Translate

Wednesday, August 5, 2015

በሳውዲ “ድምጻችን ይሰማ” ላይ የተቃጣው ሴራ ከሸፈ


riyadh KSA

ሳውዲ ኢትዮጵያውያን ሙስሊም የትግል አንድነት ላይ የተቃጣው የህወሃት/ኢህአዴግ ሴራ መክሸፉ ተሰማ! ከዕርዳታ አሰባሰብ ጋርም በተያያዘ የተፈጸመው ተግባር ለሕዝብ ይፋ ሆኗል፡፡

የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎች መቀመጫቸውን ሳውዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ ካደረጉ ወዲህ የህዝበ ሙስሊም እንቅስቃሴ ለማፈን የተለያዩ ስልቶችን ነድፈው ከአካባቢው የመንግስት ሹማምንቶች  ጋር ሲንቀሳቀሱ እንደ ነበር ይታወቃል። እነዚህ ምስለኔዎች ለአገዛዙ ባላቸው ታማኝነት ከጅዳ እስከ ሪያድ  በዘለቀ የስለላ መረባቸው በሳውዲ “ድምጻችን ይሰማ የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” በሚያደርገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፉ ሙስሊም ወገኖቻቸውን ስም ዝርዝር ለኢህአዴግ በማቅረብ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ግፊት ሲያደርጉ የነበረ ከነፍሳቸው ይልቅ ለጥቅም ያደሩ መሆናቸውን አያሌ የእምነቱ ተከታዮች ይገልጻሉ፡፡
በተለይ እነዚህ ተላላኪዎች ባላቸው መጠነኛ ሃይማኖታዊ እውቀት ጥቂት የእምነቱን ተከታይ የሆኑ ወንድምና እህቶቻቸውን በማሳሳት ለዚሁ መንግስታዊ ሴራ ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ግብዓት አድገዋቸዋል፡፡ ከህወሃት/ኢህአዴግ ስርዓት በሚወርድላቸው በጀት ጡንቻቸው ከግዜ ወደ ግዜ እየፈረጠመ የመጣው ምስለኔዎች የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት በመበታተን በሳውዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ትግል አንድነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር መቻላቸው በጌቶቻቸው ዘንድ ምስጋና ሲቸራቸው በአንጻሩ በህዝብ እየተተፉ የመምጣታቸው ምስጢር የነዚህ ተላላኪዎች ማንነት እርቃኑን አስቀርቶታል።
በተለይ እነዚህ ወገኖች  በኃይማኖት ሽፋን ዘረፋ ላይ መሰማራታቸውን የሚገልጹ ምንጮች ጅድና ሪያድ ጨምሮ በተለያዩ የሳውዲ ግዛቶች ውስጥ “ጽናት” ብለው ባደራጁት ስብስብ በመታገዝ የአባላት መዋጮ፤ ልዩ መዋጮ፤ ለታሰሩ የትግል አጋሮቻችን ቤተሰብ ድጎማ ወዘተ በሚል ምክንያት እስከ 300.000 ሪያል ወይም ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ያለደረሰኝ ከህዝበ ሙስሊሙ ኪስ በመሰብሰብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በግፈኞች ወህኒ እየማቀቁ የሚገኙ  ዑስቷዝ ያሲን ኑር ዒሳ፤ አህመዲን ጀበል በቅርቡ ከወህኒ ቤት “ፈርዖን የአምባገነኖች ተምሳሌት፤ የህይወት ግብህን ቅረጽ” በሚል ርዕስ የጻፉትን ጽሁፍ ዘርፈው በማሳተም ከመጽሀፉ ሽያጭ የተገኘውን በሚሊዮን የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸውና ለዚሁ ኢህአዴጋዊ ድብቅ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ማዋላቸው በአብዛኛው ሙስሊም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ቁጣን አስነስቷል።
ከዚህ ባሻገር ይህ በኃይማኖት ሽፋን ዜጎቻችን ላይየሚፈጸመው ምዝበራ በተለይ ሳውዲ በሚኖሩ ሙስሊም ሴት እህቶቻችን ላይ ያነጣጠር መሆኑን የሚናገሩ ምንጮች ለዚህ ተግባር ማስፈጸሚያ ጅዳ፤ ጣይፍ እና መካ ከተሞች ውስጥ እስከ 150 የሚሆኑ የተለያዩ  የዎትሳፕ “whatsApp” ግሩፕ እንዳሏቸውና እያንዳንዱ ቡድን ወርሃዊ  መዋጮ የሚከፍሉ ከ50 በላይ ሴት እህቶቻችንን በአባልነት ማቀፉን ያስረዳሉ። ይህ እራሱን “ጽናት” እያለ የሚጠራው የካድሬዎች ስብስብ ሪያድ ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ከ70 በላይ የዎትሳፕ “whatsApp” ግሩፕ እንዳሉት ቢነገርም ሪያድ የሚገኙት “የጽናት” ኃላፊዎች  ከእህቶቻችን ቦርሳ  ህገወጥ በሆነ መንገድ ለወራት ሲሰበስቡ የከረሙትን  ከ80.000 ሺህ ሪያል አሊያም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ ጅዳ ለሚገኙት የአገዛዙ ታማኞች ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በተፈጠረ አለመግባባት በተከሰተ ግጭት እስካሁን  ከሁለቱም ወገን የተጎዳ ባይኖርም የህወሃት/ኢህአዴግ ስርአት ስውር ደባ መክሸፉን የሚናገሩ ምንጮች  በሳውዲ አረቢያ “ድምጻችን ይሰማ” የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ መሰንበቱን አልሸሸጉም።
ይህን ተከትሎ በሙስሊሙ የትግል አንድነት ላይ የተቃጣውን ስውር ደባ ሕዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን ጠብቆ ህወሃት/ኢህአዴግ ላይ የጀመረውን ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ  አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሰሞኑን በሳውዲ አረቢያ “ድምጻችን ይሰማ” ሪያድ ከተማ ላይ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ማካሄዱን ፍትሕ ራዲዮ ካሰራጨው ዘገባ መረዳት ተችሏል። በዚህ ዙሪያ ጅዳ የሚገኘውን “የጽናት” ሃላፊ ሼክ መሃመድ ዘይን ዘህረዲን የዝግጅት ክፍላችን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም። (ለጎልጉል፡- ኢንጅነር መሃመድ አባስ ሪያድ)

No comments:

Post a Comment