Translate

Monday, March 24, 2014

ኢህአዴግ ባደባባይ የወደቀውን ፈተና “በጓሮ” አለፈ

ግልጽነትና ተጠያቂነት ፈረዱ ወይስ ተፈረደባቸው?

short eiti eprdf


ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ብሎም ለህዝቦች ጥቅም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ህግ ደንግጎ የተቋቋመው ዓለም ዓቀፋዊ ተቋም ኢህአዴግ ያቀረበውን የይግባኝ ማመልከቻ ተቀብሎ ማጽደቁ አነጋጋሪ ሆኗል። በ2009 ኢህአዴግን “ያወጣሁትን መስፈርት አታሟላም” በማለት እውቅና የከለከለው ይህ ተቋም፣ ኢህአዴግ በሚከሰስባቸው ዋና ጉዳዮች ለውጥ ሳያደርግ የራሱን ውሳኔ የገለበጠበት አካሄድ እየተመረመረ እንደሆነ የጎልጉል ምንጮች ጠቁመዋል።

የኢህአዴግን የእውቅና ይግባኝ ጥያቄ ተቀብሎ ያጸደቀው የተፈጥሮ ሃብትን በትክክለኛ መንገድ ለሕዝብ ጥቅም መዋሉን በመከታተል ለአገራት እውቅና የሚሰጠው The Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) የሚባለው ዓለም ዓቀፋዊ ተቋም ነው። ተቋሙ ኢህአዴግ በ2009 አቅርቦት የነበረውን የእውቅና ጥያቄ ውድቅ ሲያደርግ የሰጠው ምክንያት “የመያዶች ህግ የተሰኘው” አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆንና በአገሪቱ የተተከሉት አፋኝ ህጎች እስካልተወገዱ ድረስ ማመልከቻው እንደማይታይ በማሳወቅ ነበር።
በ2009 ጠ/ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ “መሰዋት” በስተቀር ኢህአዴግ አንዳችም ለውጥ ባላደረገበት ሁኔታ ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 19፤2006 (March 19፤2014) ይኸው እውቅና ሰጪ ተቋም የራሱን ውሳኔ ቀልብሶ ለኢህአዴግ እውቅና መስጠቱ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ከውሳኔው ቀናት በፊት በጓሮ የሚወጠን ድርጊት እንዳለ መረጃ ደርሶት የማሳሰቢያ ተቃውሞ ያሰራጨው ሂውማን ራይትስ ዎች የተሰኘውየሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዳለው ከሆነ ከተገለበጠው ውሳኔ በስተጀርባ ሚስ ክሌር ሾርት ከፊት ረድፍ ተቀምጠዋል።
ማመልከቻው እንደገና እንዲታይና የቦርዱ የቀድሞ ውሳኔ እንዲገለብጥ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የቀድሞ የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ ትብብር ሚ/ር የሆኑት ክሌር ሾርት መሆናቸውን የድርጅቱ መግለጫው ይፋ አድርጓል። እኚህ ግለሰብ የአፍሪካ አምባገነኖችን በመደገፍ የሚታወቁ ሲሆን ይህ ከጥቅማቸው ጋር የተሳሰረው ግንኙነታቸው አሁንም ኢህአዴግን እንዲደግፉ እንዳደረጋቸው ይነገራል፡፡ እንዲሁም በሌሎች ኢህአዴግ ባቋቋማቸው ዓለምአቀፋዊነት ሽፋን በተላበሱ ድርጅቶች ውስጥ የአመራር አባል በመሆን ሚስ ሾርት እንደሚያገለግሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማ አባል በነበሩበት ወቅትም ያላወጡትን ወጪ አውጥቻለሁ በማለት በብዙ ሺዎች የሚገመት ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ መሆናቸው በወቅቱ ዴይሊ ቴሌግራፍ ባወጣው መረጃ አጋልጦ ነበር፡፡ የተወሰነውን ገንዘብ የመለሱ ቢሆንም ጋዜጣው በወቅቱ ያወጣው መረጃ ግለሰቧ የሕዝብን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው የተጠቀሙ “ሙሰኛ” መሆናቸውን ያስረዳል፡፡
clare
ክሌር ሾርት
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እንደሚሉት ከሆነ ባለፈው ረቡዕ ኦስሎ፤ ኖርዌይ ላይ ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት ሚስ ሾርት በግልጽ የኢህአዴግ ደጋፊ በመሆን ተጽዕኖ በማድረግ ወደ ውሳኔ እንዲደረስ ግፊት አድርገዋል፡፡ ግለሰቧ ባላቸው ኃላፊነት በመጠቀም (የEITI የቦርድ ኃላፊ ናቸው) እንዲህ ዓይነቱ ግልጽና ወገናዊነት የታየበት ድጋፍ በማድረግ ከድርጅቱ አሠራር ውጪ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረጋቸው ለወደፊት በሚቀርቡ ማመልከቻዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የአሠራር ችግር እንደሚያስከትል ካሁኑ እየተጠቆመ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከማዕድን ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ማህበራዊ ቀውስ የደረሰባቸው አካባቢዎች እንዳሉ የሚታወቅ ነው። በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አካባቢዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ባልጸዳ የሽያጭ ሂደት ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ የገዙት ሻኪሶ የወርቅ ማዕድን በህዝብ ላይ እያደረሰ ችግር የሚዘገንን ነው። በየጊዜው ግልጽ ባልሆነ የማስፋፊያ ውል የሚፈናቀሉና ከፋብሪካው በሚወጣው ዝቃጭ ለከፍተኛ ብክለት የተጋለጡ ዜጎች ድምጻቸውን ሲያሰሙ መታሰራቸው፣ መገረፋቸው፣ ለይስሙላ በተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች የተፈረደባቸው እንዳሉ ታዛቢዎች ያስታውሳሉ።
