Translate

Wednesday, March 27, 2013

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ


(በሰሎሞን ተሰማ ጂ.)

Email: solomontessemag@gmail.com
ማንም በዕድሜው ብዛት አያስጠራም ስሙን
በጥቂቱም ዕድሜው ይሠራል ሐውልቱን፡፡
ታሪክ ሲያበላሸው ረጅሙም ያጥራል፣
ታሪክ ሲያሳምረው አጭሩም ይረዘማል፤
ብዙ ዘመን ቢኖር ዕድሜውም ቢበዛ፤
በሳቅ በጨዋታ ዋዛን በፈዛዛ፣
ሲለዋውጥ ኖሮ ሃሳቡን ሳይገዛ፣
እንዲሁ ይቀራል እንዲያው እንደዋዛ፡፡
(“ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ” (2004)፤ ገጽ 191)
ከላይ የተጠቀሱት ስንኞች የማንን “ዕድሜ” እና “ታሪክ” ለማሳመር እንደሚበጁ ለመወሰን አያዳግትም፡፡ ሥንኞቹ ጉልሕ አጽንዖት የሚሰጡት ዕድሜው ስላልበዛው ሰው ነውና፤ የዚህ መጽሐፍ ደራሲም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ “38 ዓመት ከ10 ወር ሊሞላው 4 ቀን ጎደል ነበር”፡፡ ለአንድ “ሩቅ አስቦ፣ ቅርብ ላደረ” ሰው የሚስማማ ዐርኬ ነው፡፡ ሌሎቹ በዚህ የመጽሐፍ ግምገማ ውስጥ የምናወሳቸው ሁለት ሰዎች፣ ከዚህ “አታላይ ዓለም” ሲለዩ ሃምሳ ሲደመር ሦስትና ለሰባ አንድ ፈሪ ነበሩ፡፡
ሦስቱም፣ ሰው “በዕድሜው ይሠራል ሐውልቱን” የሚለው ሐረግ መንፈሳቸውን “ደስፈቅ” ያደርገዋል፤ (በፍፁም ደስታና ተድላ ይሞላዋል)፡፡ ሁሉም፣ በዚህ ለግምገማ በመረጥነው መጽሐፍ ውስጥ የየራሳቸውን ሐውልት፣ የውኃ ልኩን ጠብቆ እንዲቆም አድርገዋል፡፡ የዚህን፣ ሦስቱንም የሚያስመሰግን ሐውልታዊ ሥራ ለመገምገም የተነሳንበትም ሰበብ ይሄው “ስማቸውን ለማስጠራት” ያደረጉትን ጥረት ዋጋ ሰጥተን ነው፡፡
መነሻ
ከአንድ ወር በፊት በየካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ አንድ መጽሐፍ ተመርቆ ነበር፡፡ የመጽሐፉም ርዕስ “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ” (2004) ይሰኛል፡፡ የመጽሐፉ ጸሐፊ፣ ገጣሚውና መምህሩ ዮሐንስ አድማሱ (ከ08/01/1929-04/10/1967 ዓ.ም) ሲሆን፣ በ1965 ዓ.ም በዓለማያ እርሻ ኮሌጅ ሳለ እንደጻፈው በመቅድሙ ላይ ገልጾታል (ገጽ-xv):: ከሠላሳ ዘጠኝ አመታት በኋላ፣ የጸሐፊው ሁለተኛ ታናሽ ወንድም፣ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ (05/02/1935-01/06/2005 ዓ.ም) አሰናኝቶት በግንቦት 2004 ዓ.ም ወደ ማተሚያ ቤት ገብቷል (ገጽ-x)፡፡ ጸሐፊው ዮሐንስና አሰናኙ ዶ/ር ዮናስ፣ የባለታሪኩን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴን (ከ23/08/1887-30/10/1939) ድረስ ያለውን የሕይወቱንና የሥራዎቹን ታሪክ በትጋተረና በቅንነት ሊያቀርቡ ጥረዋል፡፡
