Translate

Friday, January 16, 2015

ባለጌና ውሻ በቤቱ ይኮራል

የመጻፍ ፍላጎት በጭራሽ አልነበረኝም፡፡ ይሁን’ይ ዛሬ እንደወትሮው አላስችልህ አለኝ፡፡ መጻፍ የማልፈልገው መጻፍን በመጥላት ሣይሆን የሀገራችን ችግር ከመጻፍም፣ ከማንበብም፣ ከመመልከትና እጅን አጣምሮ በመቀመጥ በቁጪት ከመብከንከንም በእጅጉ ያለፈ በመሆኑ ነው፡፡ አዎ፣ ጊዜው የወሬና የሀተታ ሣይሆን የተግባር መሆን ይገባዋል – ልብ ላለው(2)፡፡ ብዙዎች – እኔንም ጨምሮ – ላለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት በከንቱ ኃይላችንን መጨረሳችንን ሳስበው ይገርመኛል፡፡ እነሱ ላይሰሙ ጆሯቸውን እንደዘጉና ዐይናቸውን እንደጨፈኑ፣ እኛም መለያየታችንና ሥልትአልባነታችን ላያርመን በግትርነት እንደተጓዝን ግማሽ ምዕተ ዓመት ሊጠባ የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ብቻ ናቸው – ሚሌኒየማዊ ከፍተኛው ዕድለቢስነት፡፡
wendimagegn Gashu
ዛሬ ያለመናገር የራስ በራስ ማዕቀቤን ያስነሣኝ በወንድማገኝ ጋሹ ቤተሰብ ላይ በወያኔ የተወሰደው “ለስላሳ” እርምጃ ነው፡፡ የሕጻናቱ አምላክ ጠብቋቸው እንጂ ወያኔን ምንም ነገር ከማድረግ የሚያግደው አንዳች ምድራዊ ሕግ የለም፡፡ ይህ የታወቀ እውነት ይመስለኛል፡፡ ወያኔ የበቀል አባት፣ የክፋት አቅማዳ፣ የመድሎና ዘረኝነት አጋፋሪ፣ የጭካኔ ምንጭና የውሸት ንጉሠ ነገሥት ነው፡፡
ሰሞኑን እንኳን ስንትና ስንት ወያኔያዊ ሀገርና ሕዝብ የማጥፋት “ጀብድ” እየፈጸመ አይደለምን? ደናቁርቱና ነገን ፈጽሞ የማያዉቁት የወያኔ ጭፍራዎች በፍርደኛ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ ሣይቀር ግድያና የእሥረኞች ጠለፋ ያካሄዱት በዚህ ሰሞን ነው፤ ከትግሬነት በዘለለ ራሳቸውን ትንሽ ከፍ አድርገው ማየት የተሣናቸው ፍጹማዊ ደንቆሮና ዕውር ወያኔዎች ላልተወሰነ ጊዜ ጋብ አድርገውት የነበረውን የኢትዮጵያን ቅርሦች ማቃጠላቸውን የቀሰቀሱት በዚህ ሰሞን ነው፤ … ስለሆነም የወንድማገኝ ቤተሰቦች በፈረንጅኛው አጠራር ፓስፖርታቸው ላይ “ዲፖርት” ተብሎ ተመትቶባቸው ከሀገራቸው መባረራቸው እንደጽድቅ የሚቆጠር እንጂ ወያኔ ሊኮነንበት አይገባም ብል ብዙም አላገነንኩም፡፡ እናቱ ወንዝ የወረደችበትና የሞተችበት እኩል ያለቅሳሉ እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር “ኢትዮጵያዊ ነኝ” እና “በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ” የሚልን ንጹሕ ዜጋ እያነፈነፉ ዘብጥያ በሚያወርዱበትና ደብዛውን በሚያጠፉበት የመጨረሻ የወያኔ ቀቢፀ ተስፋ ዘመን ላይ “ኢሳት ውስጥ ስለሚሠራ ባለቤቱንና ሦስት ልጆቹን አንገላትተው ከሀገር አስወጡበት” ብሎ ዜና መዘገቡ፣ በመዘገብ ደረጃ ጥፋት ባይኖርበትም እንደሀገራዊ እውነታ ግን ቅንጦት ይመስለኛል፡፡ እኛ እንዴት ያለ የእንስሳ ኑሮ እንደምንኖር የማያውቅ መሆን አለበት ይህን ‹ገራገር› የወያኔ ድርጊት ሊኮንን የሚቃጣ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ- ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ያለች የመሰለው የዋህ ዘጋቢና ፖለቲከኛ፡፡
