Translate

Wednesday, August 12, 2015

የአብዮቱ አይቀሬነትና ጥቁምታዎቹ!


revolution
በፖለቲካ ሳይንስ መዝገበ ቃላት ውስጥ “አብዮት” የሚለው ቃል “አዲስ ሥርዓትን በመሻት የነባሩን መንግስታዊ ወይም ማህበራዊ ሥርአት በግዳጅ ማስወገድ” በሚል የትርጉም ማዕቀፍ ላይ ሊያርፍ ይችላል፡፡ ‹የሰው ልጅ አብልጦ የሚሻው የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት በየአገራቱ አስካልተመሰረተ ድረስ አብዮት በየትኛውም የዓለም ክፍል አይቀሬ ክስተት› እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስ መምህራኑ አብዝተው ያስተምራሉ፡፡
ሰሚ የለም እንጂ፡፡ ኢህአዴግ የሚባል ገዥ መደብ ፣ ሩብ ክፍለ ዘመን ያህል አገሪቱን እንደ “መንግስት” በመራበት ተራዛሚ የአገዛዝ ዘመኑ ከፍ ሲል ከአምሮ በላይ የሆኑ፣ ስልጣን ላይ በወጣ ስብስብ ይፈፀማሉ ተብለው የማይታሰቡ ውስብስብ የፖለቲካ ሴራዎችን በመስራት ያደረሰው ሰብአዊ ውድመት፤ ዝቅ ሲል ደግሞ ከሰውነት በታች በወረደ የዝቅተኝነት ስሜት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው የማህበረ ኢኮኖሚ ድቀት ታክሎበት በአናቱም የግንባሩ የጠቅላይ ፓርቲነት ጉዞ በአገሪቱ የፖለቲካ ተቆማት ላይ የፖለቲካ ብዝሃነትን በመቅበር የተደመደመ በመሆኑ የአገሪቱ የፖለቲካ አደባባይ አብዮት ለማስተናገድ እያሟሟቀ ያለ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል በነባራዊ ሁነት የሚገልፅ አለመሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡፡ በሰሜን ምዕራብ ተራሮች ስር እያፏጩ ያሉ የጥይት አረሮች የአብዮቱ ፊሽካ መሆናቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ከባዱ ዝምታ በግብታዊም ሆነ በፊሽካዊ ግፊት የሚያበቃበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም፡፡
አደናጋሪ እንጂ ብርቱ ተፎካካሪ ፓርቲ ማየት የማይሻው ገዢው ግንባር የመደበለ ፓርቲ ስርዓትን ግብዓተ-መሬት በ2007ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ አረጋግጧል፡፡ የምርጫ-ፖለቲካ ዳግም ላያንሰራራ ከክፉ ትዝታው ጋር ለመቀበሩ ከዚህ በላይ ማሳያ ማቅረብ የሚቻል አይመስልም፡፡ አንድ አይነት ጠቅላይ ገዢ ሀሳብ ለመጫን በሚደረገው ጥረት የአደባባይ ምክንያተኝነት እንዲፈጠር የሚተጉ የነፃዉ ፕሬስ ቤተሰቦቸ እስርና ስደት የሙያቸው እጣ ክፍል እንዲሆን ተበይኖል፡፡ ዛሬ ላይ በነፃ-ፕሬሱ ጎዳና ላይ ተንጠባጥበው የቀሩትም ቢሆን ከአንድ ምንጭ የሚቀዳውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ “የሚዲያ ህግ” አሜን ብለው የተቀበሉ ፈፃሚዎች ናቸውና በስም እንጂ በግብር ከ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ለይቶ ለማየት ይቸግራል፡፡ እስር፣ እንግልት፣ ስደት፣ ስቅየትና ሞት ከገዢው መደብ በተቃራኒ የተሰለፉ ዜጎች የሕይወት መዳረሻ ስለመሆኑ መናገር አንባቢን አለማክበር ይመስላል፡፡
