Translate

Friday, January 16, 2015

ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና ሌሎች ሁለት የፓርቲ አመራሮች ምስክርነታቸውን ሰጡ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ስለሺ ፈይሳ እና የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ዛሬ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት ቀርበው የተከላካይ ምስክርነታቸውን ሰጡ፡፡
ህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ተዘጋጅቶ በነበረው የአዳር ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቅስቀሳ በራሪ ወረቅት ሲበትን ለእስር የተዳረገው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሲሳይ ዘርፉ በፌደራል አቃቤ ህግ በቀረበበት ክስ ተከላካይ ምስክር ሆነው የቀረቡት የፓርቲ አመራሮቹ፣ አቶ ሲሳይ ባለፈው ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የአቃቤ ህግ ሁለት ምስክሮች ቀርበው በተከሳሽ ላይ ምስክርነት በመስጠታቸውና በዕለቱ ዳኛው በበራሪ ወረቀቱ ላይ የተጠቀሰውን ‹‹የኢህአዴግ መንግስት ያፍናል፣ ያጭበረብራል፣ ይገድላል…›› የሚለውን በመጥቀስ ድርጊቱ ወንጀል ስለሆነ ተከሳሹ መከላከል አለበት ማለቱን ተከትሎ የመከላከያ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ተከሳሹ አቶ ሲሳይ ዘርፉ ‹‹…‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ› ለመላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ….ተብሎ የተጻፈበት በራሪ ወረቀቶች ለህብረተሰቡ ሲያከፋፍል እጅ ከፈንጅ በመያዙ በፈጸመው የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል…›› በሚል ነው ክስ የቀረበበት፡፡


በመሆኑም የተከሳሽ ተከላካይ ምስክሮቹ ተከሳሹ ሲያሰራጨው የነበረውን ወረቀት ያዘጋጁት የትብብሩ አባል ፓርቲዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ተከሳሹ እንደማነኛውም አባል የፓርቲዎቹን መልዕክት ለህዝብ ከማድረስ ባለፈ በግሉ የራሱን መልዕክት አለማስተላለፉን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በበራሪ ወረቀቱ ላይ የሰፈረውን መልዕክት በተመለከተም፣ ‹‹የኢህአዴግ መንግስት ያፍናል፣ ያጭበረብራል፣ ይገድላል…›› የሚለው አገላላጽ ትክክል መሆኑን የተለያዩ ሪፖርቶችን በማጣቀስ አስረድተዋል፡፡
ምስክሮቹ የኢህአዴግ መንግስት ‹‹ያፍናል፣ ያጭበረብራል፣ ይገድላል…›› የሚለው እውነት ስለመሆኑ በምርጫ 97 ወቅት 193 ዜጎች መገደላቸውን መንግስት ራሱ ያቋቋመው አጣሪ ኮሚሲዮን ማረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚያም በኋላ በቅርብ ጊዜ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎችን ግድያ እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ በተመሳሳይ ሰልፍ የወጡ ዜጎችን ግድያ አንስተው አስረድተዋል፡፡
‹‹ያጭበረብራል›› የሚለውን በተመለከተም በ97 ምርጫ ወቅት የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ ቡድን ያወጣውን ሪፖርት በማስረጃነት አንስተዋል፡፡ ‹‹ያፍናል›› የሚለውን በተመለከተም መንግስት በተለያዩ ወቅቶች የመብት ጥያቄ ያነሱ የዴሞክራሲ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለውን እስር አውስተዋል፡፡ በተለይ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጦማርያንን እንዲሁም በሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ ምክንያት የታሰሩ አካላትን አጣቅሰው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአጠቃላይ በበራሪ ወረቀቱ ላይ የሰፈረው መልዕክት የሀሰት ወሬ እና ስም ማጥፋት ሳይሆን ተጨባጭ እውነታ መሆኑን በምስክርነታቸው ቃል አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እስካሁን የነበረውን የአቃቤ ህግ እና የተከሳሽ ምስክሮችን ቃል አገናዝቦ ብይን ለመስጠት ለጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment