Translate

Tuesday, July 17, 2012

ያንዱ ጥቃት ለሌላው ውጋት ሊሆን ይገባል!

በሀገራችን ላለፉት 21 ዓመታት የተንሰራፋው የህወሓት /ኢህአዴግ አገዛዝ የሕዝቡን አጠቃላይ ኑሮ ወደ አዘቅት የከተተው አልበቃ ብሎ አሁንም በከፋፍለህ ግዛው ስልት የጭቆና Ethiopian People's Congress for United Struggle (Congress)አገዛዙን አጠናክሮ ለመቀጠል እየተፍጨረጨረ ነው።
ህወሓት/ኢህአዴግ በትረ መንግስቱን እንደጨበጠ የሃገሪቱን መከላከያ ሃይልና የደህንነት ዘርፍ እንዳለ በማፍረስና በብቸኛነት የሚቆጣጠረውን ጦር ቦታውን እንዲይዝ በማድረግ ያለተከላካይ የቀረውን ሕዝብ ሲያሸብር ቆይቷል፤ አሁንም ያሸብራል፣ ያስራል፣ ያፈናቅላል፡ ንብረቱን ይወርሳል ሲሻውም ይገድላል። ይህንኑ ሲፈጽም እጅግ በጣም በተሰላና በተጠና የመከፋፈል ዘዴ በመጠቀም አንዱን በአንዱ ላይ በማስመታት ነው።

በዚህ ሂደት ለአመታት የዘለቀው የዚህ አምባገነን አገዛዝ የአሁኑ ተረኛ ተጠቂዎች ደግሞ የሀገሪቱ ሙስሊም ዜጎች ሆነዋል። ለአለፉት በርካታ ወራት በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ሲቀርቡ የነበሩ የመብት ጥያቄዎችን በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ ባለፈው ሳምንት የተለያዩ የአምልኮ ቦታቸውን በመድፈር አገዛዙ ጥቃት አድርሷል። በአዲስ አበባ የአወልያ መስጂድ ለሰደቃ ዝግጅት በተሰበሰቡ ምእመናን ላይ የግቢ በር ሰብሮ በመግባት የፈጠረው ሸብር የአገዛዙን ማናአለብኝነት የሚያመለክት መሆኑ ግልጽ ነው ። የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖች የጠየቁት መሰረታዊ የእምነት ነጻነታቸው እንዲከበርና የሀይማኖቱን መሪዎች ያለምንም የመንግስት ጣልቃ ገብነት፣ በራሳቸው መምረጥ እንዲችሉ ሆኖ እያለ አገዛዙ ፖሊሱንና ነጭ ለባሾችን አዝምቶ መብታቸውን በሰላም የጠየቁትን ዜጎች በሀገር ላይ ደባ እንደፈጸሙ በማስመሰል ጭካኔ የተሞላበት ጉዳት አድርሷል። ምግብ በማብሰል የተሰማሩትን በሌሊት ከቦ አስለቃሽ ጋዝ በመርጨት ምእመናኑን ደብድቧል፣ አሰቃይቷል፣ አቁስሏል፣ ገድሏል፣ አስሯል።
አገዛዙ የሕዝብን ድምጽ ለማፈንና መሰረታዊ የስብዓዊ መብትን ለመግፈፍ የሚያደርጋቸውን ይህንን እና መስል የሽብር እርምጃዎቹን የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አጥብቆ ያወግዛል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የታሰሩትንም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሕዝቡ የተባበረ ትግል እንዲያደርግ ይጠይቃል።
ሸንጎው ለመሰረታዊ የስብዓዊ መብቱ መከበር ትግል ከሚያደርገው ከህዝበ ሙስሊሙ ጎን መቆሙንም ያረጋግጣል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋር ትግል ሸንጎ በአሁኑ ወቅት ለሰላማዊ ለውጥ፡ ለፍትህና ለዴሞክራሲ እውን መሆን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ባሰሙና ብእራቸውን ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለአንድነትና ለዴሞክራሲ እውን መሆን ባነሱ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች መታሰርን እና የተጣለባቸውን ህገወጥ ብይን በጥብቅ ይቃወማል። በአስቸካይ ያለምንን ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱም ይታገላል።
ከዚህም በተጨማሪ በልማትና በተለያየ ፖለቲካዊ ስበቦች ዜጎችን ከሚኖሩበት ቦታ የማፈናቀሉ ተግባር በአስቸካይ እንዲቆም፣ የአምልኮ ቦታዎች የሆኑት የገዳማትና አድባራት ብሎም መስጂዶች ይዞታ እንዲከበር አጥብቆ ይታገላል።
በአንድ በኩል፣ በአስከፊው ጭቆና እየተንገፈገፈ ያለው ሕዝባችን አልገዛም ባይነቱን እያጠናከረ መምጣቱ፣ በሌላ በኩል የስርዓቱ ቁንጮ የመለስ ዜናዊ መታመምና ይህም ሁኔታ በአምባገነኑ ቡድን መካከል የፈጠረው የስልጣን ሽኩቻና የውስጥ መናጋት መጀመር፣ የአገዛዙን ወደ ከርሰ መቃብሩ የመውረዱን ሁኔታ እያፋጠነው መሆኑ የማይታበል ነው። ይህ ሁኔታ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ፣ ሕዝቡን የማረጋጋታና አቅጣጫ የማስያዝን ሀላፊነት የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አጥብቆ የሚጠይቀው ነው። ትግሉ በተናጠል ሳይሆን የተቃዋሚው ጎራ ህብረትን፣ ትግስትንና መመካከርን ብሎም በአንድነት ህዝብን ማስተባበርን የሚጠይቅበት ወሳኝ የታሪክ ምእራፍ ላይ ደርሷል። በመሆኑም ሸንጎው ሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ትግላቸውን አስተባብረው በአንድ ላይ በመቆም የሕዝቡን ትግል ያስተባብሩ ዘንድ ጥሪ ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ፣ ህዝቡ በሃይማኖት፣ በብሄረሰብ፣ በጾታ…ወዘተ ሳይከፋፈል በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በአንድ ላይ በመነሳት አስከፊውን አገዛዝ ገርስሶ በምትኩ የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ ዜጎች መሠረታዊ የስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው በተግባር የሚውልበት፣ የሕዝብ ልዑአላዊነት እውን የሚሆንበት ስርዓትን ለመመስረት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደትን ለመጀመር በአንድነት እንዲቆም ጥሪ ያደርጋል።
የመከላከያ ሠረዊቱና የጸጥታ ኃይሉ ከኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ጎን እንዲቆም፣ በዜጎች ላይ የጥቃት እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብና የሀገሪቱን ዳር ድንበር በማስከበር ላይ እንዲያተኩር ሸንጎው ጥሪ ያደርጋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንዱ ጥቃት የሌላው ውጋት ሆኖ ሊሰማው ይገባል እንላለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
July 16, 2012
http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/3521

No comments:

Post a Comment