በመሠረቱ በርዕሴ እንደጠቀስኩት ወያኔ ኢትዮጵያን በጉልበቱ ይዞ ለተወሰነ ጊዜ ቤቱ ማድረጉ እስካልቀረ ድረስ ባለጌ ነውና በቤቱ መኩራቱን በተደጋጋሚ እያሳየን እንደሆነ በበኩሌ ተረድቻለሁ፡፡ እንደውነቱና እንደኢትዮጵያዊ የቀድሞው ጨዋ ባህል አንድ ሰው በቤቱ እንግዳ ሲመጣ በክብር ተቀብሎ በደስታ አስተናግዶ ይሸኛል እንጂ አያዋርድም፡፡ እንግዳው ቢያጠፋ እንኳን እንደምንም ታግሦ ወደመጣበት እንዲሄድ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ እንግዳ አይሰደብም፤ አይዋረድም፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ ምንም እንግልትም አይደርስበትም – ትልቅ ነውር ነው፡፡ የወያኔ ጉጅሌ ግን ከሞራልም ከምግባርም ከሰብዓዊነትም ከሃይማኖትም ከኢትዮጵያዊ ዜግነትም … ምን አታከታችሁ ከሁሉም የበደለው በመሆኑና ከመነሻው ኢትዮጵያን የማጥፋት ብቸኛ ዓላማና ግብ ሰንቆ የተነሣ በመሆኑ እንዲህ ያለ አስነዋሪ ድርጊት ቤታቸውን በቀማቸው ንጹሓን ኢትዮጵያውያን ላይ በተገላቢጦሽ ሲያደርግ እናያለን፤ በዚህም የተለዬ ድርጊት መዳፋችንን አገጫችን ላይ ጣል አድርገን በ”እስከማዕዜኑ ትረስዓኒ ሊተ” የዳዊት መዝሙር እንተክዛለን፡፡ ለትካዜ ጥፎን፡፡
wondimagegn
ሰሞኑን የምንሰማውን ወያኔያዊ መስተንግዶ ጠለቅ ብለን ስንመለከተው ከግርምት ያለፈ ነው፡፡ ለቀልዳዊ ማዋዛት ስል ከፍ ባለው አንቀጽ የተናገርኩትን ዚቅ መሰል ቁም ነገር እዚች ላይ ብዙም አታስታውሱብኝና ወያኔ አንድን ዜጋ ምንም ጥፋት ወይም ወንጀል ሣይሠራ፣ ከነአካቴውም ለአቅመ-ወንጀል ያልደረሰን ሕጻን በአባቱ “ወንጀለኛነት” ምክንያት ከሀገር ማባረር ምን ሊባል እንደሚችል እያዘዋወርኩ ባስበው አልገባህ አለኝ፤ ይህ ዓይነቱ ባሕርይው ለብዙዎች ዜጎች አንገት ደፍቶ መኖር ምክንያት መሆኑን ሳስታውሰው ደግሞ የኔም ፈሪነት ቁልጭ ብሎ በእግረ መንገድ ታዬኝ – ያሳዝናል፡፡ አንድ ሰው ባልሠራው ሥራ ለምን ሰብኣዊና የዜግነት መብቱ ይደፈጠጣል? ወንጀለኝነት በዘር የሚተላለፍ ደዌ ይመስል ስለአባታቸው ሥራ ቀርቶ ስለምግብ አበላል በቂ ግንዛቤ የሌላቸውን ሕጻናት ከነእናታቸው እንዲያ ማባረራቸውና ማጉላላታቸው እነዚህን “ሰዎች” ብቻ ሣይሆን ለዴሞክራሲ ጥብቅና ቆሜያለሁ የሚለውን “ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ” ሣይቀር ለትዝብት ይዳርጋል – መቼም የወያኔ የጡት አባቶች ይህንን ጉድ አይሰሙም አይባልም፤ በልጃቸው ማፈር አለባቸው፡፡ (በነገራችን ላይ ወንድማገኝ ወንጀለኛ ሣይሆን የሰብኣዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ – ሊያውም የለብላቢው እ(ኢ)ሳት – መሆኑን ዐውቃለሁ – እናም እንኳን ቤተሰቡን እሱንም ቢሆን የሚያሸልም እንጂ የሚያስወነጅል ሥራ እንዳልሠራ እረዳለሁ፤ ወላድ በድባብ ትሂድ አቦ!)፡፡
