Translate

Thursday, March 28, 2013

አቶ አዲሱ ለገሰ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን በሀሜተኝነት ነቀፉ፤ አስጠነቀቁም


መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:- “ስለዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ስናወራ በአስተሳሰብም በተግባርም ወደ አንድ መምጣት መቻል አለብን። አሁን ባለው አቀራረብ ከሄድን ግን መቀራረቡ አይደለም የሚጨምረው”ሲሉ አቶ አዲሱ ለገሰ  የ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን አስጠነቀቁ።
 የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራር የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ አባል ድርጅቶቹን ያስጠነቀቁት “መተካካቱ በብአዴን ውስጥ በተቀመጠው እቅድ አልተተገበረም” በማለት  እርሳቸውና ድርጅታቸው በሌሎቹ ድርጅቶች አመራሮች በመታማታቸው ነው።
ሰንደቅ እንደዘገበው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሰሞኑን በተናጠል ባካሄዱት ጉባዔ ነባር አመራሮችን ወደማዕከላዊ ኮሚቴ መልሶ የመምረጥ ሁኔታ መታየቱ ከመተካካት መርህ አንጻር በግንባሩ አባላት ሳይቀር ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል።
ህወሃት አቶ አባይ ጸሐዬን፣ ብአዴን እነአቶ አዲሱ ለገሰን እና አቶ ህላዊ ዮሴፍን በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የመረጡ ሲሆን፤ ሌሎችም በአዲስ መተካት ያለባቸው ነባር አባላት በአመራርነት መቀጠላቸው ጥያቄ አጭሯል።

