Translate

Wednesday, August 12, 2015

ለኢትዮጵያዊውስ ማን አለው?

በያሬድ ታዬ መኮንን፤ ቶሮንቶ
ቶሮንቶ ከመጣሁ ሶስተኛ ሳምንቴን ያዝኩኝ፡፡ ቀኑን ሙሉ፤ ከሰሜን ደቡብ፤ ከምስራቅ ምእራብ ሳካልለው ውዬ፤ መጀመሪያ በጓደኛዬ ቤት፤ አሁን ደግሞ መንግስት በሰጠኝ፤ በቶሮንቶ፤ ኦንቴርዮ ጎዳና ላይ በሚገኘውና እኔና ሌላ አንድ ሰው በምንጋራው ክፍል ጣሪያ ስር ሆኜ፤ ወደጣሪያው አንጋጥጬ፤ የኢትዮጵያና የካናዳ ህይወቴን፤ እንዲሁም ነጻነቴን ማሰላሰል ይዣለሁ፡፡ ነጻነት እንዴት ይጥማል፡፡ ድህነት አንድ ነገር ነው፡፡ መራብም አንድ ነገር ነው፡፡ ሰው ግን ነጻነቱንና ክብሩን እንዴት ባገሩ ይነፈጋል፡፡ እነሆ በማያውቁን፤ በማላውቃቸው፤ በሰው አገር የተሰጠኝን ክብርና እንክብካቤ እያጣጣምኩ ሳለሁ፤ የሩቅ ጓደኛዬ የነገረኝ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡ ይህ የሩቅ ጓደኛዬ አውነተኛ ታሪክ ነው ብሎ ያጫወተኝን፤ እኔም የተቀበልኩትን ገጠመኝ ላጫውታችሁ፡፡
እውነት መሆኑን እንዴት ተቀበልከው፤ ያላችሁኝ እንደሆነ ኢትዮጵያ ሃገሬ ውስጥ እንኳን ይሄ ይቅርና፤ ወያኔ “ተቃዋሚዎችም መርጠውኛል” ብሎን ተቀብለነው የለም እንዴ? መቼ ነው ያለው፤ ለምትሉኝ ደግሞ አሁን ባሳለፍነው ምርጫ 2007፤ በአይኔ ያየሁት፤ ምናልባትም ብዙዎቻችሁ በሶሻል ሜዲያ ያነበባችሁ፤ እና ያሰገረማችሁ የምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው፤ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች፤ ከ1000 መራጮች መካከል ኢህአዴግ፤ 1000 ከ1000 ተብሎ በምርጫው ጣቢያ ሲለጠፍ፤ አስቡት እንግዲህ፤ ይህ 1000 መራጭ የተቃዋሚ ተመራጭ ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ መሆኑን፡፡ እንግዲህ ይህንንም አምነን “አሜን” ብለን ተቀብለን የለም ወይ? እንግዲህ የጓደኛዬንም የህይወት ገጠመኝ አምኜዋለሁ፡፡