እነዚህ “ሰዎች” – ወያኔዎች – ሥሪታቸው ከምን እንደሆነ ቀን አልፎ ጥናት የሚያካሂድባቸው ተመራማሪ ቢገኝ ደስ ይለኛል – ለበጀቱም የበኩሌን አስተዋፅዖ ለማድረግ ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡ የሚከተሉት ቀመር ወይም ፖለቲካዊ ፎርሙላ በጭራሽ ለማንም የሚገባ አይደለም – ምናልባትም ለነሱም ጭምር፡፡ ዐብደዋል ልበል? የሚሠሩትን ሁሉ ስናይ ሰው ያደርገዋል ብለን የምንገምተው አይደለም፡፡ አስቀድሜ እንደገለጽኩት “ነገ” ስለሚባል የጊዜ ተውሳከ ግስ አንድም የሚያዉቁት ነገር ያለ አይመስለኝም – እንደዐውሬ በ“ዛሬ” ፍቅር ብቻ የተለከፉ ናቸው – ማንኛው የፈረንሣይ ንጉሥ ነበር -“After me the deluge” ያለው? ከነሱ በዕጥፍ የምትሻለዋ አህያስ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ብላ የለም? ዳሩ እነዚህን መሰል የእፉኝት ልጆች ለማስተማር ማን ያልተቀኘ አለ – ችግሩ ፀማማት መሆናቸውና መስማትና ማየት አለመቻላቸው እንጂ፡፡ እንደጋሪ ፈረስ በዘረኝነት ጭምብል ተሸፍነውና በጥጋብ ተነድተው የሚያደርጉትን ቅጥ ያጣ የጥፋት ማዕበል ስንታዘብ እነሱን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩናል፤ ዝም ብለንም እንደመማለን – ለጊዜው መደመም ብቻ፡፡ ቋቱ ሲሞላ እንዴት ያለ አበሣ እንደሚገጥማቸው በማሰብ ጭምር፡፡ የሚያሳዝነኝ – እጅግ የሚያሳርረኝ – በነዚህ ጥጋበኞች ምክንያት የትግሬ ዘር በሞላ መወቀሱ ነው፡፡ አዎ፣ የማንሸሸው እውነት ነው፡- ገራፊውና አሣሪው ኮማንደር ግደይና ኢንስፔክተር ሐጎስ እየተባለ ሲነገርና ተገራፊውና ታሣሪው እንዲሁም እንደዐይጥ ባልተወለደ አንጀት ተጨፍጫፊው አቶ ስንሻውና እመት አበቅየለሽ እየተባለ ሲነገር ለጊዜው ሁሉም ነገር ተወነባብዶብን የምንጨብጠውንና የምንለቀውን ብናጣ ቀኑ ሲጠራ፣ ወርቃማ ዘመን ሲብት የትግሬ ብሀየር ምን ዓይነት ደግ፣ ሩህሩህና ሀገሩንና ሌላውን ወገኑን የሚወድ መሆኑን በግልጽ እናያለን፡፡ አሁን ግን ከጎመን ጋር የተገኘሽ መጭ እንዲሉ በነዚህ ዕውርና ደምባራ የጋራ ማፈሪያ ልጆቻችን ምክንያት በሁለት እሳት መሃል እየተገረፈ ይገኛል፡፡ ግዴለም፤ ሁሉም ማለፉ አይቀርምና እያየነው ያለውን ውርጅብኝ ሁሉ ከመለኮት እንደተላከ ቅጣት እንውሰደው፡፡
እንጂ ሰው እንደሰው ይህን መሣይ ለከት ያጣ ወንጀልና ጥፋት ያውም በመንግሥት ስም ተቀምጦ አያደርግም ነበር፡፡ በ24 እና በ40 ዓመታት ውስጥ የማይበርድ ቂምና ጥላቻ ደግሞ በመቶና በሺም አይለቅምና ወያኔን በምርጫና በማባበል እገላገላለሁ ማለት ህልም ብቻ ሣይሆን ቅዠት ወይም የለዬለት ዕብደት አለዚያም በአጫፋሪነት በመሰለፍ የጥቅም ተጋሪነትን እንደመግለጥ ነው፡፡ ወያኔ በምንም ዓይነት መንገድ በምርጫና በሰላም አይለቅም፡፡ በማይም ፌዴራል ተብዬ ወታደርና በማይም የቀበሌ ግሪሣ ካድሬ ሀገር ምድሩን ያጥለቀለቀው ወያኔ በምርጫና በድርድር ሥልጣን ያስረክባል ማለት ቂልነት ነው፡፡ “በምርጫው እንሳተፋለን” የሚሉ ወገኖችን ስሰማ እንዴት እንደምቃጠል አትጠይቁኝ፤ ለነገሩ የት አግኝታችሁ ትጠይቁኛላችሁ? ይልቁንስ ምርጫውን ትተው ለምርጫው የሚወጣውን ብዙ ገንዘብ ለፕሮጀክቶች ቢያውሉት ደግ ነበር፡፡ በድግስ፣ በዝርፊያ፣ በሙስናና በዘመድ አዝማድ የምዝበራ ሰንሰለት ከሚቦጠቡጡት የሀገር ሀብት በተጨማሪ በዚህ የቀልድና የፌዝ ምርጫ የሚያወድሙት ገንዘብ በውነቱ በጣም ይቆጫል፡፡ በስንቱ ነው የምንከስል እናንተዬ!