ሕግ የሚሉት ነገር የጠሉትን መምቻ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ በባለ ስልጣናቱ በኩል ያልታየው መተካካት፣ ያለ ጥፋተኝነት ከነ ንፅህናቸው ወደ እስር በሚወረወሩ ወጣቶች ላይ ሲተገበር እያየን ነው፡፡ “በኢትዮጵያ ያሉ የእምነት ተቋማት የአክራሪነት እና የፅንፈኝነት መፈልፈያ ቦታ ናቸው” በሚል ሽፋን ፣ ከፖለቲካ ፍላጎት አንፃር ቤተ-እምነቶች የገዢው መደብ የፖለቲካ ማስፈፀሚያ ክንፍ ሆነዋል፡፡ በተለይም አገዛዙ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ የሚያደርገው ልኩን ያለፈ እስላም ጠል (Islamophic state) ባህሪያቶቹ በድርጊት ታጅበው ገሀድ ወጥተዋል፡፡ የሙስሊሙን ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ ያስመልሳሉ በሚል በህዝበ ሙስሊሙ የተመረጡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በካንጋሮው ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የኮሚቴው አባላት ጥፋተኛ የተባሉበት የሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ከአስራ አምስት አመት እስከ ሞት ቅጣት የያዘ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ለመጣል ለሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የፍርድ ቤቱን ተጠባባቂ የቅጣት ውሳኔ ተከትሎ የሚፈጠረው ፖለቲካዊ ግለት አገሪቱ የግፉአን ድምፅ የበረከተባት ለመሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ይሆናል፡፡ (ይህ ጦማር ከብያኔው በፊት የተጻፈ ቢሆንም ሰሞኑን እንዳየነው ህወሃት/ኢህአዴግ በመፍትሔ አፈላላጊዎቹ ላይ እስከ 22ዓመት እስራት በይኗል)
አገሪቱን በማን አለብኝነት ስሜት እየገዛ ባለው ግንባር ውስጥ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ፖለቲከኞች ጠቅላይነት፣ አዛዥ ናዛዥነት ገዝፎ ይታያል ከዚህም ባለፈ የሆላ ታሪክን መሰረት ካደረጉ ቅራኔዎች አንስቶ አሁን ያሉ የግንባሩ የውስጥ ትግል (ተመጣጣኝ ውክልና/ወንበር ጥያቄ) በፓርቲዉ ውስጥ አለመተማመን እየፈጠረ ሄዷልና ግንባሩ የፖለቲካ መናፍቃን መፈልፈያ ወደመሆን ያዘመመ ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ መረጃዎችን በየጊዜው የሚያቀብሉ የውስጥ አርበኞች ከወደ ገዢው ግንባር የመኖራቸው ሚስጢር ይህን ተከትሎ የመጣ ሳይሆን አይቀርም፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ቋንቋ ተናጋሪነትን መሰረት ያደረጉ የገቢ ኢ-እኩልነቶቸ መታየት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም በከተሞች አካባቢ የብሔር መልክ ያለው የገቢ ኢ-እኩልነት በገሀድ መታየት ጀምሯል፡፡ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ድረስ ባለው መንግስታዊ መዋቅር እየታየ ያለው አስደንጋጭ ሙስና፣ ዜጎች በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጡ እያደረጋቸው መጥቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ በከተሞች ላይ የሚስተዋሉ የማህበረ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ህዝባዊ ምሬትን እየፈጠሩ ያሉበት ሁኔታ በመኖሩ እነኚህ ምሬቶች በአንድ ላይ ተደምረው ግብታዊ አብዮት መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ የፖለቲካ ተሀድሶ ለማድረግ ያልታደለው ህወሓት መራሹ ግንባር ከዕለት ዕለት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ለአብዮታዊ ሁኔታዎች ማገዶ ሲሆኑ እያስተዋልን ነው፡፡ የ1966ቱን አብዮት በቆሰቆሱት የጊዜው ዘመነኛ ወጣቶች እንደተባለው “ጊዜው እየነጎደ ሲሄድ፣ ለህመሙ የሚታዘዘው ክኒን ምሬትም እየጨመረ መጣ” ሆኗል ነገሩ ፡፡
እያወራን ያለነው ስለ አይቀሬው የኢትዮጵያ አብዮት ነውና ተጠባቂው አብዮት ‹ምን አይነት አብዮት?› ይሆን የሚለውን ገዢ ሀሳብ በአደባባይ ከሚታዩ ብሶቶች ጋር አስተሳስሮ መስመር ማስያዙ ይጠቅማል፡፡ አብዮትን በተመለከተ ከዘመን ዘመን (ለአብነት፡- ከእንስቷ ምሁር ቴዳ ስኮፓል እስከ ጃክ ጎልድስቶን ድረስ) በተለያዩ መምህራን በጽንስ ሐሳብና በዓይነት ደረጃ የተለያዩ ትርጓሜ ተሰጥቷታል፡፡ በፅሁፉ መግቢያ ላይ የተመለከተውን አጠቃላይ የአብዮት ትርጉም ተንተርሰን፣ የመምህራኑን አንደበት ተውሰን የአብዮት አይነቶችን በአራት ምድብ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ መንግስታዊ ተቋማትን በመቀየር ላይ ብቻ የሚያተኩረው አብዮት “ፖለቲካዊ አብዮት” ሲባል፣ በተወሰኑ ልሂቃን ትግልና መሪነት ብቻ ተቀነባብረው ለለውጥ የሚተጉት “የልሂቃን” አብዮት ይባላል፣ በታችኛው የህብረተሰብ ክፍል በሚቀጣጠለው አመጽ የሚፈጠረውን አብዮት “ህዝባዊ አብዮት” ሲሉት፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ስርዓትን የሚቀይሩ አብዮቶችን ደግሞ “ብሉይ አብዮት” በማለት ይጠሯቸዋል፡፡
እርግጥ ነው የአብዮቱ ባቡር ላይ ለመሳፍር እያኮበኮብን ነው እንጂ አልተሳፈርንም፡፡ አንድን አብዮት ‹እንዲህ ነው!› ብሎ ለመበየን ከሂደቱ እስከ ውጤቱ ድረስ ያለዉን ሁኔታ በውል ማጤን ያስፈልጋል፡፡ እንደውም አንዳንድ አብዮቶችን በአይነት ደረጃ ለመፈረጅ አብዮቱ የተመራበትን መንገድና ያስከተለውን ውጤት (የለውጥ ደረጃ) በጊዜ ሂደት ምንአልባትም በአመታት ደረጃ መመዘንና መገምገም አስፈላጊ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያችን አሁን ላይ ካለችበት የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ውጥንቅጦች አኳያ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ መፈጠር እንዳለበት ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ እናም አብዮቱ በሀገሪቱ ውስጥ የችግሩ ግፈት ቀማሽ የሆነውን የታችኛው ህብረተሰብ ክፍል እና ንኡስ ከበርቴውን ባሳተፈ መልኩ በለውጥ በሚያምኑ ልሂቃኖች የሚመራ ቢሆን በውስን መስዋዕትነት ሕዝባዊ ድል መቀዳጀት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አብዮቱ ከቡድን ጥቅም በተሻገረ መልኩ ለህዝባዊ ጥቅም በቆሙ ልህቃን እስከተመራ ድረስ ስኬታማ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡ እርግጥ ነው አቢዮት ደራሽ ማዕበል ነው፡፡ ግና፤ አብዮቱን በህዝባዊ ፍላጎት ማነፅ ከተቻለ የደራሽነቱ ማዕበል ጉዳት ለገዢው መደብ እንጂ ለለውጥ ፈላጊው አደጋ የመሆን እድሉ ጠባብ ነው፡፡ ቁምነገሩ የአብዮቱ መሰረታዊ ጥያቄ ህዝባዊነት መላበሱ ላይ ነው፡፡eth demo
