Translate

Friday, July 20, 2012

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ቃል አቀባዩና እኛ

ከፋሲል አያሌው
በቅርቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጤናቸው መታወኩንና በስራ ገበታቸውም ሆነ በኔፓድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መገኘት አለመቻላቸው እየተዘገበ ይገኛል:: በሌላ ዜና ደግሞ ሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ. ም. ሲታከሙበት ከቆዩበት ቤልጅየም ይሁን ጀርመን በውል ባይታወቅም ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን የሚገልጽ ዜና ሰምተናል:: የኢትዮጵያ መንግስት ውሉ ባልታወቀ ምክንያት ጠቅላይ ሚንስትሩ መታመማቸውንና በሃገር ውስጥ እንዳልነበሩ መግለጽ ያልፈለገ ቢሆንም ኢሳትና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ጠ/ሚንስትሩ መታመማቸውን ሲዘግቡ ቆይተው በኔፓድ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ጠ/ሚንስትሩ መታመማቸውንና በጤና እንዲመለሱም መልካም ምኞታቸውን ገልጸው የሰውየውን መታመም እርግጥ አድርገውታል::


ከዚህ ሁሉ ግን የሚገርመው የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ጠ/ሚንስትሩ አለመታመማቸውንና እንደውም ይሄ የኢሳት የፈጠራ ወሬ ነው ብለው በተናገሩበት ሰሞን ምክትል ጠ/ሚንስርትና የውጭ ጉዳይ ምንስትሩ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጠ/ሚንስትሩ መታመማቸውንና በህክምና ላይ መሆናቸውን መግለጻቸው ኢትዮጵያ በምን አይነት ሃላፊዎችና ካድሬዎች እንደምትመራ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው::

ጠ/ሚንስትሩ እንደማንኛውም ሰው ሊታመሙ፣ታመውም ህክምና ሊወስዱ፣ ህክምና ወስደውም ሊድኑ ወይንም ህክምናው ካልተሳካ ሊሞቱ ይችላሉ ይሄ የተፈጥሮ ሂደት ነው:: ለሳቸው ጠ/ሚንስትር ስለሆኑ ተፈጥሮ አዳልታ የጨመረችው ነገር የለም ለሌላውም የቀነሰችው ነገር የለም ምናልባት ጠ/ሚኒስትር ስለሆኑና ሁሉ ነገር በእጃቸው ስላለ ሌላው ተራው ሰው በቀላሉ ሊያገኘው የማይችለው በየትኛውም የአለም ክፍል ተዟዙረው የፈለጉበት ቦታ የመታከም አቅሙም ስልጣኑም ይኖራቸው ይሆናል ሆኖም ግን ፈጣሪ ካለላቸው እድሜ ከፍ እንደማይሉ ራሳቸውም ያውቁታል::

ይህ እርግጥ ሆኖ ሳለ የመንግስት ቃል አቀባይን የሚያክል ትልቅ የመንግስት ስልጣን የያዘ ግለሰብ ጠ/ሚንስትሩን መታመም ለመደበቅና ለማድበስበስ መሞከር ምን ያህል አሳዛኝና ትዝብት ላይ የሚጥል ነገር ነው:: (እርግጥ እኛ የመንግስትን ስራ እያየን መታዘብ ብርቃችን ባይሆንም) እንደመንግስት ቃል አቀባይነታቸው ሲሆን ሲሆን ትክክለኛውን መረጃ ማድረስ ምናልባትም መረጃው ካልደረሳቸው አይ ለጊዜው ስለዚህ ነገር የማውቀው ነገር የለኝም የሚል ገላጻ ሲጠበቅባቸው ከመዋሸትና ከማድበስበስ አልፈው ዜናውን የዘገበውን ሚዲያ ለመውቀስ መቸኮላቸው እኝህ ሰው በትክክል የተቀመጡበትን ወይንም የተመደቡበትን የስልጣን ወንበር በትክክል ያውቁታልን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል:: ከዚህም ጎን ለጎን ሰውየው እንደ ጠላት ከፈረጇቸው ሚዲያዎች ጋር እልህና እንካሰላምቲያ ነው የያዙት ወይስ የመንግስትን ቃል በተገቢው ሁኔታ እያቀበሉ ነው? የሚለውም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው:: በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመራው ጠ/ሚንስትርን የጤንነት ሁኔታ የማውቅ መብት እንዳለው ማግኘት ያለበትም መረጃ (Information) ትክክለኛና የተረጋገጠ መሆን እንዳለበት እኝሁ ቃል አቀባይ የጠፋቸው ይመስለኛል::