ይህን የወንድማገኝን ቤተሰባዊ ክስተት በኢሣት እንደሰማሁ ወደ አንድ ኮማንደር ወያኔ ጓደኛዬ ደውዬ ወይም በአካል እቢሮው ሄጄ ምን እየተካሄደ እንደሆነ፣ በርግጥ ጤናማ ሰው ነው ወይ ያ ዓይነት የለየለት ሕገወጥ እርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘው ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችን ልጠይቀውና ይህ ዓይነቱ አካሄድ ትክክል አለመሆኑን፣ ሀገርንም እንደሚያዋርድ የውድባችንን ስምም እንደሚያጠለሽ በቀጥታም ባይሆን በተለሳለሰ አነጋገር ጠቁሜ እኔም እተነፍሳለሁ ብዬ ሳስብ ይቺ ነገር ጦስ ትሆንብኝና ሌላ ነገር ታስከትልብኛለች በሚል ፍራቻ ተውኳት፤ “ፈሪ ለናቱ ያገለግላል – ምጎጎ ስ’ጥድ ሙግድ ያቀብላል” ይባላል፡፡ በመፍራቴ ምክንያት በልቶ ከመተኛት ውጪ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማያውቁ፣ የሀገር ጉዳይ ቢጠበስ የማይሸታቸው፣ እየሆነ ባለው ነገር ሁሉ የማይሞቅ የማይበርዳቸው ስድስት ክቡራንና ክቡራት “ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት” ልጆችን ከሚስቴና ከራሴ አብራኮች አፍርቼ በ“ጎመን በጤና”ዊ ወያኔያዊ “ሰላም” በመታጀብ እያሳደግሁ ነው፡፡ ማን ያውቃል – ነገም ሌላ ቀን ይሆን ይሆናል፤ እናም ዛሬ አካማሌ የሆነው ነገር ሁላ ነገ ወደቦታው ሊመለስና ሀገር ልትፈጠር ትችል ይሆናል፡፡ “ደግ ተመኝ ደግ እንድታገኝ” ነው ተረቱ፡፡
ይህችን ገጽ ልሙላና እንለያይ፡፡
ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት 23 ተኩል ዓመታት ወዲህ መንግሥት የላትም፡፡ መንግስት እንዳልነበራትና እንደሌላትም ለማስረዳት አልሞክርም፡፡ ተብሎ ተብሎ ያለቀን ጉዳይ ለማስረዳት መድከም ትርፉ አሁንም ድካም ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ቅንና ተቆርቋሪ ተቃዋሚ ኖሯት አያውቅም – ሊኖራት ቢችል እንኳን ከፍ ያለ ዕድል አላገኘም ወይም አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይህንን እውነት መካድም ዐላዋቂነት ወይም አድርባይነት ነው፡፡ ሀገራችን መንግሥትና ከግለኝነት ያለፈ ሁነኛ ተቃዋሚ ቢኖሯት ኖሮ የአሁኑ ቅርጽዋ በአወንታዊነት መልኩ በእጅጉ በተለወጠና ቢያንስ ከመፈራረስ ድና ባለችበት እንኳን መጓዝ በቻለች ነበር፡፡ ለዚህ የጉስቁልና ደረጃ ያበቋት ቅኝ ገዢው የትግሬ ወያኔና በውጪም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ መሣይ “ተቃዋሚዎች” ናቸው ማለት እችላለሁ – በበኩሌን፡፡ እርግጥ ነው ሌት ተቀን የማይተኙላት የወያኔ እስፖንሰሮች መኖራቸውን ለአፍታም ልዘነጋ አልፈልግም፡፡ የኢትዮጵያ መፈራረስ ችግር መንስኤ ቀንዱ ሀገር ውስጥ ያለ ቢመስልም ጭራው ውጭ ሀገር በተለይም የኢትዮጵያዊነትን ብሔራዊ ስሜት መዳበርና የአንድነቷን መጠናር እንደሥጋት ከሚቆጥሩ የውጭ ኃይሎች ዘንድ ነው፡፡ ያዋጁን በጆሮ ሆነብኝ እኮ – ታዲያ ምን ላውራ? ታፍኖ ይሞታል እንዴ?
የሚገርመው ነገር ግና ማንም ይሁን ማን በሕዝብ አላግጦ የሚቀር አለመሆኑ ነው – የሀገር ውስጥ ምንደኛም ሆነ የውጭ ደመኛ ሁሉም በመጨረሻው መጨረሻ ላይ የየድርሻውን ያገኛል፡፡ ሕዝብን መናቅ፣ ሀገርን ማዋረድ አይቻልም አይባልም ፤ ይቻላል፤ በተደጋጋሚ እንደታየው ደግሞ ተችሏልም፡፡ ነገር ግን ማንም በማንም ላይ አሹፎና ፈትፍቶ እንደማይቀር በተለይ ከቀዳማዊ ኃ. ሥላሤ መንግሥት ወዲህ ያሉ ደም መጣጭ መሪዎችንና ጎታች ሥርዓቶችን የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ በማየት በእግዚአብሄር ኃያልነትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ እሣትነት ፍጹም መተማመን ይቻላል፡፡ ያገሬ ባላገር “የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀረው ጌታ ፍርዱን ይሰጠኛል!” እያለ ወደ ላይ የሚጮኸው ይህን በተለይ በኢትዮጵያ ምድር ተዘንግቶ የማያውቅ የፈጣሪና የተፈጥሮ ሕግ በመረዳት ነው፡፡ “ይህ ገበሬ ምን ያውቃል፤ ቀጥቅጦና በማይምነት ሸብቦ እንደሚወቃ እህል በጥይትና በችጋር እያበራዩ መግዛት ነው እንጂ!” ብለው በተደጋጋሚ አራት ኪሎን የፊጥኝ የሚሉ ገዢዎች መጨረሻቸው ምን እንደሆነ እያየን ከርመናል – ፈጣሪ አያሣፍሬ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የምናመልከው አምላክ በሰሜን ኮሪያ እንደሚመለከው ዓይነት አምላክ እንዳልሆነ ዱሮም አይተናል፤ ዕድሜውን አይንፈገን እንጂ አሁንና ዛሬም በቅርብ እናያለን፡፡ “የናቁሽ እግርሽ ሥር ተደፍተው ይሰግዱልሻል” የተባለላት እምዬ ማርያም ብቻ ሣትሆን ቅድስት ኢትዮጵያም ናት፡፡ አላግጦባት በነፃነት ዕድሜ ልኩን የተንደላቀቀ ካለ ጠቁሙኝ፤ የለም – ባለኝ ሁሉ እወራረዳለሁ፤ በልጆቼ ሣይቀር፡፡
እናም እኔም አምናለሁ፡፡ ኃይለኞች ክንዳቸው ይዝላል፤ ደካሞች በብርታታቸው ደጀን በፈጣሪ ተደግፈው ታፍኖ የነበረ ሣምሶናዊ ኃይላቸው ይጠነክራል – የኃይላችን ምሥጢር የአንድነት ፀጉራችን የተላጨ ቢመስልም አሁን በፍጥነት ያቆጠቁጣል፡፡ በመጨረሻም እንደተራራ የገዘፉ ይመስሉ የነበሩ ጎልያዶች፣ እንደቁጫጭ በተናቁ ዳዊቶች ድምጥማጣቸው ይጠፋል፡፡ ደግሞም እላለሁ – የማሸነፍና የመሸነፍ ምሥጢር ምንጩ የፍትሕ መረገጥና የዕንባ ሙላት እንጂ የመሣሪያ ጥራትና የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ “ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም”ና፡፡ አንዱ ከአንዱ ሣይማር ጀምበር የመጥለቋ ጉዳይ ግን ሁል ጊዜ ያሳዝነኛል – እንደአካሄድ፡፡ ምን ዓይነት ዘላለማዊ ሞኝነት ይሆን? “ያበራሽን ጠባሣ ያዬ በእሳት አይጫወትም” የሚባለው ተረት በጎረምሶች ሠፈር ብቻ ነው ማለት የሚተረተው?… እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በእስካሁኑ ሁኔታ መንግሥትና ተቃዋሚ የለምና አልነበረም ካልኩ ዘንድ መንግሥት ሲኖር ምን መደረግ እንደሚገባው ጥቂት ልናገር – ጊዜው ገና ቢሆንም፡፡
መንግሥት ከስሜት ነጻ የሆነ ተቋም እንጂ በግለሰብ ወይም በቡድን አስተሳሰብና ስሜት የሚነዳ ግለሰባዊ ባሕርይ የተላበሰ ‹ሰው› መሆን የለበትም፡፡ ሰውና መንግሥት ከተቀላቀሉ ነገሩ ሁሉ ይበለሻሻል፡፡ በመንግሥቱ ኃ/ማርያም ዘመን ሰውና መንግሥት ተቀላቅለው ፍዳችንን አየን፡፡ በቀደሙትም ሥርዓች የነበረው ከዚያ የተለዬ አልነበረም – በአንጻራዊነት አንዱ ከሌላው የተሻለ ቢመስልም፡፡