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔት አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥርዓተ ለውጥ ፈላጊ ነው፡፡ የለውጥ ፈላጊው አይነት በእድሜ በፆታ፣ በሙያ፣ በብሔር፣ የሚከፈልም አይደለም፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ በሀገሪቱ የፖለቲካ አደባባይ ላይ የሚታዩ የአፋኝነት ድርጊቶችን ተከትሎ ኢሕአዴግ በሰላማዊ ትግል መቃብር ላይ ለመቆሙ ማሳያ ሆነዋልና በሰላማዊ ትግል በተለይም በምርጫ ፖለቲካ የሚያምኑ አካላት ከአርባ አመት በፊት የአገሪቱን የፖለቲካ መንገድ የቀየረውን አማራጭ የትግል ስልት ማሰላሰል ጀምረዋል፡፡ እናም ገዢውን መደብ ከስልጣን ለማውረድ ብቸኛው አማራጭ አብዮትና አብዮት ብቻ ነው፡፡
ከሰሜን ምዕራብ ተራሮቸ ስር እስከ መሀል አገር ድረስ ባሉ ቦታዎች በግልጽም ሆነ በህቡዕ እየታዩ ያሉ አብዮታዊ ሁኔታዎች የማይቀረውን ለውጥ አመላካች ሆነዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ሶስተኛው የኢትዮጵያ አብዮት ከዚህ እንደሚከተለው በቀረቡ ሁለት የቢሆን እድሎች በአንዱ ይፈጠራል የሚለው ትንበያ የዚህ ፁሁፍ አቅራቢ እምነት ነው፡፡
የቢሆን እድል አንድ፡- ግብታዊ አብዮት
ከአለም የአብዮቶች ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ግብታዊ አብዮቶች መነሻ ቦታቸዉ የከተማ ብሶትን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ ከሩቁ የፈረንሳይ አብዮት እስከ ቅርቡ የአረብ አገራት ‹የፀደይ አብዮት› ድረስ ያሉ አብዮቶች የከተማ ብሶትን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ግብታዊ አብዮት የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት አለያም የምርጫ ቅስቀሳን ተገን አድርጎ የሚቀጣጠል የአደባባይ አመፅ አይደለም፤ ይልቁንስ የማህበረ-ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለአብነት፡- መቆሚያ ያጣውን የኑሮ ውድነት የውሃና፣ የመብራት እጦት፣ የትራንስፖርት ችግር፣ ስራ አጥነት፣ የእምነት ነፃነት እጦት፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና በመሰል ተያያዥ ጉዳዮች በተወጠረ ህዝብ መሀከል፣ በአንድ አጋጣሚ ውስን ዋጋ በሚሰጠው የወዲያው ገፊ ምክንያት (Immediate Cause) የተነሳ ህዝቡ ያለ አንዳች ቀስቃሽ ሥርዓቱን ለመጣል ወደ አደባባይ ፈንቅሎ ለመውጣት በቂ ምክንያት ሆኖ የሚቀርብ ነው፡፡
ለአብነት፡- የአረብ አገራት የፀደይ አብዮት መነሻ የሆነችው ቱኒዚያ፣ በቤን አሊ ፍዝ የተራዘመ የአገዛዝ ዘመናት የተከማቹ የማህበረ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች በተለይም የወጣቶች ሥራ አጥነትና የገቢ ኢ-እኩልነቶች፣ የሙሐመድ ቦአዚዝ ምሬት አዘል ሞት የወዲያው ገፊ ምክንያት በመሆን ‹የጃስሚን አብዮት› የተባለለትን ሕዝባዊ ማዕበል እንደቀሰቀሰ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ የቱኒዚያን ተሞክሮ ወደ ሀገረ-ኢትዮጵያ ስናመጣው በጊዜ ሂደት ወደ ዝግ አምባገነንነት