Translate

Saturday, January 10, 2015

“ጥምቅት በዓል ላይ ሰማያዊ ቲሸርት መልበስ አይቻልም” – ኢህአዴግ

“ጥምቅት በዓል ላይ ሰማያዊ ቲሸርት መልበስ አይቻልም” – ኢህአዴግ

blue shirt

በተለይ ምርጫ ሲደርስ ቀለማዊ ነክ ነገሮችን በጣም የሚያስፈራው ህወሃት/ኢህአዴግ በመጪው የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ሰማያዊ ቀለም እንዳይታይ መከልከል መጀመሩ ተዘግቧል፡፡ የደኅንነትና የፖሊስ አባላቱን በማሰማራት በግልጽ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ያለው ኢህአዴግ ለዘመናት በቆየው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የጨመረው ባለ ሰማያዊ መደብ ኮከብ በበዓሉ ላይ እንዳይታይ አብሮ ካልከለከለ በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማነት የሰየመውን የኢህአዴግ ዓርማ መቀየር አለበት በማለት አንዳንዶችተሳልቀዋል፡፡ በሰማያዊ መደብ ቢጫ ኮከብ ያለውን የኢህአዴግ ዓርማ በቲሸርት በማሰራት “ለኢህአዴግዬ ያልሆነ … ይበጣጠስ” በማለት “አምረውና ደምቀው” በበዓሉ ለመታየት ያሰቡ ካድሬዎቹና አፈቀላጤዎቹም በዚህ ጉዳይ ላይ አመራር ካልተሰጣቸው “ከኑግ የተገኘ …” የመሆን ዕጣ እንዳይደርሳቸው “ያስፈራል” ተብሏል፡፡

ጉዳዩ በስላቅ ቢገለጽም ቀለም ፈሪው ኢህአዴግ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለጥምቀት አከባበር በሰማያዊ ቲሸርት ላይ ከዚህ በፊት እንደተለመደው መንፈሳዊ ጥቅሶችን በመጠቀም ያዘጋጁትን ቲሸርት ለብሰው መውጣት እንደማይችሉ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ እየሰጠ መሆኑንከነገረ ኢትዮጵያ የፌስቡክ ገጽ የተገኘው ዜና ያስረዳል፡፡ ዜናው በዚህ መልኩ ቀርቧል፡፡
ለጥምቀት ሰማያዊ ቲሸርት እንዳይለበስ ተከለከለ
ህዝብን ያነቃቃሉ የተባሉ መንፈሳዊ ጥቅሶች መጠቀም አይቻልም ተብሏል
የክርስትና እምነት ተከታይ ወጣቶች ጥምቀት በዓል ላይ ሰማያዊ ቲሸርቶችን እንዳይለብሱ መከልከላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ጀምሮ እስከ ጃንሜዳ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች በተለያዩ ማህበራት ስር ለጥምቀት በዓል ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ምንጮቹ ከዝግጅታቸው መካከል ቲሸርት አሳትሞ መልበስ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ወጣቶቹ ለጥምቀት በዓል የተለያዩ የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅሶች የታተሙበት ሰማያዊ ቲሸርት ማሳተማቸውም ተከትሎም ደህንነትና ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በየቤታቸው እየዞሩ “ጥምቅት በዓል ላይ ሰማያዊ ቲሸርት መልበስ አይቻልም” እያሉ እያስጠነቀቁ መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያገልጸዋል፡፡ በነገው ዕለትም ካድሬዎች ከፈረንሳይ ሌጋሲዮን እስከ ጃን ሜዳ አካባቢ የሚገኙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ስብሰባ መጥራታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ህዝብን ያነቃቃሉ ከሚል ስጋት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቲሸርት ላይም ሆነ ሌላ ለጥምቀት በዓል ላይ በማድመቂያነት በሚውል ነገር ላይ ማተም እንደማይቻል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ወጣቶቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ለጥምቀት በዓል ማድመቂያነት እንዳይውሉ ከተከለከሉት ጥቅሶች መካከል “የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚያብሄር ትዘረጋለች፣ የአባቶቻችን ርስት አንሰጥም …” የመሳሰሉት ይገኙበታል ተብሏል፡፡ እነዚህን መንፈሳዊ ጥቅሶች መጠቀም እንደሚያስቀጣም ደህንነትና ፖሊሶች የበዓሉ አዘጋጅ ወጣቶችን አስጠንቅቀዋል፡፡
ወጣቶቹ ሰማያዊ ቲሸርትም ሆነ የተከለከሉትን መንፈሳዊ ጥቅሶችን በሃይማኖታዊ ፋይዳቸው ምክንያት ባለፉት የጥምቀት በዓላት ላይ ሲጠቀሙባቸው እንደቆዩ፣ አሁን ደህንነቶች እነሱ ካላሰቡት ፖለቲካ ጋር ማገናኘታቸው እንዳሳዘናቸውና ከሃይማኖታዊ ፋይዳቸው ውጭ ምንም አይነት ትርጉም እንዲኖራቸው ታስበው የተሰሩ ባለመሆናቸው በበዓሉ ላይ እንደሚጠቀሙባቸው ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment