Translate

Sunday, January 11, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ


ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትን እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሑፍ ይቅርታ ይጠይቅ በማለት የተላለፈው ውሳኔ ከሕግ አግባብ ውጪ ስለሆነ ተቃውሞውን በመግለጽ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ፡፡

የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ባለፈው ሐሙስ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድን ስም አጥፍቷል ብለዋል፡፡ ‹‹በተሻሻለው የምርጫ ሕግ አንቀጽ 102 (4)ሀ፣ ለ እና ሠ እንዲሁም 102 (6) ሐ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን ሥልጣን መቀበል፣ ሕጋዊ ትዕዛዙንና መመርያውን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው የጋራ የምክክር መድረኮች ወይም ሌሎች መድረኮች ላይ ወኪል የመላክ ኃላፊነት እንዳለባቸውና በሐሰት ስም ከማጥፋት መቆጠብ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ግን ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ያዘጋጃቸውን የጋራ ምክክሮች እንዲበተኑ ሙከራ አድርጓል፣ እየረገጠ ወጥቷል፣ በሐሰት ቦርዱን ወንጅሏል፡፡ እንዲሁም የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርጓል፤›› በማለት ፓርቲው በጽሑፍ ይቅርታ እንዲጠይቅ ቦርዱ ወስኗል በማለት አስታውቀዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ውሳኔውን አስመልክቶ፣ ‹‹እኛ ይህን የምንረዳው የምርጫ ቦርድ የራሱ አቋም ሳይሆን ኢሕአዴግ በቦርዱ ውስጥ ምን ያህል ሚና እንዳለው ያጋለጠ ውሳኔ መሆኑን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰጠነው አስተያየትና ስብሰባ ረግጠን መውጣታችን ዘለፋ መስሎ ከተሰማቸው አትዝለፉን እንነጋገር ማለት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ይቅርታ ጠይቁኝ ብሎ ማስፈራራት አገራችንን አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ይቅርታ መቀለጃ አይደለም፡፡ እኛም በዚህ ምክንያት አናስተናግደውም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በተጨማሪም በመሠረቱ እኛ አንድ ድርጅት ነን፡፡ ምርጫ ቦርድም እንዲሁ አንድ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሊግባቡ የሚችሉት ደግሞ በሕግና በደንብ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ካጠፋ ወይ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል፣ ወይም ቦርዱ ባለው ሥልጣን ችግሩ ይፈታል፡፡ ቦርዱም ካጠፋ እንዲሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ይቅርታ ጠይቀኝ ብሎ መጠየቅ ፍፁም ተቋማዊ አሠራር አይደለም፤›› በማለት ውሳኔውን ፓርቲያቸው እንደሚቃወም አስታውቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment