Translate

Tuesday, August 4, 2015

ቴድሮስ አድሃኖም “ኢህአዴግ ቂመኛ አይደለም” አሉ

አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ በቂም ስለሚፈጸው ወንጀል አልተጠየቁም

tedros a voa


የኢህአዴግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም “ኢህአዴግ ቂመኛ አይደለም” ሲሉ ከቪኦኤ አማርኛው ክፍል ባልደረባ ትዝታ በላቸው ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታወቁ። ሚኒስትሩ ድርጅታቸውን ከደርግ ጋር በማነጻጸር ከቂም የጸዳ እንደሆነ ሲያስረዱ ጋዜጠኛዋ አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ በቂም በቀል ስለተፈጸመውና እየተፈጸመ ስላለው ግፍ ጥያቄ አላቀረበችም። ሚኒስትሩ ኢህአዴግ በህግ የበላይነት ስለማመኑ በመረጃ አልተሞገቱም

በዘር፣ በብሄርና በጎሳ ላይ ተንጠልጥሎ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው ኢህአዴግ፣ በ፩፱፰፫ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በገሃድ አማርኛ ተናጋሪዎችን ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በማናከስ፣ ቂም በማቋጠር፣ የስርአተ ማህበሮችን ችግሮች ከነፍጥ ጋር በማያያዝ እያላከከባቸው፣ “ነፍጠኛ” የሚል ስም በመስጠት የህዝብ ንብረት በሆነው መገናኛ የጥላቻ ዘመቻ በማራገብ የደረሰው ጥፋት ሰፊ ነው። የኢህአዴግ የቀድሞ አመራሮች በተለያዩ አጋጣሚዎቸ ይፋ እንዳደረጉት ይህንኑ አማርኛ ተናጋሪ የህብረተሰብ ክፍል ለይቶ የማጥፋትና የማጥቃት እቅድ በፕሮግራም ደረጃ የተቀመጠ ነው።
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ለኅልፈት የተዳረጉት “አማራው ተሟጋች አጣ” በሚል ስለ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በቂም ተወልዶ፣ በቂም እዚህ የደረሰው ኢህአዴግ ከዚህ ከማይደበቀው ታሪኩ ፊት ለፊት ቆሞ “እንዴት ቂመኛ አይደለሁም ሊል ይቻለዋል” የሚሉ ወገኖች ቴድሮስ አድሃኖምን ለመታዘብ ጊዜ አልወሰዱም።
“ደርግ ያለ ርህራሄ ፷ ሚንስትሮችን ረሸነ፣ የውሻ ያህል እንኳን ክብር አልሰጣቸውም” እያሉ የሰው ልጅ ክቡርነትን በመጥቀስ ቂም ኢህአዴግ ቤት እንደሌለ ለትዝታ በላቸው ያስረዱት የኢህአዴግ ሹመኛ፣ “ኢህአዴግ በመሆኔ ደስ የሚልኝ ቂመኛ ድርጅት ባለመሆኑ ነው” ሲሉ ተመጻድቀዋል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከተማ ሽርሽር እንደሚወጡና የአዳማን ልማት ተመልክተው መደሰታቸውን የጠቆሙት ቴድሮስ ይህ ሁሉ ኢህአዴግ ቂመኛ ድርጅት ላለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ላብቶፕ ተሰጥቷቸው መጽሃፍ ጽፈው ወደማጠናቀቁ መዳረሳቸውን እግረመንገዳቸውን ጠቁመው ያለፉት ቴድሮስ፣ ይህ ሁሉ የፓርቲያቸውን ርኅሩኅነት የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል። በሌሉበት የሞት ፍርድ የተበየነባቸው አቶ አንዳርጋቸው ይቅርታ የመጠየቅ መብት አላቸው፣ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቀም ብለዋል። በቤተሰብና በጠበቃ ለመጎብኘት ፈቃድ መከልከሉን አስመልክቶ “ትንሽ የሚጠየቃቸው ጥያቄዎች ሰለነበሩ ነው” ሲሉ አቃልለው መልስ ሰጥተዋል። አሁን ወደ መደበኛ ማረሚያ ቤት በመዘዋወራቸው ሁሉም ነገር እንደሚመቻች ገልጸዋል።