ሰውና መንግሥት ሲቀላቀሉ ውሉ ሁሉ ይጠፋና አዛዥና ታዛዥ ድንብርብራቸው ይወጣል፡፡ የተጻፈም ሆነ ያልተጻፈ የመንግሥትና የኅሊና ሕግጋት ድራሻቸው ይጠፋና ስሜትና አምባገነንነት ብቻ ቁልጭ ብለው ይወጣሉ – ከዚያ ግለሰብን እንደጣዖት ማምለክና የርሱን እስትንፋስና ቅዠትና ቅብዥር እየተከተሉ ሀገር ምድርን በእሳት ማጋየት ይለጥቃል – እንደነ መንግሥቱ፣ ሙጋቤ፣ ሙሴቪኒ፣ መለስ፣ ጋዳፊ፣ አሣድ፣ ሂትለር፣ ሙሶሊኒ፣ ወዘተ. ፡፡ ለምሳሌ የጌታህን ስሜት ተከትለህ ጌታህን ያስቀየመ አንድን ዜጋ ለመበቀል በማሰብ በአንድ ጀምበር ሕገ መንግሥት የምትሽር ወይም አዲስ ሕግ የምታወጣ ከሆነ መንግሥትን አፈረስክ ማለት ነው፤ ሕግን ተማምኖ ወደጨዋታ ሜዳ የገባን ዜጋ በሕገ መንግሥቱ አንቀፆች ሲሞግትህ “ሕገ መንግሥት የምትለውን ወረቀት ቀቅለህ ብላው፤ እንትንህን ጥረግበት፤ ….” የምትለው ከሆነ የሀገር ኅልውና አከተመ ማለት ነው ፡፡ ከዘጠና ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ በሚኖርባት ሀገር ውስጥ ዘጠና ሚሊዮን ጊዜ ሕግና ሕገ መንግሥት የምታጸድቅ ከሆነ የምትመራው በዕውር ድንብር የስሜት ፈረስ እንጂ የዜጎችን ይሁንታ ባገኘ ሕግ/ሕገ መንግሥት አይደለም፡፡ መንግሥት ትልቅ ነገር ነው፡፡ መንግሥት ተቋም ነው፡፡ እንደዜጋ ለጠላትህም ለወዳጅህም የሚሠራ በቀላ በጠቆረ፣ በከሣ በወፈረ፣ ያንተን ቋንቋ በተናገረ ባልተናገረ፣ በተዛመደ ባልተዛመደ ወዘተ ከሆነ አዲዮስ መንግሥት፡፡ የመንግሥት ተቋም ለመንግሥትና ለሕዝብ እንጂ ለግለሰብ ወይም ለቡድን ወይም ለፓርቲ ተጠሪነትና ተጠያቂነት የለበትም፡፡ ተመልከት – መንግሥቱ ኃ/ማርያም ለምሳሌ የተሻለ መንግሥታዊ ሥርዓት ነበረው ማለት እንችላለን፤ ኒቆዲሞስ ዜናዊ፣ ዜናዊ አስረስ፣ ሌሎቹም የመለስ እህቶችና ወንድሞች በማንነታቸው ሣያፍሩና በዜግነታቸው ሣይኮማተሩ አንዳንዶቹ በአዲስ አበባ አንዳንዶቹ በዐድዋና በሌሎች የትግራይ ክፍለ ሀገር አካባቢዎች በሰላም ይኖሩ ነበር፡፡ ልጁ ጫካ ገብቶ ኢትዮጵያን እያፈራረሰ ለሚገኘው ለዜናዊ አስረስና ለሌላው ዜጋ የዚያኔው መንግሥት ቁንጮ ሥልጣን ወዳዱ መንግሥቱ ኃ/ማርያም እንኳን ነፍስ ዐውቆ በግዳጅ ያቆመው ሥርዓት ለሁሉም ዜጎች እኩል ነበር፡፡ መንግሥት እንደሕጻን የሚያኮርፍና የሚቆጣ አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም፡፡ የግለሰቦችን እስትንፋስ እየተከተለም ሀገርን እስከማጥፋትና ሕዝብን እስከመበታተን የሚደርስ ባሕርይ በፍጹም ሊኖረው አይችልም፡፡ ኢትዮጵያን ዕድሜ ልኳን የኋሊት ሲጎትታት የነበረው ይህ ዓይነቱ የስሜትና የተቋም መጫፈር ነው፤ ድንበራቸው ሊከበር ይገባል – ፓርቲ፣ መንግሥት፣ መከላከያ፣ የፍትህ አካላት፣ ወዘተ. እንዳስፈላጊነቱ አንድም ብዙም ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ እስካልተወገደ ድረስ ሀገርና ሕዝብ አይኖሩም፡፡ ሲቀላቀሉ ሀገራዊ ፊስቱላ ይፈጠርና ሁሉም ተበለሻሽቶ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑ ቀርቶ ጠበንጃና መቁሽሽ እንደሆነ ይቀራል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በሀገር ደረጃ ይቅርና በቤተሰብና በተራ ጓደኝነትም ሊታይ አይገባም፡፡ ስለሆነም ከዚህ ዓይነቱ አሣፋሪ ጉዞ ባፋጣኝ እንውጣ፡፡