በርግጥ ግለሰቡ አለቆቻቸው ከሚሰጧቸው መመሪያንና ትዕዛዝ ውጭ መሆን እንደማይችሉ ይታወቃል በመሆኑም ይሄ የመደበቅ፣ የመዋሸትና የማድበስበስ ልማድ ከራሱ ከመንግስት የመጣና የቆየ ተግባሩ ስለሆነ ብዙም ላይደንቅ ይችላል::

ይህ በዚህ እንዳለ የጠ/ሚንስትሩን መታመመ ተከትሎ የተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ አስተያየት እየሰጡ ሲሆን ምናልባትም ጠ/ሚንስትሩ ከዚህ በኋላ ወደ ስልጣን ተመልሰው ሊሰሩ አይችሉም ከሚል እምነት በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ አብዮት ሊከሰት ይችላል የሚል አስተያየት በብዛት እየተደመጠ ነው::

እርግጥ ጠ/ሚንስትሩ በፓርቲያቸው ኢህአዲግና ህወሃት ውስጥ እጅግ ቁልፍ ሰው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በህመምም ይሁን በሌላ ምክንያት ከፓርቲያቸው ቢገለሉ ፓርቲው ውስጥ ሊፈጥረው የሚችለው መደናገጥ ከፍ ሲልም ወደ መተራመስ ሊሄድ እንደሚችል ቢገመት ግምቱ ከግነት ይልቅ ወደ እውነትነት ማጋደሉን ከሚከተሉት ምክንያቶች መረዳት ይቻላል::

ምክንያት ፩- ኢህአዲግ(ህወሃት) ትግል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ድርጅቱን በመምራት ረጅሙን እድሜ ያስቆጠሩት ጠ/ሚንስትር መለስ ሲሆኑ ይህ የሚያሳየው የድርጅቱ አባላት በእሳቸው ላይ ምን ያህል እምነት እንዳለውና ከሳቸው ሌላ ለሌላ አባል ስልጣኑን ለመስጠት እምብዛም ያለመፍቀዱ::

ምክንያት ፪ – በድርጅቱ ውስጥ በአባላቱ ዘንድ ባላቸው ተጽእኖ ፈጣሪነትና ተሰሚነት በጠ/ሚንስትሩና በሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መካከል ከፍተኛ ልዩነት መኖር ማለትም እንደ እርሳቸው ከፍተኛ ተቀባይነትና ተሰሚነት ያለው አመራር በድርጅቱ ውስጥ አለመኖር (ይህም በሌሎች አመራሮች መካከል ወደአላስፈላጊ ፉክክር ሊያስገባ የሚችል ነገር ሊፈጥር ይችላል)::

ምክንያት ፫- ምንም እንኳን ድርጅቱ ጠ/ሚንስትሩ በህመምም ሆነ በሌላ ምክንያት ከድርጅቱ ቢገለሉ ሌላ ተተኪ አመራር መርጦ የሚቀጥል ቢሆንም በድርጅቱም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ድርጅቱ ለሚያጋጥመው ችግሮችና ተግዳሮቶች ከመለስ ውጭ በድርጅቱ መሪነት ደረጃ ተቀምጦ ችግሮችን የተጋፈጠ እንዲሁም ከዚህ በፊት ድርጅቱ እንዳጋጠመው አይነት የመከፋፈል አደጋ ቢገጠመው ይህንንም ሊወጣ የሚችል ልምድ ያለው መሪ ከመካከላቸው ይኖራል ተብሎ ስለማይገመትና በሌሎችም ምክንያቶች በድርጅቱ ውስጥ መደናገጥና ባስ ካለም ወደ መተራመስ ሊሄድ እንደሚችል መገመት ይቻላል::

