Translate

Tuesday, March 11, 2014

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዘገባ በግድብ ሥራ ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

“ለሕዝባችሁ የምታስቡ ከሆነ ገንዘቡን ለሌላ ተግባር አውሉት”

dam1


ታላላቅ ግድቦችን በመሥራት ላይ የሚገኙ ታዳጊ አገራት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረገው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ዘገባ መሠረት አገራቱ ለከፍተኛ ዕዳ እና ከዚያ ጋር ተዛማጅ ለሆኑ ችግሮች የሚጋለጡ መሆናቸውን ፋይናንሺያል ታይምስ ጥናቱን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ “ለሕዝባችሁ የምታስቡ ከሆነ ገንዘቡን ለሌላ ተግባር አውሉት” በማለት ምክርም ሰጥቶዋል፡፡

እኤአ ከ1934ዓም ጀምሮ በ65 አገራት የተገነቡ 245 ግድቦችን በማካተት የተደረገው በዓይነቱ ለየት ያለው አጠቃላይ ጥናት በቅርቡ እየተገነቡ ያሉትን ታላቅ ግድቦችንም ያካተተ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ካለው የግልገል ጊቤ ሦስት ግድብ ጀምሮ እስከ ብራዚሉ የአማዞን ቤሎ ሞንቴ የግድብ ፕሮጀክቶችን የሚገነቡት ታዳሽ ኃይልን አጠቃቀም ለማጎልበት እና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለመጨመር በሚል እንደሆነ የጠቀሰው ጥናታዊ ዘገባ ግንባታው በርካታዎችን ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ የሚያደርግና ለብዝሃ ህይወት አደጋ እንዲጋለጡ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
እንደነዚህ ዓይነቱን የግድብ ሥራ የሚቃወሙ ቡድኖች እንደሚሉት የታላላቅ ግድቦች የኮንስትራክሽን ወጪ ሲጀመር ከታሰበው በጀት በአማካይ ከ90 በመቶ በላይ ተጨማሪ ወጪ የሚያስከትል እንዲሁም ከአስር ግድቦች ስምንቱ ከተወሰነላቸው የመጠናቀቂያ ጊዜ እንደሚያልፉ ይናገራሉ፡፡ በመሆኑን በኢትዮጵያና በብራዚል የሚገነቡት ግድቦች የፓኪስታንንና የምያንማርን (በርማ) ጨምሮ “ከፍተኛ ወጪ እንዲሁም ከመመጠናቀቂያ ጊዜያቸው በማለፍ የአገራቱን የኢኮኖሚ ገጽታ ችግር ውስጥ” እንደሚከቱ ዘገባው ያስረዳል፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት ምሁራን እንደሚሉት ግድብ መሥራት አስፈላጊና እነርሱም በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃዋሚ አለመሆናቸውን በአጽዕኖት ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ያለው ታዳጊ አገራቱ ካላቸው የኢኮኖሚ ሁኔታ አኳያ በእንደዚህ ዓይነት የታላላቅ ግድብ ሥራ ላይ መጠመዳቸው ወደፊት ግድቦቹ በሥራ ላይ ሲውሉ ከሚጠይቁት ከፍተኛ ወጪና አገራቱ ግድቦቹን ለማንቀሳቀስ ከሚጠፈለግባቸው ከፍተኛ የፋይናንስ ጥያቄና ብቃት ማነስ አኳያ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በመዘርዘር አስረድተዋል፡፡ “በመሆኑም” ይላሉ ከምሁራኖቹ አንዱ “በመሆኑም ይህንን ሁሉ ሁኔታ አንድ ላይ ስንወስደው ግድቦቹን መገንባት ስሜት የሚሰጥ አይደለም፡፡”
እንዲህ ያለው መረጃና ማስጠንቀቂያ ይፋ ቢሆንም የግድቦቹን መሠራት የሚደግፉ ወገኖች ቀድሞ የተሠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ አድርገን ነው የምንገነባው በማለት ለሚቀርበው ማስረጃ መከላከያ ይሰጣሉ፡፡ ሆኖም የኦክስፎር ዩኒቨርሲቲ ዘገባ የበርካታ ዓመታት መረጃ በመውሰድ ያወጣው ዘገባ ላይ እንዳመለከተው የግድቦቹን ሥራ ለማጠናቀቅ፣ ከተሰሩም በኋላ ለጥገናና ግድቦቹ በሥራ ላይ እንዲቆዩ ለማካሄድ የሚወጣው ወጪ ባለፉት በርካታ ዓመታት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንዳልመጣ ያስረዳል፡፡ በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሌላው ምሁር ሲናገሩ “እነዚህ ኢኮኖሚያችን እያደገ ነው የሚሉ አገራት በእርግጥ ለዜጎቻቸው ዋስትና ግድ የሚላቸው ከሆነ ገንዘባቸውን ከታላላቅ ግድብ ሥራ ይልቅ በሌላ (ሰብዓዊ) ተግባር ላይ ቢያውሉት ይሻላል” ብለዋል፡፡
ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት የኦሞ ወንዝን ተከትሎ በሚገነባው ግድብ ላይ ስለተፈናቀሉት ዜጎች በቅርቡ ባወጣው በሳተላይት ፎቶ በተደገፈ ማስረጃ መሠረት በኢትዮጵያና በኬኒያ የኦሞን ወንዝ ተከትለው የሚኖሩ እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች በግድቡ ሥራ ምክንያት የመኖር ኅልውናቸው ያከተመ መሆኑን ዘግቦ ነበር፡፡ ሰሞኑን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት (ከግብርና ሚ/ር) በኢህአዴግ ፓርላማ ሲጠየቁ በሰጡት ቃል አንዳችም የተፈናቀለ ሰው የለም በማለት የመለሱ ሲሆን በተደጋጋሚ ማስረጃ ተደግፎ የሚወጣውን መረጃ አጣጥለውታል፡፡ (ፎቶ: AP)

No comments:

Post a Comment