እያዘገመ ባለው አገዛዝ የፖሊሲ ክሸፈት የተነሳ የአገሪቱ የማህበረ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች እየተባባሱ በመሄዳቸው በቀጣይ ጊዜያት በሚፈጠር አንዳች ክስተት፣ የወዲያውኑ አነሳሽ ጉዳዮች (ስር የሰደዱ የማህበረ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች) ታክለውበት የሥርዓት ለውጥ እንዲፈጠር የሚያስገድድ ሕዝባዊ ማዕበል የሚፈጠርበት bouaziziሁኔታ ይኖራል፡፡ በአዙሪት ከታጀበው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ካለፈ ስህተት መማር የተለመደ አይደለም፡፡ ይህ እንደ ፖለቲካዊ ባህል እየታየ ካለ አዙሪታዊ ስህተት መውጣት ግብዓዊውን አብዮት መስመር ለማስያዝ ይበጃል፡፡ ከቀደመው ታሪክ እንደምንረዳው በ1966ቱ ያልተጠበቀ አብዮት ውስጥ የሂደቱ አወዛጋቢ ኃይል ሆኖ የወጣው “የምርጥ መኮንኖች” ስብሰብ ደርግ በውስጣዊና ውጫዊ ግፊቶች ታጅቦ አብዮቱን የጠለፈበትን አጋጣሚ እንዲሁም ከክስተቱ በኋላ እንደ አገር አገሪቱ የተጓዘችበትን የጥፋት መንገድ በማስታወስ ቀጣዩ የከተማ አብዮት በአንዳች ዘመን የደገፈው የፖለቲካ ቡድንም ሆነ ባለ ብረት መዳፍ አካል ተጠባቂው አብዮት እንዳይጠለፍ በለውጡ አስፈላጊነትና በአብዮቱ የትኩረት አቅጣጫዎች (ሕዝባዊ መሰረትነት) ተቀራራቢ ምልከታ መያዝ ከአዙሪቱ ለመውጣት ተኪ የሌለው መንገድ ነው፡፡ ተቀራራቢ ምልከታ ሲባል፡- ህዝባዊ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ የለውጥ ጥያቄዎችን ማስፈፀም በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ በተለይም የአብዮቱ ግብ በሚበይኑ አካሄዶች ላይ ሕዝቡንና ሕዝቡን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝ ለማለት ያህል እንደሆነ ልብ ይባል፡፡ ግብታዊ አብዮት ሰኞና ማክሰኞ ይመጣል ተብሎ ቀን አይቆረጥለትም፡፡ ግና፣ ”አይመጣምን ትተሸ ይመጣልን አስቢ” ነውና ነገሩ በአይቀሬው አብዮት መዳረሻ ግቦች ላይ የወል ተቀራራቢ ምናባዊ – ስዕል መያዙ ይበጃል፡፡
የቢሆን እድል ሁለት፡- ሁለገብ የትጥቅ ትግል እንደ አብዮቱ ካፒቴን
በብዙዎቹ የኢትዮጵያ ነገረ-ፖለቲካ ተከታታዮች ስጋትና ተስፋ አዘል አስተያየቶች እየተሰጠበት ያለው “የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ” አይቀሬውን የኢትዮጵያን አብዮት ከሚቆሰቁሱትና ከሚያቀጣጥሉት ብረት አንጋች ኃይሎች ውስጥ ከፊት መስመር መሰለፍ የሚቸል የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ በተለይም በምርጫ ፖለቲካ ክሽፈት በተቆጡት የቀድሞ የቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥቂት አመራሮች የተመሰረተው “ግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል” ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በኤርትራ በረሃዎችና በሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ግዛቶች እየተንቀሳቀሱ በደፈጣ ውጊያዎች የአገዛዙ ራስ ምታት ከሆኑት “አርበኞች ግንባር” ጋር ወታደራዊና አጠቃላይ ድርጅታዊ ውህደት ከፈጠረ በኋላ በተከተላቸዉ የፕሮፖጋንዳና