ሰሞኑን በባህርዳር በተካሄደው ጉባኤ ላይ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ እና ጥያቄ ሲያስነሳ የሰነበተው  የመተካካት ጉዳይ ሲሆን፤ ይህንኑ አስመልክተው ነው አቶ አዲሱ ማብራሪያ እና ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት። 
“ብአዴን የአመራር መተካካትን በተገቢው መንገድ አልፈጸመም “በሚል የተነገሩ ሐሜቶች መሠረተቢስ ናቸው” ያሉት አቶ አዲሱ “ ሁኔታውም በአመለካከት ደረጃ ለግንባሩ አይጠቅምም” ብለዋል።
“ስለመተካካት ስናነሳ ማነው፤ ማንን የሚተካው የሚለው መታየት አለበት” ያሉት አቶ አዲሱ አንዳንዴ በትግሉ ጊዜ  አመራር የነበሩትን መተካት ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።
አያይዘውም “እንደሰማሁት ብአዴን መተካካቱን በደንብ አልሄደበትም የሚል ሃሜት አለ። ግን ይሄ አይጠቅምም። አንዱ ለግንባራችን አደጋ የሚመስለኝ ፣ በግሌም የሚሰማኝና ወደፊትም መታየት አለበት ብዬ የማምነው፤ አንዱ ድርጅት ውስጥ ጉድለት እንኳን ቢኖር ጉድለቱ እንዲታረም እንደታጋይ መታገል ተገቢ ነው። የአንዱ ጉድለት ለሌላው ጥንካሬ ሊሆን አይችልም። የአንዱ ጥንካሬ ለሌላው ድርጅት ግን ጥንካሬ ሊሆን ይችላል። በስልጠናም ብዙ ጊዜ ያየነው ይህን ነው። አንድ ድርጅት ሲደክም ለምን ደከመ? አንድ አካሌ ነው የደከመው? ይህ አካሌ ደግሞ በዛው ከቀጠለ እንደኢሕአዴግ እደክማለሁ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።”ብለዋል አቶ አዲሱ።
የብአዴኑ አቶ አዲሱ አክለውም፦” በፍጥነትም ለማደግ የሚቻለው፤ የአንዱ መድክም የእኔም መድከም ነው የሚል አመለካከት ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ጨፍልቆ አንድ ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም። ስለዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ስናወራ፤ በአስተሳሰብም፣ በተግባርም ወደ አንድ መምጣት መቻል አለብን። አሁን ባለው አቀራረብ ከሄድን ግን ፤መቀራረቡ አይደለም የሚጨምረው” በማለት መለያየት ሊኖርም እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ የማስጠንቀቂያ ደወል አሰምተዋል።
እንደ ሰንደቅ ዘገባ፤አቶ ሕላዊ ዮሴፍም በጉባኤው ውስጥ ስለሚወራው ሃሜት ጥያቄ በማቅረብ ነበር ሃሳባቸውን ያቀረቡት።
“የመተካካት መሠረታዊ ጭብጥ የተጀመረውን መስመር ማስቀጠል መሆኑን ግንዛቤ ከወሰድን፤ የግለሰቦችን ጉዳይ በአጀንዳነት ማንሳቱ ለምን አስፈለገ? ምንስ ይጠቅማል? ድርጅታችንን እየጎዳው ያለው ነገር ምንድን ነው? የሚሉትን ትንሽ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገሩ የሚጠቅም ይመስለኛል።”፡ያሉት አቶ ሀላዊ፤” ድርጅታችን ወደፊት ማራመድ በሚቻልበት አግባብ ላይ እርግጠኛ ምላሽ በምናገኝበት ሁኔታ ተግባብተን መውጣት አለብን። አለበለዚያ በነገሮች ሁሉ ፊት ለፊት ሳንተያይ በጎን እየተላለፍን ሊሆን ይችላል።”ብለዋል።
አቶ ህላዊ አክለውም፦”በተረፈ ሁሉም በየድርጅቱ የነበረው ሂደት ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ። የእኛም ሁኔታ በበቂ መረጃ የቀረበ ነው። ከስልሳ አምስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ውስጥ ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆኑት አዲስ ተተኪዎች ናቸው። ይህ ሆኖ ሳለ፤ በሁለት ሰዎች ላይ እናተኩር፣ አይናችንን ጥለን እንሂድ የሚባል ከሆነ ፤ልማቱን አላራምድ ያለ አደርባይነት እዚህ ቦታ እንዴት ይገለፃል ብለን ብናየው ጥሩ ይመስለኛል” ሲሉ ሀሜት አምተዋል  ተብለው ሚጠበቁትን ያስደነገጠ ንግግር አድርገዋል።
አቶ አዲሱ ለገሰንና አቶ ህላዊ ዮሴፍን ጨምሮ ነባር የኢህአዴግ አመራሮች በአዲሱ ስራ አስፈፃሚ ወስጥ መካተታቸወ፡ይታወቃል :፡
በተለይ አቶ አዲሱ ለገሰ -ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ባስተዋወቁበት ወቅት በመተካካቱ መመሪያ  ከፖለቲካው እንዳረፉና በአማካሪነት እንደሚያገለግሉ ቃል ከገቡ በሁዋላ፤ አቶ መለስ ማረፋቸውን ተከትሎ  በአዲሱ የብአዴን አመራር ውስጥ መካተታቸው ብዙዎችን አነጋግሯል።
“በአሁን ሰዓት ስለመተካካት የሚወራው ማዕከላዊ ላይ ምን ተደረገ? ስራአስፈፃሚው ላይ ምን ለውጥ አለ? የሚሉ ናቸው።” በማለት ሀሳባቸውን መስጠት የጀመሩት የህወሀቱ አቶ አባይ ፀሀዬ በበኩላቸው፤” ቁምነገሩ ያለው መካከለኛው አመራር ላይ በጥራትና በስፋት የሚተካ አመራር መፍጠር ላይ ነው። ይህ ሲሆን ማዕከላዊ ኮሚቴውንም፣ ሌላውንም ለመተካት ብዙ አማራጭ ይኖራል። ስለዚህ የመተካካት ሂደቱን ስንገመግም ከበላይ ያለውን አመራር ብቻ መሆን የለበትም። “ብለዋል።
“የመተካካት ፖሊሲዎቻችን ምንድናቸው?” በሚል ጥያቄ አስተያየት መስጠት የጀመረት አተ በረከት ሰምዖን በበኩላቸው ፤ እኔ እንደሚገባኝ፣ መተካካት የሚባለው ለትግል ቀጣይነት፣  የሚደረግ ሂደት ነው። የመተካካት ግቡ የሰዎች መተካካት አይደለም። ግቡ የመስመር ትግበራ ነው። “ብለዋል።
አክለውም፦“ነባሮች በጣም ከመድከማቸው በፊት በተለይ ከፊት መስመር ቦታውን ለወጣቱ ትውልድ ማስረከብ አለባቸው፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ የተረከበውን መስመር በዲሲፕሊን በታማኝነት በፅናት ተግባራዊ በማድረግ መቀጠል አለበት። ነባሩም ከፊት መስመር በመውጣት በጎን ማገዝ ይጠበቅበታል። ሌላው፤ በመንግስት ኃላፊነት ነባሩም ሆነ ተተኪው ከሁለት የምርጫ ጊዜ በላይ አያገለግልም። በፓርቲ ኃላፊነት ውስጥም አንድ ሰው እስከ ስልሳ አምስት ዓመት ብቻ ነው የሚያገለግለው። የፓርቲያችን የመተካካት ፖሊሲዎችም ዋነኛ ቁምነገሮች እኔ እስከማስታውሰው ድረስ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ናቸው።”ብለዋል።
ጋዜጣው እንዳለው በጉባኤው ላይ የተንፀባረቀው የመተካካት አተገባበር ወጥነት የሌለው እና ድርጅቶቹ በተናጠል የሄዱበት በመሆኑ፤ ግንባሩ የአፈፃፀም የፖሊሲ አቅጣጫ እንጂ የአተገባበር ዝርዝር መመሪያዎች የሌሉት በመሆኑ በጉባኤው ተሳታፊው አባላት ውስጥ የመተካካቱ ሂደት ለሃሜት የተጋለጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
“ ሌላው ተተኪ ከሚባለው አዲሱ አመራርም መተካካቱን በተመለከተ ከፍተኛ ሙግት ያንፀባረቀ አልነበረም ያለው “ጋዜጣው፤” በአብዛኛው የቀድሞ የድርጅቱ ነባር ታጋዮች ተሳትፎ የጎላበት ጉባኤ ነበር ማለት ይቻላል” ብሏል።

No comments:

Post a Comment