቸው ሰዎችና ቡድኖች ማውረስ አይችልም፡፡ መራጩ ሕዝብ የሚሰይመውን መሪ “ከራሱ-በረሱ-ለራሱ!” መምረጥ አለበት፡፡

ይህ ስርዓት “አንድ ድምጽ ለአንድ ሰው” ባይ ነው፡፡ ድምጽ ሰጪ ሰዎች ሁሉ “እኩል” ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ከሥረ-መሠረቱ ሃሳቡ በሁለት ስህተቶች ላይ የተገነባ ነው፡፡ አንደኛ፤ ሰዎች በአዕምሮአቸውና በስነምግባራቸው (in their mental and moral capacities) እኩል አይደሉም፡፡ ስለዚህም, ወኪሎቻቸውን እኩል በሆነ አቅምና ማገናዘብ ሊወክሉ እንዴት ይችላሉ? ሁለተኛ፤ የምረጡኝ ቅስቀሳውና ሂደቱ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ገንዘብ በዲሞክራሲያዊ አካሄድ ውስጥ ይናገራል-ያናግራል፡፡ ገንዘብ የመራጮችን ልብ ለማማለል፣ አልፎ-አልፎም ድምጽ ለመሸመቻ ያገለግላል፡፡ (አታዩም ወያኔን በሠላሳ ብርና በካኔቴራ የወጣቶችና የሴቶች ፎረም እያለ ሲያንጫጫ!) ያለገንዘብ የብዙኃኑን ድምጽ ማግኘት ከንቱ ነው፡፡ ከንቱ! የከንቱ-ከንቱ ነው! ገንዘብ ያላሰባሰቡ፣ በብቃታቸውና በስነ-ምግባራቸው የበቁና-የነቁ ተወዳዳሪዎች እንኳን ቢሆኑ የማጣሪያ ዙሩን ሊያልፉ አይችሉም፡፡ ዲሞክራሲ ገንዘብ ነው!

የስዩመ-እግዚአብሔርንና የስዩመ-ህዝብን ግራና ቀኝ የሚያናጽሩት ሊቃውንት አሉ፡፡ የሁለቱንም ደካማና ጠንካራ ጎኖች ነቀሰው ሲያበቁ፣ “በእግዜርም ሆነ እኩል ባልሆነው ህዝብ የተመረጡት” አያዋጡም ብለው ይሟገታሉ፡፡ ስለሆነም፣ ”ችሎታ ያለው/ያላቸው ይግዛ!/ይግዙ!” ይላሉ፡፡ ይህን መሰሉም አመራር መኳንንታዊ (Aristocracy) ይባላል፡፡ ቀልቡ ያለው፣ “እውቀትን፣ ብቃትንና ስነምግባርን” የተካነ መሪ ካለ ይምራ በሚለው ላይ ነው፡፡ ዋነኛ ግቡም፣ ተቅዋማትን መፍጠር ነው፡፡ የባለሙያው ችሎታ፣ ክህሎትና እውቀት የሚተገብርበትን፣ ዜጎች በእኩልነት የሚገለገሉበት፣ የሚዳኙበት፣ በፖለቲካ እንደራሴዎቻቸው በኩልም ዜጎች የሚቆጣጠሩትን ተቋማት ለመገንባት ይጣጣራል፡፡ መኳንንቱ “ዕውቀት ኃይል ነው!” ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ አገዛዝ/ዘመራር እውቀት ገንዘብ ነው፤ እውቀት ኃይል ነው፤ እውቀት “ኲሉ-በኲልሄ” ነው፡፡

ምን ይበጃል?
ወደ ቀደመው ጥያቄያችን እንመለስ፡፡ “ኢትዮጵያን “ማን ይምራት?” የትኛውስ ሥርዓት ይሆን የተሻለ የሚያስተዳድራት? ንጉሣዊ አስተዳደር ወይስ ዲሞክራሲያዊ አመራር? ወይንስ የመኳንንታዊ አስተዳደር ቢኖራት ነው የሚበጀው? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ቀላል አይሆንም፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ከባድ ፈተና አለበት፡፡ ምክንያቱም፣ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነንና ነው፡፡

የህዝብ አስተዳደርና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎችም በጉዳዩ ላይ በጥልቅ እንዲያስበበት ያሻል፡፡ እንምከርበት፡፡ እንወያይበት፡፡ ምን ዓይነት አስተዳደር ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እንደሚበጅ እንመካከር፡፡ እኛ እናልፋለን፡፡ ተራ በተራ ወደማይቀረው አላለማዊ ጉዞ እንነጉዳለን፡፡ ለትውልድ የሚተላለፍና በመጪው ትውልድ የሚዘከር ስራ እንስራ፡፡ የኢትዮጵያውያን ችግር፣ ችጋር፣ ስደትና እንግልት ሁሉ ከአስተዳደር በደልና ከገዢዎቹ ግፈኝነት የሚመነጭ ነው፡፡ ድሃ አይደለንም፡፡ የከፋው ሁሉ “ጥራኝ ዱሩ፣ ጥራኝ ጫካው” ባለ ቁጥር ችግሩና ችጋሩ እየተራባ፣ ስደትና እንግልቱም እየተበራከተ ሄዷል፡፡ ለወደፊቱም ላለመበራከቱ ምንድነው ዋስትናው? ምንም!