የመጽሐፉ የሕትመት ዘመን ላይ ግንቦት 2004 ዓ.ም ይበል እንጂ፣ ከግንቦት 2004 ዓ.ም እስከ ጥር 2005 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች በአሳታሚው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስና በኤክሊፕስ ማተሚያ ቤት መካከል በነበሩት ልዩ ልዩ ውጥንቅጦች ሲጉላላ ከርሞ፣ በጥር 2005 ዓ.ም አቅመ-ሕትመቱ እውን ሆኖ፣ ለዩኒቨርሲቲ ፕሬሱ መጋዘን ገቢ ተደርጓል፡፡ ለምረቃው ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜም ሲቀረውም፣ አሰናኙ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ በመሆኑም፣ ባለታሪኩ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴም ሆኑ፣ ወንድማማቾቹ “የአድማሱ ልጆች” (ዮሐንስና ዮናስ- ወይም በምረቃው ወቅት የመድረክ አስተዋዋቂው አቶ ሃይማኖት አለሙ እንዳለው “ሦስቱ ዮ-ዎች”) በመጽሐፉ ምረቃ ወቅት በአፀደ ሕይወት ባለመኖራቸው፣ የሚነሱ ጥያቄዎች ቢኖሩንም መልሳቸው ሩቅ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም፡፡ በተለይም፣ ሳያነቡና ሳይመረምሩ ጫፍ ይዘው ለሚያነበንቡ ሰዎች የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡ ይሄውም፣ “መጽሐፌን ሳታነብ ዘላበድክ፣” ወይም “መጽሐፉ ሳይገባህ የገባህ አስመሰልክ!” ብሎ አንጃ-ግራንጃ ውስጥ የሚገባ ሰው ባለመኖሩ የሥነ-ምግባር (የሞራል) ግዴታውን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ሦስቱም ባለታሪኮች “አገር ያወቃቸው፣ ፀሐይ የሞቃቸው፣” እና ዜና-ዕረፍታቸውም የመገናኛ ብዙኃንን ሽፋን ያገኘ ነበር፡፡ ይኼ-“ሦስቱን ዮ-ዎች” ባንድነት ያጣመረ መጽሐፍ ከብዙኃኑ አንባቢያን እጅ የደረሰው በተመረቀበት ዕለት (የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም) ነበር፡፡ ዋጋው አንድ መቶ አስራ አራት (114.00) ብር ነው፡፡ አንባቢያን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፣ ከቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ከፍተኛ ቁም ነገሮችንና ታሪካዊ ኩነቶችን መገብየታቸው አያጠያይቅም፡፡ መጽሐፉ በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል የዮፍታሔ ንጉሴን “የሕይወቱን ታሪክና የጽሑፉን ታሪክ” የሚተርክና የሚተነትን ሲሆን (ከገጽ 01 እስከ 213 ድረስ ይሸፍናል)፤ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ፣ የዮፍታሔን “መዝሙሮች፣ ስለምኖችና ቅኔዎች” ሃተታ የያዘ ነው (ይሄውም፣ ከገጽ 215 እስከ 272 ድረስ ይዘልቃል)፡፡ በተጨማሪም፣ መጽሐፉ “መዘክር”፣ “አኮቴት”፣ “ምስጋና”፣ “መቅድም” እና “መግቢያ”ም ያካተተ ነው፡፡ በመጽሐፉ በስተመጨረሻም፣ የማጣቀሻ መጽሐፍት ዝርዝር፣ አባሪዎችና መፍትሔ ቃላትም አካቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ 542 የግርጌ ማስታወሻዎችን በጥንቃቄና በፍጽምና ደጉሷል፡፡ ሁሉንም የመጽሐፉን ዋነኛ ክፍሎችና ቅድመ እንዲሁም ድሕረ መረጃዎች፣ ደጋግሞ ማንበብ የበለጠ መጠቀም ነው፡፡ በትዕግሥትና በምልዓት የተከወነ መጽሐፍ ስለሆነ፣ ለጥልቅና መጢቃ አንባቢ የተመቸና ትርፋማም ነው፡፡
