Translate

Friday, August 7, 2015

የፕሬዚዳንት ኦባማ የአፍሪካ ኅብረት ንግግርና እንደምታው


def-thumbየዩ ኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓም አዲስ አበባ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት ያደረጉት ንግግር በርካታ ቁምነገሮችን የያዘ በመሆኑ አንጽዖት ሊሰጠው እንደሚገባ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል።
ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንግግራቸው የአፍሪቃን በተለይም ደግሞ የአገራችንን ችግሮች ነቅሰው አሳይተዋል። ሰብዓዊ መብቶች ሰው በመሆናችን ያገኘናቸው በመሆኑ በቆዳችን ቀለም፣ በተወለድንበት አካባቢ፣ በምንናገረው ቋንቋ ወይም በሌላ ማናቸውም ምክንያቶች ሊሸራረፉ የማይገቡ መሆኑን በመግለጽ “ሁላችንም እኩል ተወልደናል” በማለት ዘረኞችን አፍ የሚያዘጋ ኃይለቃል ተናግረዋል። “ሁላችንም ከአንድ ግንድ የበቀልን ነን፤ ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን፤ ሁላችንም አንድ ጎሳ ነን” ካሉ በኋላ በዓለም ያለው አብዛኛው ችግር ይህንን መረዳት አለመቻላችን፤ ራሳችንን በእያንዳንዳችን ውስጥ ማየት አለመቻላችን ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ በብዙ የአፍሪቃ አገሮች፣ ዜጎች ነፃነታቸው የተገፈፈ መሆኑን፤ ምርጫ መኖሩ ብቻ ዲሞክራሲ ሰፈነ ማለት አለመሆኑ አብራርተዋል። ጋዜጠኞች፣ የተቃውሞ ፓለቲካ መሪዎችና ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች፣ የሲቪክ እንቅስቃሴዎች መሪዎችን በእስር ቤት እያጎሩ ወይም በነፃነት እንዳይቀሳቀሱ እያደረጉ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አደረግን የሚሉ አገሮች መኖራቸው ለመግለጽ ኢትዮጵያን በዋቢነት ጠርተዋል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ የሰላምና የደህንነት ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን በሰፊው ከገለጹ በኋላ ለሰላም ሲባል ነፃነትን መንፈግ ሁለቱንም ሊያሳጣ የሚችል መሆኑም አስገንዝበዋል።
እድገትን በማፋጠን ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት አዲስ አስተሳብ ያሻል፤ ለአዲስ አስተሳሰብ ደግሞ በነፃነት ማሰብ፤ ድምፃቸው የሚሰማ ዜጎች መኖር እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል። የአፍሪቃ መሪዎች ሥልጣን ላለመልቀቅ የሚሄዱትን ርቀት በማንሳት ተሳልቀውበታል፤ ሙስናም የልማትና የመልካም አስተዳደር ፀር መሆኑን አስምረውበታል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይኸ ቀራቸው በማይባል ሁኔታ በአህጉራችን በአፍሪቃ በተለይ በኢትዮጵያ የሰፈነው ክፉ አገዛዝ መተቸታቸው፤ ይህንን እዚያው የአፍሪቃ መዲና በሆነችሁ አዲስ አበባ ተገኝተው መናገራቸው በበጎ ይመለከተዋል። እሳቸው ያነሷቸውን ቁም ነገሮችን አድምጠው ማስተካከያዎችን የሚያደርጉ ገዢዎች ኑረውን ቢሆን ኖሮ የኛ ትግል ባላስፈለገ ነበር። ችግሩ መስማት እንጂ ማዳመጥና መተግበር የማያውቁ ገዢዎች የሰፈኑብን መሆኑን ነው።
ስለሆነም፣ አርበኞች ግንቦት 7: ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪቃ ኅብረት ንግግራቸው ሀቁን አብጠርጥረው በመናገራቸው የተሰማውን አድናቆት ይገልፃል፤ በዚሁ አጋጣሚ ደግሞ በንግግራቸው ያነሷቸው ቁምነገሮችን መደመጣቸውና በተግባር መተረጎማቸውን እንዲከታተሉ አበክሮ ይጠይቃል።
የፕሬዚዳንት ኦባማ ንግግር በሀቅ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ የህወሓት ሽማምንት የተከፉ ቢሆንም የኢትዮጵያን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እውነታ የመቀየር ኃላፊነት የእኛው የኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት፤ ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለአገር አንድነት ግድ ያለን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተባብረን አገራችን ከዘረኛውና ፋሽስታዊ ህወሓት አገዛዝ ነፃ የማውጣት ተጋድሎዓችን አጠናክረን እንድንቀጥል አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment