Translate

Saturday, March 30, 2013

ስለ አባይ ግድብ “አድርባይ” እንሁን?


ስለ አባይ ግድብ “አድርባይ” እንሁን?

cant keep quiet
ሰሞኑን ኢህአዴግ ጉባኤውን ሲጨርስ “አድርባይነት አሰጋኝ” ብሎናል። አባላቶቼ አድርባይ ሆነዋልና በዚህ ከቀጠልኩ እሰምጣለሁ የሚል ስጋት እንዳለበትም አስታውቆናል። ከፍርሃቻው ብዛት የተነሳ አድርባይነትን ለመዋጋትና “መድረክ ላይ ለመጥለፍ” በቁርጠኛነት እንታገላለን ብለው አቋማቸውን ነግረውናል። የሚገርመው ግን አድርባይነትን የፈጠረና ያነገሰው ራሱ ኢህአዴግ መሆኑን መዘንጋቱ ነው።
ኢህአዴግ አድርባይ ሚዲያዎች አሉት። አድርባይ ባለሃብቶች አሉት። ኢህአዴግ አድርባይ የኔቢጤዎች አሉት። ኢህአዴግ አድርባይና የማደናገሪያ ፕሮጀክቶች አሉት። ኢህአዴግ አድርባይ ድርጅቶች እንጂ ነጻ ድርጅቶች የሉትም። ኢህአዴግ አድርባይ ባለስልጣናት እንጂ ነጻ አመራሮች የሉትም። ሁሉም አድርባዮች ተጠሪነታቸው ለህወሃት ስለሆነ ተጠያቂውም ራሱ የኢህአዴግ ሾፌር ህወሃት እንጂ ሌሎች ሊሆኑ አይገባም። “ፈጣሪያቸው” የሚገመግማቸው፣ እነሱም አምነው የሚገመገሙት ታማኝ አድርባይ ስለሆኑ ብቻ ነው።
አሁን እየተለመደ የመጣው የመፈክርና የቀረርቶ ጉዳይ አጥወልውሎ የሚጥል ደረጃ ያደረሰንም ለዚህ ነው። ቃላት ማምረትና ማራባት የተካነበት ኢህአዴግ በየጊዜው የሚፈለፍላቸው ቃላቶች እያንገፈገፉን ነው። በተለይም ታላላቅ ዋጋ ባላቸው “ውድ” ቃላቶች ላይ አደጋ እየፈጠረም እንደሆነ ይሰማናል፤  ይጫወትባቸዋል። አድርባይ ሚዲያዎችና አድርባይ ጋዜጠኞች የማከፋፈሉን ስራ ይሰራሉ። ይህ በአገር ደረጃ የተንሰራፋው አድርባይነት ለኢህአዴግ ስጋቱ አይደለም፤ ኩራቱ እንጂ!!
ይህንን ያነሳነው ወድደን አይደለም። ባለፈው ሳምንት ባወጣነው የአባይ ግድብ ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ አይደለም የሚል ዜና አድርባይ እንድንሆን ያሳሰቡን በመኖራቸው ነው። ስለ አባይ ግድብ ያሰራጨነው ዜና ያስደነገጣቸው በርካቶች ናቸው። የአባይ ግድብ መገደብ እውን መሆን አለበት። አባይ ተገድቦ አገር መልማት አለበት። አባይን ለልማት ለመጠቀም ለሚገጥም ችግር ሁሉ ሁላችንም “ልዩነት” ሳይገድበን ዘብ እንቆማለን!! ግን የግልጽነት ጥያቄ ያሳስበናል። ያስጨንቀናል። “በልማትና ዕድገት” ስም የተድበሰበሱ ውሎችና ስምምነቶች እኛንም ሆነ መጪውን ትውልድ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ እናምናለን። በዚህ ጉዳይ ላይ አድርባይነት የለም!!
በአባይ ላይ የሚሠራው ግድብ ከግማሽ በላይ የሆነው ድርሻ የኢትዮጵያ እንዳልሆነ የጻፍነው ለዜና ፍጆታ ወይም ለዝነኝነት ወይም “ዜና አገኘን” በሚል በኢህአዴግ ላይ ነቀፋ ለመሰንዘር በጎመጀ ስሜትና ኢህአዴግን ለማሳጣት በመፈለግ አይደለም፡፡ ከላይ በመነሻው እንዳልነው አውቆ የማሳወቅ ሃላፊነት ስላለብን ነው። ስለሚመለከተን ነው። “አያገባችሁም፣ ዝም በሉ፣ አትጠይቁ” የሚባሉ ወገኖች ሊኖሩ ስለማይገባ ነው፡፡ ኢህአዴግ በሚያስተዳራት ኢትዮጵያ ሁሉንም ዜጋ መስፈር በሚፈልግበት የአድርባይነት መስፈሪያ መሰፈር ስለሌለብን ነው፡፡