ምንም እንኳ ዛሬ-ዛሬ የብዙኃኑን ሊሂቃንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አትኩሮትና ቀልብ የተቆጣጠረው የምዕራባውያኑ “ዲሞክራሲ” ቢሆንም ቅሉ፣ ሌሎች አማራጮችም እንዳሉን ልናስብበት ይገባል፡፡ ከራሳችን ነባራዊ ሁናቴ ጋር አስማምተንና አመዛዝነን ልንቀይሰው የምንችላቸው አማራጮች አሉን፡፡ የግድ ሰምና ጨርቅ፣ ቅቤና ድልህ፣ መርፌና ክር አናደርጋቸውም ይሆናል፡፡

በበኩሌ ሦሥት ሃሳቦች አሉኝ፡፡ ወግ አጥባቂና ወግ ጠባቂ የሆኑትን (ማለትም፤ በካሕናት፣ በኢማሞች፣ በባህላዊዎቹ አናውቅላችኋለን ባዮችና በከለቻ ተፅዕኖ ስር ያሉትን) የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክልና ተቀባይነት ያለው ሥዩመ-እግዚአብሔር አስተዳደር እንዲኖረው መብቱን እናክብርለት፡፡ መቼም፣ ንጉሠ ነገሥቱና ዘውዳዊ ምክር ቤቱ ባህላዊና ልማዳዊ የሆኑትን እሴቶቻችንን እንዲጠብቅልን ሰንደቅ ሆኖ ከመስራቱም በላይ፣ የማንነታችን አሻራዎች ተፍቀው ድራሻቸው እንዳይጠፉ የበጀናል፡፡ በህዝቡ ሰያሚነት በሚቋቋመው አስተዳደርና በመኳንንቱ ሙያዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዳይገባ በሕገ-መንግስታችን ውስጥ (In the Magna Karta) በቅጡ ደንግገነው ስናበቃ፣ ንጉሠ ነገሥቱን አምላካዊነት ልናስቀረው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ የታወቀ ሥርወ-መንግሥት ያላት ሀገር ናትና፣ “በሕግ አምላክ!” “በጃንሆይ!”….ለሚሉት ወገኖቻችን ወኪል እንስጣቸው፡፡ ንጉሡ “የአፄ ዮሐንስ ወይስ የአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ወይንስ የአፋሩ ሱልጣን ወይም የጂማው አባ ጂፋር” ዝርያ ይሁን በሚለው ዙሪያ መነጋገር ይቻላል፡፡ ቀላል ጉዳይ አይደለም – ግን ይቻላል፡፡ ፖለቲካ የውክልና ጣጣ ነውና ለህዝባችን ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

ሁለተኛው ሃሳቤ ደግሞ፣ ሥዩመ-ሕዝብ ስለሆነው ሥርዓት ፋይዳ ነው፡፡ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላትና ርዕሰ-ብሔሩ በቀጥታ በሕዝቡ ይሁንታና ዓመኔታ ይመረጡ፡፡ የፖለቲካ ውክልናና የፖለቲካ ሹመት ለሚያስፈልጋቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ልዩ ልዩ ሕዝባዊ ጽሕፈት ቤቶች በህዝብ ተመራጮች ይመሩ፡፡ ለተወሰነ ዙር ብቻ (ማለትም፣ ለሁለት ዙር – ለአምስት አምስት ዓመታት ያህል ብቻ) የአንድ ባለሥልጣን የሥራ ዘመን ይሁን፡፡ የአገልግሎት ዘመኑን ከጨረሰ በኋላ ወደሌሎች የሕዝባዊ ወይም የኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተዛውሮ አገሩንና ህዝቡን ያገልግል፡፡ ሚኒስቴር የነበረውን የክልል ፕሬዝደንት ወይም ከንቲባ፣ ኮሚሽነር የነበረውን የሆነ አገር አንባሳደር፣ ጄነራል የነበረውን ባለውለታ አፈ-ጉባኤ በማድረግ አናወናብድ፡፡ ሕዝብ ድርጅታዊ አፈናዎችንና አመቃዎችን ያውቃቸዋል፡፡ ከነችግሩ፣ ዲሞክራሲ ማለት ለዜጎች እኩል እድልንና ተስማሚ ሁናቴን መፍጠር ነው፡፡” ጉልቻዎቹን ማቀያየር አይደለም፡፡ “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም!” አይደል ከነተረቱስ?!