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ደረጃ ግን ጠ/ሚኒስትሩ በተለያዩ ምክንያቶች ከስራቸው ቢገለሉ ባለው የተቃዋሚ ቡድን አሰላለፍና አሁን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለተቃዋሚዎች ባለው የተለያየ ስሜት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የፖለቲካ አብዮት ውስብስብ ይመስላል:: በርግጥ ያለ ጊዜያቸው ወይንም ድንገት ጠ/ሚንስትሩ ስልጣን ቢለቁ በሃገሪቱ አዲስ ስሜት መፍጠሩ የማይቀር ቢሆንም ሀገሪቷ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ያመጣል ብሎ ለመገመት የሚያስደፍር ጊዜ ላይ ያለን አይመስለኝም::
ጠ/ሚንስትሩ በተለያየ ምክንያት ስልጣናቸውን ቢለቁ ፓርቲው ባዘጋጀው ህገ መንግስት መሰረት ተተኪ መድቦ ስራውን የሚያስቀጥል ቢሆንም የተተካው መሪ ለምን ያህል ጊዜ ሃገሪቷን ማስተዳደር ይችላል የሚለው አብይ ጥያቄ ይመስለኛል:: ይህን ጥያቄ እንዳነሳው ያስገደደኝ እንደ አቶ መለስ አይነት ለረጅም ጊዜ በአመራር ላይ የቆየ አምባገነን መሪ ድንገት ስልጣን ሲለቅ በሃገሪቷ ላይ አንዳች የለውጥ ስሜት ሊቀሰቅስ የሚችል ቢሆንም አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ (ማለትም በዘርና በጎሳ የመከፋፈሉና የመለያየቱ ጠባሳ ህዝቡ ለተቃዋሚዎች ባለው የተለያየ ስሜት ወዘተ) ህዝቡ ምን አይነት እንቅስቃሴ(Reaction) ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ያስቸግራል::

በንጉሱ ዘመን ተማሪው ስያደርግ የነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተማሪውም ሆነ በሲቪል ማህበረሰቡ ዘንድ የተደራጀና የሃገሪቱን ስልጣን ተረክቦ ሀገሪቱን ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ሊመራ የሚችል ጠንካራ ሃይል አለመኖሩ ስልጣን በቀላሉ በጊዜው በነበረውና በተደራጀው ወታደራዊ ሃይል(military) እጅ ልትገባ ችላለች:: ከዚያም በኋላ ህወሃት ኢሃዲግ ራሱን አደራጅቶ ወደ ጫካ ትግል በመግባት ለአስራ ሰባት አመታት ከታገለ በኋላ የሃገሪቱን ስልጣን ተቆጣጥሮ እስካሁን እያስተዳደረ ይገኛል:: ይህ የሚያሳየን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ስልጣን ወደ ተደራጀና ለአንድ አላማ ወደ ተሰለፈ ቡድን ወይም ፓርቲ መሸጋገሯን ነው::

ከዚህ በተጨመሪ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አብዛኛውን ህዝብ ያሳተፈ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተካሄደው በ1997 ዓ. ም. ምርጫ ሲሆ ን የአራት ፓርቲዎች ውሁድ የነበረው ቅንጅት ካለው ህብረ ብሄራዊነት በተጨማሪ ገዚው ስርአት በፈቀደለት ትንሽ የሚዲያ አየር ሰአት ተጠቅሞ ራሱን ለህዝቡ በተገቢው ሁኔታ ማስተዋወቅ መቻሉና ህዝቡም ከገዚው ስርአት ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ በማግኘቱና በሌሎችም ምክንያቶች በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጎት ነበር::ታዲያ ምን ያደርጋል ሲያልቅ አያምር እንዲሉ የነበረበትን ጫና ተቋቁሞ መቀጠል ሲገባው በውስጡ በተነሳ አለመግባባት ሊፈርስ ችሏል::

እንግዲህ ከላይ በጥቂቱም ቢሆን ለመግለጽ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንደሚያሳየን ስልጣንን ወደ ህዝብ ለማውረድ አንድ የተደራጀና በህዝብ ዘንድ የታመነበት ህዝባዊ ተቋም በሌለበት የጠ/ሚንስትሩ መታመምም ሆነ ከስልጣን መልቀቅ ያን ያህል የጎላ ለውጥ ያመጣል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ ሲሆን ምናልባትም እንኳን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ቢደረግ ስልጣን ወዴት እንደሚሄድና በማን እጅ እንደሚውድቅ መገመት እንኳን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው::
ከዚህ አንጻር ዶ/ር ፍስሃ እሸቱና አጋሮቻቸው የጀመሩት የኢትዮጵያ የሽግግር ም/ቤት ጉባኤ ከፊቱ እጅግ ከፍተኛ ስራ የሚጠብቀው ቢሆንም የትሻለ ሃሳብ ነው ብዬ አምናለሁ::
ቸሩ አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቅ!!!!!!!!!
መልካም ጊዜ!
Fasil_ayal@yahoo.com

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/3566

No comments:

Post a Comment