ከሰኔ፩፮ ቀን ፳፩፮ ጀምሮ ባልታወቀ ስፍራ ታስረው የቆዩት አቶ አንዳርጋችው ጽፈውታል የተባለውና በቅርቡ ለንባብ ይበቃል የተባለው መጽሃፍ “ስልጣን ላይ ያለው አካል በአቶ አንዳርጋቸው ስም ያዘጋጀው ነው” ሲል ኢሳት ይፋ ያላደረጋቸውን ምንጮች ጠቅሶ አመልክቷል። ኢሳት እንዳለው በመጽሃፉ ዝግጅት ላይ ህላዊ ዮሴፍ በረከት ስምዖን፣ አባይ ጸሃዬ እንደተሳተፉበት አመላክቷል። የመጽሃፉ ይዘት በኤርትራ ያለውን ትግል የማንኳሰስና የግንቦት ሰባት አመራሮች ስብእና ላይ ያተኮር መሆኑንም አስታውቋል።
እሳቸው ብቻ ተናጋሪ በሆኑበት ቃለ ምልልስ ሚኒስትሩ አስቂኝ ትንተና በመስጠት የቅዳሜውን የቪኦኤ ዝግጅት መዝናኛ አድርገውት ነበር። “እኛ” አሉ አቶ ቴድሮስ፣ “እኛ መቶ በመቶ ምርጫ አላሸነፍንም። ይህ መስተካከል አለበት። ያሸነፍነው በተወዳደርንበት ቦታ ብቻ ነው” ትዝታ ታዳምጣለች ቴድሮስ ቀጠሉ። ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች ጥምረት መሆኑን አስረዱ። የተቀሩት “አጋር” እንኳን ሲሉ ያልጠሯቸውን የጎሳ ድርጅቶች “ተቃዋሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ” አሏቸውና አረፉት።
የጋምቤላ፣ የቤኒሻነጉል፣ የአፋር፣ የሶማሌ ከልል ኢህአዴግ ሰራሽ /እንደራሴ/ ወይም ድቃይ ድርጅቶች “እንደ ሌሎች ተቃዋሚዎች ድምጻቸውን አውጥተው አይቃወሙንም እንጂ የማንግባባቸው ጉዳዮች አሉ” በማለት እነሱ በሚያስተዳደሩት ከልልሎች ውስጥ ኢህአዴግ አለመወዳድሩን በማሰረዳትና በመተንተን ኢህአዴግ መቶ ከመቶ ምርጫውን አሸነፈ ሊባል እንደማይቻል አመላክተዋል።
አዲስ አበባን አስመልክቶ ኢህአዴግ ትንሽ ከስልሳ በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘቱን፣ ተቃዋሚዎች አርባ በመቶ የሚጠጋ ድምጽ አግኝተው እንደነበር፣ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተቃዋሚዎች ያገኙት ድምጽ ሲደመር ኢህአዴግ ካገኘው በላይ ቢሆንም አንድ ባለመሆናችው ሊያሸንፉ አለመቻላቸውን፣ ያመለከቱት የህወሃቱ አባል ቴድሮስ፣ “ተቃዋሚዎች የተበጣጠሱ ናቸው፤ እኛ አንድ ልናደርጋቸው አንችልም። አንድ ቢሆኑ በርግጠኛነት ከሰላሳ በመቶ በላይ መቀመጫ ማግኘት ይችላሉ” ሲሉ የቀጣዩን ምርጫ ውጤት ተንብየዋል።
ሚኒስትሩ ባልተለመደ መልኩ በመቻቻል፣ በመፋቀር፣ በመረዳዳት፣ በህብረት አገር ለማሳደግ ሁሉም ወገኖች ሊሰሩ እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል። “አዲስ የዴሞክራሲ ግንባታ በመሆኑ ብዙ እናበላሻለን” ሲሉ ችግሮች ስለመኖራቸው ያልሸሸጉት አቶ ቴድሮስ፣ ስለመተባበር ጥሪ ቢያቀርቡም የአርበኞች ግንቦት ፯ ሃይል ታጋይና ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋን በስም በመጥራት ወደ ኤርትራ ማቅናታቸውን ጠቁመው “የሚያመጣው ነገር የለም። እርግጠኛ ነኝ የሚፈይደው ነገር የለም። ዜሮ፣ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም” ሲሉ አጣጥለዋቸዋል። እሳቸው ይህንን ቢሉም ኤርትራ የመሸገው የአርበኞ ግንቦት ፯ ሃይል በተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘሩን፣ ጉዳት ማድረሱን፣ ቁጥራቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑ የአየር ሃይል አባላት ከዱ ስለመባሉ ኢህአዴግ በይፋ ሲያስተባብል አልተደመጠም።

No comments:

Post a Comment