የአባይ መገደብ አስፈላጊነትና ለአገር ጥቅም መዋል ለክርክር መቅረብ የሚገባው ጉዳይ አይመስለንም፤ “አባይ ይገደብ” እየተባለ ከተፎከረና ከተዘመረ በርካታ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ የአባይ ጉዳይ ኢህአዴግ አጀንዳ ወይም በባለመብትነት የሚመራው ጉዳይም አይደለም፡፡ ነገር ግን ከአባይ ጋር የሚመጣው ዓ-ባ-ይ-ነት ያሳስበናል፡፡ እየተከሰተ ያለው የግልጽነት መታጣት ጉዳይ የሁሉም ዜጋ የቁጭት ጥያቄ ሊሆን እንደሚገባው በአጽዕኖት ስለምናምን ነው፡፡ ይልቅ ሊያሳስብ የሚገባው ዝምታው ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በእንደዚህ ዓይነት አገራዊ ጉዳይ ላይ እስከጥግ በመሄድ ሕዝብን የማሳወቅ ኃላፊነት ሲወጡ አለመመልከት ጥያቄ ስለሚፈጥርብን ነው፡፡
ጉዳዩ የቦንድንና የባለድርሻነት “share” ልዩነት ካለማወቅ የመነጨም አይደለም፡፡ ያገኘነው መረጃ አስተማማኝነቱም ሆነ እርግጠኝነቱ የጸሐይ በምስራቅ የመውጣትና በምዕራብ የመጥለቅ እርግጠኝነት ያህል ለጥያቄ የማይቀርብ ነው፡፡ ሆኖም የኢህአዴግ ሰዎች ሥርዓቱ ከፈጠረው የራሱ የሆነ ዝግነትና የማስፈራሪያ ስልት አኳያ በዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ሲናገሩ ራሳቸውን ዓይኑን ካፈጠጠ መረጃ በማራቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተስተዋለ ሁኔታ ነው፡፡ እየተቀለደ ግን ያለው ምትክ በሌላት አገር ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ታዲያ ይህ እየተከናወነ ነው ከሚባለው ልማት በላይ ካላሳሰበን ሌላ ምን ሊያሳስበን ይችላል?
ስለሆነም የአባይ ጉዳይ ግልጽ ይደረግ እንላለን! ኢህአዴግ አገር እያስተዳደርኩ ነው እንደሚለው ሁሉ ይህንንም በሕዝብና አገር ስም እየተዋዋለ ነውና ጉዳዩን ለሕዝብ ይፋ ያድርግ፡፡ በልማት ስም ተጠያቂነትን ወደ ጎን ማለትም ሆነ ከግልጽነት መራቅ ልማት ሳይሆን ጥፋት ነው! ውድመት ነው!
በጅቡቲ ላይ ኢትዮጵያ ሙሉውን ወጪ ሸፍና የምታስገነባውን ወደብ አስመልክቶ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲናገሩ “የህዳሴውን ግድብ” ቦንድ ከገዙት አገሮች መካከል ጅቡቲን ጨምረው የተወሰኑ የአፍሪካ አገራት እንዳሉ ጠቅሰው ነበር፡፡ ቦንድ በመግዛት ብቻ ያልተወሰኑትን ሌሎች አገራት በነካ እጃቸው ማሳወቅ ይገባቸው ነበር፤ ወደፊትም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ጉዳይ ይፋ ለማድረግ ያብቃው እንጂ እኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥፋት ከሰራን ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነን፡፡ እርሳቸውም ሆኑ ኢህአዴግ ይህንን ባያደርጉም አገራቸውን የሚወድዱ በተገኘው መንገድ መረጃውን ሲሰጡ ግን ማዳመጥና መርምሮ ምላሽ መስጠት የግድ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን “ለምን መረጃው ይፋ ሆነ” በሚል ሳይገባን እስክስታ የምንወርድ ከሆነ “በአባይ ጉዳይ ላይ እኛም አድርባይ እንሁን?” ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡
““የህዳሴው ግድብ” ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ አይደለም” በሚል ርዕስ የጻፍነውን ዜና ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡

No comments:

Post a Comment