በሦስተኛው ረድፍ የምንጠቅሳቸው፣ ከሙያዊ ብቃታቸውና ክህሎታቸው ጋር የተያያዘ የፖለቲካ ውክልና ስለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ነው፡፡ ችሎታና ብቃቱ ያለው ዳኛ ይዳኝ፡፡ ይፍረድ፡፡ ጠበቃው ደንበኛውን ይጠብቅ፡፡ ሃኪሙም ህመምተኞችን ያክም፡፡ መምህሩ ያስተምር፡፡ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ዲኑም ይምራ፡፡ ይከውን – የቲያትርና የሙዚቃ ባለሙያው፡፡ ፖሊሱና መከላከያውም ሰላምንና ሉዓላዊነትን ይጠብቅ፡፡ መሃንዲሱ ይቀይስ፡፡ ሯጩም ይገሥግሥ፡፡ ጋዜጠኛው ይፃፍ-ይናገር፡፡ ነጋዴውም ይነግድ፡፡ ገበሬውም ያምርት፡፡ ባለገንዘቡም (ኢንቨስተሩም) ምዕዋለ ንዋዩን ያፍስ፡፡ ምንደነው እንዲህ ሙያተኛውን አጉል ወደፖለቲካ መጎተት? ለምንድነው ዜጎች ችሎታቸውን በነፃ መንፈስ እንዳያወጡ በገዢዎች የሚጎነተሉት? “ሙያተኞች ሆይ፣ ከኛ ጋር ካልሆናችሁ ዞር በሉልን እንዳናያችሁ መባሉ – ለምንድነው?

ቢያንስ-ቢያንስ፣ ሙያተኞች ነፃ የሙያ ማህበራት እንዳይኖራቸውና እንዳይደራጁ የሚደረገው ስለ አሪስቶክራቶች ፋይዳ በወጉ ስላልገባን ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ሲደራጅና በአግባቡም ሲወከል የለውጥና የመረጋጋት ተስፋ የረሆናል፡፡ ተቋማት የሚፋፉትም ሆነ የሚያድጉት የአሪስቶክራቶቹ ጤናማ የሆነ ውክልና ሲኖራቸው ነው፡፡ ሙያተኛ መኳንንቶች በፖለቲካ ታማኞች ሲተኩ ሁለት ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ “አላዋቂ ሳሚዎች ብዙኃኑን ንፍጥ ይለቀልቁታል!” በበርካታ መንግስታዊ ድርጅቶች ውስጥ የሙስናውና የንቅዘቱ ምንጭ ይሄው ያላዋቂዎቹ “ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ምን ይበጀው” የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ አላዋቂነትና ሙስና እንደጉንጉን ነው፡፡ አንዱ ባንዱ ላይ የተገመደ! ሁለተኛው ችግር፣ ተቋማቱ ቀስ-በቀስ ወደ መሞት ይገሰግሳሉ፡፡ በሙስናውና በንቅዘቱ ሰበብ፣ ተቋማቱ ተዓማኒነት ያጣሉ፡፡ በጎንም የሕገ-ወጦቹ የጥቅም ሰንሰለት ተቋማቱን ወደ ፍፃሜ ይገፈትራቸዋል፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ፣ መንግስትም ሆነ ተቋማቱ “የብቁ ባለሙያ የለህ!” ይላሉ፡፡ ዛሬ ያአሜሪካንም ሆነ የአውሮፓውያን ድቀት በአብዛኛው ምክንያቱ የአሪስቶክራቶች መጥፋትና የጨዋ ልጆች በመደዴዎች መተካታቸው ነው፡፡

ለማጠቃለል እፈልጋለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ሦስቱም የአመራር አማራጮችና የፖለቲካ ውክልናዎች ያስፈልጓታል፡፡ ዘውዳዊው አስተዳደር ወግ-አጥባቂዎቹን የሚወክል ሲሆን፣ ሕዝበ-መንግሥትም የብዙኃኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ማህበሮች ፍላጎት መወከል ይችላል፡፡ ሙያተኞችና የጨዋ ልጆችም ችሎታቸውና እውቀታቸው በሚፈቅድላቸው መሰረት የፖለቲካ ሹመት በማይፈልጉ የሙያ ተቋማት ውስጥ በነፃነት ይስሩ፡፡ በሙያ ማህበሮቻቸውም አማካኝነት በወጉ ይወከሉ፡፡ ሙያተኛ የሚፈልገው ድርጅትና ተቋም እንዴት ተደርጎ በፖለቲካ ደላሎችና የሥርዓቱ ታማኝ አጎብዳጆች ሊያዝ ይችላል? ውጤቱ ዜሮ ነው የሚሆነው፡፡ (ይሄንን ያህል ሃሳቦቻችሁን ለመጎንተል ያህል ብያለሁ፡፡ ያለውን የወረወረ “ንፉግ” አይባልምና የበኩላችሁን አተያይ ጻፉልን፡፡)

No comments:

Post a Comment