እዚህ ላይ የወያኔን የሽፍታ መንግሥት ብዙ ጉድለቶች ማንሣት በቻልኩ፡፡ ግን አስቀድሜ ይህ ቡድን መንግሥት ያልሆነ፣ በመንግሥትነትም ሊጠራ የማይገባው ከማፊያ የወረደ የመተዳደሪያ ደንብ ያለው – ያም ደንብ መሠረቱ ፍጹም በዘቀጠ ኢ-ሞራላዊነት የተበከለ መሆኑን በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ በመግለጼ ለምሳሌነትም አይበቃም፡፡ …. ሰንደቅ ዓላማ የሌለው ሕዝብ፣ ብሔራዊ መዝሙር የሌለው ሕዝብ፣ ብሔራዊ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት የሌለው ሕዝብ፣ … መንግሥት አለው ማለት አንችልም፡፡ እንደኢሣት ያሉ የሕዝብ ብሶት መተንፈሻ ሚዲያዎች ይህን የወሮበሎች ጥርቃሞ “የኢትዮጵያ መንግሥት” እያሉ ሲጠሩት ምን ያህል እንደሚያም እንግዲህ ፍረዱ፡፡ ነውር ነው፡፡ መንግሥት የሌላትን ሀገር ይልቁንም አንድን ታሪክ ወደ አንድ ብሔር የብቻ ታሪክነት በማጠጋጋት ያ በጥላቻ የሚታየው ብሔር ጭምር የመላ ሀገሪቷ ታሪክ በእሳትና በሥርቆት/በዘረፋ እየወደመባት የምትገኝን ሀገር መንግሥት ያላት አስመስሎ መናገር ወያኔን ባለማወቅም ቢሆን እንደመደገፍ ይቆጠራል፡፡ የነኮሎኔል ዓለሙና ደምሰው እንዲሁም አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎች ብዙዎች ወገኖቻችን ኃጢኣታቸው ባልቀረበላቸው ምርጫ መሠረት አማራ ሆነው መፈጠራቸው ነው፡፡ ጣይቱ ሆቴል በደቂቃዎች ውስጥ በእሳት የወደመው ካለምርጫው በአማራነት በተፈረጁት አጤ ምኒልክ ዘመን በመታነጹ ነው – ጥፋቱ “አማራነቱ” መሆኑ ነው፡፡ ይህ የገባቸው ሤረኛ ፈረንጆችና ዐረቦች በወያኔ ድርጊት አንጀታቸው ቅቤ ይጠጣል – ድጋፋቸውንም በግልጽም ሆነ በሥውር ያጎርፉለታል፡፡
እኛ ደግሞ በአንጻሩ አንተ አማራ አንተ ትግሬ አንተ ኦሮሞ አንተ ምንትስ አንቺ ምንትስ እየተባባልን የቂላቂል ጠላት ተከል ጨዋታችንን እንቀጥላለን፤ ግሩም ነው፡፡ ግን ደግነቱ ይህም ያልፋል፡፡ የሚያልፈው ግን ጌታ በቃችሁ ሲለንና የራሱን ሙሤዎች ሲልክልን እንጂ በዚህ ወይም በዚያ የዳመነ የነፃነት ችቦ ስላስገመገመ እንዳይመስላችሁ፡፡ የነፃነት ቀን መቅረቧን ለማወቅ የወያኔን ግፍ ጫፍ መንካት ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ (አንድ ጅብ ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን ይገባል አሉ፡፡ ከበሮውን በአንገቱ አጥልቆ ሊወጣ ሲል የገባበት በር ይጠረቀምበትና ይሆነውን ያጣል፡፡ ከቆዳ የተሠራ የከበሮ ግዳይ እንደያዘ ለመውጣትና ወደጎሬው ወስዶ ለመቆርጠም ሙከራውን ይቀጥላል፡፡ ይሁንና ከበሮው ከግድግዳው ጋር ሲጋጭ በሚፈጥረው ድምጽ ጅቡ እየበረገገ በቤተ ክርስቲያኑ የወንዶች፣ የሴቶችና የቅኔ ማኅሌት ወለሎች ሁሉ እንትኑን ይለቀው ገባ፡፡ ጧት ካህናትና ምዕመናን ሲመጡ የቤተ ክርስቲያኑ ወለል በአያ ጅቦ ነጭ እንትን ኖራ የተቀባ መስሎ ተበለሻሽቶ አገኙት፡፡ ወያኔም በፍርሀት እየተሸበረ ኢትዮጵያን በግማት ክርፋቱ እያጨቀያትና እያከረፋት ይገኛል፡፡ ይህ የዘረኝነትና የሙስና እንዲሁም የማይምነትና የሆዳምነት ክርፋትና ግማት ስንት ሚሊዮንና ቢሊዮን ሊትር