አንባቢያን መጽሐፉን አንብበው ሲጨርሱ፣ በብሔራዊ ቴያትር በነበረው የመጽሐፉ ምረቃ ምሽት የነበሩት ተናጋሪዎች (ፕ/ር ሽፈራው በቀለ፣ ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነና አቶ አስፋው ዳምጤ ሲናገሩት ከነበረው በላይ ሁለቱ ወንድማማቾች በዚህ መጽሐፍ ይዘትና ቅርጽ ላይ በእጅጉ መልፋታቸውን) ይረዱታል፡፡ እርግጡን ለመናገር፣ በምረቃው ዕለት፣ “ስለዮፍታሔ ንጉሴ የሕይወትና የጽሑፍ ታሪክ” ምረቃ ተብሎ ይነገርና ይደሰኮር የነበረው በአመዛኙ ስለ“አድማሱ ልጆች” (ስለዮናስና ስለዮሐንስ) ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ፣ የመድረክ አስተዋዋቂው አቶ ሃይማኖት አለሙ – ራሱን ሲያንቆለጳጵስና ሲያሞግስ ማምሸቱ አስገራሚም አሳፈሪም ትዕይንት ነበር፡፡ “በማሚቴ ክርስትና፣ እነሃብትሽን ምስጋና! ለምን አስፈለገ?” ያላለ ታዳሚ አልነበረም፡፡ የመድረክ አስተዋዋቂው – ሃይማኖት አለሙ፣ ከአንድ ታዋቂና የተመሰገነ የመድረክ ሰው የሚጠበቅ የመድረክ ስነ ሥርዓት አላሳየም ነበር፡፡ የዮፍታሔን፣ የዮሐንስንና የዮናስንም ድካም ሁሉ፣ በ“እኔነቱ አንቀልባ” ውስጥ ሰብስቦ ጠፈረና ኮረኮዳቸው፡፡ ማለት፣ ዝግጅቱን የኮከበ ጽባሕና የቀ.ኃ.ሥ ትምህርት ቤቶች ሙገሳና ትዝታ እንደ ዳዊት እንዲደጋገምባቸው አደረገ፡፡ (መቼም፣ ይህ “የእኔና የእኔነት አባዜ”ው ሌላ ጊዜና ሌላ ቦታ በ“ፊት-ለፊት” እንደማይደገም ተስፋ እናደርጋለን፡፡)
የሆነው ሆኖ፣ አሁንም የምንገመግመው መጽሐፍ እጅግ ከፍ ያለ ሚዛን የሚያነሳና ከፍተኛ የዋጋ ድልድል የሚሰጠው፤ የሃይማኖት (የሥነ-መለኮት)፣ የአብነትና የቤተ-ክህነት ትምህርት፣ የታሪክ፣ የቋንቋና የቴያትር፤ እንዲሁም የሥነ-ጽሑፍ ይዘት ያለው ሥራ ነው፡፡ እንደሚታወቀው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍትን መጻፍና ማሳተም እየተለመደና እያደገ የመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት፣ “የዘመናዊቷ (የአዲሲቷ) ኢትዮጵያ ምስረታ ከተጀመረ በኋላ የተነሱትን ባለታሪኮች ልቀትም ሆነ ድቀት በማጥናት የተሻለች ሀገርና የዘመነ ህብረተሰብን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ያግዛል፣” ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ አሁን ያለንበትን የታሪክ ጅረት (ፍሰት) በቅጡ ለመረዳት፣ የኋላ ማንነታችንን ከሥረ መሠረቱ ጀምረን ለማወቅ፣ እና አውቀንም ከጅረቱ ሙላትና ጉድለት ለመጠቀም ስለሚያስችለን ነው፡፡ ባጭሩ፣ ፍሬውን ከገለባው ለመለየት፣ እውነቱን ከሐሰቱ ለማበጠርና ወደ ነፃነት ድንኳን የምናደርገውን ጉዞ ለማቀላጠፍ መንገድ ስለሚያሳዩ ነው፡፡ ሁለተኛው ሰበብ ደግሞ፣ እንደሚታወቀው፣ “20ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ማንነትና