በጋምቤላ ኢንቨስትመንት ህዝብን እየበላ እንደሆነ የሚጠቁሙት ክፍሎች “ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ የሚደገፍና የሚበረታታ ተግባር ቢሆንም፣ ኢህአዴግ ፍትሃዊ በሆነ ደረጃ መጠቀም፣ ማስተዳደር፣ መምራትና ኢንቨስትመንቱን ህዝብ “የኔ” ብሎ በመቀበል እንክብካቤ እንዲያደርግ የሚያስችል ስርዓት አለማበጀቱን እንደ ዋንኛ ችግር ያነሳሉ። ኢህአዴግን ያዘጋጀው ህወሃት በራሱ ሰዎች አማካይነት ከውጪ ሰዎች ጋር እየተሻረከ ለህዝብ ጥቅም ሊውል የሚገባውን ሃብት ወደ ውስን ቋት እንደሚያግዝ የሚገልጹት እነዚሁ ክፍሎች” ይህ ዓለም የሚያውቀውን፣ ራሳቸው ህወሃቶችም የማይክዱትን እውነት ነው ብለዋል። ዜጎች የአገራቸው ሃብት ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ አካባቢያቸው ባደላቸው የተፈጥሮ ሃብት ሳቢያ መከራ ሲደርስባቸው፣ ሲሰቃዩ፣ ሲገረፉና፣ ሲገደሉ ማየት በተለመደባት ኢትዮጵያ ውስጥ ለኢህአዴግ የማይገባውን ካባ መደረብ ውሎ አድሮ የሚጋለጥ ክፉ ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል።
አነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙና ኢህአዴግ “ልማታዊ” የሚላቸው ኢንቨስተሮች ሳይሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የሚመደብ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ ባለሃብቶች ኢንቨስት የሚያደርጉበትን አገር ለመምረጥ የመጀመሪያው መለያቸው የEITI ድረገጽ የአባል አገራት ዝርዝር እንደሆነ ስለ አሰራሩ የሚያውቁ ይናገራሉ። ኢህአዴግም አስፈላጊውን የምዝገባና የማመልከቻ መስፈርት በማሟላት የተቋሙን እውቅና የጠየቀው በድርጅቱ ድረገጽ ላይ ለመመዝገብ ነበር። የሁለት ጊዜ ሙከራው ቢከሽፋም በመጨረሻ ተሳክቶለታል። ስኬቱንና የስኬቱን መንገድ፣ በተለይም የዳይሬክተሯ ክሌር ሾርት ጉዳይና የተዘጋውን ፋይል በማንሳት ውሳኔው የተገለበጠበት አካሄድ ኦስሎ በሚገኘው ሃያ የቦርድ አባላት ባሉበት ተቋም ውስጥም ግራ ያጋባቸው እንዳሉ መረጃዎች አሉ።
ኢህአዴግ አጓድለሃል ተብሎ የሚከሰስባቸውን የዴሞክራሲ ግባቶችና የሰው ልጆች የተፈጥሮ መብቶች፣ አንዲሆም አፋኝ የተባሉትን ህጎች አጠናክሮ ተግባር ላይ ባዋለበት ሁኔታ፣ የዚሁ የአፈናው ሰለባዎች በተለያዩ ማጎሪያዎች ውስጥ ሆነው ድምጻቸውን በሚያስተጋቡበት ወቅት፣ EITI ከተቋቋመበት ዓላማና “መሰረቴ” ከሚለው የግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ በተጻራሪ ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው መልኩ ለኢህአዴግ የደረበው ብሉኮ ጉዳይ እየተመረመረ አንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ጉዳዩን የሚከታተሉ “ግልጽነትና ተጠያቂነት በኦስሎ ተፈረደባቸው” ሲሉ ምጸት ሰጥተዋል፤ የክሌር ሾርትንም አካሄድ በEITI የህወሃት/ኢህአዴግ ተወካይ በማለት ተችተዋል። ይህንኑ ጉዳይ እመልክቶ ከሳምንት በፊት ለሪፖርተር አጭር መልስ የሰጡት የማዕድን ሚኒስትሩ EITI ውሳኔውን ያነሳል የሚል ጥርጣሬ እንዳለባቸው የሚያሳብቅባቸው መልስ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ዳያስፖራው እንደሚገባው አለመንቀሳቀሱ እንደ ሽንፈትና አቅጣጫ መሳት እንደሚቆጠር ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ጠቁመዋል፡፡ ዳያስፖራው ከጥቃቅንና ስሜታዊ ጉዳዮች በማለፍ በከፍተኛና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የማድረግ አመለካከቱን ማስፋት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ አለበለዚያ ኢህአዴግ እንደዚህ ዓይነቱን አጋጣሚ በመጠቀም የራሱን ገጽታ በዓለምአቀፍ መድረኮች እየወለወለ በማቅረብ የሥልጣን ዘመኑን እንደሚያራዝም ጠቁመዋል፡፡

No comments:

Post a Comment