የውስጥ አርበኞች ማፍራት ዘመቻ የለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ለመሳብ በቅቷል፡፡ በተለይም የወጣቱን፤ በፕ/ር መሳይ ከበደ አገላለፅ እንደ አንድ የትግል ሜዳ እያገለገለ ባለው ኢሳት የዜናና የልዩ ፕሮግራም ዘገባ ሽፋን እንዲሁም በድርጅቱ የውስጥ አርበኞች አነሳሽነትና መንገድ ጠራጊነት ወጣቶች ትግሉን መቀላቀል መጀመራቸው የድርጅቱን ትኩረት ሳቢነት የሚጠቁም አስረጅ ምሳሌ ነው፡፡ ምንም እንኳ በሦስተኛ ወገን መተማመኛ ባይሰጥባቸውም በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ግዛቶች ላይ የደፈጣ ውጊያዎች መጀመራቸው፤ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች የህይወት መስዋዕትነትን በሚጠይቀው የትግሉ ቦታ መገኘታቸውና መሰል ተያያዥ ክስተቶች እየታዩ መሆኑ አይቀሬውን የኢትዮጵያ አብዮት የሚያቀርበው ይሆናል፡፡ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት የመሪዎችን የኋላ ታሪክ፣ የትግል g-7ስትራቴጂ እና የድጋፍ መሰረቶችን ከወቅታዊው ሕዝባዊ ብሶት ጋር ያገናዘቡ ፀሐፍቶች እንደሚጠቅሱት፣ ከሌሎች ብረት ያነሱ ኃይሎች በተሻለ መልኩ አገዛዙን የመነቅነቅ እድል እንዳለው ይጠቅሳሉ፡፡ ከገዥው ግንባር አባል ፓርቲዎች መካከል በአንዳንዶቹ ውስጥ (ቀዳሚ ተጠርጣሪ የብአዴን መካከለኛ አመራሮች ናቸው) የኃይል መሠረቱን እንዳደላደለ፣ ከአገዛዙ ወታደራዊ ክንፍ ውስጥም መረጃ አቀባይ የውስጥ አርበኞችን እንዳደራጀ የሚነገርለት ድርጅት መሆኑ፤ አብዮቱን በመቆስቆስና በማቀጣጠል ረገድ የፊት መስመር ተሰላፊ ያደርገዋል፡፡
የድርጅቱ የፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ አመራሮች ‹ነፃ መሬት እየያዙ የትጥቅ ትግሉን ወደፊት ማራመድ› በሚለው የጦርነት ስልት የማያምኑ መሆናቸው የበዛ መስዋዕትነትን ለመቀነስ አይነተኛ እድል ይኖረዋል፡፡ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ግለትና የአለም ተጨባጭ ሁኔታ መደበኛ ጦርነት ለማድረግ የማያመች ከመሆኑ አኳያ እንዲሁም የወታደራዊ አቅም አለመመጣጠን ታክሎበት ትግሉ በአብዮት ቆስቋሽነትና አቀጣጣይነት ቢያተኩር የተሻለ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ላይ በተለይም በሕወሓቱ “ኢፈርት” እና በብአዴኑ “ጥረት” ስር ያሉ ድርጅቶችን፣ መስሪያ ቤቶችን እንዲሁም ተሸከራካሪዎችን በመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ አፈራራሽ/አውዳሚ የመሳሪያ ጥቃቶችን በማድረግ ከዚህም ባለፈ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ባለስልጣናት ላይ ግድያ በመፈጸም የገዥውን መደብ የሥልጣን መሰረት ለማናጋት የሚያስችሉ ታክቲካል የትግል ስታራቴጂዎችን ወደ መሬት በማውረድ የከተማ ነዋሪዎችን ድንገታዊ የአደባባይ አመፅ የማድረግ ድፍረት የሚሰጥበት ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ፣ ለጊዜው በሰሜን ምዕራብ ተራሮች ስር የሚሰሙ የጥይት ጩኽቶች ለመኅሩ ጊዜ መቃረቢያነት የደወል ድምፆች ናቸው፡፡
እንደ መውጫ
በእስካሁኑ አዝጋሚ የሰላማዊ ትግል ጉዟችን ለውጥ መምጣት አለበት የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ቢሆንም “እንዴት ሊመጣ ይችላል?” በሚለው ዙሪያ ግን የልዩነት ሀሳቦች ይስተዋሉ ነበር፡፡ አሁን ለምርጫ ፖለቲካ ክሽፈት ከበቂ በላይ ማሳያ የተገኘ በመሆኑ ‹ኢሕአዴግ በአምስት አመት አንዴ በሚደረግ ምርጫ ከስልጣን ሊወርድ ይችላል ወይስ አይችልም?” የሚሉ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ዳግም ላይመለሱ ተሰናብተዋል፡፡ ከእንግዲህ ምርጫው እንድና አንድ ነው ሕዝባዊ መሠረት ያለው አብዮት በኢትዮጵያ ምድር ማቀጣጠል፡፡ የአብዮቱ ግብ በዴሞክራሲያዊ እኩልነት የተገነባች፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት፣ የባህል እኩልነት የሚንፀባረቅባት የጋራ ኢትዮጵያን በመገንባት ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡ በስካሁኑ የአዙሪት ጉዟችን ስልጣን የህዝብ የሆነበት አጋጣሚ አልታየም፡፡ ሦስተኛው የኢትዮጵያ አብዮት ለዚህ ምላሽ ሊኖረው ይገባል፡፡ መንግስት እንጂ ህዝብ ሲፈራና ሲከበር የታየበት የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር አልተቻለም፡፡ ለዚህኛውም ቢሆን ሦስተኛው የኢትዮጵያ አብዮት ምላሽ ሊኖረው ይገባል፡፡ ቋንቋ ከመግባቢያነቱ ባለፈ ለማስፈራሪያነት ሲያገለግል ለመቆየቱ ያለፉት ሁለት አስርታት ጉዟችን ቋሚ ምስክር ናቸዉ፤ ለአብዮቱ ጥብቅና እስከ ቆምን ድረስ ቋንቋ ከማስፈራሪያነት ወደ መግባቢያነት እንዲመለስ ማድረግ ይቸላል፤ ህዝብ በ“እኔ አውቅልሀለሁ” ባይ ፖለቲከኛ ሳይሆን በወደደውና በፈቀደው የሕዝብ አስተዳደርና መዋቅር እንዲመራ የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር የአብዮቱ ወሳኝ ግብ ሊሆን ይገባል፡፡
ገብረ ፃድቅም ሆነ ኤጀታ ነገራ፣ ራም ኬሎም ሆነ ደመላሽ ፈጢማም ሆነች ወለተ ስላሴ፣ ሼህ ኑሩም ሆነ ቄስ ሞገሴ፣ ፓስተር ጋዲሳም ሆነ ነብይ ደንድር ኢትዮጵያዊ እስከሆኑ ድረስ እንደ ዜጋ በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ እኩል የመወሰን እድል ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የአንዱ ብሔር ቅን አሳቢ የሌላው ደግሞ ልዩ ተጠርጣሪ፣ የአንዱ ሐይማኖት አሸባሪ የሌላው ተሸባሪ ተደርጎ የሚወሰድበት ሥርዓት ሊወገድ ይገባል፡፡ ሶስተኛው የኢትዮጵያ አብዮት ከፖለቲካ ነፃነት እስከ ተመጣጣኝ የፖለቲካ ስልጣን ውክልና ድረስ ያሉ ፖለቲካዊ መደላደሎችን መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡ እናም የትናንቱ ትውልድ “ይህ ትውልድ በባርነት ከሚኖር በደም ያልፋል” በሚል ዘውዳዊውን ስርዓት እንደገረሰሰው፣ አምባ-ገነኑን የደርግ ሥርዓት እንደተፋለመው ሁሉ ይህኛው ትውልድም ሕግንና ፍርድን በእጁ በመጨበጥ፤ ራሱን ከመንግስትነት ወደ ቋሚ ሽፍታነት የቀየረውን የገዥ መደብ ስብስብ በማፈራረስ ኢትዮጵያን እንደ አገር መታደግ ይኖርበታል፡፡
በደማችን ታሪካችን በደማቁ ይፃፋል!
በደማችን አገራዊ ህልውናችን ይፀናል!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
(በላሎ ሰአረ ተጽፎ በተለይ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የተላከ)

No comments:

Post a Comment