ምንትነት በእጅጉ አመሰቃቅሎታል፡፡ በርካታ መጤና አዳዲስ ማሕበረሰባዊ ቀውሶችም የሀገራችንንና የሕዝባችንን ዕዝነ-ልቦና አመሰቃቅለውታል፡፡ ብዙው ማንነታችንና ባሕላዊ አብነቶቻችንም የጠፉት፣ የተሰረቁት፣ እንዲሁም ወድቀው የቀሩት” በዚሁ ጊዜ ስለሆነ፣ ያንን ለመፈለግ ሲባል የሕይወት ታሪክ (Biography) እና ግለ-የሕይወት ታሪክ (Autobiography) መጽሐፍት (ከነችግራቸውና ከነጉድለታቸው) በአንባቢያን ዘንድ ተፈላጊ ሆነዋል፡፡
እርግጥ ነው፣ በተለያዩ ማተሚያ ቤቶችና በተለያዩ አሳታሚ ድርጅቶች አማካይነት በርካታ (ግለ) -ሕይወት ታሪክ መጽሐፍት ታትመዋል፡፡ ከነዚህም የአሳታሚ ድርጅቶች ውስጥ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አንዱ ነው፡፡ (ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ላለፉት 21 ዓመታት በጥራትና በትጋት የሠራ፣ “ብቸኛው ፕሬስ ነው!” ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከዚህ ለግምገማ ከመረጥነው መጽሐፍ ሌላ፣ አራት ግለ-ሕይወት ታሪኮችን አሳትሟል፡፡ ለምሳሌም ያህል፣ የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያምን “ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)”ን (በ1998)፤ የመርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን “የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፤ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት 1896-1922” (በ1999)፤ የልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴን “ካየሁትና ከማስታውሰው” (በ2001)፤ እንዲሁም የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድን “የአክሊሉ ማስታወሻ” (በ2002) አሳትሟል፡፡ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ታላቅ አገልግሎትና ከፍ ያለ ውለታም ነው፡፡ (ሆኖም፣ ፕሬሱ ለደራሲዎች (ለወራሾቻቸው) የሚከፍለው ክፍያ እና የሕትመት ቢሮክራሲው ደራሲያንን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ የፕሬሱ ቦርድ አባላትም ችግሩን ከዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ካልቀረፉት በተቀር፣ የተጀመሩት ጥረቶች የሆነ ጊዜ እንደሚቋረጡ ጥርጥር የለንም፡፡)
****
ወደዋናው ትኩረታችንና ለግምገማ ወደመረጥነው መጽሐፍ ሃቲት እንመልስ፡፡……ከላይ እንዳወሳነው የመጽሐፉ ርእስ “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ” ይባላል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱና አሰናኙ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ዋናው የትምህርት ጥናታቸው ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ወንድማማቾቹ – የጻፉትና ያሰናኙት መጽሐፋቸው በቋንቋና በሥነ-ጽሑፍ ይዘቱና ቅርጹ እጅግ ጥልቅና መጢቅ ቢሆን ምንም ያህል አያስደንቅም፡፡ወንድማማቾቹ፣ የዮፍታሔ ንጉሴን ሕይወትና የጽሑፉን ታሪክ (ኩነቶችን)ና የዮፍታሔን የሥነ-ጽሑፍ ሥን (ኪነታዊት እውነትን) ሊመጥኑ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ ዮሐንስ በገጽ-62 ላይ እንደገለጸውና፣ አሰናኙ ዶ/ር ዮናስ አድማሱም በገጽ-307 ላይ እንዳስረገጡት፣
“ኪነትና ኬነውት (ከያኒያን) በጽኑ መዋግደ ኅሊና በሚጠመዱበት (ኅሊናቸው በዘመኑ ቀውስ በሚታወከበትና መንፈሳቸው ዕረፍት በሚያጣበት) ዘመን፣” ታሪክን በኪናዊ ስለምን (ዘይቤ) ለሕዝባቸው ማስተማሪያ መጠቀማቸው ተፈላጊ እንደሆነ ይጠቅሳሉ (ገጽ-62)፡፡ የከያኒው የኖረበት ዘመንና ኪነታዊ ውበት ግንኙነታቸው የአንድ ኩታ ሁለት ጠርዝ ዓይነት ነው፡፡ ኩነቶች ያለ ኪነታዊ ቋንቋ ሲጻፉ፣ እጅ እጅ ይላሉ፡፡ ዮሐንስ በገጽ 118 ላይ እንዲህ ይላል፤ “በጠቅላላው ለኪነት ሥራ፣ በተለየ ደግሞ ለሥነ ጽሑፍ መላ ምት ዐይነተኛና መሠረታዊ የሆነ ነገር ነው፡፡” ኩነቶችን አስፍቶ፣ ተንትኖ ወይም አበጥሮ አይደለም፤ በድሳሳውና በአጭሩ ነው፤” የሚያቀርባቸው፡፡ ጸሐፊው ዮሐንስ ሃይለ ቃል፣ ከዮፍተሔ “አፋጀሽኝ” ተውኔት ገጽ-31 ተውሶ፣ “ልትናገሩ ብትፈቀዱ ነገር አታበዙ፣ የመናገር ጌጡ ማሳጠር ነውና፤” ይላል (ገጽ-118)፡፡
ዮሐንስ በገጽ 186 ላይ አቶ በለጠ ገብሬን ዋቢ ጠቅሶ እንደገለጸው ከሆነ፣ ንጉሠ ነገሥቱና ፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ እንደተነበዩትም፣ “ዮፍታሔ ሥራውን ንቆ ተወው እንጂ የኢትዮጵያው ሼክስፒር የሚባልበት ጊዜ” መምጣቱ አይቀርም ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ዮፍታሔ በሰኔ 7 ቀን 1934 ዓ.ም (ከሱዳን ስደቱ በተመለሰ ልክ በአንድ ዓመት ከአንድ ወሩ) በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር አዲሲቱ ኢትዮጵያ በዜማና በትምህር በኩል የምትሻሻልበትን መንገድ በማሰብ በዜማና በግጥም መሥሪያ ቤት በኪነ ጥበብ ውስጥ እንዲቋቋም ወስኗል፡፡ የዚሁ ሥራ አስኪያጅነት በወር 150 ብር” እያገኘ ኃላፊነቱ ተሰጠው፡፡ ሆኖም፣ የ47 ዓመቱ ዮፍታሔ “የዘፈን ሹም ሁን” እንዴት እባላለሁ ሲል አሻፈረኝ አለ፡፡ ንጉሡና ፀሐፌ ትዕዛዙ ይኼንን ነው፣ “ሥራውን ንቆ ተወው እንጂ” ሲሉ የተቆጩት፡፡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ግን፣ ምኽኛት ነበረው፡፡ በገጽ 179 ላይ እንደተገለጸው፣ “የነገረ ዓለሙ አካሄድ አነሰ ሲሉት ተቀነሰ ሆነና፣ ከአንድ ዓመት በላይ ያለ ሥራ ተቀመጠ፡፡ ተሰጥቶት የነበረው ተስፋም ጤዛ፣ ተን ሁኖ ቀረ፡፡ ‘አገራቸውን ለጠላት የሸጡ፣ እምነተ ቢሶች’ ወይም ‘ታረከ ክፉ’ዎች የነበሩት፤ አንደኛ፣ ቀድመውት ማለፊያ ማለፊያ ሥራ ያዙ፤ ሁለተኛ፣ ለእሱ ሥራ ማግኘትና አለማግኘት፣ ለዕድሉ መቃናት ወይም መድለም የሚገባውን ሥራ በማደላደል፣ ቀለበን በመቁረጥ ረገድም” እነዚሁ አገር ሻጮች ፈላጭ ቆራጭ ሆኑ፡፡ ዮፍታሔም ለስደተኞች የሚሰጠውን ስድሳ ብር እየተቀበለ ከሚያዝያ 1933 – ጥቅምት 1935 ዓ.ም ድረስ ሥራ ፈት ሆኖ ተቀመጠ፡፡ በዚሁ ወቅት ነበር፤