የወያኔን ጉድ እስቲ ይሁን ብለን እንለፈውና ወደዋናው ታሪክ እንመለስ፡፡ በነገራችን ላይ ስም መጥቀስ ስላላስፈለገኝ፤ ጓደኛዬ እያልኩ በመተረኬ፤ ቅር አይበላችሁ፡፡ ያው እንደምታውቁት ጊዜው አስቸጋሪ ስለሆነ ስም ባይጠቀስ ይሻላል ብዬ ነው፡፡
ይህ ጓደኛዬ እና አንድ የስራ ባልደረባው ከስራ በኋላ መሸትሸት ሲል ለመዝናናት፤ 22 አካባቢ ወደሚገኙት የመዝናኛ ቤቶች ጎራ ይላሉ፡፡ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላኛው በመቀያየር ሲዝናኑ ይቆዩና፤ አትላስ አካባቢ ወደሚገኝ አንድ ታዋቂ የጭፈራ ቤት (በተለምዶ ክለብ) ይገባሉ፡፡ በክለቡ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች የነበሩ ሲሆን፤ ከእነዚህም መሀከል ከወደምስራቅ አካባቢ የመጡም (በግምት ቻይናውያን ይመስሉታል) ነበሩበት፡፡ ሙዚቃው ቀጠለ፤ ጨዋታውም ደራ፡፡ መቼስ በዳንስ ውዝዋዜ መሀል መነካካት አይጠፋም፤ የጓደኛዬ ጓደኛ ከአንዱ ቻይናዊ ጋር ይነካካል፡፡ ከዚያም ይቅርታ ጠይቆ ጨዋታውን ይቀጥላል፡፡ ቻይናዊው ጉዳዩን በቀላሉ አልተመለከተውም፡፡ “ሳታውቅ ሳይሆን እንደው ነገር ስትፈልገኝ ነው” በማለት እምቧ ከረዮውን አቀለጠው፡፡ ሰዎች ነገሩን ለማረጋጋት ቢሞክሩም፤ አጅሬ ቻይና ካልደበደብኩት ብሎ ሰፈሩን ቀውጢ አደረገው፡፡ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ መሆን በጀመረበት ሰዓት፤ የሀገሬው ፈላጭ ቆራጭ፣ ምንም ቢያደርግ ጠያቂ የሌለው፣ ማሰር፣ መደብደብ ካሻውም መግደል መብት የተሰጠው፤ መቼስ ታውቁታላችሁ ስለማን እያወራሁ እንዳለ፤ የወያኔ አካል የሆነው፡ ፈደራል ፖሊስ መጣ፡፡ ግርግሩም ቀዝቀዝ እያለ ሁሉም በመረጋጋት ስሜት ባሉበት ሁኔታ፤ ቻይናዊው ፌዴራሉን ሲመለከት የልብልብ ተሰምቶት ኖሮ፤ እጁን ሰንዝሮ የጓደኛዬን ጓደኛ በቡጢ ቢለውስ፡፡ ያኛውስ ከማን አንሶ በእጁ በሶ አልጨበጠ መልሶ ቢቦቅሰውስ፡፡ ታዲያ ይኽኔ ነበር ግራ የሚያጋባውና ማንነትን የሚፈታተነው ጉዳይ የተከሰተው፡፡
እንዲህ ነው የሆነው፡፡ ከፌዴራል ፖሊሶቹ መሀከል ሁለቱ ተንደርድረው መሃል በመግባት አንደኛው ቻይናዊውን ወደ ጎን ሲያደርገው፤ ሌላኛው የጓደኛዬን ጓደኛ በዚያ በያዘው የሚያቃጥል ቆመጥ (መቼስ የቀመሰ ያውቃታል) ሲዠልጠው ለተመለከተ ማንኛውም ሰው፤ እጅግ በጣም አስገራሚና አሳዛኝ ነበር፡፡ ቻይናዊውም ለካስ ይኼን አውቆ ኖሯል እንደዛ የልብልብ ተሰምቶት ቦክስ የሰነዘረው፡፡ ለጓደኛዬ ጉዳዩን ዝም ብሎ መመልከት አልሆንለት ቢለው፤ ጠጋ ብሎ በልመና መልክ ለማግባባት እየሞከረ፤ “ኽረ እባካችሁ ተውት እሱ ምንም አላጠፋም” በማለት ለማስረዳት ቢሞክር፤ አንተስ የት ይቀርልሃል ብለው ያላንዳች ማመንታት የዚያች ቆመጥ ተቋዳሽ በማድረግ፤ ሦስት አራት ጊዜ ካቀመሱት በኋላ፤ ቻይናዊውን በክብር ከይቅርታ ጋር ወደ ውስጥ እንዲገባ በምልክት (ያው እንደምታውቁት ቋንቋ ችግር ነው) ይነግሩት እና ጓደኛዬን እና ጓደኛውን በያዙት ፒክ አፕ መኪና ጭነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ፡፡
ለመዝናናት የወጡት እኚህ ኢትዮጵያውያን፤ በገዛ ሀገራቸው ክብር ተነግፏቸው፤ ለውጭ ዜጋ ጎንበስ ቀና ባለማለታቸው የመዝናኛ ጊዜያቸውን በፖሊስ ጣቢያ አሳልፈው፤ እንዲህ አይነት ነገር እንዳይለመዳቸው ከማስጠንቀቂያ ጋር በበነጋታው መለቀቃቸውን የነገረኝ፤ እጅግ በንዴት እና በቁጭት መንፈስ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ክስተቶች በተለያየ መንገድ ያጋጠመን ሰዎች እንኖር ይሆናል፡፡ ያላጋጠማችሁም ወደፊት ቢያጋጥማችሁ ግር አይበላችሁ፡፡ እንደው ነገርን ነገር አነሳውና ነው እንጅ፤ ከዚህም የባሰ ብዙ አይተናል ሰምተናል፡፡
ሁሌም ውስጤን የሚያንገበግበው ነገር ቢኖር፤ ቢያንስ ለሌሎች ዜጎች ሀገራችን ላይ የሚሰጣቸውን ክብር ያክል እንኳን ሰው በሀገሩ የማይሰጠው ከሆነ ለኢትዮጵያዊውስ ማን አለው? ማንስ አለሁልክ፤ አይዞህ ይለዋል?
ሁሉም ነገር ከራስ ነው የሚጀምረው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፍቅርም ቢሆን፣ አክብሮትም ቢሆን ለራስ ሰጥቶ ነው ወደሌላኛው የሚኬደው፡፡ እራሱን እና የራሱ የሆነውን የማያከብር፤ ሌላውን አከብራለሁ እጠብቃለሁ ቢል፤ ለእኔ እንደማስመሰል ነው የምቆጥረው፡፡ እዚህ ላይ የሌላ ሀገር ዜጎች አይከበሩ እያልኩኝ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሰው ከሀገሩ የበለጠ ጥበቃ እና ከለላ ሊያገኝ የሚችልበት የተሻለ ቦታ የት ነው ያለው? ያደጉት እና እኛን ጥለው የሄዱት ሀገራት ከሀገራቸው አልፈው በሰው ሀገር ስለሚገኙት እያንዳንዱ ዜጎቻቸው ክትትል በማድረግ፤ ያሉበትን ሁኔታ ሰላማዊነት ሲያረጋግጡ የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገራችን ውስጥ ግን ለሚከሰተው ማንኛውም ጉዳይ የዜጎቹን መብት ሊያስከበር የሚችል ስራ የመስራት ግዴታ የመንግስት አንዱ ሃላፊነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሰው ሀገር አለኝ ብሎ በሀገሩ ሰርቶ እና ተለውጦ፣ የዘር፣ የጎሳ፣ እንዲሁም የቀለም ልዩነት ሳይገጥመው መኖር ካልቻለ፤ ከመሰደድ ውጭ ምን አማራጭ ይኖረዋል? አስቡት እስቲ በሀገሩ ክብር ተነፍጎት በሰው ሀገር ተከብሮ የሚኖረውን ስትመለከቱ ምን ይሰማችኋል? እንደው ወያኔ የሀገር ትርጉም አልገባውም እንጂ ቢገባው ኖሮ ይሄንን ግጥም ያዜምልን ነበር፡-
ሀገርን ሀገር ያሰኘው
ሰው የተባለው ፍጡር ነው!
ያሬድ ታዬ መኮንን፡ ሀምሌ/ነሀሴ፤ 2015፡ ቶሮንቶ

No comments:

Post a Comment