ጠበል ተረጭቶ ኢትዮጵያን ሊለቅ እንደሚችል አስቡት፡፡ ከባድ ሀገራዊ ቀውስ ነው ወያኔ እያስቀመጠብን የሚገኘው፡፡ ብዙውን ሰው እኮ ስታዩት በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስ ፈረንጆቹ “ዞምቤ” የሚሉት ዓይነት በድን አካል ነው የሚመስላችሁ፡፡ ለነፍስ ሣይሆን ለሥጋ ምግብ የሚተጋ፣ ለዕውቀት ሣይሆን ለወረቀት የሚጣጣር፣ ከመንፈሣዊ ቅናት ይልቅ በሥጋዊ ምቀኝነት ዕንቅልፍ የሚያጣ፣ ስለሀገርና ስለሰው ሣይሆን ገንዘብ እንዴት እንደሚገኝ የሚጨነቅ፣ በጥቅሉ በሜካኒካዊ ሕይወት የሚንከላወስ ሮቦታዊ ፍጡር ሀገር ምድሩን እየሞላው ነው – በኢትዮጵያ፡፡)
ለማንቻውም ወያኔ በቅርቡ ሲወድቅ ከስሜት የጸዳ መንግሥታዊ ተቋም እንዲኖረን ሁላችን መጸለይ እንደሚገባን ደግሜ ማሳሰብ እፈልጋለሁ – ከዛሬ ይልቅ ነገ ይበልጥ ያስጨንቃልና፡፡ የምንጋግረው ቂጣና ዳቦ ለስንት ጊዜ ይረርብን? ስደት እንዳይቀጥል፣ የዕንባ ጎርፍም ቀጥሎ ነበልባላዊ ግርፋቱ ቀጣዩንም መንግሥት በሂደት ለብልቦና አቃጥሎ እንዳይፈጅብንና መቅኖ አሳጥቶን እንዳይቀር ይህን ጉዳይ በጥሞና እናስብበት፡፡ ጊዜው የተግባር ይሁን፡፡ ሁላችንም በየምንችለው ለነፃነታችን እንትጋ፡፡ የሰው ወርቅ አያደምቅም፡፡ የራሳችን ወርቅ ባለቤት ለመሆን ጊዜው ደርሷልና አንዘናጋ፡፡ ትልቁ በመጀመሪያ ማድረግ የሚገባን ግን ራሳችንን ፈትሸን ወደ መደበኛ የሰውነት ደረጃ መመለስ ነው፡፡ ሰው የመሆን ምልክቱ ደግሞ ገንዘብ ወይም እውቀት ብቻ አይደለም – ጥበብ ነው፡፡ ጥበብን እንሻት፤ ዕውቀትና ግንዛቤያችንን ወደጥበብ ለመለወጥ እንትጋ፡፡ ማንበብ ጥሩ ነው – እናንብብ፡፡ ማዳመጥ ጥሩ ነው – እናዳምጥ፡፡ ከጠብና አምባጓሮ መታቀብ ጥሩ ነው – እንታቀብ፡፡ ፍቅርና መዋደድ ትሩ ነው – እንፋቀር፤ እንዋደድም፡፤ ዘረኝነት መጥፎ ነው – ከዚህ ወያኔያዊ መርዝ እንራቅ፡፡ መቻቻልና ትግሥተኛነት ጥሩ ናቸው – እንቻቻል፤ ግልፍተኝነትንም እናስወግድ፡፡ ጥላቻን በፍቅር፣ ቂመኝነትን በሆደሰፊነት እንተካቸው፡፡ ይቅር ባይነት ደግሞ ከሁሉ የበለጠ መፍትሔሥራይ ነውና ይቅር ለእግዜር እየተባባልን በእውነተኛ ያንጀት ፍቅር ተቃቅፈን አዲስ ሰው እንሁን፡፡ ሆዳችን አይግዛን- ኅሊናችን እንጂ፡፡ ለሆድ ቅድሚያ ከሰጠነው ሀገርና ሕዝብን ብቻ ሣይሆን ልጅና ሚስታችንን/ባላችንን እስከማሸጥ ይደርሳል፡፡ ይሁዳ ጌታውን የሸጠው በሠላሣ አላድ ነው – ላይበላውና በፀፀት ታንቆ ከመሞት ላያድነው፡፡ የሆድ ነገር መጨረሻ እዳሪ ነው – የኅሊና ግን ከመቃብር በላይ የሚኖር መልካም ታሪክ ያጎናጽፈናል፡፡ መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል እንዲል መጽሐፉ ወደዬኅሊናችን ባፋጣኝ ተመልሰን መንገዳችንንና ፍላጎቶቻችንን እንቃኝ፤ ወደ “ጠባቡ” መንገድም እንመለስ፡፡ ሰፊውን መንገድ እስኪበቃን – ምናልባትም እስኪገለማን – አየነው፡፡ ከራስ ወዳድነት ወጥተን ስለሌሎችም መቸነቅን እንጀምር፡፡ በመጀመሪያ ሺህ ዓመት አንኖርም፤ ለዚች አጭር ምድራዊ ሕይወት ብለን ደግሚ ልክ አምስትና ስድስት ሺህ ዓመታትን የምንኖር ያህል እያሰብን በስግብግብነትና በራስ ወዳድነት የድሆችን ሀብትና ጥሪት ወደራሳችን ካዝና አናግበስብስ፡፡ በቃኝን እንወቅ፡፡ እኔም አሁን በቃኝ ልጄ፡፡
ነፃነት ዘለቀ (nzeleke35@gmail.com)

No comments:

Post a Comment