ለጌሾው ወቀጣ፣
ለጌሾው ወቀጣ፣
ማንም ሰው አልመጣ፡፡
ለመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ፡፡”
ሲል በምፀቱ የሸነቆጣቸው፡፡ የየትም አይገኝ ባለቅኔው-ዮፍታሔ፣ በ1930ዎቹ የነበረውን የሞራል ዝቅጠትና ስግብግብነት በአራት ስንኞች ቅልጥጥ አድርጎ አጎላው (ገጽ 173)፡፡
በመጨረሻም፣ በጥቅምት 18 ቀን 1935 ዓ.ም “በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድና ትዕዛዝ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት” ሆኖ እንዲሠራ ታዘዘ (ገጽ 182)፡፡ በዚሁ ሥራውም እስከ ሐምሌ 1/1939 ዓ.ም ድረስ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በዚሁ ወቅት ልጁን ጌዴዎንን ካርቱም አቶ ዑመር አቡበከር ዘንድ ልኮ ማስተማር ጀመረ፡፡ ጠርጣራውና ገንጋኙ ዮፍታሔ፣ ልጁን ወደ ካርቱም ከላከ በኋላ ሥጋት ተቀነሰለት (ገጽ 194)፡፡ የዮፍታሔን ጠርጣራነትና ገንጋኝነትም በተመለከተ፣ በገጽ 184 ላይ እንዲህ ይላል፤ “አለልክ ጣርጣሪ ሰው ነበር፡፡ በመርዝ እሞታለሁ የሚልም ረቂቅ ፍርሃት በሰውነቱ ውስጥ ነግሦ ነበር፡፡” ዮሐንስ ዋቢ ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ የዮፍታሔ ሕመሙም ሆነ አሟሟቱ በሚገባ አልታወቀም፡፡ “በከሰል ጢስ ታፍኖ ሞተ!” የሚለውንም ወሬ “ተረት-ተረት” ነው ሲል ያጣጥለዋል (ገጽ 205)፡፡ ስለዮፍታሔ አሟሟትም አንስቶ በርካታ ማስረጃዎችን አውጥቶና አውርዶ ሲያበቃ፣ ለአንባቢያኑ ከበድ ያለና ተገቢ ማሳሰቢያ ያቀርባል፡፡ የየትም አይገኝ ባለቅኔው፣ የዮፍታሔ እናት፣ ወ/ሮ ማዘንጊያ ወልደ ኄር “ሰኔ ሠላሳ ቀን ተኝቶ አደረበት አንሶላ ላይም የተገኘው ቅጠል የመሰለ ትውከቱም አንሶላው እየታጠበ እስካለቀ ድረስ አለቀቀም ነበር፤” ማለታቸውን ጽፏል (ገጽ-206)፡፡ በዚህ ማስረጃውም መሠረት፣ ወ/ሮ ማዘንጊያ እንደገመቱት፣ ዮፍታሔ እንደፈራውና እንደጠረጠረው ተመርዞ ሞቷል የሚለው ግምት ሚዛን የሚደፋ ሆኗል፡፡ ምንስ ቢሆን፣ “እናት ለልጇ ነቢይ ናት!” አይደል – የሚባለው፡፡
ዮሐንስ አድማሱ ለመጽሐፉ ዋና መነሻ የሆነውን ሃሳብ እንዴት እንዳገኘው ሲገልጽ፣ ስለ ዮፍታሔ “በልጅነቴ ከእናት አባቴ እሰማ ስለነበረና፣ አንዳንዴም እናትና አባቴም መዝሙሮቹን ሲያዜሙ አዳምጬ በጉልምስናዬ ልጠቁመው የማይቻለኝ ደስታ ያን ጊዜ ሰውነቴን ሲወረው ከመሰማቱና ደስፈቅ በማለቱ” ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ “የስሜት ጣጣው” ገፋፍቶ እንዳጠናውም አይሸሽግም (ገጽ xiv እና xv ይመልከቱ)፡፡ ቀጠል አድርጎም፣ “ከሚቀር ይጥቆር ብዬ ነው” ሲል በትሕትና ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም፣ ይህ ጥናት ከ1900 አስከ 1928 ዓ.ም ድረስ የነበሩትን የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ከያንያን በተከታታይ ለማጥናት የታቀደ እንደነበርም ገልጧል፡፡ ሆኖም፣ “ሩቅ አሳቢው” ዮሐንስ፣ ብዙ በሚሰራበት ዕድሜው ስላረፈ ውጥኑ ተገታ፡፡ ያሳዝናል፤ እጅግ ያሳዝናል፡፡
የዮሐንስ ትልምና ዕቅዱ፣ እዚህም እዚያም ተበታትነው የሚገኙትን የ20ኛው ክፍለ ዘመን ደራሲያን የሕይወትና የጽሑፍ ታሪክ አጥንቶ ለማቅረብ ነበር፡፡ የነጋድራስ አፈ ወርቅ ገብረ ኢየሱስን (1860-1939)፤ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን (1873-1931)፤ የፊታውራሪ (በጅሮንድ) ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያምን (1873-1972)፤ የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን (1879-1911)፤ የአቶ መልአኩ በጎ ሰውን (1888-1932)፤ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን (1862-1936)፤ የአለቃ ታዬ ገብረ ማርያምን (1862-1936)፤ የአቶ ማኅተመ ወርቅ እሸቴን (-1929)፤ የብላታ ገብረ እግዚአብሔር ሐማሴኔውን (1860-1911)፤ እንዲሁም ይህንን ለግምገማ የመረጥነውን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴን ጥናት የሚያጠቃልል ነበር፡፡ በመቅድሙ ሥር እንዳተተው፣ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን ሕይወትና የጽሑፍ ታሪክ ብቻ እንኳን፣ በሰባት ቅፆች ከፋፍሎ ሊያቀርብ አስቦ ነበር፡፡ “ሰው ያስባል፣ እግዜር ይፈጽማል” ነውና፣ ይኼው የመጀመሪያው ክፍል ቢዘገይም ወጣ፡፡ በመቅድሙ መሠረትም፣ ስለዮፍታሔ ንጉሤ የሚያትቱ ስድስት ቀሪ ቅፆች አሉ፡፡ “የት ናቸው፤ በምንስ ይዞታ ላይ ይገኛሉ?” ስለሚለው ጉዳይ አሰናኙ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ያሉት ነገር የለም፡፡ ዮሐንስ ግን ከያሉበት አሰባስቦና ተፈላልጎ በእጁ ያስገባቸውን የዮፍታሔ ሥራዎች ይዘት ተማምኖ ይመስላል፣ በሰባት ቅፆች ከፋፍሎ ሊጽፈው ያቀደው፡፡
መጽሐፉ በጠቅላላ መልኩ፣ የተሰባጠሩትን አሳቦችና ኩነቶች ኪነታዊ በሆነ መልኩ ለመግለጥ መቻሉን እንገነዘባለን፡፡ ደራሲው ዮሐንስ፣ ባማርኛ ተመዛዛኝ ቃል ባጣ ቁጥር እጁን ወደ ግዕዝ ቋንቋ ዘርግቷል፡፡ ባዶውንም አልተመለሰም፡፡ ቀዋሚ ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ ቃላትን፤ ለምሳሌ፣ “ላዕል፣ መሲሕ፣ መዓልት፣ መዋግደ፣ ሚጠት፣ ምርፋቅ፣ ስለምን፣ ሶበድዓት፣ ዘይቤ፣ ደስፈቅ፣ ልቡና፣ አንቀጽ፣ አኃዝ፣ ብፁዓን፣ ተረፍ፣ ውርዛዌ፣ ዋዕየ፣ ጸዋትው፣ ጽሩይ፣ ጽርየት፣….” ወዘተርፈን ከግዕዝ ወስዷል፡፡ አሰናኙ የሁሉንም ትርጉም ከገጽ 304-319 ድረስ በጥንቃቄ ተሰናድተዋል፡፡ እነዚህም ቃላት የረቀቀ የኪነታዊ አሳብን ለመግለጥም ተስማሚ ናቸው፡፡ በዚህ አኳኋን፣ አሰናጁና አሰናኙ ሁለት ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ አንደኛ፣ የባዕድ ቃላትን ከመዋስና በጉራማይሌ ቋንቋ ግራ ከመጋባት አድነውናል፡፡ ሁለተኛ፣ የዮፍታሔን “የአማርኛና የግዕዝ ሀብት መሳ ለመሳ ሊገልጹ፣ ሊያትቱና ሊደሰኩሩ የሚችሉትን ቃላት ለማግኘት የሚቻለው ከግዕዝና ከአማርኛ ነው እንጂ ከሩቅና ከባዕዳን ኩረጃ አይደለም፤” የሚል ይፋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በላቀ ብቃትና ትጋት ለአማርኛ ቋንቋ ባለውለታነታቸውን ስለፈጸሙ፤ በእጅጉ የሚያስመሰግን ውለታ ውለዋል፡፡ (የሚገርመው ደግሞ፣ ሁለቱም ወንድማማቾች እንግሊዝኛን ከነፈሊጡና ከነውስጠ ወይራው አበጥረው የሚያውቁ መሆናቸው ላይ ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስ የዶ/ር ዮናስን ያህል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሀብትና ክኅሎት ያላቸው ሰዎች ውሱን መሆናቸውን ነው፡፡)
“ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ” በቃላት አሰካክና አደራደሩ ስርዓትን የተከተለ ነው፡፡ ቃላቱ፣ ለአጫፋሪነትና ለአዳማቂነት ፈፅሞ ልሰፈሩም፡፡ በዮሐንስ ሃተታም ውስጥ ሆነ በዮናስ ገለጻ ውስጥ ግጥምንና ስድ ንባብን እያዛነቁ ሊያቀርቡት ተጨንቀዋል፡፡ ስለሆነም፣ አንባቢው በሁለቱም ስልቶች በኩል፣ ደራሲው ዮሐንስና አሰናኙ ዮናስ ያላቸውን የሃቲት ተሰጥዖ ያደንቃል፡፡ በመጽሐፉም ኅብረ-ጠባይ አንባቢያኑ በእጅጉ ይረካሉ፡፡ ከአንድ ቦታ በስተቀር፣ ያለማሰሪያ አንቀጽ የተቀምጠ ዐረፍተ ነገር አላገኘሁም፡፡ በገጽ 118 ላይ፣ በአንቀጽ 7.08 ያየሁት ነው፡፡ በተረፈ፣ ቃላትና ሃረጋት እንዳያደናቅፉ ተደርገው ተሰናድተዋል፡፡ ዶ/ር ዮናስ በገጽ 304 ላይ እንደገለጹት፣ እነዚህን በተገቢ ቦታቸው በሥርዓት የተሰደሩ ቃላትና ሃረጋት ያለመፍትሔ ቃላት ቢወጡ ኖሮ “ከደርግ ወዲህ ወደዓለም ለመጡት ወጣቶች ማዳገታቸው እሙን ነው፡፡”
ማጠቃለያ፤ ከላይ እንደገለጽኩት የመጽሐፉ ምሉዕነትም ሆነ ጉድለት ያለው በወንድማማቾቹ ቤተሰቦች ዘንድ ነው፡፡ ዮሐንስ በመቅድሙ ውስጥ የጠቀሳቸው ስድስቱ ቀሪ ቅፆች ካልተሟሉ በተቀር፣ የወንድማማቾቹን የዮሐንስንም ሆነ የዶ/ር ዮናስን ስም በጉድለቱና በተገባው ቃል-ኪዳን ምክንያት ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ስለሆነም፣ የተከበረው አቶ ዳንኤል አድማሱም ሆነ፣ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ምግባረ-ብርቱው ዮሐንስ አድማሱ፣ ከዮፍታሔ ንጉሴ ቤተሰቦችና ጓደኞች ያሰባሰባቸውን መጽሐፍትና ተውኔቶች ከተቻላቸው የማሳተም፣ ካልሆነ ደግሞ ለጥናትና ምርምር እንዲያመቹ አድርገው የማስተላለፍ የሥነ-ምግባር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህ መጽሐፍ እውን መሆን የተጉትንና ዋናውን ባለታሪክ ዮፍታሔ ንጉሴን ነፍስ ይማርልን፡፡ አሜን! (ቸር እሰንብት!)

No comments:

Post a Comment